ጥሩ መሪ በመሆን ጥሩ ሰራተኛ ይፍጠሩ። መመሪያዎችንም እነሆ።
የተለያዩ አለቆች ወይም መሪዎች ሠራተኞቻቸው ስራቸውን እንዲያከናውኑላቸው የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ። ብዙዎቹ ግን የሚጋሩት ነገር ቢኖር የአመራር መንገዳቸው ፈላጭ ቆራጭነት፣ ባለስልጣነት፣ ቁጣ እና ማስፈራራት የተሞላበት መሆኑ ነው። እነኝህ መንገዶች ደግሞ ብዙውን ጊዜ ሰራተኞችን በማሸማቀቅ ለስራ ያላቸውን ተነሳሽነት በእጅጉ ይገላሉ። ይህ ሲሆን ደግሞ የሰራተኞች አምራችነት በእጅጉ ይቀንሳል። ሰራተኞች የጠንካራ ተነሳሽነት ስሜት ባለቤት ሲሆኑ ስራቸውን በጥራት ይሰራሉ፣ ለስራቸውም ሆነ ለሚሰሩለት ተቋም ጠንካራ የባለቤትነት ስሜትን ያዳብራሉ፣ የፈጠራ ችሎታቸው ክፍ ይላል፣ በጥቅሉ የለውጥ ምሳሌ ይሆናሉ።
በምሳሌ ሌሎችን እንዴት መምራት እና ለለውጥ ማነሳሳት እንደሚችሉ የሚረዱ ምክሮች እነሆ።
1. በማንኛዉም ሁኔታ እና ጊዜ በሙሉ በሙሉ ሐቀኛ እና ግልጽ ይሁኑ
እምነት የሁሉም ነገር መሰረት ነው። በሁሉም ግንኙነቶች ላይ እምነት ማጣት ሌሎች ነገሮችን ሁሉ ማጣትን ያስከትላል። በሚያደርጉት ነገር ሁሉ ግልጽነትን ሲያሳዩ ሰራተኞችዎ ታታሪ ሰራተኞችና የለውጥ ኃይል ይሆናሉ። ግልፅነትዎ ለጊዜው አንዳንድ ነገርን የጎዳ ቢመስልዎትም እንኩዋን፣ ግልፅነትን መምረጥ ከተከታዮችዎ ጋር ዘላቂ ለሆነ ግንኙነትን ስለሚመሰርትልዎ ግልፅነትን ይምረጡ። ተቃራኒውን ማድረግ ተከታዮችዎ እምነትን እንዳይጥሉብዎ ያደርጋል፣ ማምጣት የሚፈልጉትን ለውጥም ከልባቸው መውሰድ እና የሚችሉትን አስተዋፅኦ የማድረግ ተነሳሽነትን ያጣሉ።
2. ከልብ ሌሎችን የማዳመጥ ፍላጎትን ያዳብሩ፣ ያሳዩ።
አንዳን ሰዎች ሌሎችን ሲሰሙ ፈልገው አደለም፣ ይህንም ሲያደርጉ ከሁኔታቸው በግልፅ ይነበባል። ተናጋሪውም ይህን በሚያነብበት ጊዜ የንቀት እና እንደ አላስፈላጊ የመቆጠር ስሜት ይሰማዋል። በሚያዳምጡበት ጊዜ ግለሰቡ የሚናገራቸውን ነገሮች ሁሉ አትኩሮት በመስጠት፣ ስሜታቸውን በንግግራቸው ውስጥ ያላቸውን ስሜት ሳይቀር በደንብ ለመረዳት ዝግጁነት ያሳዩ። ይህን ሲያደርጉ ለተናጋሪው ያለዎትን ጥልቅ እንክብካቤ እና ክብር ያሳያል። ተናጋሪውም አብርዎት ሁሌም ለመስራት እና ለመተባበር ተነሳሽነትን ያገኛሉ።
3. የተከታዮችዎ ጓደኛ ይሁኑ
ሰራተኞችዎ ጓደኛቸው ሲሆኑ የፍርሃት እና ጭንቀት ተወግዶ እውነተኛ የለውጥ አጋርዎ ለመሆን ይጥራሉ።
4. ሐቀኛ በሆነ ሁኔታ በተደጋጋሚ ያመስግኑ።
ተከታዮችዎ ወይም ሰራተኞችዎ ምን እንደሚሰሩ ይመልከቱ እና በደንብ ለሚሰሩት ስራዎቻቸው ከልብ የመነጨ ምስጋና ያቅርቡ። ምስጋና ለሰው ያለንን አድናቆት የማስተላለፊያ ጠንካራ መሳሪያ ነው።
