ድርጅትዎን ይክፈቱ
ድርጅትዎን ይክፈቱ
የንግድ ፈቃድ ምዝገባ
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 6 ላይ እንደሚደነግገው ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሳይመዘገብ ማናቸውም የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ ሥራ መሥራት አይችልም፡፡ ስለሆነም ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶችን በማሟላት በአቅራቢያው በሚገኝ የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤቶች መመዝገብ አለበት፡፡ ማንኛውም ሰው በተለያዩ ቦታዎች የተለያየ የንግድ ሥራ ቢሰራም የንግድ ምዝገባ የሚያካሂደው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡
ሀ. የንግድ ሥራ ፈቃድ
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 31/1 መሰረት በንግድ ሥራ ለመሰማራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው የፀና የንግድ ስራ ፈቃድ ሊኖረው እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ ስለሆነም ሥራ ፈጣሪዎች አዲስ የንግድ ሥራ ለመጀመር እስካሁን የተመለከትናቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ካሟሉና በየትኛው የንግድ ድርጅት አይነት ህጋዊ እውቅና ለማግኘት እንደሚፈልጉ ከመረጡ በኋላ የንግድ ምዝገባ ማካሄድና የንግድ ፈቃድ ማውጣት አለባቸው፡፡ የንግድ ፈቃድ ለማውጣትም በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 32 መሰረት የሚከተሉትን ዝርዝር ጉዳዮች በማሟላት አመልካቹ ከሚያቀርበው ማመልከቻ ጋር ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ እነዚህም፡-
- አዲስ የተሰጠ ወይም የታደሰ የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት፣
- የራሱን ወይም የሥራ አስኪያጁን በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሣውን ፎቶግራፍ፣
- የውጭ ባለሀብት ከሆነ የኢንቨስትመንትና የመኖሪያ ፈቃዱን፣
- እንደ ሀገር ውስጥ ባለሀብት ለመቆጠር የሚፈልግ የውጭ ሀገር ዜጋ ከሆነ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የተሰጠ ማረጋገጫና የመኖሪያ ፈቃድ፣
- ማመልከቻው የቀረበው በወኪል ከሆነ የተረጋገጠ የውክልና ሠነድ እና የተወካዩ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ፣
- ለንግድ ሥራው የተመደበውን ካፒታል የሚያሳይ ማስረጃ፣ እና
- የንግድ ሥራው የሚከናወንበት ቤት ለንግድ ሥራው ተስማሚ መሆኑን ከሚመለከተው የመንግሥት መስሪያ ቤት የተሰጠ ማረጋገጫ፣ አያይዞ ማቅረብ አለበት፡፡
- የዋና መሥሪያ ቤቱ እና ያለም ከሆነ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹን ትክክለኛ አድራሻ፣ እና
- ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ቤት የራሱ ከሆነ የባለይዞታነት ካርታ፣ የኪራይ ከሆነ በሰነድ አረጋጋጭ የተረጋገጠ የኪራይ ውል እና ስለቤቱ አድራሻ ከቀበሌ መስተዳድር የሚሰጥ ማረጋገጫ፡፡
አመልካቹ የንግድ ማኀበር ከሆነ፡-
- የንግድ ምዝገባ የምሥክር ወረቀት፣
- የማኀበሩ መመሥረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ የተረጋገጠ ዋና ቅጂ፣
