የገቢ ምንጫችን ምንያህል አስተማማኝ እና ትክክለኛ ነው?

Published by Abreham D. on

በዚህ ጊዜ ለኑሮ ከሚያስፈልጉን ግብአቶች ዋነኛው ገንዘብ እንደሆነ እሙን ነው ይህ ግን ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎቶች የሉንም ማለት አይደለም ጤና፣ ማህበራዊ ህይወት እና መንፈሳዊ ህይወት በተለይ ለሰው ልጅ የተሟላ ማንነት እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ እናምናለን ዛሬ የገንዘብ ፍላጎታችንን በተመለከተ ብቻ እንወያያለን።

የገቢ ምንጫችን ምንያህል አስተማማኝ እና ትክክለኛ እንደሆነ ለማየት እንደሚከተለው ከፋፍለን እንመልከታቸው።

ገቢ ያለን ማናችንም ሰዎች የገቢ ምንጫችን በዋናነት ከነዚህ ከአራት መንገዶች ይመደባሉ።

1. ከቅጥር የሚገኝ ገቢ፡- በግልም ሆነ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት በወር አንድ ጊዜ የሚገኝ ገቢ ሲሆን፡ ይህ የገቢ ምንጭ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የተሰማራበት ሲሆን ቆየት ባሉ ጊዜአቶች የተከበረና ህይወትን የሚለውጥ የኑሮ መስክ ነበር በአሁኑ ሰአት ግን ከእጅ ወደአፍ ያላለፈ፣ የጊዜ ነፃነት የሌለበት፣ መብት የሚጣስበት፣ የውሳኔ ነፃነት የሌለበት፣ እጅ ሳይገባ ቀድሞ ከፍተኛ ግብር ሚከፈልበት፣ የገቢ ምንጭ ሲሆን መልካም ጎኑ ተብሎ መነሳት የሚችለው በየወሩ ድርጅቱ ቢከስርም ቢያተርፍም ሳይቋረጥ መምጣቱ ነው።
ይህ የገቢ አይነት ሁላችንም እንደምንስማማበት ህይወትን የሚቀይር፡ ሀብት እዲኖረን የሚያደርግ አይደለም። በቅጥር ውስጥ ገብተው ልምድ አጊንተው የተወሰነ ገንዘብ አጠራቅመው ወደ ግል ስራ ገብተው ስኬታማ የሆኑ ብዙ ሰዎችን ተወልክተናል። አገራችን ብዙ ተቀጣሪ ሰራተኞችን ትፈልጋለች ሁሉም ሰው የግል ባለሀብት መሆን አይችልም የቅጥር ህይወት የሚመጥናቸው ወጥቶ መስራት መታገል፡ መልፋት ማይፈልጉ ትንሽም ብቶን ቋሚ የወር ገቢ አጊንተው መኖር የሚመርጡ እንዳሉ ሁሉ በቅጥር ውስጥ ሆነው የራሳቸውን ስራ ለመስራት አላማቸውን ለማሳካት እንቅልፍ የሌላቸው ሌት ተቀን የሚያስቡ በስራቸው ደስተኛ ያልሆኑ ብዙዎች እንዳሉ እናውቃለን። ሀብት ማፍራት አላማ ላለው ሰው ይህ የገቢ ዘርፍ ትክክለኛ አይደለም።
(በቅጥር ውስጥ የምንገኝ እንደእሳት የሚቀጣጠል ወጥቶ የግልስራ የመስራት ራዕይ ለላን እንዴት ህልማችንን ማሳካት እንደምንችል በቅርቡ እንወያያለን)

