የነካው ሁሉ ወርቅ

የነካው ሁሉ ወርቅ

የአይጥ መርዝ ነበር …
እሱ ግን አልጠረጠረም፡፡ ጨርሶ አልገባውም… ሊገባው ባልቻለ ሁኔታ እንቅልፍ ባይኑ አልዞር እያለ ያስቸግረው ጀመር፡፡ እስከ ለሊቱ አስር ሰዓት ድረስ እንቅልፍ በመናፈቅ እየተሰቃየ ቀን መቁጠር ጀመረ… ልክ አንደኛ ወሩ ላይ እንቅልፍ ከማጣቱ በባሰ ሁኔታ የመመገብ ስሜቱ ድራሹ ጠፋ፡፡
ወደ ሞት አፋፍ እየሄደ መሆኑን ጨርሶ እንኳን አላሰበውም… ሊያስበውም የሚያስችለው አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ የእንቅልፍ መድሀኒት መቃሙ፣ የመመገብ ፍላጎትን የሚያስጨምር መድሀኒት መውሰዱ ፈፅሞ መፍትሄ ሊሆግ አልቻለም፡፡ ያልገባው አንድ ችግር ቢኖርም እንኳን ቀለል ያለ ህክምና ወስዶ ስቃዩን ከማጣጣም በበለጠ አንዳች አላደረገም፡፡
የሰውየው እንቅልፍ ማጣትና የመመገብ ችግር የታወቃቸው ባለቤቱና ወንድሙ ጭንቀታቸው ቢያይል ጊዜ መፍትሄ ማፈላለጉን ተያያዙት፡፡ እሱ ግን እየባሰበት… የማያውቀው ስሜት ሰውነቱን ውርር እያደረገ በጭንቀት ማጥ ውስጥ ያዳክረው ጀመር፡፡
ሰውነቱን ለመውረር አልፎ ተርፎ ውስጥ እግሩ አሳት እንደተለቀቀበት ያህል ሰጉድ እያቃጠለው በስቃይ ላይ ስቃይ ይደራረብበት ሆነ፡፡
መለስ ቀለስ ያለባቸው ጥቃቅን ህክምና ማዕከሎች የሞት ጉዞው ጨርሶ ሊያውቁለት አልቻሉም፡፡
ሰውየው ባልታወቀ ምክንያት ወደ ሞት አፋፍ መንደርደሩን ቀጥሏል…
ፀጉሩን በእጁ ሲነካው ሸልቅቅ እያለ ከራሱ ላይ በመነሳት ባዶውን ቀረ፡፡ ፀጉር የሚባል በራሱ ላይ ማግኘት የማይታሰብ ሆነ፡፡ ወደያው ደሞ በሚገርም ሁኔታ ጨርሶ በቅሎ የማያውቅ ቀይ ፀጉር ማውጣት ጀመረ፡፡ ባለቤቱና ወንድሙ ነገሩ ቢያሳስባቸው እንዳው ለውጡ የመመገብ ፍላጎቱን ይፈጥርለት ይሆናል ብለው ወደ አንድ ሆቴል ራት ሊጋብዙት ይዘውት ወጡ፡፡ ሆቴሉ ውስጥ ወንበር ላይ እንደተቀመጠ አዙሮት ከወንበሩ ላይ ወደቀ፡፡
ቀጥታ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ይዘውት ሄዳ፡፡ ሀኪሞቹ ታማሚው ጥሬ ስጋ እንደሚወድ በነገራቸው መሰረት የኮሶ መታየት ችግር ነው ብለው ደመደሙ፡፡ ለጉብኝት የመጡት እነ ፕሮፌሰር ነቢያት ግን አዲስ ያበቀለውን ቀይ ፀጉር ተመለከቱና የአይጥ መግደያ መርዝ መብላቱን አወቁ፡፡
እዚህ ታክሞ መዳን የማይታሰብ ሆነ፡፡ ስቃዩ ሲብስ በሀኪም ትእዛዝ ሰገራና ሽንት ሲመጣበት ያለ እንግልት እንዲጠቀም አልጋው ተቀደደለት፡፡ ለሁለት ወራት ያህል ይህ ስቃዩ ከታማሚው አልፎ ለባለቤቱና አህቱ ተርፎ አንገሽጋሽ ሆነባቸው፡፡
ሁኔታውን የሰሙት የኦሪስ ኩባንያ ባለቤት ወደ ስዊዘርላንድ ለህክምና ይምጣ ብለው ሁኔታውን አምቻቹ፡፡ መንቀሳቀስ ፈፅሞ የማይታሰብ ነገር ነበርና በስትሬቸር ሆኖ አውሮፕላን ውስጥ ገባ፡፡ ሮም ድረስ ሁኔታውን የሚከታተል ዶክተር በኦሪስ ኩባንያ ባለቤት በኩል ተልኮ ስለነበር ከሮም ዙሪክ፣ ከዙሪክ ባዝል ከታማሚው ጋር ሆኖ ብሩዶይሬልዝ ሆስፒታል ድረስ እንክብካቤ እየተደረገለት ገባ፡፡ ወደያውም ምርምራ ተደርጎለት ያለበትን ችግር ካሳወቀ በኋላ ከጀርመን ሀገር የኮሶ ኪኒን ተገዝቶ መጣ፡፡ ክኒኑ ለውሻ የሚሰጥ መሆኑን ዶክተሮዡ ተናገሩ፡፡ ያም ሆኖ ግን ያንን ክኒን ወስዶ ካሻረው በኋላ ኮሶው ባሻረው ወቅት የቀላው ፀጉሩ ነጭ ሆነ፡፡
