የንግድ ድርጅት ምስረታ አይነቶች
የንግድ ድርጅት ምስረታ አይነቶች
የንግድ ድርጅት አይነቶች
በአደረጃጀታቸውና በአሰራራቸው የተለያዩ የንግድ ድርጅቶች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ድርጅቶችን ለትርፈ የተቋቋሙና አትራፊ ያልሆኑ ብለን በሁለት መክፈል እንችላለን፡፡ እንደገናም በግል ባለቤትነት የተያዙ እና የመንግስት ብለን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ በእኛ ሀገር በመንግስት የተያዙ የንግድ ድርጅቶችን ሳይጨምር ሶስት አይነት የንግድ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን እነሱም፡-
- የግለሰብ ነጋዴ
- የንግድ ማህበራትና
- የኀብረት ሥራ ማህበራት ናቸው፡፡
እነዚህ የንግድ ድርጅቶች እያንዳንዳቸው የተለያየ ባህሪና ውስጣዊ አደረጃጀት ያላቸው ሲሆን የተለያየ ጠቀሜታም አላቸው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው ወደ ንግድ ተግባር ከመግባቱ በፊት ከእነዚህ የንገድ ድርጅት አይነቶች የበለጠ የሚስማማቸውን በመምረጥ ህጋዊ እውቀና ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የተሻለ የሚሉትን ለመምረጥ ደግሞ ስለእያንዳንድ የንግድ ድርጅት አይነት በቂ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ስለ እነዚህ የንግድ ድርጅቶች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡
1.የግል ኢንተርኘራይዝ ወይም የግለሰብ ነጋዴ
ይህ የንግድ ድርጅት አይነት በአንድ ሰው የግል ሀብት የሚመሰረትና የሚተዳደር ሲሆን የድርጅቱ ባለቤት በድርጅቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ብቸኛ ውሳኔ ሰጭ የሆነበት ነው፡፡ የዚህ አይነት ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ካፒታልና ሙያዊ የሆነ እውቀት የማይጠይቁ ሥራዎች ላይ ሰዎች በቀላሉ የንግድ ፈቃድ አውጥተው የራሳቸውን የንግድ ሥራ የሚመሰርቱበት አደረጃጀት ነው፡፡ በመሆኑም ብዙ ሰዌች የሚመርጡትና የተጠቃሚዎች ቁጥር ከሌሎች የአደረጃጀት አይነቶች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ነው፡፡
እንደዚህ አይነት የንግድ ድርጅት ለመመስረት እና የንግድ ምዝገባ ለማድረግ በኢትዮጵያ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 መሰረት፡-
- የአመልካቹ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ጉርድ ፎቶግራፍ፣
- የአመልካቹ የከተማው ወይም የአካባቢ የመታወቂያ ካርድ ፎቶ ኮፒ፣
- ዕድሜው 18 ዓመት የሞላው መሆን እና
- ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ቤት አድራሻ ያለው መሆን ብቻ የሚጠይቅ ነው፡፡
ሀ/ የግለሰብ ንግድ ጠቀሜታው
በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱት ጥቅሞች ይኖሩታል፡፡
- በቀላሉ የሚመሰረት መሆኑ፡- የዚህ አይነት የንግድ ድርጅት ለመመስረት ከሌሎች ሰዎች ጋር መሻረክ፣ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ወዘተ. የማይጠይቅና ሙሉ በሙሉ በግለሰቡ ውሳኔ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ሂደቱን ቀላል የያደርገዋል፡፡ አንድ ግለሰብ በፈለገው ሙያ፣ በፈለገው ጊዜና ቦታ ንግዱን የመመስረት ሙሉ ነፃነት አለው፡፡
- በአነስተኛ ካፒታል ይመሰረታል፡- የዚህ አይነት የንግድ ድርጅት ለመመስረት የሚያስፈልገውን የካፒታል መጠን የሚወስን ህግ ባይኖርም ግለሰቡ የመረጠውን የንግድ ሥራ ማስኬድ አሰከቻለ ድረት አነስተኛ በሆነ ካፒታል ሊመሰረት ይችላል፡፡
- የንግድ ሥራው ብቸኛ ተጠቃሚ መሆኑ፡- የንግድ ሥራው የሚመራውና የሚተዳደረው በአንድ ግለሰብ እንደመሆኑ በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ የሚገኘውን ጥቅምም እንዲሁ ብቸኛ ተጠቃሚ ይሄው ግለሰብ ይሆናል ማለት ነው፡፡
- ድርጅቱን የመምራት ነፃነት፡- የንግድ ድርጅቱን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ማለትም ድርጅቱን የመምራት፣ የማስፋፋት ካልፈለገም ደግሞ የማፍረስ ወይም የመዝጋት፣ ሰራተኛ የመቅጠር ወይም የማሰናበት ወዘተ. ውሳኔዎችን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ባለቤቱ ብቻውን የመወሰን ሙሉ ነፃነት አለው፡፡
- የንግድ ሚስጢር ከመጠበቅ አኳያ፡- አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው የሚመራው በአንድ ግለሰብ እንደመሆኑ ለንግድ ስራው ጠቃሚ ናቸው የሚባሉና የሚስጢር መያዝ ያለባቸው ጉዳዮች በራሱ በባለቤቱ ብቻ የተያዙ በመሆናቸው ከራሱ ፈቃድ ውጭ በሆነ መንገድ ሊባክኑ አይችሉም፡፡
- ግብር ከመክፈል አኳያ፡- በአንድ ግለሰብ የሚመራ የንግድ ድርጅት ግብር የሚከፍለው አንድ ጊዜ ብቻ በመሆኑ በግብር አከፋፈል ረገድ ተጠቃሚ ነው፡፡