- የማኀበሩ ሥራ አስኪያጅ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ጉርድ ፎቶግራፍ፣
- ማመልከቻው የቀረበው በወኪል ከሆነ የተረጋገጠ የውክልና ሠነድ እና የተወካዩ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ ያቀርባል፡፡
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 34 የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብትና ግዴታዎችን ይደነግጋል በዚህም መሰረት ማንኛውም የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው፡-
- የንግድ ፈቃድ የተሰጠባቸውን የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን በአንድ ሥፍራ ወይም ቤት ውስጥ አጣምሮ መሥራት በተጠቃሚው ሕዝብ ጤንነትና ደህንነት ወይም ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ እነዚህን ሥራዎች በተለያዩ ስፍራዎች ወይም ቤቶች በተናጠል የማካሄድ፣
- በሸማቾች ወይም በደንበኞች ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ፣ ወይም የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ሥራዎችን አጣምሮ ያለመሥራት፣
- የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልጽ ሥፍራ በሚታይ ቦታ ማመልከት ወይመ በንግድ ዕቃዎቹ ላይ የመለጠፍ፣
- የንግድ ሥራ ፈቃዱን በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ቦታ የማስቀመጥ፣
- የንግድ ፈቃዱን ለሌላ ለማንኛውም ሰው እንዲገለገልበት ወይም በመያዣነት አንዲይዘው ወይም አንዲከራየው አሳልፎ ያለመስጠት፣
- የንግድ ሥራ ፈቃድ በስሙ የተሰጠው የንግድ ማህበር በፍርድ ቤት እንዲፈርስ ሲወሰንበት የተሰጠው የንግድ ሥራ ፈቃድ በሥራ ላይ ያለማዋል፣ መብትና ግዴታዎች አሉበት፡፡
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 36 ላይ የንግድ ስራ ፈቃድ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜና እድሳት አስመልክቶ እንደሚከተለው ይደነግጋል፡፡ ይሄውም፡-
- የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልጽ ሥፍራ የሚታይ ቦታ ማመልከት ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ የመለጠፍ፣
- የንግድ ሥራ ፈቃዱን በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልጽ የሚታይ ቦታ የማስቀመጥ፣
- የንግድ ፈቃዱን ለሌላ ለማንኛውም ሰው እንዲገለገልበት ወይም በመያዣነት እንዲያይዘው ወይም አንዲከራየው አሳልፎ ያለመስጠት፣
- የንግድ ሥራ ፈቃድ በስሙ የተሰጠው የንግድ ማህበር በፍርድ ቤት እንዲፈርስ ሲወሰንበት የተሰጠው የንግድ ሥራ ፈቃድ በሥራ ላይ ያለማዋል፣ መብትና ግዴታዎች አሉበት፡፡
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 36 ላይ የንግድ ስራ ፈቃድ ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜና እድሳት አስመልክቶ እንደሚከተለው ይደነግጋል፡፡ ይሄውም፡-
- የንግድ ሥራ ፈቃዱ የተሰጠበት ወይም የታደሰበት የበጀት ዓመት ካበቃ በኋላ ባሉት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ ተገቢው ክፍያ ተፈጽሞ ካልታደሰ ለነጋዴው የተሰጠው የንግድ ሥራ ፈቃድ በማንኛውም ሁኔታ በሥራ ላይ ሊውል አይችልም፡፡