5. ትሁት ይሁኑ እንጂ ትዕቢተኛ አይሁኑ።
ከሰራተኞችዎ ጋር ያለወት ግንኙነት ትህትና የተላበሰ ሲሆን ሁሉም ሰው የቤተኛ ስሜት ይሰማዋል። ለሚመሩት ስብስብ እና ማምጣት ለሚፈልጉት ለውጥም ሁሉም ሰው አውንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው በእጅጉ ያስገነዝባል።
6. ታች በመውረድ ከተከታዮችዎ ጋር በአካል በመገናኘት ይምሩ።
ከተከታዮችዎ ጋር ታች በመሄድ በአካል ካልተገናኙ ያሉባቸውን ችግር ማወቅ አይችሉም። ከቢሮዎ በመውጣትና ወደነሱ በአካል ሄደው መገናኘት እርስዎም የሰራተኞችዎ አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል።
7. ከሠራተኞችዎ የሚጠብቁትን የሥራ ስነ-ምግባር እራስዎ ሆነው በመገኘት በምሳሌ ያስቀምጡ።
ሰራተኞችዎ ሊላበሱት የሚገቡ ትሕትና፣ ታታሪነት፣ ተቆርቋርነት፣ ፈጠራ፣ ተነሳሽነት እና ሌሎች በጎ ስነ-ምግባሮች እርስዎ ሆነው ለማሳየት በመሞከር በምሳሌ ያሳዩ። እነዚህ ለስራ የሚያስፈልጉ ስነ-ምግባሮችን እርስዎ ይዘው ካልተገኙ በተከታዮችዎ ዘንድ አስፈላጊ እና ውድ የሰራተኛ ፀባዮች ሆነው ሊታዩ አይችሉም።
8. ደግ እና እራስዎን በሌሎች ጫማ ውስጥ በማስገባት የሎሎችን ስሜት መረዳት የሚችሉ ይሁኑ።
አንድ ታላቅ መሪ ደግነት በሌሎች ላይ ለረዥም ጊዜ ታማኝነትን እንደሚፈጥር ያውቃል። ደግ መሆን ማለት የሌሎችን ስሜት የመረዳትና የመጋራት ችሎታ ይጠይቃል።
9. አስፈራር፣ አፀያፊ ቋንቋን በጭራሽ አይጠቀሙ።
ሰዎችን በጭካኔ ማነሳሳት አይችሉም። ጭካኔ እና አፀያፊነት የተሞላባቸውን ቋንቋዎች ሲጠቀሙ የተሳሳተ ምሳሌ እያስቀመጡ እንደሆነ ይረዱ። በተጨማሪም ይህን ሲያደርጉም ተከታዮችዎ እርስዎን በሙሉ ፍላጎት ላለመቅረብ ይመርጣሉ።
10. ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን ክብር ይስጡ።
እያንዳንዱ ሰው 100% ክብር እንደሚገባው እና በጣም መጥፎ የሆነ ነገር ካላደረገ በስተቀር ሁሌም ክብሩ መሸራረፍ እንደሌለበት ለራስዎ ይንገሩት። ይህን ከልብዎ አምነው ሲታዩ፣ ተከታዮችዎ የሚገባቸውን ጥሩ ስሜት ይሰማቸዋል፣ ተነሳሽነታቸውም ይጨምራል።
11. “እንዴት ልረዳዎት እችላለሁ?” የተሰኘውን ጥያቄ ይጠይቁ።
ይህ ጥያቄ ብዙ መልእክትን ያስተላልፋል። ለተከታዮችዎ ይህን ጥያቄ ሲያቀርቡ ለነሱ ፍላጎቶች እንደሚጨነቁ ይናገራል፣ ስኬታማ እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ ይናገራል፣ በጥቅሉም ስለነሱ እንደሚጨነቁ ይናገራል።
12. ምግባርዎ ንፅሕና ይኑረው።
ተከታዮችዎ ባይመለከቱም እንኩዋን የሚያረጉት ነገር ሁሉ ንፅና የተሞላ ይሁን። ይህም ሲሆን በራስዎ መተማመን ይችላሉ፣ ሰራተኞችዎትም እምነትን ይጥሉብዎታል።
13. “ይሆናል፣ ማድረግ እንችላለን” የሚል አመለካከት ይኑርዎት።
“አይሆንም፣ አዳጋች ነው፣ አስቸጋሪ ነው” የሚል መሪን የሚከተል ተከታይ፣ ሰራተኛ የለም። ሁሌም በፈገግታ የተሞሉ እና “ይሆናል፣ ይህን ማሳካት እንችላለን” የሚል አመለካከት ሲይዙ ለሌሎች ብርታት፣ ሞራል፣ እና ተነሳሽነት ይሰጣሉ። በጣም ከባድ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳን ጥረት ካለ ማሳካት እንደሚቻል ያሳዩ።
14. ራዕይ ያለው መሪ ይሁኑ።
በተሰማሩበት ሥራ ላይ ቁልጭ ያለ ዓላማ ሊኖርዎት እና እሱንም ግልጽ በሆነ መልኩ ለሠራተኞችዎ ማስተላለፍ ያስፈልግዎታል። ሰራተኞች ተልዕኮውን ማከናወን ለምን ጥሩ እንደሆነ እና ለምን እዚያ ላይ መድረስ አስፈላጊ እንደሆነ እንዲያውቁ ያድርጉ። ይህ ራዕይ ትልቅ እና ሰፊ መሆን አያስፈልገውም። የልቁንም ራዕዩ ጥሩ፣ የሚደረስበት፣ እና ሁሉም ሊረዱት የሚችሉት ይሁን።
15. ሰራተኞችዎን መንገድ ይምሯቸው እንጂ አይንዷቸው።
ሰራተኞች መንገዶች እና የሚጠበቁት ነገሮች ሁሉ አውቀው ለመስራት ነፃነቱን ተገቢ በሆነ ምክንያት ሲሰጣቸው የበለጠ ምርታማ መሆን ይችላሉ። መንገዳቸው ላይ ከቆሙ እና ሊነዷቸው ሲሞክሩ ግን የፈጠራ ችሎታቸው ይቀንሳል፣ ምርታማነታቸውም ይወርዳል።
16.ስህተትን የሚለቅሙ ብቻ አይሁኑ።
ሁላችንም ስህተቶችን እንሠራለን፣ እና ሁላችንም ከነሱ መማር ይገባናል። ስህተትን ብቻ እየለቀሙ ግን እንዴት ከስህተታቸው መማር እንደሚችሉ አለመምራት ማማረር እንጂ መምራት አይደለም። ስለዚህ፣ ተከታዮችዎ ከስህተታቸው እንዴት እንደሚማሩ ይርዷቸው። እንደቡድን ጥሩ ነገር ሲሆን ብቻ ሳይሆን ነገሮች ሲበላሹም ለመፍትሄው ሁሉም አብሮ መስራት እንዳለበት የመፍትሄው አካል በመሆን ያሳዩ።
17. መጀመሪያ ከባድና አስቸጋሪ የሆኑ ስራዎችን ከሰሩ በኋላ ወደ ቀላሎቹ ይሸጋገሩ።
ብዙ ሰዎች ከባድና መስራት የማያስደስታቸውን ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ስራዎችን ወደኋላ ይገፋሉ። እውነታው ግን፣ እነዚህ ስራዎች ሳይሰሩ ምንም አይነት ፕሮጀክት ወደፊት መራመድ አይችልም። ስለዚህ ሁሌም በስራዎ ውስጥ፣ መጀመሪያ ከባድ እና አስቸጋሪ የሆኑ ስራዎችን አስቀድሞ በመጨረስ ለተከታዮችዎ ምሳሌ ይሁኑ።
ሁሌም ከበታችዎ ያለ ሰራተኛ ወይም ተከታይ የእርስዎ ነፀብራቅ ነውና ጥሩ መሪ በመሆን ጥሩ ሰራተኛ ይፍጠሩ