2. ከግል ስራ የሚገኝ ገቢ፡- በራስ ጉልበት እና በራስ እውቀት ለእራሳቸው ከሚሰሩ ሰዎች ገቢ ይመደባል። ለምሳሌ ደላሎች፣ አናፂፆች፣ ሊስትሮ፣ የጉልበት ሰራተኞች፣ ሱቅ በደረቴ እና ሱቅ በመስኮትን ጨምሮ የታክሲ ባለቤቶችን አካቶ አብዛኞቹ እራሳቸውን ቀጥረው ሙሉ ጊዜአቸውን ለራሳቸው የሚሰሩ ናቸው።
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከለኛ የጊዜ ነፃነት ሲኖራቸው የትርፋቸውም (የገቢያቸውም) መጠን እንደየ ስራቸው መጠን የሚወሰን ነው፡ የመንግስት የገቢ ግብር በጥቂቱ ብቻ ሚነካቸው ናቸው።
በስራቸው ላይ ሙሉ የውሳኔ ነፃነት ሲኖራቸው አለቃቸውም ስራቸው ነው። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በሀብት ደረጃ የሚለወጡት ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኞቻችን ግን እዛው በነበርንበት የግል ስራ ሳንለወጥ እንቀራለን ለምሳሌ ሰፈር የምናውቃቸው ጫማ ሰፊ እና ልብስ ሰፊዎች ወደ ጫማ እና ልብስ ማምረቻ ሳያድጉ እስከ መጨረሻው የተቀደደውን እየሰፉ አእጅ ወደአፍ የሚኖሩ ብዙ ናቸው። አንዳንድ የሰፈራችን ሱቆችም በነበሩበት ሳይለወጡ ለረጅም ጊዜአት ተመልክተናል። አናጢም ደላላም የሆነ ሰው ሁሌም የሚያገኘውን እየበላ ባለበት የሚኖረው ይበዛል። ከላይ ለተጠቀሱት የግል ስራዎች ውስጥ የምንገኝ ሰዎች ላለመቀየራችን ዋና ምክንያት አስቀምጬ ልለፍ። የግል ስራ እየሰራን እድሜያችንን ሙሉ የማንቀየረው የገቢ ምንጫችን የተሳሳተ ስለሆነ ሳይሆን በስራችን ላይ እራዕይ ስለሌለን እና ያንን ለማሳካት ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ስላልሆንን ነው በምሳሌ ሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ያላት ሴት ይህ ሱቅ ወደ ትልቅ ሱፐር ማርኬትየማሳደግ ራዕይ ስለሌላት እና ይህን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ስላልሆነች ነው። አናፂ፣ ደላላ፣ ጫማሰፊ፣ ልብስ ሰፊ፣ የኮስሞቲክስ፣ የልብስ ሱቅ፣ የታክሲ ባለቤቶች እንዲሁም በሌሎች የግል ስራዎች ውስጥ የምትገኙ የስራ ፈጣሪዎች የተሰማራችሁበት የገቢ ዘርፍ ተመራጭ ቢሆንም በየጊዜው የግል ስራችሁን ትርፋማነት ለማሳደግ ራዕይ እና ትጋት ሊኖረን ይገባል። (እንዴት አነስተኛዋን የግል ስራ ወደትልቅ ሀብት መቀየር እንችላለን የሚለውን በቅርቡ የምንወያይበት ይሆናል)

3. ከድርጅት የሚገኝ ገቢ፡- ይህ የገቢ አይነት ሰዎች ከአመታት በፊት ለፍተው ባቋቋሙት ንግድ፣ ድርጅት፣ ወይም በገነቡት ቤትና ህንፃ፣ መኪና፣ ማሽን ኪራይ የሚያገኙት ገቢ ነው ይህ ከግልስራ ገቢ የሚለየው ባለቤቱ ኖረም አልኖረም ቀድሞ በፈጠረው ሀብት በየጊዜው ገቢ የሚያገኝበት ዘርፍ ነው። ከፍተኛ የጊዜነፃነት ያለበት አገራዊ አስተዋፆ ያለው ከፍተኛ ገቢ የሚገኝበት ዘርፍ ነው። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከፍተኛ የገንዘብ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ እንዲሁም የረዥም ጊዜ ድካም ልምድ እንዲሁም ኮኔክሽን ይፈልጋል። ወደዚህ ትልቅ ቦታ ለመድረስ ራዕይ ከትጋት ገር ሊኖረነሸ ይገባል።

4. በህገወጥ መንገድ የሚነኝ ገቢ፡- በዚህ ዘርፍ ብዙዎች በአሁን ሰአት በአቋራጭ፣ ባልተገባ መልኩ ህገወጥ በሆነ መንገድ፣ የሰውን እምነት በመካድ እዲሁም በስርቆት በአጠቃላይ በወንጀል ሀብት ለማግኘት ተሰማርተው ይገኛሉ። በየትኛውም አለም በየትኛውም ዘመን በዚህ አይነት መንገድ ሀብት ያፈራ በዘመኑ አልያም በልጆቹ በእጥፍ ዋጋ ያልከፈለ የለም፡ በተለይ የአዕምሮ ሰላም በማጣት ለእብደት እና ያለጊዜአቸው ለሞት ይዳረጋሉ ብዙዎች ለእስር ሲጋለጡ ተመልክተናል። ሀብት ማፍራት የሚያስደምመው ደስታም የሚኖረው በህጋዊ መንገድ በላባችን ታማኝ ሆነን ማህበረሰቡን አገልግለን ችግር ፈተን ስናገኘው ነው። በዚህ አይነት መንገድ የተሰማራን ብዙዎች በየመስሪያ ቤቱ ሀላፊነታችንን በመሸጥ በሙስና ሀገርን እየገደልን ለማደግ ምንሞክ ዛሬ ነገ ሳንል ወደትክክለኛው ሀገርን እራስንም ወደሚጠቅም የሀብት ምንጭ መመለስ ይጠበቅብናል ከኛ ጋር ወደፊት በምናረጋቸው ውይይቶች የተሻሉ አማራጮቾን እንሰጣችሗለን።

ከላይ ከተጠቀሱት የገቢ ምንጮች እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ ጉዳትና ጥቅም እንዳላቸው ለማስቀመጥ ሞክረናል። እኛ የምንገኝበትን ዘርፍ በመለየት በማመዛዘን ማግኘት የምንፈልገውን እንዴት ማግኘት እንዲሁም መሆን የምንፈልገውን እንዴት መሆን እነደምንችል እንወያያለን።

select another Language »