ይህም ማለት በየአመቱ ከሐምሌ አንድ እስከ ጥቅምት 30 ባሉት ጊዜያት የንግድ ሥራ ፈቃዳችንን ማሳደስ አንዳለብን የሚገልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አንቀጽ 36/3 መሰረት ቀጥሎ ባሉት የህዳር እና የታህሳስ ወራት የንግድ ሥራ ፈቃዱ ያለቅጣት ሊታደስ እንደሚችል ይገልፃል፡፡
- በእነዚህ የፈቃድ ማሳደሻ ጊዜያት ውስጥ የንግድ ሥራ ፈቃዱን ማሳደስ ካልቻለ ከጥር 1 ቀን እስከ ሰኔ 30 ላለው ጊዜ ከፈቃድ ማሳደሻው በተጨማሪ ፈቃድ ማሳደሱ ለዘገየበት ለጥር ወር ብር 2,500.00 (ሁለት ሺ አመስት መቶ ብር) እና ለሚቀጥለው እያንዳንዱ ወር ብር 1,500.00 (አንድ ሺ አምስት መቶ ብር) ቅጣት በመክፈል ፈቃዱን ያሳድሳል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ የንግድ ፈቃዱን በቅጣት ማሳደስ ያልቻለ ሰው የንግድ ሥራ ፈቃዱ ይሰረዝበታል፡፡
- የንግድ ሥራ ፈቃድ ለእድሳት ይዘን በምንቀርብበት ጊዜ አንቀጽ 36/8 ላይ በግልጽ እንደሰፈረው የገቢ ግብር፣ የቦታ ግብር፣ የሰራተኛ ገቢ ግብር፣ ሌሎች ግብሮችና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ክፍያዎችን እና ሌላ ማናቸውም ለመንግሥት የሚከፈል ዕዳ ለመክፈሉ አግባብ ላለው ባለሥልጣን በአድራሻው የተፃፈ ማረጋገጫ ማቅረብ፣ የታደሰ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት፣ እና የፈቃድ ዕድሳት ማመልከቻ ቅጽ በመሙላት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡
እዚህ ላይ የንግድ ስራ ፈቃዳችንን ለማሳደስ ግብር ወይም ሌላ ማንኛውም ከመንግሥት የሚፈለግበትን ክፍያ የመክፈሉ በግብር አስከፋዩ መስሪያ ቤት የሚሰጠን ማረጋገጫ ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ በአንድ ወር ውስጥ የንግድ ሥራ ፈቃዳችንን ማሳደስ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻልን ግን የእነዚህ ማስረጃዎች የአገልግሎት ጊዜ ስለሚያበቃ እንደገና የሚፈለግብንን እዳዎች ከፍለን በድጋሚ ለማውጣት እንገደዳለን ማለት ነው፡፡
2.ግብር
ሀ. ግብር ምንድነው
ግብር የዜጎች ሁሉ መብትም ግዴታም ነው፡፡ በአንድ ሀገር የተረጋጋ መንግስታዊ ስርዓት እንዲኖር፣ ዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባሮቻቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማከናወን እንዲችሉና በግለሰብ ደረጃ ሊሟሉ የማይችሉና የጋራ መገልገያ የሆኑ እንደ መንገድና የፖሊሳዊ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚቻለው ከምንከፍለው ግብር ነው፡፡ ስለዚህ ግብር የምንከፍለው በመንግስት በኩል ለምናገኛቸውና በቀጥታ ክፍያ ለማንጠየቅባቸው አገልግሎቶች ነው ማለት ነው፡፡
በመሆኑም ግብር በህግ ስለተደነገገ ወይም የግድ መክፈል ስላለ ብቻ ሳይሆን አንድ ሥራ ፈጣሪ ወይም በንግድ ሥራ ለመሰማራት የሚፈልግ ሰው ያሰበውን ዓላማና ግብ ለማሳካት የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በሚከፍለው ግብር የተመቻቹ መልክ አጋጣሚዎች ላይ ሆኖ መስራት ከቻለ ብቻ መሆኑን በመረዳት ተነሳሽነት የሚፈለግበትን ግብር በወቅቱ መክፈል አለበት፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ የሚፈለግብን ግብር የትኛው ነው? መቼ ነው መክፈል ያለብኝ? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ እርግጥ ነው ማኝም ሰው የተረዳውንና ያመነበትን ነገር ለማድረግ የሚያዳግተው ነገር አይኖርም፡፡ ችግሩ ግን ስለ እነዚህ ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ መኖሩ ላይ ነው፡፡ የብዙዎቻችን ችግርም ይሄውነው፡፡ በተለይ አዲስ ወደ ንግድ ሥራ የምንገባ ሰዎች ስለ ግብር በቂ ግንዛቤ የለንም፡፡
በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት ከ83 ከመቶ በላይ የሚሆኑ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች የተርን ኦቨር ታክስ በወቅቱ መክፈል ባለመቻላቸው የተቀጡ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንተርኘራይዞች ሊቀጡ የቻሉበት ዋነኛው ምክንያት ቀድሞውኑ ስለተርን ኦቨር ታክስም ሆነ ሌሎች የታክስ አይነቶች እውቀቱ ስላልነበራቸው ነው፡፡ አዳዲስ ሥራ ፈጣሪዎች ከዚህ መገንዘብ ያለብን አንድ ሥራ ለመስራት ስንዘጋጅ የሚፈለጉብን ግዴታዎች ወይም ኃላፊነቶችን ምንድናቸው የሚለውንም ጭምር ከግምት ወስጥ ማስገባት እንዳለብን ነው፡፡ የግብር አይነቶችና የመክፈያ ወቅቶችን በሚመለከት ቀጥሎ በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
ለ. የግብር አይነቶች
የግብር ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነሱም ቀጥተኛ ታክስ እና ቀጥተኛ ያለሆነ ታክሶች በመባል ይታወቃሉ፡፡
ሀ. ቀጥተኛ ታክስ /Direct Taxes/
ቀጥተኛ ታክስ የሚባለው ማንኛውም ግለሰብ ወይም ድርጅት በየትኛውም የስራ መስክ ይሰማራ ከሚያገኘው ገቢ ላይ የሚከፍለው የታክስ አይነት ነው፡፡ በዚህ ስር የሚካተቱ የግብር ወይም ታክስ አይነቶችም በገቢ ግብር አዋጁ አንቀጽ 8 ላይ እንደሚያመለክተው፡-
- ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ግብር፣
- ከኪራይ ከሚገኝ ገቢ ግብር፣
- የንግድ ሥራ ገቢ ግብር እና
- ሌሎች ገቢዎች ማለትም፡-
- የፈጠራ መብትን በማከራየት የሚገኝ ገቢ፣
- ከኢትዮጵያ ውጭ ከሚሰጥ አገልግሎት የሚገኝ ገቢ፣
- በእድል ሙከራ ውድድር አሸናፊነት የሚገኝ ገቢ፣
- ቋሚ ባልሆነ ሁኔታ ከንብረት ኪራይ ከሚገኝ ገቢ፣
- ከወለድ ገቢ፣
- ከንግድ ሥራ ጋር ካልተያያዘ የካፒታል ዋጋ እድገት ጥቅም ናቸው፡፡
ለ/ ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች /Indirect Taxes/
ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶች ደግሞ ታክሱን የሚከፍሉት በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሳይሆኑ በተዘዋዋሪ የምርቱ ወይም የአገልግሎት ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ቀጥተኛ ከሆነው ታክስ ይለያሉ፡፡ እነዚህ የታክስ ዓይነቶችም የተርን ኦቨር ታክስ፣ ኤክሳይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና የቴምብር ቀረጥ ናቸው፡፡
- የተርን ኦቨር ታክስ /Turn Over Tax/
የተርን ኦቨር ታክስ በአዋጅ ቁጥር 308/95 መሰረት በተጨማሪ እሴት ያልተመዘገቡ ሰዎች በሀገር ውስጥ በሚሸጧቸው ምርቶችና በሚያቀርቧቸው አግልግሎቶች ላይ ተሰልቶ የሚከፍሉት የታክስ አይነት ነው፡፡ አከፋፈሉም፡-
- በማናቸውም በሀገር ውስጥ በሚሸጡ እቃዎች ላይ ሁለት በመቶ (2%)፣
- የስራ ተቋራጮች፣ የእህል ወፍጮ ቤቶች፣ የትራክተርና ኮምባይን ሃርቨስተሮች አገልግሎት ሁለት በመቶ (2%)እና
- ሌሎች አገልግሎቶች አስር በመቶ (10%) ሲሆን ታክሱ የሚሰላው በጠቅላላ የሽያጩ ወይም የአገልግሎቱ ዋጋ ላይ ነው፡፡
- ኤክሳይዝ ታክስ /Exeise Tax/