ለ/ የግለሰብ ንግድ ጉዳቱ
በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች ጥቅም እንዳላቸው ሁሉ ጉዳትም አላቸው፡፡ ከጉዳቶቹ መካከል ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
- ኃላፊነቱ ያልተወሰነ መሆኑ፡- በአንድ ግለሰብ የሚመሰረት የንግድ ድርጅት ኃላፊነቱ ያልተወሰነ በመሆኑ የእዳ ተጠያቂነቱ ከድርጅቱ ያልተወሰነ በመሆኑ የእዳ ተጠያቂነቱ ከድርጅቱ ሃብት አልፎ የግል ንብረቱንም ጭምር የሚነካ ነው፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ ድርጅቱ እዳ ቢኖርበትና እዳውን ለመክፈልም ሆነ አትራፊ ሆኖ ለመቀጠል የማይችልበት ደረጃ ላይ ቢደርስ እዳውን ለመክፈል ድርጅቱ ብቻውን በቂ ካልሆነ ከድርጅቱ ውጭ ያሉና በግል ያፈራቸው ንብረቶች ተሽጠው እዳው እንዲከፈል ህግ ያስገድደዋል፡፡
- አነስተኛ የፋይናንስ አቅም ያላቸው መሆኑ፡- በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች የፋይናንስ ምንጭ ራሱ መስራቹ ብቻ በመሆኑ ድርጅቱን ለማስፋፋት የሚኖረው የገንዘብ አቅም ውስን ነው፡፡ አበዳሪ ድርጅቶችም ለዚህ አይነቱ የንግድ ድርጅት የሚሰጡት የብድር መጠን ከሚኖረው አደጋ /Risk/ ጋር በማነፃፀር ስለሆነ ብድር የማግኘት እድሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ብድር ቢያገኝም የሚያገኘው የብድር መጠን የሚያቀርበው መያዣ/ዋስትና ልክ ስለሚሆን አነስተኛ ይሆናል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች የማደግና የመስፋፋት እድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡
- ድርጅቱን የማስተዳደር ችሎታ ውስንነት፡- በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ የንግድ ሥራ መሪ፣ ፈፃሚና ተቆጣጣሪ፣ ችግሮች ሲያጋጥሙም ውሳኔ ሰጭ ወዘተ. አንድ የድርጅቱ ባለቤት ብቻ ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ ሁሉንም ለመስራት የሚያስችል በቂ የሆነ እውቀትም ሆነ ጊዜው ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለሆነም ድርጅቱን በማስተዳደርና ትርፋማ ሆኖ አንዲቀጥል በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ውስንነት ያለበት ነው፡፡
- ብዙ ሰራተኞች የማይመርጡት መሆኑ፡- ብዙ ጊዜ በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች ላይ ሰራተኞች ያላቸው የመቀጠር ፍላጎት ዝቅተኛ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያት የሚሆነው በሥራ ላይ ስጋት ስለሚያድርባቸው ነው፡፡ ይህም በድርጅቱ እድገት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተዕፅኖ ያሳድራል፡፡
- የድርጅቱ ቀጣይነት አስተማማኝ ያለመሆን፡- በአንድ ግለሰብ የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች በገበያ ውስጥ የመቆየት እድላቸው በአንድ ግለሰብ ውሳኔ እና አቅም ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ስለሆነም በኪሳራ፣ ባባለቤቱ ህመም ወይንም ሞት ምክንያት በቀላሉ ድርጅቱ ሊዘጋ ወይም ሊፈርስ ይችላል፡፡
- የንግድ ማህበራት አይነቶች
የንግድ ማህበራት ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን አዋጥተው በጋራ ለመስራት ተስማምተው የሚመሰርቱት የንግድ ድርጅት አይነት ነው፡፡ በንግድ ህጉ አንቀጽ 212 መሠረት በእኛ ሀገር ስድስት አይነት የንግድ ማህበራት አሉ፡፡ እነሱም፡-
- ተራ የሽርክና ማህበር /Ordinary Partnership/
- የአሽሙር ማህበር /Joint Ventur/
- የህብረት ሽርክና ማህበር /General Partnership/
- ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር /Limited Partnership/
- የአክሲዮን ማህበር /Share Company/ እና
- ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር /Private Limited Company/ ናቸው፡፡
እነዚህን የንግድ ማህበራት በአንድ ግለሰብ ከሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች የሚለዩት ከፈተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቁና ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች የሚተዳደር መሆኑ ሲሆን ትላልቅና ዘርፈ ብዙ ተግባራት ያላቸውን የንግድ ድርጅቶች ለመመስረት ጠቀሜታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የንግድ ማህበራት እንደ ግለሰብ ነጋዴ ሁሉ ጠቀሜታና ጉዳት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ስለ እነዚህ ማህበራት በጥልቀት እንመለከታለን፡፡