ከስምንት ቀናት ቆይታ በኋላ በ17 ዶክተሮች ልዩ ምርመራ ተደረገለትና የአይጥ መግደያ መርዝ መብላቱ ተረጋግጦ መርዙን (ታሊየሙን) ከደሙ ውስጥ አወጡት፡፡ እንዴት መርዙን እንደበላው ግን እንቆቅልሽ ነው የሆነበት፡፡
ሶስት ወራት ተገቢውን ህክምና ካደረጉለት በኋላ በአንድ ድምፅ መትረፋን ገልፁና ተከዝ ብለው ለመስማት አንኳን የሚዘገንን መርዶ አረድት… “ትድናለህ… ግን ህይወትህን በዊልቼር ላይ ሆነህ ልትገፋ ትችላለህ”
ተስፋ የሚያስቆርጥ አስደንጋጭ ዱብ እዳ ነበር፡፡ የውብሸት ወርቃለማሁ ፊት ከሞት ያልተናነሰ ሀዘን ሰፈነበት፡፡ ያኔ ውብሸት ትናንቶቹን በትዝታ ማየት ጀመረ፡፡ ህይወቱ ከዊልቼር እንደተጣበቀች ትቀር ይሆን? ወይም በፅናት፣ በብርታትና በጥንካሬ መልሳ ድልን ትቀዳጅ ይሆን?
  
ከሶስት ቀናት ነፍስ ግቢ፣ ነፍስ ውጪ አስጨናቂ ምጥ በኋላ በሀገሩ ባህል መሰረት ብረት መዳመጫ ላይ አንድ፣ ይህችን ዓለም ተቀላቅያለሁ የለበት የለቅሶ ድምፅ ግርማ ሞገስ ያለው ህፃን ተወለደ፡፡ መስከረም 5 ቀን 1936 ዓ.ም ዕሁድ ከጠዋቱ 1፡30 ላይ ነበር በመንዝና ይፋት አውራጃ ማፋድ ወረዳ አንቃውሀ በምትባል ቀበሌ የተወለደው፡፡ በባህሉ መሰረት ከእንኳን ደህና መጣህ እልልታው ተከትሎ ለአዲሱ መጥ እንግዳ ልዩ ፍቅር ያደረባቸው አያቱና እናቱ ዋርካ ተከሉለት፡፡
ያካባቢው ነዋሪ ከሚቋደሰው እጣ ፈንታ ውጪ ያልተተነበየለት ያ ህፃን እንደዋርካ ገዝፎ፣ የኢትዮጵያን የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ የሚለውጥ ታላቅ የማስታወቂያ አምባሳደር ይሆናል ብሎ የገመተ ቀርቶ ያቃዠው እንኳን አልነበረም፡፡ ምናልባት ግን አያቱ እማሆይ ዘነበችና እናቱ ወ/ሮ ተናኘወርቅ ለራሳቸውም ሳይታወቃቸው የልጁን የግዙፍነት እጣ ፈንታ በገቢር መተንበያቸው ይሆናል ዋርካ መትከላቸው፡፡
ነፍስ እያወቀ ሲሄድ ራሱን ከአካባቢው ጋር ከማጣጣምም አልፎ ጎደሎ ነገሮችን እየፈለገ በአእምሮው በመሙላት ማሻሻልና ውጤቱን እያየ መፈንጠዝ የእርካታው ጣራ ሆነ፡፡ ዘጠነኛ አመቱን እንደሞላ በትውልድ አገሩ የገበያ ቦታዎች ያሉትን ሁኔታዎች አየና የሆነ ነገር ማድረግ፣ ማድረግ አሰኘው፡፡ እስካሁንም ምን እንደገፋፋው ለይቶ የማያውቀው ሁኔታ ሰንጋ ይዘው፣ ጥራጥሬ ዘርግተው ፀሀይ ሲጋቱ የሚውሉት ነጋዴዎች ቶሎ ሸጦ አለመግባት ምክንያት ገባውና ጠጋ እያለ “ቶሎ፣ ሸጣችሁ እንድትገቡ እኔ እየለፈፍኩ ገዥ ልሳብሳችሁ… ላሻሸጥላችሁ… እናንተ ደሞ ማርትሬዛ ትሰጡኛላችሁ” ሲላቸው እንደ ሀገሬው ልማድ “ከሆነልሽ ምን ችግሮን!” እያሉት …. አዋጅ፣ አዋጅ በሚለው ምናልባትም በሚያውቀው ብቸኛ ዜማ ሞቅ አድርጎ ያስተዋውቅ ጀመር፡፡