ኤክሳይዝ ታክስ የቅንጦት እንዲሁም መሰረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ፍላጎታቸው በማይቀንስ እቃዎች እና የኀብረተሰቡን ጤና በሚጎዱና የማህበራዊ ችግር በሚያስከትሉ እቃዎች ላይ አጠቃቀሙን ለመቀነስ ሲባል የሚጣል ታክስ አይነት ነው፡፡ ኤክሳይዝ ታክስ አገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ የተወሰኑ እቃዎች ላይ የሚጣል ሲሆን የክፍያ መጠኑም ከአስር እስከ መቶ ከመቶ (ከ10% -100%) የሚደርስ ነው፡፡
- የተጨማሪ እሴት ታክስ /Value Added Tax/
የተጨማሪ እሴት ታክስ ቀደም ሲል ይጣል የነበረውን የሽያጭ ታክስ በመተካት በስራ ላይ የዋለ የታክስ አይነት ሲሆን የሚጣለውም በማንኛውም በተመዘገቡ ሰዎች ታክስ በሚከፈልበት ግብይት፣ ነፃ ከተደረጉት በስተቀር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ በተጨማሪ እሴት ታክስ የሚከፈለው ከላይ በተገለጹት ምርትና አገልግሎቶች አጠቃላይ የሽያጭ ዋጋ ላይ (15%) አስራ አምስት ከመቶ በማስላት ነው፡፡
በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ አንቀጽ 16 መሰረት ታክስ የሚከፈልበት የንግድ ሥራ የሚያንቀሳቅስ ሆኖ በአንድ አመት ውስጥ ያከናወነው ግብይት ከብር 500,000.00 /ከአምስት መቶ ሺህ ብር/ በላይ ከሆነ መመዝገብ እንዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ ከሰባ አምስት ከመቶ በላይ ዕቃ የማቅረብና አገልግሎት የመስጠት ሥራ የሚያከናውነው ለተመዘገቡ ሰዎች የሆነ እና ከላይ በተገለፀው መሰረት ለመመዝገብ የማይገደድ ሰው በፍላጎቱ መመዝገብ እንደሚችልም እንደዚሁ በአዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡
- የቴምብር ቀረጥ /Stamp Duty/
የቴምብር ቀረጥ የሚከፈለው ሰነዶችና ውሎች ህጋዊ ማስረጃ ሆነው እንዲያገለግሉ ለማድረግ ሲሆን ይሄውም በመመስረቻና መተዳደሪያ ጽሁፎች፣ የግልግል ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ወይም በሚሰጥበት ጊዜ፣ በውል ወይም በስምምነት ሰነዶች ላይ፣ በማረጋገጫ ሰነዶች በመያዣ ሰነዶችና በንብረት ባለቤትንት ስም ማስመዝገቢያ ሰነዶች ላይ ተግባሩ ከመፈፀሙ በፊት ወይም በሚፈፀምበት ወቅት ክፍያው መፈፀም እንዳለበት የቴምብር ቀረጥ አዋጅ 110/1990 ዓ.ም ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ሐ. የግብር ከፋዮች ምደባ
በሚኒስትሮች ምክር ቤት የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 78/1994 ዓ.ም መሰረት ግብር ከፋዮች በሶስት ደረጃዎች ተመድበዋል፡፡ እነሱም፡-
- ደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች
በኢትዮጵያ ወይም በውጭ ሀገር ህግ መሰረት የተቋቋመ የህግ ሰውነት የተሰጠው ድርጅት፣ እና
የአመቱ ጠቅላላ ገቢው ብር 500,000.00 /አምስት መቶ ሺህ ብር/ የሆነ ወይም ከዚህ ብልጫ ያለው ገቢ የሚያገኝ ማንኛውም ሌላ የንግድ ሥራ በደረጃ ሀ ግብር ከፋይነት የተመደበ መሆኑን ህጉ ያስቀምጣል፡፡
ይህም ማለት በሽርክና፣ በአክሲዮን ማህበር እና በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ህጋዊ እውቅና ወይም የህግ ሰውነት የተሰጣቸው ማህበሮች ሁሉ የንግድ እንቅስቃሴያቸው ሳይገድባቸው በደረጃ ሀ ግብር ከፋይነት የተመደቡ መሆኑን እና በግል ኢንተርኘራይዝ የተመዘገበ ከሆነ ደግሞ የአመቱ ጠቅላላ ገቢው ብር 500,000.00 /አምስት መቶ ሺህ ብር/ እና ከዚህ በላይ ከሆነ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡
- ደረጃ ለ ግብር ከፋዮች