ሀ. ተራ የሽርክና ማህበር
ተራ የሽርክና ማህበር የሚባለው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በጥሬ ገንዘብ፣ በአይነት ወይም በሌላ መንገድ መዋጮ አድርገው በጋራ የሚመሰርቱት የንግድ ድርጅት ነው፡፡
እንደ ሳራ ሰለሞን (2001 ዓ.ም) አገላለጽ ደግሞ ተራ የሽርክና ማህበር የሚባለው አንድ ንብረት የብዙ ሰዎች ሆኖ ያልተከፋፈለ ንብረት ወይም ንብረቶች ለማስተዳደር የሽርክና ማህበር ሲያቋቁሙ ነው፡፡
የዚህ አይነቱ የሽርክና ማህበር በንግድ ህጉ አንቀጽ 213 ላይ “ከተራ ሽርክና በቀር ሌላው የንግድ ማህበር… ዐይነተኛ የንግድ ሥራ ድርጅት ይሆናል” የሚልና አንቀጽ 227 ደግሞ “ተራ የሽርክና ማህበር ተብሎ የሚጠራው በዚህ ህግ (የንግድ ህጉ ማለት ነው) በሌላ አንቀጽ የተወሰኑት የሌሎች የንግድ ማህበሮች ልዩ ጠባዮች የሌሉት እንደሆነ ነው፡፡” የሚሉ አንቀፆች በመኖራቸው ተራ የሽርክና ማህበር የንግድ ማህበር ለመሆን አይችልም ማለት ነው፡፡
ለ. የአሽሙር ማህበር
የአሽሙር ማህበር ሁለትና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች የሚቋቋም ሲሆን ከሌሎች ለየት የሚያደርገው በጽሁፍ መረጋገጥና በሌሎች የንግድ ማህበሮች የተደነገጉ የማስመዝገብ ሰርዓቶች የማይፈፀሙበት፣ በህግ መሰረት ህጋዊ እውቅና የሌለውና በሶስተኛ ወገኖች ዘንድ የማይታወቅ መሆኑ ነው፡፡
ሐ. የህብረት ሽርክና ማህበር
የህብረት ሽርክና ማህበር በንግድ ህጉ አንቀጽ 280 መሰረት የህበርተኞች እያንዳንዳቸው ባንድነትና ሳይከፋፈል እርስ በርሳቸውና ለማህበሩ ግዴታዎች አላፊዎች የሚሆኑበት ማህበር ነው፡፡ ይህም ማለት ማህበሩ ለሚያጋጥመው አደጋ ወይም እዳ ሁሉ እያንዳንዱ አባል በግሉ፣ ወይም ሁሉም በአንድነት ወይም ከሁሉም የተወሰኑት ብቻ በተናጥል ለእዳው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
የህብረት ሽርክና ማህበር የተቋቋመው ለንግድ ዓላማ ከሆነም ማህበርተኞቹ እንደነጋዴ ይቆጠራሉ፡፡ ይህ አይነቱ ማህበር ሲመሰረት በንግድ መዝገብ የመመዝገብ ግዴታ ያለበት ሲሆን ማህበሩ መብት የማግኘትና የግዴታ ውል የመግባት እና አንዲሁም በማህበሩ ስም በፍርድ ቤቶች መክሰስ ወይም መከሰስ ይችላል፡፡
በንግድ ህጉ መሰረት የዚህ አይነቱ ማህበር የማህበር ስም የሚኖረው ሲሆን በማህበሩ ስም ላይ የማህበርተኞቹ ስም ሁሉ ይኖርበታለ፡፡ ይህ ካልሆነ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ስም ተጽፎ ከስማቸው ቀጥሎ “የህብረት ሽርክና ማህበር፡ ተብሎ መፃፍ አለበት፡፡ በስሙ ላይ ከማህበርተኞቹ ስም በቀር ሌላ ስም ሊገባበት አይችልም፡፡
የህብረት ሽርክና ማህበር ከሌሎች የሽርክና ማህበራት ሁሉ በብዛት የተለማመደና በርካታ የንግድ ሰዎች የሚመርጡት የሽርክና አይነት ነው፡፡
መ. ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር
ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር ከስሙ እንደምንረዳው ሁለት ዓይነት ማህበርተኞች ወይም አባላት አሉት፡፡ እነሱም ኃላፊነቱ ያልተወሰነ ማህበርተኛና ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበርተኛ ናቸው፡፡
በንግድ ህጉ አንቀጽ 296 መሰረት ኃላፊነታቸው ያልተወሰነ ማህበርተኞች የሚባሉት ለየራሳቸውና ያለወሰን አንድ ላይ ሆነው እርስ በእርሳቸው ለማህበሩ ግዴታዎች ሙሉ ኃላፊ የሆኑ ናቸው፡፡ ኃላፊነታቸው ያልተወሰነ ማህበርተኞች የሚባሉት ደግሞ በማህበሩ ውስጥ ባላቸው መዋጮ መጠን ብቻ ኃላፊ ወይም ተጠያቂ የሚሆኑ ሲሆን በማህበሩ የሥራ አስኪያጅ ሥራ ወይም አስተዳደራዊ ሥራ ውስጥ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፡፡ ነገር ግን ከማህበሩ ጋር ውል በማድረግ በማህበሩ ውስጥ ተቀጥረው እንዲሰሩ ሊፈቀድላቸው ይችላሉ፡፡ ይህም የአባልነት ልዩነት በማህበሩ መመስረቻ ጽሁፍ ላይ ተለይቶ መፃፍ እንዳለበት ህጉ ይደነግጋል፡፡
የዚህ ዓይነቱ ማህበር ስም የሚያስፈልገው ሲሆን ስሙም የሁሉንም ማህበርተኞች ስም በመያዝ ከስሙ ቀጥሎ “ሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር” የሚል ጽሁፍ ይጨመርበታል፡፡ ማህበሩ ሲመሰረት በንግድ መዝገብ የመመዝገብ ግዴታም ያለበት ነው፡፡
ሀ/ የሽርክና ማህበራት አጠቃላይ ባህሪ
- የኀብረት ሽርክና ሕጋዊ ሕልውና ያለው ከንግዱ ማኀበራት ወይም ድርጅቶች ሁሉ ቀላል ቅርጽ ያለው ነው፣
- የሽሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ብቻ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ግን ያለተገደበ መሆኑ፣
- የአንስተኛ ካፒታል መጠን በህግ ያልተደነገገ መሆኑ፣
- ማህበሩ የሚመሰረተው በአባላት መዋጮ መሆኑ፣
- አስተዳደራዊ ሥራዎችን በሚመለከት አባላቱ የሚወስኑ መሆኑ፣
- የሙያ ወይም የአገልግሎት መዋጮ የተፈቀደ መሆኑ፣
- የሥራ አስኪያጅ ብዛት አንድና ከአንድ በላይ ሊሆኑ እንደሚችሉ የተፈቀደ መሆኑ፣
- ከሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር በስተቀር ሥራ አስኪያጆች ከአባላቱ መካከል ወይም ከውጭ ሊሆኑ የሚችሉ መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ለ/ አክሲዮን ያልሆነ የንግድ ማህበር የንግድ ምዝገባን በሚመለከት
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ 686/2002 መሰረት ማንኛውም ማህበር ለንግድ ምዝገባ ሲቀርብ የሚከተሉትን በማሟላት ከማመልከቻ ቅጽ ጋር አያይዞ ማቅረብ አንዳለበት ይደነግጋል፡፡
- ማመልከቻው የተፈረመው በወኪል ከሆነ በሁሉም መስራች አባላት የተሰጠ የውክልና ሥልጣን ማረጋገጫ ሰነድ፣ የወኪሉ እና የሥራ አስኪያጁ የቀበሌ መታወቂያ ወይም የፀና ፓስፖርት ፎቶ ኮፒ እና ሥራ አስኪያጁ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሳው ጉርድ ፎቶግራፍ፣
- የማኀበሩ የመመስረቻ ጽሑፍ እና የመተዳደሪያ ደንብ ዋና ቅጂዎች፣
- የዋና መሥሪያ ቤቱ እና ያለም ከሆነ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹን ትክክለኛ አድራሻ፣ እና
- ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ቤት የራሱ ከሆነ የባለይዞታነት ካርታ፣ የኪራይ ከሆነ በሰነድ አረጋጋጭ የተረጋገጠ የኪራይ ውል እና ስለቤቱ አድራሻ ከቀበሌ መስተዳድር የሚሰጥ ማረጋገጫ፣
- ከአባላት በመዋጮ ከሚሰበሰበው የማህበሩ ካፒታል ውስጥ በጥሬ ገንዘብ የሚዋጣ ገቢ ለመደረጉ የባንክ ማረጋገጫ እና በአይነት ለሚዋጣው አግባብነት ያላቸው ሰነዶች መቅረብ አለባቸው፡፡
መዝጋቢው መሥሪያ ቤትም በምስረታ ላይ ላለው አክሲዮን ማህበር ያልሆነ የንግድ ማህበር የማህበሩ የገንዘብ መዋጮ ካፒታል በባንክ በዝግ ሂሣብ አንዲቀመጥ ለባንኩ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡ የማህበሩ የንግድ ምዝገባ ሲጠናቀቅ በዝግ ሂሣብ የተቀመጠው የማኀበሩ ካፒታል እንዲለቀቅ መዝጋቢው መስሪያ ቤት ለባንኩ ደብዳቤ ይጽፋል፡፡
ሐ/ የሽርክና ማህበር ጠቀሜታው
- በቀላሉ ለመመስረት የሚቻል መሆኑ፡- ከሌሎች ማህበራት ጋር ሲነፃፀር የሽርክና ማህበርን ለመመስረት የሚወስደው ጊዜና ገንዘብ አነስተኛ በመሆኑ በቀላሉ ህጋዊነትን በማግኘት ወደ ንግድ ሥራ ለመግባት ያስችላል፡፡
- በአነስተኛ ካፒታል መመስረት የሚቻል መሆኑ፡- ከግለሰብ ነጋዴ ቀጥሎ በአነስተኛ ካፒታል ልንመሰርተው የምንችለው የንግድ ማህበር የሽርክና ማህበር ነው፡፡
- የተሻለ ካፒታል ለማሰባሰብ የሚያስችል መሆኑ፡- የሽርክና ማህበራት ከግለሰብ ነጋዴ የሚለዩት ሁለትና ከሁለት በላይ ሆነው የሚመሰርቱት በመሆኑ እያንዳንዳቸው ሽሪኮች ከግለሰብ ነጋዴ የተሻለ በዓይነትና በገንዘብ በማዋጣት ካፒታላቸውን የተሻለ ማድረግ መቻላቸው ነው፡፡ የተሻለ ካፒታል ማዋጣት ከቻሉ ደግሞ የተሻለ የንግድ ሥራ ላይ የተሻለ አቅም ኢንቨስት ማድረግ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
- የሽርክና ማህበራት እንደ አክሲዮን ማህበራት ታክስ ወይም ግብር ሁለት ጊዜ ስለማይከፍሉ የታክስ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
- የሽርክና ማህበራት አባላት ድርጅታቸውን በራሳቸው ማስተዳደርና መምራት የሚችሉ መሆኑ፡፡
መ/ የሽርክና ማህበር ጉዳቱ
- ኃላፊነታቸው ያልተወሰነ መሆኑ፡- ከሁለት አይነት ኃላፊነት ያለበት የሽርክና ማህበር በስተቀር ሌሎች የሽርክና ማህበራት ሽሪኮች በማህበራቸው ላይ ለሚያጋጥማቸው እዳዎችና ኃላፊነቶች ሁሉ በማህበሩ ላይ ካላቸው ድርሻ በላይ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ነው፡፡
- በባህሪ አብረው ሊሄዱ የሚችሉና እርስ በእርስ የሚግባቡ ሽሪኮችን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ፡፡
- የድርጅቱ ቀጣይነት አስተማማኝ ያለመሆን፡- በሽርክና የሚመሰረቱ የንግድ ድርጅቶች በአባላት መውጣትና መግባት፣ እርስ በእርስ አለመግባባት አና በመሳሰሉት ምክንያቶች የድርጅቱ ህልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡
- በአባላት/ሽሪኮች መካከል አለመግባባትና ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
- የአክሲዮን ባለቤትነት ወይም ድርሻ በቀላሉ የማይተላለፍ መሆኑ፡፡
- የስነምግባር ችግር ያለበትን ሽሪክ ለማስወገድ አስቸጋሪ መሆኑ፡፡
ሠ. የአክሲዮን ማህበር
የአክሲዮን ማህበር ማለት በንግድ ህጉ አንቀጽ 304 መሰረት ዋናው ገንዘቡ ወይም ካፒታሉ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዮን የተከፋፈለና ለዕዳው ንብረቱ ብቻ ዋስ የሆነ ማህበር ነው፡፡ ይህም ማለት አባላት አስቀድሞ ተወስኖ የተከፋፈለ አክሲዮን በመግዛት የንግድ ማህበሩ ባለቤት የሚሆኑበት ሲሆን ማህበሩ በሚያጋጥመው ማናቸውም አይነት አዳ እያንዳንዱ አባል ኃላፊነት ሊወስድ የሚችለው በማህበሩ ላይ ባለው ካፒታል መጠን ብቻ ነው ማለት ነው፡፡