ደርሶ ነገሩ እንግዳ የሆነባቸው ሁሉ በማፌዝም፣ በመገረምም-ሰሞንኛ ትኩረት ሰጡትና እያደረ እየለመዱት፣ አልፎ ተርፎም በለዛው በመሳብ ይመስላል እሱ ወዳለበት ጠጋ እያሉ-የሚያስተዋውቃቸውን ነገሮች እየሸማመቱ ማርትሬዛውን ያስታቅፉት ጀመር፡፡
ነገሩ እየጣመው ሲሄድ እናቱ ፍየል ስታርድ ቆዳውን እንድትሰጠው እግሯ ላይ እየወደቀ ይለምናት ጀመር፡፡ ፈቃዷን ሲያገኝም ትውልድ መንደሩ በሚደረገው ሁኔታ ቆዳውን በደንብ እነዲወጥሩለትና እንዲያደርቁለት ያስደርግና ንፁህ ሲሆን ፈትጎ አጤፋሪስ በሚባል ቅጠል ከጥላሸት ጋር ለውሶ ጥሩ ቀለም እንዲሆን ሶስት ቀናት ያሳድረዋል፡፡ ከሶስት ቀናት በኋላም በዚያ የፍየል ቆዳ ላይ “ይህን ያህል ሰንጋ ከራሳ መጥቷል… ይህን ያህል ምስር ከደጋ መጥታል…” እያለ በመፃፍ ለዕይታ ምቹ በሆነ የገበያው ቦታ ያንጠለጥል ነበር፡፡
ይሄ ሁሉ ሆኖ ግን ያ ትንሽ ልጅ ምኞቹ ጠቅላላ ገዥ፣ ካልሆነም አውራጃ ገዥ፣ አለበለዚያም ሲባል የሰማውን ፓይለት ወይም አፈቀላጤ (የፕሮፖጋንዳ ሰው) መሆን ነበር፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ገዠ ወይም አውራጃ ገዥ ሆኖ በዙፋን ወንበር ላይ ባይቀመጥም የማስታወቂያውን ዙፋን ተንሰራፍቶ እንዳይቀመጥበት ግን የከለከለው አንዳችም እንኳን አልነበረም፡፡
ያ አንድ ፍሬ ልጅ የማይገባበትን የማይሞከረው አልነበረም፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁሌም ግንባር ቀደምና መሪ መሆኑ ነው፡፡ ዲያቆን ሆኖ አንደኛ ደረጃ ዲያቆን፣ ሲቀኝም ቅኔው የሰጠ፣ ሲያስተዋውቅም፣ ሲያስተባብርም፣ ሲበጠብጥም ቁጥር አንድ ነበር ውብሸት ወርቃለማሁ፡፡
እድል ቀኟን ሰጥታው አስተዳደጉ ከከብት ጋር የተቆራኘ አልነበረም፡፡ ደብተራ ሸዋ የሚባሉ አስተማሪ ተቀጥረውለት ነበር የሚማረው፡፡ ትምህርቱን ተከታትሎ ጎበዝ ዲያቆን ከሆነ በኋላ ለእውቀት ከነበረው የጋለ ፍላጎት በመነሳት በራሱ ፈቃድ የቅኔ ትምህርት ቤት ገባ፡፡
ስለዚያ ትንሽ ልጅ ሲወራ ፓንት የሚባል ነገር ባያውቅም (በኋላም የለመደው በመከራ ነው) ሶስት ልብስ፣ ጥልፍልፍ የአዳል ጫማ የነበረው የልጅ ሀብታም እንደነበር ሳይነገር ጨርሶ መታለፍ የለበትም፡፡ አዳኝ የመሆን ፍላጎት ስለነበረውም ነጭ በነጩን ከነአዳል ጫማው ግጥም አድርጎ ሲለብስ መትረየስ ሽጉጡን የሚስጥር ኪሱ ሻጥ አድርጎ ለራሱ ላቅ ያለ ግርማ ሞገስ አለብሶ መጎማለል ደስታው ነበር፡፡
ልጁ በህፃናቶች ላይ ሰልጠን ያለ አለቃ ነበር፡፡ በተለምዶ ቅዳሜ በሚውለው የማፋድ አምሀ እየሱስ ገበያ አካባቢ ገበያተኞች ችግር እንዳይፈጠርባቸው በማሰብ ህፃናትን እያስተባበረ በየመንገዱ ላይ ያለውን እሾህ፣ ጠጠርና እንቅፋት የሚሆን ድንጋይ ያስለቅም ነበር እዚህ ላይ እሳት የላሰ ተናጋሪ ሆኖ በማሳመን ብቻ ሳይሆን እልቅናውን ለማሳየት በአርጩሜ ጭምር እየገረፈ ነበር የሚያስተባብረው፡፡ ለነገሩ ልጅነቱን የሚያውቁ ሁሉ ወጣ እሳት የሚል ቅፅል ስሙንና ረፍት የለሽ ደብረ በጥብጥነቱን አሁን የሆነ ያህል ነው ልቅም አድርገው የሚያስታውሱት፡፡
