“የሰው ውበቱ አንደበቱ ነው”

“የሰው ውበቱ አንደበቱ ነው” ይላል አንድ ወዳጄ፡፡ አንደበት ውበት ብቻ ሳይሆን ሃብት፣ ስልጣን፣ እና ጉልበትም ነው፡፡ ሃሳባቸውን በሚገባ አደራጅተው አሳማኝ በሆነ መንገድ መግለጽ የሚችሉ ሰዎች ከሌሎች የበለጠ ተደማጭ ናቸው፡፡ ቢናገሩ ያምርባቸዋል፤ ጥሪ ቢያቀርቡ ተከታይ ያገኛሉ፤ በንግዱ ዓለምም ቢሆን የተሻለ አትራፊ ነጋዴ ናቸው፡፡ ለዚህ ይመስለኛል መጽሐፍ ቅዱስም “ሰው የአንደበቱን ፍሬ ይበላል”የሚለው፡፡

ይህንን ክህሎት የተወሰኑ ሰዎች ሲፈጥራቸውም የታደሉት ሊሆኑ ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ ግን በልምምድ እና ውስን ስልቶችን ጠንቅቆ በማወቅ አንደበተ ርቱዕ ሰው መሆንም ይቻላል፡፡የተወሰኑ ጠቃሚ የምላቸውን ስልቶችን ላጋራችሁ፡፡

ቅለት

ማስተላለፍ የምትፈልጉትን መልዕክት ቀላል፣ ግልጽ እና አጭር አድርጉ፡፡ የተራዘመ መልዕክት በአንድ በኩል አሰልቺ ነው፡፡ የሚፈለገውን ግብም አይመታም፡፡ አጥብቆ ለሚጠራጠረም ይህ ሁሉ እኔን ለማሳመን የሚደረግ ጥረት ከጀርባው ሌላ የተሸፈነ ፍላጎት አለ ወይ የሚል ሃሳብም እንዲያድርበት በር ሊከፍት ይችላል፡፡የዓለማችን ግዙፉ የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል መስራች ስቲቭ ጆብስ “አንድን ነገር ቀላል በሆነ መንገድ መግለጽ መቻል ትልቅ ጥበብ ነው” (Simplicity is the ultimate sophistication) ይላል፡፡

ሌሎች ሊያገኙ የሚችሉት ጥቅም ላይ ትኩረት ማድረግ

“እኔ ምን አገኝበታለሁ?(What’s in it for me?) ”የተለመደ ጥያቄ ነው፡፡ ሰዎች ባይናገሩ እንኳን በውስጣቸው ይህንን ስሌት ከመስራት ወደ ኋላ አይሉም፡፡ በመሆኑም ለዚህ ወሳኝ ጥያቄ በቂ ማብራሪያ ማቅረብ መቻል በቀላሉ ሃሳባችንን ሰዎች እንዲገዙን ያደርጋል፡፡

በራስ መተማመን

አንዳንዴ እውነታው ከምናስተውለው የተለየ እንደሆነ ውስጣችን እያወቀ የተናጋሪው በራስ መተማመን ውሳኔያችንን ሊያስለውጥ፣ ሃሳባችንን ሊያስቀይር ወዘተ ይችላል፡፡ የምንናገረውን ነገር እንደምንተማመንበት ሁለመናችን ሊያስረዳ ይገባል፡፡ በሰዎች መካከል በሚደረግ የእርስ በእርስ ግንኙነት ውስጥ ቃላዊ ባልሆነ መንገድ የሚተላለፉ መልዕክቶች በቃል ከሚተላለፉት ያልተናነሰ ጉልበት አላቸው፡፡

በሌሎች ዓይን ማየት

ከሚመስሉን ሰዎች ጋር መስራት እንፈልጋለን፡፡ የጋራ ታሪክ አለን ብለን የምናስብ ከሆነ፣ ሃሳባችን ከተመሳሰለ፣ ምርጫች ከገጠመ ወዘተ ውስጣችን ፍላጎት በቀላሉ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ይህንን የአንድነት መንፈስ ሊፈጥሩ የሚችሉ ነገሮችን ማድረግ የማሳመን ኃይላችንን ከፍ ያደርጋል፡፡ በቀጥታ የዓይን ግንኙነት መፍጠር፣ በትኩረት ማዳመጥ፣ ግንባርን አልፎ አልፎ ዝቅ ከፍ ማድረግ የመሳሰሉት ስልቶች እየተባለ የሚገኘው ነገር እየገባን እንደሚገኝ የሚጠቁሙ ምልክቶች ናቸው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የማሳመን አቅማችንንም እንዲሁ በዛው ልክ ከፍ እንዲል ያደርጋሉ፡፡በወደደው ሰው ተጽእኖ ጥላ ስር በቀላሉ ያልወደቀ መቼም አይጠፋም፡፡

ያለማቋረጥ ጥረት ማድረግ   

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ትምህርት ቤት እያለሁ አንድ መጽሔት ዝግጅት ውስጥ ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ አንዱን ዕትማችንን በምናዘጋጅበት ወቀት አንድ ቢሮ በተደጋጋሚ መሄድ ነበረብኝ፡፡ በወቅቱ ሳላስተውል፣ይህ ስልት ሰዎችን ሊያሳምን እንደሚችል ሳላስብበትም ነበር አደርገው የነበረው፡፡ በስተመጨረሻ የመስሪያ ቤቱ ኃላፊ የስፖንስርሺፕ ደብዳቤያችን ላይ ከመራበት በኋላ “ይህንን ያደረጉት ተስፋ አልቆርጥ ስላልከኝ ነው”እንዳለኝ ትዝ ይለኛል፡፡ እንደየ ሁኔታው ያለ ማቋረጥ ጥረት ማድረግም ሰዎች ሃሳባችንን ሃሳባቸው እንዲያርጉ ይረዳል፡፡

እጥረትን መፍጠር

ዋልያ የሀገር ኩራት ምንጭ፣ የንግድ ስያሜ መጠሪያ፣ የብሔራዊ ቡድናችን አርማ ወዘተ መሆን የቻለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ በመገኘቱ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ብርቅዬ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ በተለያየ መልኩ መሸጥ የምንፈልገው ሃሳብም ይሁን ቁስ ከሌላው በምን መልኩ እንደሚለይ፣ በምን እንደሚሻል ወዘተ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ እዚህም እዚያም እንደ ልብ ለሚገኝ ነገር ፍላጎታችን እምብዛም ነው፡፡

ዝግጅት

ስለምንናገረው ነገር ጠንቅቀን ማወቅ፣ አስቀድመን የቤት ሥራችንን በሚገባ መስራት ማሳመን የምንፈልገውን አካል ለማሳመን ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በራስ መተማመናችንንም ይገነባል፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »