በሕይወታችን የት መድረስ እንደምንፈልግ ማወቁ አስፈላጊ ሲሆን፣ ለምን መድረስ እንደፈለግን በውል ማወቅ የበለጠ አስፈላጊ ነው። አንዳንዶቹ ይህን መድረስ ከምንፈልግበት በስተጀርባ ያለውን ምክንያት እውነተኛው ግብ እያሉ ይጠሩታል። የሕይወት አጭር ወይም ረጅም ግብ (goal) ማዘጋጀት ለምን እንደሚጠቅም ባለሙያዎች እንደሚከተለው ያብራራሉ።
ፍላጎታችን እና ምኞታችን ይሟላል – በሕይወታችን አንድ ነገር ላይ መድረስ ለምን እንደምንፈልግ አስቀምጠን ስንቃኝ፣ ያስቀመጥነው ግብ በእውነትም ያንን ውጤት ሊያመጣልን እንደሚችልና እንደማይችል መመርመር እንችላለን። ስለሆነም በስሜታችን ፣ በደስታችን እና በማንነታችን ላይ ለውጥ የሚያመጡ ነገሮች ላይ ብቻ አተኩረን እንድንሰራ ይረዳናል።
በሕይወታችን ምን እንደሚያነሳሱን ብሎም እራሳችንን የበለጠ እንድናውቅ ይረዳናል – ግቡን አስቀምጠን የሚያመጣልንን ደስታ እና ትርፍ ስናመዛዝን በዚያ ሂደት ከሕይወታችን ምን ማግኘት እንደምንፈልግ ብሎም ደስታችን በምን ላይ የተመሰረተ እንደሆነ የበለጠ እናውቃለን። ይህም ለበለጠ የእራስ ማስተዋል እና ግምገማ ጥሩ ዕድል ይፈጥርልናል። ወደ ጥሩ የሕይወት አላማም ለመጉዋዝ ማስተካካያወች እንድናደርግ ይረዳናል።
ለአእምሯችን ጤንነት ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል – የሕይወት ግቦችን ማስቀመጥ እና እንደምንደርስባቸው ለራስ መንገር ለአምሯችን ሰላም መሰማት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። አእምሮአችን፣ ወደ ግባችን ለመድረስ ስንሰራ ደስታን ያገኛል፣ በዚህም የተነሳ ስለወደፊት ሕይወታችን ያለን አመለካከት ከፍ እያለ ይመጣል። በዚህም ትልቅ የአእምሮ ሰላም እናገኛለን።