ደስተኛ እንዳንሆን የሚያደርጉ 10 ልማዶች
ደስታ ብዙዎች ማግኘት የሚፈልጉት ትልቅ የህይወት ስኬት ነው፤ ሆኖም ግን የሚፈለገውን ያህል በሰዎች ዘንድ እየተገኘ አይደለም ለዚህም ነው ብዙ ሰዎች በሕይወቴ ደስተኛ ለመሆን የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም ሲሉ የሚስተዋሉት፤ ታዲያ ደስታን እንዴት ማግኘት ይቻላል; ደስተኛ እንዳንሆን የሚያደርጉንስ ነገሮች ምንድ ናቸው?
ደስተኛ እንዳንሆን የሚያደርጉ 10 ልማዶች
1.የማያቋርጥ ቅሬታ ማቅረብ
ደስተኛ እና ስኬታማ ሰዎች በተደጋጋሚ ቅሬታ አያቀርቡም፤ ሆኖም ግን በአንጻሩ ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ሁሌም በማያቋርጥ ቅሬታ ውስጥ ናቸው፡፡ ሌሎች ሰዎች ደስተኛ በሚሆኑባቸው ነገሮች ራሱ የሚያነሱት የሆነ አሉታዊ ነገር ይኖራል፤ ስለዚህም የራሳችን ሁኔታ ምንም ይሁን ምንም መቀበል እና ለማስተካከል መሞከር ነው እንጂ በተደጋጋሚ ቅሬታን የምናቀርብ ከሆነ ደስታን ከእኛ እያራቅነው ነው የምንሄደው።
2.ከአቅማቸው በላይ ይኖራሉ
ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ሁልጊዜም ራሳቸውን ፉክክር ውስጥ ይከታሉ፤ ደስታንም ማግኘት የሚችሉት ከእነሱ የተሻሉት ሰዎች ያላቸው ነገሮች ሲኖራቸው ይመስላቸዋል፤ በዚህም አቅማቸው ከሚፈቅድላቸው በላይ ወጪ እያወጡ ነገሮችን ይገዛሉ፤ ይህም ገንዘባቸውን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን ባወጡት ገንዘብ ደስታን እንዳላገኙ ሲረዱ በጸጸት ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፤ ይህም ህይወታቸውን ሰላም፣ ደስታ እና እረፍት የሌለው ያደርገዋል፡፡
3.የተለያዩ ሱሶች
ምግብም ሆነ መጠጥ በልኩ ሲሆን የምንወስደው ለመኖር ወይም እስትንፋስን ከማስቀጠል ዘሎ ያዝናኑናል፤ ሆኖም ግን እነዚህ ነገሮች በተለይ ደግሞ መጠጥ እና አደንዛዥ ዕፆች ከመጠን በላይ ሲወሰዱ ሱስ የሚሆኑበት አጋጣሚ በጣም ሰፊ ይሆናል፤ ስለሆነም ደስተኛ ያልሆኑ ሰዎች ከሚያዳብሩት ልምዶች መካከል አንዱ ሱሶችን ማዳበር ነው ወይም ደግሞ ባጭሩ ደስታችንን ከሚነጥቁን ነገሮች መካከል ሱስ አንዱ ነው፡፡
4.ባለፈው ነገር መቆጨት
ባለፈው ህይወታችን የሰራናቸው እና መልሰን ልናስተካክላቸው ወይም ደግሞ ልናርማቸው የማንችላቸው አያሌ ነገሮች አሉ፤ ታዲያ እነዚህ ነገሮች ደግመው ደጋግመው እየመጡ በፀፀት አለንጋ ይገርፉናል፡፡ አርግጥ ቁጭት እና ጸጸት በጥሩ ሁኔታ ከተጠቀምንበት ለተሻሉ ነገሮች ያዘጋጁናል፤ ሆኖም ግን ጸጸት በሌላኛው ጽንፍ ደግሞ አጅግ በጣም ከባድ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፤ የተለያዩ ጥናቶች እንደጠቆሙትም ተደጋጋሚ የሆነ ጸጸት እና ቁጭቶች ባለፈው ህይወታችን በወሰድናቸው ውሳኔዎች ጋር የተገናኙ አስተሳሰቦች ትልቅ ጭንቀት እና ድባቴ ውስጥ እንደሚከቱን ጠቁመዋል፡፡ ጥናቶቹ ጨምረው እንደደገለጹት ጸጸትን ለመከላከል ወይም ለመቋቋም የተለያዩ መንገዶችን መከተል ይኖርብናል ብለዋል ከእነዚህም መካከል ከስህተቶች መማር ያለብንን ነገር ነቅሰን ማውጣት፣ ነገሮችን መቀየር ካልቻልን ደግሞ አምኖ መቀበል በተጨማሪም ያሉትን እና የተፈጠሩትን ሁኔታዎች በአዎንታዊ መልኩ ማየት መልካም ነው ይሉናል፡፡
5.ስለወደፊት አብዝቶ መጨነቅ