ድርሳነ ሚካኤል ያነበበ እንደሁ ሲያንበለብለው ለጉድ ነበር፡፡ ያቺ አጭር ቁመቱ እንደልብ ሰው ፊት እንዳታይ መሰናክል ብትሆንበትም ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተቀጥሎለት ወይ ደሞ ቁመት ባላቸው ሰዎች እንኮኮ ተብሎ ትልቅነት እየተሰማው ይሄን ድርሳነ ሚካኤል በደንብ ይወጣው፣ ቅኔውን ያዥጎደጉደው፣ ልፈፋውን ያንበለብለው፣ ማስታወቂያ ስራውን ያጣድፈሉ… ሁለገብነቱን ያጧጡፈው ነበርና ወጣ እሳት ተባለ፡፡
መቼም ሳይደግስ አይጣላ እንዲሉ አቶ ታሪኩ የሚባሉ ረጂም ሰው ምናልባት ከሁለት ሜትር በላይ ይሆናሉ እንኮኮ እያሉት ቆርቆሮ እያንኳኳ “አዋጅ አዋጅ! ያልሰማህ ስማ … የሰማህ አሰማ! ይሄ ሰንጋ ጥሩ ነው… በሽታ የሌለበት ከብት ነው… ይህችን መሲና የገዛህ እንደሆነ ጮማ ነች… ይህችን ጥገት ላም የገዛህ እንደሆን ለልጆቷ ወተት ትሰጣለች..” እያለ በማስተዋወቅ ማርትሬዛ ብር መቀበል እንዲችል አተስዋፅኦ ባያደርጉለት (እርግጥ ለሳቸውም ይከፍላል) እጣ ፈንታው ምን ይሆን እንደነበር መገመት በከበደ፡፡
ይሄን በየአበባባዩ እየጮሁ ማርትሬዛ ብር የመቀበሉን ስራ ያልወደዱለት አያቱ “እንደላሊበላ እየጮህክ የባትህን ስም ልታስጠፋ ነው ወይ?” በሚል ማጀቢያ አስረው ልቡ እስኪጠፋ በመግረፍ ረገብ አደረጉት፡፡ ያዳቆነ ሰይጣን… እንዲሉ ድጋሚ ግርፏም እንዳትመጣበት ወደ ደብረሲናና አስፋቾ እየወጣና እየወረዳ ቆርቆሮ እያንኳኳ “የአቶ ክብረት መኪና አይገለበጥም፣ ገደል ተምዘግዝጎ ነው የሚያሳልፈው፣ እንቅፋት እንኳ ቢያጋጥም ዘሎ ይሄዳል እንጂ አይገለበጥምና በእሳቸው መኪና ሂዱ” እያለ ሰውን በሳቅ እየፈጀ የድብቅ ማስተዋወቅ ስራውን ቀጠለ፡፡ የሆነው ሁሉ ይሁንና የዚያን ጊዜው ስራ ገና ዘጠኝ አመቱን ላልዘለለ ልጅ የእድሜ ልክ እንጀራው ይሆናል ብሎ መተንበዩ ቀርቶ ማሰቡ ራሱ የማይታሰብ ነበር፡፡
ልጁ በጥባጭነትና ተንኮል ስጦታው ይመስሉ መገለጫዎቹ ነበሩ፡፡ ረፍት የለሽ ስለነበር ብዙም እንቅልፍ የመተኛት ልምድ የለውም፡፡ ያኔ እንቅልፍ ሲያጣ ተንኮሏ መጥታ በአዕምሮው ትገጠገጥ የለ? ሌሊት ይነሳና ነብርና ጅብ መከላከያ ቆመጥ ዱላውን ይዞ በመሄድ የቤተክርስቲያኑን ደውል በመደወል ህዝቡን ሁሉ ያለሰዐቱ ማህሌት እያስገባ ማበሳጨቱን ተካነበት፡፡ አልፎ ተርፎም በቅዳሴ ሰዐት የቆንጃጅት ልጃገረዶችን ጭን እየቆነጠጠ በማስጮህ ቁጥር አንድ ሆነ፡፡
ይሄ ተንኮሉ ደግሞ የማይወደውን ሰው ለማበሳጨት ከጓደኞቹ ጋር በመሆን “እገሌ ሞቷልና ቀብር ድረሱ!” እያለ በመስለፈፍ ህዝቡን ለቅሶ እስከማስወጣት፣ ሰው እያጣላ እስከማደበደብ… እንዲያ ሲልም እራሱ ተደባዳቢ ከመሆን አልፎ ለቴአትር ስራ ወደ አንድ ጠቅላይ ግዛት በሄዱበት ወቅት “ይሄ ጭንጋፍ!” ብሎ የሰደበውን ልጅ ተኩሶ የልጁን ጆሮ እስከ መበጠስ ደርሶ መታሰሩን ሳይቀር የቅርብ ጓደኞቹ አምባጓሮኛነቱን ሲገልፁ አፅንኦት ይሰጡበታል፡፡
በትምህርቱ ዓለም በእጅጉ የሚጠቀስለት ነገር ቢኖር ራሱን በራሱ ያስተማረ መሆኑ ነው፡፡ ሀገሩ እያለ በመንዝና ይፋት አውራጃ አብዬ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ጀምሮ ያቋረጠ ቢሆንም ወደ አዲስ አበባ ታላቅ ወንድሙ ልጅ ገብረአምላክ ወርቃለማሁ ቤት ጠቅልሎ በመምጣቱ እንደገና ተስፋ ኮከብ የሚባለው አዳሪ ትምህርት ቤት ገባ፡፡ እዚያም ለተማሪዎች የሚቀርበውን ቅንጨ የአራት ሰው ድርሻ ብቻውን በመብላትና ሰንደቅ አላማ ሲሰቀል “ደሙን ያፈሰሰ” የሚባል መዝሙር ለማጀብ ይነፋ የነበረውን ጥሩንባ ካልነፋሁ ብሎ ሲሞክር ትንፋሽ አጥሮት በጀርባው በመዘረር ታዋቂነትን አትርፎ ቁጭ አለ፡፡
የቀለም ትምህርቱን እስከ 8ኛ ክፍል ብቻ ተምሮ ተወውና ወደ ቴአትሩ ሙያ ጭልጥ ብሎ ገባ፡፡ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በቴአትር ክፍል፣ በደራሲነት፣ በአስተዋዋቂነት፣ በፕሮግራም ኦፊሰርነት ሰርቷል፡፡ ይህ የቲያትር ስራው ባንድ ወቅት እሳቸውን አስመስሎ በመስራቱ ከአፄ ሀይለስላሴ እጅ ወርቅና ካባ እንዲሸለም ምክንያት ሆኖታል፡፡ ያን ጊዜም ጃንሆይ ይጠሩትና “አንተ ወስላታ እንዴት አጠናኸን?” ይሉታል፡፡ እሱም ሲመልስ “እንዴ ግርማዊ ሆይ እንዴት አላውቅዎትም ባክዎ?” ብሎ አስቋቸዋል፡፡ ያኔ ታድያ ለማኝ ሆኖም መጫወት በደንብ የሚዋጣለት ሰው ነበር፡፡
“ጥጋበኛ የወገን ደመኛ” የሚለውን ሀገር ፍቅር የታየውን ቴአትር እንዲሁም “እኔና ሀያ ሰባት ገረዶቼ” ፣”የጥንቆላ መዘዝ” ፣ “ውለታ በጥፋ”፣”ሶስት ለአንድ” የመሳሰሉ የቴሌቭዥንና የመድረክ ድርሰቶችን ፅፎ ቀርቦለታል፡፡ ይሁንና በወቅቱ ለአርቲስት የሚሰጠው ክበር ዝቅ ያለ ከመሆኑም በላይ ሀገር ፍቅር የሚሰራ ሰው ከትልቅ ቤተሰብ መርጦ ለመግባትም ችግር ነበረበት፡፡ ከዚህም የተነሳ ቤተሰቦቹን ዘመዶቹ ስራውን እንዲያቆም ግፊት አደረጉበት፡፡
አርቲስት ከደከመ፣ ካረጀ እንዳሮጌ ግትቻ መውደቅ እንጂ የሚደግፈው እንደሌለና ለጋማ ከብትም ተጭኖ፣ ተደልዞ፣ እስከጠቀመ ተሰርቶበት ሲያረጅና ሲሞት የትም እንደሚጣል የገባው ውብሸት በጊዜው አርቲስት መሆንና የጋማ ከብት መሆን ልዩነቱ አልታይ ብሎት ተስፋ ሲያጣበት ቲያትሩን ትቶት ለነፍሱ ጥሪ የተሻለ መልስ ወደሚያገኝበት ብሄራዊ ሎተሪ በማስታወቂያ ሰራተኝነት ተቀጥሮ መስራት ጀመረ፡፡
ያኔ ታዲያ “እማሆይ እንዴት ሰነበቱ በህልሜ አይቻለሁና የሎተሪ ትኬት ይግዙ!” ብሎ ሲያስተዋውቅ እብድ ነበር የተባለው፡፡ የሬዲዮና የቴሌቭዥን ማስታወቂያን ሀ ብሎ የጀመረው እሱ ነው፡፡ ጂንግል (የማስታወቂያ ማጀቢያ ሙዚቃ) ታዋቂ ድምፃውያንን በማስጠናት ማሰራቱንም እንዲሁ የባረከው እሱ ነው፡፡ አዲስ ነገር ለመፍጠርም ብሎ አለቃውን በማስፈቀድ ከሰበታ በሃያ አምስት ብር ዥንጉርጉር አህያ በመግዛት ብር በእሷ ላይ በመጫን እየዞረ ያስተዋውቅ ነበር፡፡ ያቺ ሚስጥሩ ያልገባት አህያ ብር ይዛ በየመንገዱ መሽቀርቀሯና ብሄራዊ ሎተሪ ደሞዝ እየተቆረጠላት መንፈላሰሷ ነገር መጎተት ቻለ፡፡
ያኔ የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጳውሎስ ኞኞ ስልክ ይደውልና “ውብሸት ያቺ እናንተ ክፍል ያለችው አህያ ምን ትሰራለች?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ይሄኔ ቀበል አድርጐ “የማስታወቂያ ክፍል አህያ ነች፡፡ ባልደረባየ ነች፣ የምትሰራውን ትሰራለች፡፡ “ሲል ይመልሳል፡፡ የጋዜጣው እዘጋጅም ይህን ከሰማ በኋላ “ብሄራዊ ሎተሪ አዳራሽ ያለችው የማስታወቂያ ክፍል አህያ ናት” በማለት ፅፎ ለንባብ ያበቃዋል፡፡ ታዲያ ይህን ፅሁፍ ያነበቡት የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስተር “እኔን ነው በአሽሙር አህያ ብሎ የሰደበው?” ብለው በንዴት ብው ይላሉ፡፡ ለንጉሰ ነገስቱም አቤቱታቸውን ያቀርባሉ፡፡ ይኸው ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይነገርና ሁኔታውን የሚያጣራ አንድ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡
የኮሚቴው አባላትም አህያዋን ለማየት ብሄራዊ ሎተሪ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ገላዋን እንደሰው የምትታጠበውን ይህችን አህያ ቢያዩዋት፣ ቢመለከቷት እሷ እንደሁ አትናገር፣ አትጋገር፡፡ በኋላ ነገሩ ግን ስለገባቸው ውብሸትን ጠርተው ምን ለማለት ፈልጐ ያንን ቃል እንደተናገረ ይጠይቁታል፡፡
“አህያዋ የማስታወቂያ ክፍል ባልደረባየ ነች፡፡ እናም እንደሌሎቹ ሰራተኞች ሁሉ ታገለግለኛለች፡፡” ሲል ይመልስላቸዋል፡፡ “እሽ እስካሁን ምን ምን ሰርታለች?” ሲሉ የኮሚቴው አባላት ይጠይቃሉ፡፡ “ከአሁን ቀደም የአቃቂ ነዋሪ የሆኑ አንድ ሰው 20 ሺ ብር የሎተሪ እጣ ደርሷቸው ነበር፡፡ እናም በፊናንስ ፖሊሶች አጃቢነት ብሩን በእሷው ጭኜ ነው የሰጠኋቸው፡፡ አሁን ማን ይሙት ሰው ቢሆን በእምነት ያን ያናል ብር ወስዶ ያደርስልኝ ነበር? እሷ ግን ጨዋ ነች፣ ታማኝ፣ የምትፈልገው ቀለቧን ብቻ ነው፡፡” ሲል በመመለሱ ነገሩ ትንሽ ፈገግታ ታክሎበት በዚሁ ሊቃለል ችሏል፡፡
ብሄራዊ ሎተሪ በሚሰራበት ወቅት ያኔ እንደትልቅ ይወሰድ የነበረውን አንድ የትምህርት ቤት ዳይሬክተር የሚከፈለውን ያህል አራት መቶ ብር ደሞዝ ያገኝ ነበር፡፡ ውቤ ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ፣ ከህብረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ጋር ቁርኝት ባላቸው፣ ህብረተሰቡ በቀላሉ እየተዝናና አእምሮው ውስጥ ከትቦ ሊያስቀምጠው በሚያስችለው ጥበብ ነበር ማስታወቂያውን የሚሰራው፡፡ ሆኖም ይህ ፈጠራ አከል ጥረቱ መዘዝ ማስከተሉ አልቀረም፡፡ ከእለታት በአንድ ቀንም መስከረም ከመጥባቱ ጋርም አያይዞ እንደ ዶሮ እየጮኸ ይህን ማስታወቂያ ይሰራል፡፡
“ኩኩሉ ተነሱ መስከረም ጠባ፣ ብሄራዊ ሎተሪ ግዙ፣ 50 ሺ ብር ለማግኘት መተኛት አያስፈልግም፣ የተኛ እንደተራበ ይቀራል፣ ነቅቶ ሎተሪ የገዛ ግን ሀብታም ይሆናል!”
ማስታወቂያውን የሰሙ የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ደጃዝማች ግርማቸው ተ/ሀዋርያት እንደ እብድ አድርጓቸው በመኪና ሲበሩ መስሪያ ቤት ከተፍ ይላሉ፡ጀ፡ ከዚያም ዳይሬክተሩን ጨምሮ የመምሪያ ሀላፊዎችና ዘቦች እንዲጠሩ ካደረጉ በኋላ ፡የንጉስ ነገስቱ ሬዲዮ ጣቢያ እንዲህ መቀለጃ ይሆን?! ለመሆኑ ዶሮ ገብቶ ሲያስካካበት ምን ትሰሩ ነበር?” ብለው ክፋኛ ይቆጧቸዋል፡፡ በማግስቱ ነገሩ ሲጣራ ግቢውን ሲያምስ የዋለው የውብሸት ማስታወቂያ መሆኑ ይደረስበታል፡፡
ከዚያም አንድ ጊዜ ዶሮ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የፈለገውን እየሆነ ይህን ጣቢያ ያስቸገረው እሱ ነው ይባልና ሚኒስትሩ ዘንድ መስከረም 3 ቀን እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡ እዛም እንደቀረበ “እንደ ዶሮ እየጮህክ በጣቢያው መቀለድ የጀመርክ አንተ ነህ?” ሲሉ በቁጣ ይጠይቁታል፡፡ እሱም ፈጠን ብሎ “የዶሮ ጩኸት የንጋት ምልክት አይደለምን? እኔም ለዚህ ነው ነግቷል ትኬት ግዙ ስል ያስተዋወቅሁት ምን ነውር አለበት?” ሲል ሳይደናገጥ መልስ ይሰጣል፡፡ ሚኒስትሩም ትንሽ ተረጋግተው “እስቲ እንዴት እንደጮህክ አሁን አሰማኝ?” ሲሉ ጥያቄያቸውን ያስከትላሉ፡፡ ውብሸትም በእጆቹ ጭኖቹን መታ መታ ካደረገ በኋላ “ኩኩሉ ተነሱ ደጃዝማች” ሲል እንደ ዶሮ ይጮሀል፡፡ ደሀድ አዝማቹም ከንዴታቸው ፈገግታቸው እንዳይቀድም የፈሩ ይመስል “በል ከዚህ ውጣልኝ!” አሉት፡፡
ብሄራዊ ሎተሪ የፈጠራ ችሎታውን ያዳበረበት፣ ከብዙዎች የተዋወቀበት ነበር፡፡ እዛው እየሰራ በወቅቱ የፊሊፕስ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ የነበረው ሚስተር ቲመር እያስጠራው በትርፍ ጊዜው ያሰራው ነበር፡፡ ሙያውን እንደነፍሱ ለሚወደው ውብሸት አጋጣሚው ጥሩ እድል ይዞለት ነበር የመጣ፡፡ የፊሊፕስ ኩባንያ ሀላፊም ውብሸት ያለውን ብቃት ተረድቶ ጠቅልሎ እነሱ ጋር እንዲሰራ ጥያቄ አቀረበለት፡፡ በወቅቱ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 10-12 ሰዓት የሚሰጠውን የአማርኛ የህግ ትምህርት ይማር ነሪርና ትምህርቱን የማይነካበት መሆኑን አጣርቶ “ምን ያህል ደሞዝ ትከፍሉኛልችሁ?” ሲላቸው አንተው ቁረጥና ንገረን ይሉታል፡፡ ብሄራዊ ሎተሪ ከሚከፈለው ላይ አንድ መቶ ብር ጨምሮ የተንበሸበሸ ሀብታም ለመሆን ሲፈራ ሲቸር “አምስት መቶ ብር ክፈሉኝ” ይላል፡፡ በሱ ቤት ብዙ ብር መጠየቁ ነው፡፡ ፊሊፕስ ግን ስድስት መቶ ብር ሊከፍለው ተስማማ፡፡
ውቤ የመጀመሪያ ደሞዙን የተቀበለ እለት ከግምቱ በላይ ነበርና ለሊቱን ሁሉ ብሩን ሲቆጥር አደረ፡፡
ለሶስት አመት አገልግሎት የሰጠበትን ብሄራዊ ሎተሪን ተሰናብቶ ወደ ፊሊፕስ ኩባንያ ጠቅሎ ከገባና ለ6 ዓመታት ካገለገለ በኋላ ፊሊፕስ ለስልጠና ወደ ሆላንድ ላከው፡፡ የውቤ ለስልጠና ወደ ሆላንድ ማቅናት የማስታወቂያ ጥበብ እውቀቱን እንዲያጎለብት ብቻ ሳይሆን አክብሮትንም ጭምር እንዲያተርፍ አስችሎታል፡፡ በቆይታው ወቅት አብረውት የነበሩ ሰልጣኞችና አሰልጣኞች ውቤ በሚወዳት አገሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በተዋናይነቱ፣ በደራሲነቱና በፋና ወጊ የማስታወቂያ ባለሙያነቱ ጭምር እንደሚታወቅ ተነግሯቸው ስለነበር ልዩ አክብሮት ነበር የቸሩት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ታላቁ ቁም ነገር ያቺ የወቤ አጭር የሆላንድ ቆይታ በውቤ ህይወት ውስጥ ልዩ አስተዋፅኦ ማበርከቷ ነው፡፡ በዚያ ወቅት … በሆነ ቀን … በሆነች ቅፅበት … ነበር በውቤ ጭንቅላት ውስጥ ድንገት ብልጭ ያለችው ሀቅ እራሱን እንዲጠይቅ፣ አይኑን እንዲከፍት ያደረገችው፡፡ አብረውት የነበሩት ሰልጣኝ የማስታወቂያ ባለሙያዎች የራሳቸው የሆነ ግዙፍ የማስታወቃያ ካምፓኒ ያላቸውና የተንደላቀቀ ህይወት የሚመሩ መሆናቸውን መገንዘቡ ያሳደረበት መንፈሳዊ ቅናት “እኔስ?” ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ አደረገው፡፡