ደረጃ ለ ግብር ከፋዮች የሚባሉት አስቀድሞ በደረጃ ሀ ያልተመደበና የአመት ጠቅላላ ገቢው ከብር 100,000.00 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ በላይ የሆነ ማናቸውም የንግድ ሥራ ነው፡፡ ይህም ማለት የንግድ ማህበራት ቀድሞውኑ በደረጃ ሀ የተመደቡ ሲሆን በዚህ ደረጃ ላይ የሚመለከታቸው የግል የንግድ ኢንተርኘራይዞችን ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡
- ደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች
ደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የሚባሉት አስቀድሞ ከላይ በደረጃ ሀ እና ለ ከተጠቀሱት በስተቀር በግብር አስገቢው ባለስልጣን የአመት ጠቅላላ ገቢው እስከ ብር 100,000.00 /አንድ መቶ ሺህ ብር/ ይደርሳል ብሎ የሚገምተው የንግድ ሠራን እንደሚያካትት ህጉ በግልጽ አስቀምጧል፡፡
መ. የግብር መክፈያ ወቅት
የግብር መክፈያ ወቅት እንደየ ግብር አይነቱ እና የግብር ከፋዮች ደረጃ የተለያየ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የትኛው ግብር ከፋይ የትኛውን ግብሩን መቼ መክፈል አንዳለበት እንመለከታለን፡፡
የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን በተለይም ደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች በአመቱ መጨረሻ የሀብትና እዳ መግለጫ አና የትርፍና ኪሳራ መግለጫ እንዲሁም ያልተጣራው ትርፍ የተሰላበትን የሂሳብ አሰራር ዘዴ፣ የሥራ ማስኬጃና የአስተዳደር ወጪን፣ ስለ እርጅና የተደረገውን ቅናሽ እና ከመጠባበቂያ ወጪ የተደረገውንና የመጠባበቂያውን ሂሳብ የሚያሳይ ሰነድ ይዘው መቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ደረጃ ለ ግብር ከፋዮች የትርፍና ኪሳራ መግለጫ ብቻ ይዘው እንዲቀርቡ ህጉ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት የደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች ግብር የሚታሰበው የሂሳብ ሰነዳቸውን መሰረት አድርጎ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡ የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች ግን ግብር የሚከፍሉት በአዋጁ አንቀጽ 68/1 አና 2 መሰረት በቁርጥ ግብር አወሳሰን ዘዴ ነው፡፡
ማንኛውም ግብር ከፋይ ግብሩን ለመክፈል ሲቀርብ በገቢ ማስታወቂያ ቅጽ ላይ ገቢውን ለመወሰን የሚያስችል ተገቢውን መረጃ በመሙላትና በማያያዝ በገቢ ማስከፈያ ጊዜያት መቅረብ ያለበት ሲሆን የገቢ መክፈያ ጊዜያትም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
- ከመቀጠር የሚገኝ ገቢ ላይ ግብር የሚከፈለው ቀጣሪው ተቋም በየወሩ ከሰራተኞች ቀንሶ ከዚያው ወር መጨረሻ አንሰቶ እስከ 30 ቀናት ድረስ ይሆናል፡፡
- ከኪራይ የሚገኝ ገቢ ለንግድ ሥራ ገቢ ግብር በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ ግብሩን ይከፍላል፡፡
- የንግድ ሥራ ገቢ ግብር የሚከፈለው፡-
- የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች በየአመቱ ከላይ የተገለጹትን መረጃዎች በመያዝ ከሂሳብ አመት መጨረሻ እስከ አራት ወራት ድረስ ነው ይህም ማለት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጥቅምት 30 ቀን ድረስ ይሆናል ማለት ነው፡፡
- የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች በየአመቱ ከላይ የተገለጹትን መረጃዎች በመያዝ ከሂሳብ አመት መጨረሻ እስከ ሁለት ወራት ድረስ ነው፡፡ ይህም ማለት ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ጳጎሜ 5(6) ቀን ድረስ ይሆናል፡፡
- ደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች በየአመቱ ከሐምሌ 1 እስከ 30 ቀን ድረስ ይሆናል፡፡
- የተርን ኦቨር ታክስ ከፋዮች እያንዳንዱ የሂሣብ ጊዜ በተጠናቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አስታውቀው የመክፈል ግዴታ ያለባቸው ሲሆን የሂሳብ ጊዜውም፡-
- የደረጃ ሀ ግብር ከፋዮች የሆኑና በተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት የመመዝገብ ግዴታ የሌለባቸው ሁሉ በየወሩ አስታውቀው መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡
- የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች በኢትዮጵያ የበጀት ዓመት ወይም በገቢ ሰብሳቢው መስሪያ ቤት ሲፈቀድ በአውሮፖ ዘመን አቆጣጣር በአመቱ የመጀመሪያ ቀን አንስቶ በየሶስት ወሩ ይከፍላሉ፡፡
- የደረጃ ሐ ግብር ከፋዮች የበጀት ዓመቱ እንዳለቀ፣ ወይም በአመት አንድ ጊዜ ከንግድ ሥራ ገቢ ግብራቸው ጋር ይከፍላሉ፡፡
ግብር ከፋዮች በተቀመጠላዠው የተርን ኦቨር ታክስ መክፈያ ጊዜ ውስጥ ታክስ የሚከፈልበት ምንም አይነት የንግድ ልውውጥ ባለመማድረጋቸው ምክንያት ሊከፍሉት የሚገባቸው ግብር ባይኖራቸው ይሄንኑ ለግብር አስከፋዩ መስሪያ ቤት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ማስታወቅ አለባቸው፡፡ ይህንን ካላደረጉ ግን በህጉ መሰረት ቅጣት ሊያስከትልባቸው እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡
.የኤክሳይዝ ታክስ
- ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ እቃዎች ላይ የኤክሳይዝ ታክስ የሚከፈለው እቃዎቹ ወደ ሀገር ሲገቡ አስመጭው ከጉሙሩክ ክልል በሚያወጣበት ጊዜ ነው፡፡
- በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ዕቃዎችን በሚመለከት እቃዎቹ ከተመረቱበት ቀን አንስቶ በ30 ቀናት ውስጥ የሚከፈል ይሆናል፡፡
- የተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበ ማንኛውም ግብር ከፋይ በአንድ የሒሳብ ጊዜ ውስጥ ታክስ የመክፈል ግዴታ ያለበት ቢሆንም ባይሆንም በእያንዳንዱ የሂሳብ ጊዜ ሂሳቡን ለታክስ ባለስልጣኑ ማስታወቅ እንዳለበት ህጉ የሚደነግግ ሲሆን ለእያንዳንዱ የሒሳብ ጊዜ የተጨማሪ እሴት ማስታወቅ ያለበት ከሒሳብ ጊዜው ቀጥሎ ያለው ወር የመጨረሻ ቀን ከማለፉ በፊት እንደሆነ ጭምር ይገልፃል፡፡
ማንኛውም ግብር ከፋይ እስካሁን የተመለከትናቸውን የግብር አይነቶች በትክክለኛ የመክፈያ ወቅት መክፈል ያለበት ሲሆን በጊዜውና በወቅቱ አለመክፈል ደግሞ ቅጣትን የሚያስከትል እንደሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡ ግብር የምንከፍለው ቀደም ሲል በዚሁ ርዕስ መጀመሪያ ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ለራሳችን መሆኑን በመግንዘብ እና ግብርን በወቅቱ መክፈል ጊዜን ገንዘብንና ጉልበትን የሚቀንስ በመሆኑ ለቅጣት ከመዳረጋችን በፊት የግብር መክፈያ ኘሮግራም ለራሳችን ለማውጣት መክፈል ከትክክለኛ ሥራ ፈጣሪ ወይም ኢንተርኘርነር የሚጠበቅ ተግባር ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው፡፡