አንድ ነገር እሙን ነው የአሃ ቤተሰቦች፤ ነገን የምንኖረው ዛሬ ላይ በምናደርጋቸው ነገሮች ላይ ተመስርተን ነው፣ ቢሆንም ስለ ነገ ከመጠን በላይ መጨነቅ አሁን ያለውን ህይወታችንን ከማመሳቀሉም በላይ እርግጠኛ ያልሆንበትን ነገን መልካም አያደርገውም፤ ስለሆነም በእርግጠኝነት የኛ ስላልሆነው ነገ አብዝተን መጨነቅ ደስተኛ እንዳንሆን ያደርገናል፤ ስለሆነም ዛሬን ኑሩ፤ ይህ ማለት ግን ነገን ፈጽመን እንርሳው ማለት አይደለም፤ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ነገን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዛሬን በሙላት መኖር አለብን፡፡
6. ህልማችንን እና እቅዶችን ማዘግየት
ብዙዎቻችን በሕወታችን ውስጥ ማሳካት የምንፈልገው እቅድ አለን፤ ወይም ደግሞ መሆን የምንፈልገው ህልም አለን፤ እነዚህንም ህልሞች እና እቅዶችንም ለማሳካት ዘወትር ደፋ ቀና እንላለን፤ ሆኖም ግን የቀን ተቀን የሆነው ህይወታችን ማለትም መስራት፣ መብላት፣ መጠጣት እና መተኛት እንዲሁም ለዚህ ብለን የምናደርጋቸው ነገሮች ይህን ነገር ወደ ጎን ገፋ እንድናደረገው ያደርጉናል፡፡
ስለሆነም ችሎታችንን እና እውቀታችንን በማስተባበር ህልማችንን ለማሳካት የማንጠቀምበት ከሆነ ደስታችንን እያጣን ነው የምንሄደው፤ ቢሆንም ዋናው ከባድ ነገር የመጀመሪያውን ደረጃ ደፈር ብሎ መግባት ነው፤ እንደምንም ብለን ከጀመርነው ግን ለማሳካት ጥረት እና ቆራጥነት ነው የሚጠይቀን፡፡ ህልምን እና ዕቅድን ማዘግየትም ደስተኛ ለመሆን ከሚያግዱን ነገሮች መካከል ይገኝበታል፡፡
7. ስለ ሰዎች ማውራት
ቁጭ ብለን ቡና ስንጠጣ ወይም ደግሞ ደግሞ አንድ ሁለት እያልን እያነሳን ከምንጥላቸው ነገሮች መካከል ስለ ሌሎች ሰዎች ስኬት ወይም ደግሞ የከፍታ ቦታ ላይ መድረስ በአሉታዊ መልኩ ልናወራ ወይም ደግሞ ልናማ እንችላለን፤ ታዲያ የዚህ ሁሉ ሀሜት መነሻው አብዛኛውን ጊዜ ቅናት ነው፡፡ ሆኖም ግን ደስተኛ እና በራሳቸው የሚተማመኑ ሰዎች ሌሎች ሰዎችን የማማት ተግባር ውስጥ አይገቡም፤ ይልቁንም ከስኬታማ ሰዎች የሚማሩትን ነገር በመውሰድ እሴት አድርገውት ይጥላሉ።
8. ቅሬታን መያዝ
መቼም ሰው እና ሰው ሆኖ የማይጋጭ አይኖርም፤ ለዚህም ነው አባቶች እግር እና እና እግር እንኳን ይጋጫል ብለው የሚያስታርቁት፤ ከሌሎች ተጨማሪ አሉታዊ ስሜቶች ጋር ተደማምሮ ቅሬታን መያዝም መጥፎ የሆነ ውጤት ነው የሚኖረው፤ ስለሆነም በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ከስራ ባልደረባ፣ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ እና ከተለያዩ ወዳጆች ጋር ያለንን ቅሬታ መርሳት፣ ይቅር ማለት እና በመተው ወደሚቀጥለው የህይወት ደረጃ መሄድ ይኖርብናል።
9. የአመጋገብ ስርዓት
የአመጋገብ ዘያችን አብዛኛውን የህይወት መስመራችንን የተስተካከለ እና የተቃና እንዲሆን ከሚያደርጉ ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፤ ለዚህም ይረዳን ዘንድ የተለያዩ ነገሮችን በውስጣቸው የያዙ ምግቦችን መመገብ ይመከራል፤ ካልሆነ ግን በጊዜ ሂደት መጥፎ የጤና ደረጃ ላይ እንድንደርስ፣ አላስፈላጊ ክብደት እንድንጨምር፣ ድባቴ ውስጥ እንድንገባ፣ ኃይል እንዳይኖረን፣ ንቃታችንም ዝቅተኛ እንዲሆን ፣ ያደርጋል እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደግሞ በተራቸው ደግሞ ደስተኛ እንዳንሆን ያደርጉናል፡፡
10 ችግሮቻችንን ማስፋፋት
ሁሉም ሰው በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሙታል፤ ታዲያ እነዚህ ችግሮች ሲያጋጥሙን በቅድሚያ ረጋ ብለን መፍትሄ ለመፈለግ ከመጣር በፊት የሚቀደመን ነገር ሲሆን ስሜታዊ መሆን ነው፤ ይህ ደግሞ ተጨማሪ ችግሮችን እየፈጠረብን በመምጣት ደስታ ይበልጥ እንደራቀን እንዲቀር ያደርጋል፤ ስለሆነም ችግሮችን በየደረጃቸው እየፈታን መሄድ መልካም ነው፡፡
ምንጭ፦ አሃ ስነ-ልቦና