የአክሲዮን ማህበር አባላት ቢያንስ አምስት መሆን ያለባቸው ሲሆን የመነሻ ካፒታሉም በሃምሳ ሺህ ብር በታች መሆን እንደሌለበት እና የማህበሩ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር አስር ማነስ እንደሌለበት የንግድ ህጉ ላይ ተመልክቷል፡፡
መስራች አባላት ለሶስተኛ ወገኖች ለማህበሩ መቋቋም ለገቡባቸው ግዴታዎች በአንድነት ሳይከፋፈል ያለወሰን ሃላፊዎች ሲሆኑ የማኀበሩም መቋቋም የሰዎች ወይም የአባላት ማንነት ላይ ሳይሆን በኩባንያው ውስጥ የሚገባውን ገንዘብ ከግምት በማስገባት ነው፡፡
ሀ/ የአክሲዮን ማህበር የንግድ ምዝገባ
በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ 686/2002 መሰረት በመቋቋም ላይ ያለ የአክሲዮን ማኀበር ለንግድ ምዝገባ ሲቀርቡ መሥራቾቹ ወይም ወኪላቸው የማመልከቻ ቅጹን እንደአግባቡ ከሚከተሉት ሰነዶች ጋር በማያያዝ ማቅረብ አለባቸው፡-
- ማመልከቻው የተፈረመው በወኪል ከሆነ በሁሉም መስራች አባላት የተሰጠ የውክልና ማረጋገጫ ሰነድ ዋናና የተረጋገጠ ቅጂ፣ የወኪሉ እና የሥራ አስኪያጁ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት እና ሥራ አስኪያጁ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተነሣው ጉርድ ፎቶግራፍ፣
- ከተፈረሙ አክሲዮኖች ሽያጭ ቢያንስ አንድ አራተኛው ገንዘብ ተከፍሎ በዝግ ሂሳብ መቀመጡን የሚያሳይ የባንክ ማረጋገጫ፣
- አክሲዮን ለመግዛት ፈራሚዎች ስብሰባ ቃለ-ጉባኤ እና ከቃለ ጉባኤው ጋር የተያያዙ ሰነዶች ዋና ቅጂ፣
- የአክሲዮን ማኀበሩ የመመስረቻ ጽሑፍና የመተዳደሪያ ደንብ ዋና ቅጂዎች፣
- የዋና መሥሪያ ቤቱ እና ያለም ከሆነ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹን ትክክለኛ አድራሻ፣ እና
- ለንግድ ሥራ የሚጠቀምበት ቤት የራሱ ከሆነ የባለይዞታነት ካርታ፣ የኪራይ ከሆነ በሰነድ አረጋጋጭ የተረጋገጠ የኪራይ ውል እና ስለቤቱ አድራሻ ከቀበሌ መስተዳድር የሚሰጥ ማረጋገጫ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ሰነዶች ትክክለኛነት በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አግባብነት ባላቸው አካላት ተረጋግጠው መቅረብ አለባቸው፡፡ በታች መሆን እንደሌለበት እና የማህበሩ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር አስር ማነስ እንደሌለበት ተደንግጓል፡፡
የዚህ አይነቱ ማህበር የባንክ፣ የኢንቩራንስና ሌሎች ተመሳሳይነት ባህሪ ያላቸውን የንግድ መስኮች ለማቋቋም አይችልም፡፡ ለምዝገባ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በሚመለከት ከላይ በሽርክና ማህበር ስር የተመለከትናቸው ለዚህም ያገለግላሉ፡፡
በዚህ ህግ መሰረት የአክሲዮን ማህበር ሥራ አስኪያጅ ከአንድ በላይ በሆኑ ማናቸውም የንግድ ማህበሮች ውስጥ በተደራራቢነት ሥራ አስኪያጅ ሊሆን አይችልም፡፡
በዚህ መንገድ የሚመሰረት የአክሲዮን ማኀበር መስራቾች ምስረታውን ለመጀመር የመዝጋቢውን መስሪያ ቤት የጽሁፍ ፈቃድ በቅድሚያ ማግኘት አለባቸው፡፡
ለ/ የአክሲዮን ማኀበር ጠቀሜታ
- ኃላፊነቱ የተወሰነ መሆኑ፡- እንደ ግለሰብ ነጋዴና የሽርክና ማህበር ባለአክሲዮኖች በማህበሩ ላይ ካላቸው ድርሻ በላይ በእዳ ሊጠየቁ አይችሉም፡፡
- የአክሲዮን ባለቤቶችና በድርጅቱ ሥራ አመራር የተለያዩ መሆኑ፡- የአክሲዮን ማህበር የአክሲዮን ባለቤቶችና የድራጅቱ ሥራ አመራር የተለያየ በመሆኑ ድርጅቱ የተሻለ ብቃት ባላቸው ሙያተኞች ይመራል፡፡
- የአክሲዮን ድርሻን ወይም ባለቤትነትን በቀላሉ ከአንዱ ወደ አንዱ ማስተላለፍ ይቻላል
- የአክሲዮን ማህበራት ያልተገደበ የጊዜ ቆይታ ያላቸው መሆኑ፡- የአክሲዮን ማህበራት ህልውና እንደ ግለሰብ ነጋዴና የሽርክና ማህበር በጥቂት ግለሰቦች ላይ የተወሰነ ሳይሆን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ባለአክሲዮኖች ሊኖሩት ስለሚችሉና የአክሲዮን ዝውውር የተፈቀደ በመሆኑ የንግድ ድርጅቱ ህልውና በቀለሉ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይችልም፡፡
- በህግ የሰውነት መብት ያለው መሆኑ፡- በስሙ የመክሰስ የመከሰስ፣ ንብረት የመያዝ፣ የመበደርና የመሳሰሉትን መብቶች አንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡
- ካፒታሉን ለማሳደግ ቀላል መሆኑ፡- የአክሲዮን ማህበራት የአክሲዮን ባለቤትነት የሚሸጋገር በመሆኑ፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ በመሆኑና የቢዝነስ ዘመኑ ያልወሰነ በመሆኑ ካፒታሉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡ የአክሲዮን ማህበራት ካፒታላቸውን ለማሳደግ ከፈለጉ በቀላሉ አዳዲስ አክሲዮኖችን ለገበያ ማቅረብና አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብ ይችላሉ፡፡
ሐ/ የአክሲዮን ማኀበር ጉዳት
- የጽሁፍና የሪኮርድ ሥራዎች የሚበዙበት መሆኑ፡– የአክሲዮን ማህበራት የመመስረቻ ሰነድ /Article of incorporation or charter/ እና የመተዳደሪያ ደንብ የሚያስፈልገው ሲሆን እነዚህ ሰነዶች ከሌሎች ማህበራት በተለየ መልኩ በርካታ ጉዳዮችን ያካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አመታዊ ሪፖርት፣ የባለአክሲዮን መረጃዎች፣ የባለአክሲዮን ስብሰባዎች ቃለጉባኤ፣ የቦርድ አመራሮች ቃለጉባኤ ወዘተ.. ሰነዶችን ማደራጀትና መያዝን ይጠይቃል፡፡
- ሁለት ጊዜ ግብር የሚከፍሉ መሆናቸው፡– የአክሲዮን ማህበራት በራሳቸው ህጋዊ የሰውነት መብት ያላቸው በመሆኑ ግብር የመክፈል ግዴታ ሲኖርባቸው ካገኙት ትርፍ ባለድርሻ የሆኑ ባአክሲዮኖችም ካገኙት ገቢ ላይ ግብር የሚከፍሉ በመሆናቸው ግብር የሚታሰበው ሁለት ጊዜ ይሆናል፡፡
- የአክሲዮን ማህበራትን ለማደራጀት በርካታ ሂደቶችን ማለፍ የሚጠበቅብን በመሆኑ ብዙ ጊዜንና ወጪን የሚጠይቁ መሆናቸው፡፡
- የባለ አክሲዮኖች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በእነሱ መካከል አለመግባባትና ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡
1.ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር
በንግድ ህጉ አንቀጽ 510 መሰረት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማለት ማናቸውም ማህበርተኛ ካስገባው መዋጮ በላይ አላፊ የማይሆንበት ማህበር ማለት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ማህበር የአባላት ቁጥር ከሁለት ያላነሰና ከሃምሳ ያልበለጠ እንደሆነ በንግድ ህጉ በግልጽ ተቀመጧል፡፡ የመነሻ ካፒታሉም ከአስራ አምስት ሺህ ብር
ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚከተሉት ጠቀሜታዎችና ጉዳቶች ይኖሩታል፡፡
ሀ/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጥቅም
- ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚመራው እንደ አክሲዮን ማህበር ሁሉ በቦርድ ሳይሆን በራሳቸው በባለቤቶቹ መሆኑ፡፡ ይህም ከሽርክና ማህበር ጋር ተመሳሳይነት አንዲኖረው ያደርገዋል፡፡
- እንደ አክሲዮን ማህበር ሁሉ ለመመስረት ብዙ ሂደቶችን ማለፍ የማይጠይቅ መሆኑ፣
- ኃላፊነተ የተወሰነ መሆኑ፡- እንደ አክሲዮን ማህበራት ሁሉ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለአክሲዮኖች በማህበሩ ላይ ካላቸው ድርሻ በላይ በእዳ ሊጠየቁ አይችሉም፡፡
- ያልተገደበ የጊዜ ቆይታ ያላቸው መሆኑ፡- ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተወሰኑ አባላት የግል ሁኔታ ህልውና በቀላሉ አደጋ ላይ ሊወድቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ በገበያው ውስጥ ረጅም ጊዜ የመቆየት እድል አለው፡፡
- ካፒታሉን ለማሳደግ ቀላል መሆኑ፡- ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ኃላፊነቱ የተወሰነ በመሆኑና ከፋይናንስ ተቋማት በቀላሉ ብድር ማግኘት የሚችል በመሆኑ ካፒታሉን ለማሳደግና ለማስፋፋት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡
ለ/ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጉዳት
- አክሲዮን ከማህበሩ አባላት ውጭ ለሆኑ ሰዎች የማይተላለፍ መሆኑ፡፡ የሚተላለፍ ከሆነም ሁሉም አባላት መስማማት ያለባቸው መሆኑ (ነገር ግን በውርስ ሊተላለፍ ይችላል)፣
- እንደ አክሲዮን ማህበር ሁሉ አክሲዮኖችን በገበያ ላይ አውጥቶ መሸጠ እና አዳዲስ ኢንቨስተሮችን መሳብ የማይችል መሆኑ፣
- ከፍተኛው የአባላት ቁጥር የተገደበ በመሆኑ እና አክሲዮን ለገበያ የማይሸጥ በመሆኑ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እድገት በእነዚህ አባላት ሀብት ብቻ የተወሰነ ነወ፡፡
- የኀብረት ሥራ ማህበራት /Cooperative Societies/
በአዋጅ 147/91 መሰረት የኀብረት ሥራ ማህበር ማለት ሰዎች በፈቃደኝነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት የሚያቋቁሙትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚያስተዳድሩት ማህበር ነው፡፡ የማህበር አባለት ቁጥር ዝቅተኛው አስር ሲሆን ከፍተኛው በህጉ ላይ የተገደበ አይደለም፡፡
የኀብረት ሥራ ማህበራት ከሌሎች የንግድ ድርጅቶችና ማህበራት የሚለየው ራሱን የቻለ የተለየ ህግ ያለውና ለትርፍ የተቋቋመ ያለመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የኀብረት ሥራ ማህበራት የሚቋቋሙት የሚከተሉትን ዓላማዎች መሰረት በማድረግ ነው፡፡
- አባላት በተናጠል ሊወጧቸው የማይችሏቸውን ችግሮች በጋራ መፍታት፣
- አባላት ያላቸውን ዕውቀት ሃብትና ጉልበት በማቀናጀት የተሻለ ውጤት ማግኘት፣
- በራስ መተማመንን ማጎልበት፣
- የኢኮኖሚ ችግር በተባበረ ጥረት መካላከል መቋቋምና ማስወገድ፣
- ለማምረት የሚያስፈልገውን ወጭ የአገልግሎት ዋጋን ለመቀነስ፣ አባላት የሚፈልጉትን ግብዓት ወይም አገልግሎት በአነስተኛ ዋጋ እንዲያገኙ፣ ምርታቸው ወይም አገልግሎታቸው የተሻለ የገበያ ዋጋ እንደያገኝ ማድረግ፣
- የቴክኒክ እውቀትን በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስፈልጉ ዘዴዎች እንዲስፋፉ ማድረግ፣
- የቁጠባና ብድር አገልግሎት አንዲዳብርና አንዲስፋፋ ማድረግ፣
- አባላቱ በግላቸው ቢሰሩ ኖሮ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጉዳትና ኪሳራ በጋራ በመካፈል የእያንዳንዱን ሰው ጉዳትና ኪሳራ መቀነስ፣
- አባላትን በማስተማርና በማስልጠን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህልን ማጎልበት ናቸው፡፡
የኀብረት ሥራ ማህበራት ከመሰረታዊ ማህበር ጀምሮ አስከ ፌደራልና አህጉራዊ ወዘተ. በየደረጃው ሊደራጁ ይችላሉ፡፡
በኀብረት ሥራ ማህበራት አዋጅ 147/91 መሰረት በኀብረት ሥራ ማህበራት ለመደራጀት አንድ ሰው የሚከተሉትን ማሟላት አለበት፡፡
- መሰረታዊ ማህበር ከሆነ ዕድሜው 14 ዓመት የሞላው፣
- የማህበሩን ዕጣ ለመግዛትና የመመዝገቢያ ክፍያ ለመክፈል የሚችል፣
- የማህበሩን ዓላማና መተዳደሪያ ደንብ የተቀበለና ግዴታዎቹን ለመፈፀም ፈቃደኛ የሆነ፣
- አዋጁን ለማስፈፀም የሚወጡ ደንቦችንና መመሪያዎች የሚወሰኑ ሁኔታዎችን የሚያሟላ እና፣
- ከመሰረታዊ ማህበር በላይ ከሆነ አግባብ ባለው ባለስልጣን የተመዘገበ ማህበር ይሆናል፡፡
በኀብረት ሥራ ማህበር ለመደራጀት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የመስራቾች ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ያላቸው መሆኑ፣
- የማህበሩ መተዳደሪያ ደንብ 3 ቅጂ፣
- የአባላት ስም፣ አድራሻና ፊርማ ማቅረት፣
- የማህበሩ አመራር አካላት ስም፣ አድራሻና ፊርማ፣
- የማህበር አባላት ሆነው የሚመዘገቡ ግለሰቦች አዋጁ በሚደነግገው መሰረት አባል ለመሆን ብቁ መሆናቸውን የሚያስረዱ ዝርዝር መግለጫዎች፣
- የማህበሩ ዕቅድ፣
- ከመሰረታዊ ማህበር በላይ ከሆነ የአባል ማህበራት ስም፣ አድራሻና ፊርማ፣
- የማህበሩ እቅድ፣
- የማህበሩ ጽ/ቤት አድራሻ ማቅረብ፣
- የመነሻ ካፒታሉን መጠንና ተሰብስቦ በባንክ ሂሣብ ገቢ መደረጉን የሚገልጽ ሰነድ ማቅረብ ናቸው፡፡
የኀብረት ሥራ ማህበራት ከሌሎች የንግድ ማህበራት የሚያመሳስላቸው አሰራሮች ያሉት ቢሆንም በዓላማቸው፣ በንግድ ሥራ አመራራቸውና በአደረጃጀታቸው ልዩነት አሏቸው፡፡ አንድነታቸውንና ልዩነታቸውን ቀጥሎ እንመልከት፡፡
ሀ/ አንድነት/ተመሳሳይነት
የኀብረት ሥራ ማህበራት እና የንግድ ድርጅቶች በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ እነዚህም፡-
- ሰራተኞችን ቀጥሮ ማሰራት፣
- የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥማቸው ከአበዳሪ ተቋማት መበደራቸው፣
- የየድርጅቶቻቸውን ዓላማና ዕቅዶች ለማሳካት፣ ድርጅታቸውን ለማስተዳደርና ለመቆጣጠር ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህንን ለማድረግም ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ ያወጣሉ፣
- ድርጅታቸውን በመምራት እንደ ማቀድ፣ ማደራጀት፣ ምርት አምርቶ መሸጥ፣ ምርትን ማስተዋወቅ ወዘተ. ተመሳሳይ የሆኑ የሥራ ሂደቶችን ይከተላሉ፣
ለ/ ልዩነቶች
የኀብረት ሥራ ማህበራት እና የንግድ ድርጅቶች በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ልዩነቶች አሏቸው፡፡ እነዚህም፡-
- የንግድ ድርጅቶች በንግድ ጽንሰ ሃሳብና በንግድ ህግ ላይ የተመሰረቱ ሲሆኑ የኀብረት ሥራ ማህበራት በአባላት የተጠናከረ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ የመረዳዳት ጽንሰ ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡
- የንግድ ድርጅቶች ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ዓላማ ሲኖራቸው ኀብረት ሥራ ማህበራት በተመጣጣኝ ወጪ በአባላት ብቃት ያለው አገልግሎት መስጠትና አባላትን በማስተማር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውን የማሳደግ ዓላማ ያላቸው ናቸው፡፡
- የንግድ ድርጅቶች አክሲዮን በገበያ ላይ የሚሸጥ ሲሆን የሚመሰረቱትም በባለሃብቶች ነው፡፡ የኀብረት ሥራ ማህበራት ግን ፈቃደኛ በሆኑና የአባልነት መመዘኛውን የሚያሟሉ ብቻ የሚመሰርቱት ሲሆን ዕጣ በገበያ ላይ አይሸጥም፡፡
- በንግድ ድርጅቶች ድምጽ የሚሰጠው በአክሲዮን ብዛት ሲሆን በኀብረት ሥራ ማህበራት ግን አንድ አባል አንድ ድምጽ ብቻ አለው፣ ድምጽ በውክልና አይሰጥም፣ የዕጣ መጠንም ለድምጽ አያገለግልም፡፡
- የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በኀብረት ሥራ ማህበራት ግን አባላት በአንድ በተወሰነ አካባቢ የሚገኙ መሆን አለባቸው፡፡
- የንግድ ድርጅቶች በሚቀጠሩ ሰራተኞች የንግድ ሥራው ሊመራ ይችላል፡፡ በኀብረት ሥራ ማህበራት ግን ማህበሩን የሚመሩት የሚቆጣጠሩትና የሚያስተዳድሩት አባላት እና ከአባላት በሚመረጡ ኮሚቴዎች አማካኝነት ነው፡፡
- በንግድ ድርጅቶች ትርፍ የሚከፋፈሉት በድርጅታቸው ባላቸው አክሲዮን ብዛት ሲሆን የፀበረት ሥራ ማህበራት ግን አባላት በማህበራቸው ባደረጉት ተሳትፎ መጠን ጭምር ነው፡፡ ባጠቃላይ እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው የንግድ ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየተሰራባቸው ያሉና በህግ የተፈቀዱ አደረጃጀቶች ሲሆኑ የትኛውም ዓይነት የንግድ ሥራ ህጋዊ ሊሆን የሚችለው ከእነዚህ የንግድ አደረጃጀት በአንዱ ከተመዘገበ ብቻ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በአንዳንድ ሰዎች የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞችን ከዚህ አይነቱ አደረጃጀት የተለዩ አድርጎ የመመልከት ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ ሆኖም የጥቃቅን ኢንተርኘራይዞችም ሆነ ሌሎች የንግድ ድርጅት ህጋዊ ሆነው የንግድ ሥራ የሚሰሩት ከላይ ከተዘረዘሩት አማራጭ የንግድ ድርጅት ዓይነቶች ፍላጎት ላይ ተመስርተው ምዝገባና ፈቃድ በማግኘት ነው፡፡
ልዩነት ያለው አሁን ባለው የመንግስት ዘርፉን የማሳደግ ፍላጎት መሰረት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞችን በሚያደራጁና በሚያስፋፉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አማካኝነት ወደ ንግድ ሥራ የሚገቡ ወጣቶችና ሴቶች የተለያዩ ድጋፎች ተዘጋጅተው የእነዚህ ድጋፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሰራ ባለው ሥራ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ የሚሰጠው ድጋፍ እነዚህን ብቻ የሚመለከት መሆን የለበትም፡፡ የራሳቸው ጥረት ያለምንም ድጋፍ ራሳቸውን ለማውጣት ጥረት የሚያደርጉ በጥቃቅንና አነስተኛ ትርጓሜ መሰረት ጥቃቅንና አነስተኛ ውስጥ የሚመደቡ በርካታ የንግድ ተቋማት በየአካባቢያችን ይገኛሉ፡፡
ቀደም ሲል እንደተገለጸው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዝ የሚባሉት በአጠቃላይ ስንመለከታቸው በሥራው ላይ ያሰማሩት የሰው ሃይል ከሰላሳ በታችና ጠቅላላ ሀብታቸው በአገልግሎት ዘርፍ ከብር አምስት መቶ ሺህ እና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ደግሞ በብር 1.5 ሚሊዮን ያልበለጠ የሆኑ የንግድ ድርጅቶችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡ ይህም ማለት የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞችን የሚያደራጀው የመንግስት መስሪያ ቤት ያላደራጃቸውን ድርጅቶች ሁሉ የሚያጠቃልል ሲሆን የመንግስት ፍላጎት እነዚህንም ተቋማት መደገፍና ከመካከላቸው በርካታ የኢንድስትሪ ባለቤት ሊሆኑ የሚችሉ ሥራ ፈጣሪዎችን ማፍራት ነው፡፡
የንግድ ፈቃድና ምዝገባ አሰጣጥን በሚመለከት በብዙ አካባቢዎች አዲስ አበባን ጨምሮ ሁለት አማራጮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የንግድ ሚኒስቴር ስር እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ባሉ የንግድ ወይም የንግድና ኢንድስትሪ ልማት ጽ/ቤቶች አማካኝነት ይህንን አገልግሎት ማግኘት የሚቻል ሲሆን በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን የሚያሟሉ ሥራ ፈላጊዎች ወይም ሥራ ፈጣሪዎች ደግሞ ተመሳሳይ አገልግሎት በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች ልማት ጽ/ቤት ሥር ባሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ውስጥ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ፡፡
የኀብረት ሥራ አደረጃጀትን በሚመለከት ይህ አደረጃጀት መደበኛ የንግድ ሥራን ለማካሄድ ሳይሆን ቀደም ሲል ለማስረዳት እንደተሞከረው የአባላትን ጥቅም ለማስከበር ሲባል የሚቋቋሙ በመሆናቸው መደበኛ የንግድ ሥራ ለመስራት በዚህ አደረጃጀት ፈቃድ ማውጣት አይቻልም፡፡ በኀብረት ሠራ ማህበር አደረጃጀት ፈቃድ ማውጣት የሚቻለው በከተሞች አካባቢ የቁጠባና ብድር የኀብረት ሥራ ማህበር፣ የሸማቾች የኀብረት ሥራ ማህበር፣ የቤቶች የኀብረት ሥራ ማህበር፣ በመሳሰሉት ሲሆን በገጠር አካባቢ ደግሞ የገበሬዎች የአገልግሎት የኀብረት ሥራ ማህበር፣ የአምራቾች የኀብረት ሥራ ማህበር የመሳሰሉትን የማህበር አይነቶች ብቻ ነው፡፡
ስለሆነም የንግድ ሥራዎን ለመጀመር ተገቢው የንግድ ድርጅት የትኛው ነው? የሚለውን በሚገባ በመረዳት መምረጥና በውሳኔ ላይ መድረስ፣ በመቀጠልም ውሳኔዎን ሊያሟሉ ይችላሉና ወደ እነዚህ ተቋማት ሄዶ አገልግሎት ማግኘትና ህጋዊ መሆን ይችላሉ፡፡