ሁኔታውን ሲገመግመው መልኩ ጥቁር ከመሆኑ በዘለለ የራሱ ጌታ ከመሆን ሊያግደው የሚችል ምንም ምክንያት እንደሌለ አወቀ፡፡ ስልጠናውን ጨርሶ ወደ አገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ከአንድ ሚኒስትር በላይ አንድ ሺ ሁለት መቶ ሰባ አምስት ብር እየተከፈለው ለአንድ ሶስት ወር ያህል ቢሰራም ሆላን ብልጭ ያለችለት ሀሳብ ጤና እየተነሳች አላስቆም አላስቀምጥ ስትለው ራሱን አለመቻል፣ የራሱ ጌታ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡
ሀሳቡን ከግብ ሊያደርስ እራሱን ፈትኖ ማንነቱን እውን ሊያደርግ የቅጥር ስራውን ተሰናብቶ ወጣ፡፡
በቅርብ የሚያውቁት ሁሉ”ይህን ያህል ደሞዝ እየተከፈለህ እንዴት የራሴን ስራ ልክፈት ብለህ አዘቅት ለመግባት ትጣደፋለህ?” የሚል ጥያቄ፣ ወቀሳና ማስፈራሪያ ቢያቀርቡለትም ውቤ ግን ጠንካራ ህልም ስለነበረው ከፊቱ የሚመጡ ውድቀቶችን በማሰብ ለፍራቻ እድል መስጠት አልፈለገም ነበር፡፡
ሁለት ሺ ብር ተበደረና በብሯ ጠረጴጣ፣ ወንበርና ታይፕራይተር ገዝቶ… ገሚሱንም በዱቤ አምጥቶ ስራውን በድፍረት ጀመረ፡፡ ጥረት ከዕድል ጋር ተቀናጁና ፊሊፕስ፣ ኮካ ኮካ፣ ብሄራዊ ሎተሪ፣ ማይሌክስ የዱቴስ ወተትን ደንበኞቹ አድርጐ ሰዎች አዘቅት ወዳሉበት እሱ የራስ ጌታ መሆን መቻል ብሎ ወዳመነበት የስኬት መስመር ገባ፡፡ እርግጥ ነው ያኔ መንገዱ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆነለትም ይልቁንም ከተለያየ አቅጣጫ ማስታወቂያ ድርጅቱን እንዳያቋቁም ኩርኮማው፣ ከባለስልጣኖች ጋር ግጭቱ ተፋፋመ፡፡ በተለይ ስሪ ኤፍ የሚባል የመንግስት ማስታወቂያ ድርጅት ጫና ድራሹን ሊያጠፋው ቢሞክርም በወቅቱ ለራሱ ቃል የገባው እንዲህ ሲል ነበር፡፡
“ህይወቴን እገብራለሁ እንጅ አለማዬ ግቡን ሳይመታ አልንበረከክም!”
እናም ለራሱ የገባው ቃል እንዲሁ ባክኖ አልቀረም፡፡ ይህን ብርቱ ኪዳን እውን ለማድረግ፣ ቁርጥ ውሳኔ ያደረገበትን አላማ ከግቡ ለማድረስ ላቡን ማፍሰስ ግድ ብሎት ነበር፡፡ አልፎ ተርፎም ብረቱና ያላሰለሰ ትግል ማድረግን፣ የላቀ ትእግስትና የበረታ የመንፈስ ጥንካሬን በፅናት ይዞ መዝለቅን እንደሚጠይቀው አላጣውም፡፡
መሸነፍ አሜን ብሎ የማይቀበለው ውብሸት ወርቃለማሁ በሚገባ በተገነባ አዎንታዊ ሰብእና፣ በመልካም ሥነ-ምግባር በታነፀ የሙያ ፍቅር፣ ይህን ብርቱ ተጋድሎ የሚጠይቅ ጥረት በማድረግ ላይ እያለ ነበር የተለያዩ ሀገራት ልዑላን፣ ፕሬዝዳንቶችና ምርጥ ሰዎች የሚሸልሙትን ጎልድ ሜርኩሪ ኢንተርናሽናል አዋርድ ተሸላሚ ለመሆን የታጨው፡፡
ለዚህ ሽልማት ከታጩት ሁሉ ትንሹ እሱ ነበር፡፡
ሽልማቱ የሚሰጠው ለአለም ሰላምና ትብብር አስተዋፅኦ አበርክተዋል ተብሎ ለሚገመቱ የአገር መሪዎች፣ ለአለም አቀፍ ግንኙነት መጠናከር ጥረት ለሚያደርጉ ልለሰቦችና ድርጅቶች እና ዜና ማሰራጫዎች ነበር፡፡ የሽልማት ድርጅቱ የተቋቋመበት ዓላማ፣ ባላቸው ተሰጥኦ አኩሪ ተግባር የፈፀሙ ሰዎችን ለመሸለም እንደመሆኑ መጠን በርካታ ሀገሮች ውስጥ ያሉ ልዑላንና ፕሬዝዳንቶች፣ የተለያየ ታለንት ያላቸው ብርቅየ ሰዎች በተሸለሙበት በዚህ ሽልማት ከአፍሪካም አንድ ሰው ሊሸለም ይገባዋል ተባለና ሸላሚው ድርጅት -ራሱን ያስተማረ፣ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆነ፣ ሰው የሚወደው፣ ራሱን ለህዝብ አገልግሎት የሰጠ፣ በሙያው የታወቀ ሰው ለማወዳደር ከአፍሪካ ሀገሮች ጥቂቶች ተመርጡና እጩ ሰዎች ተለዩ፡፡ ታዲያ ከውብሸት ጋር ተወዳዳሪ እጩዎች የሆኑት በሙሉ አፍሪካዊ ይሁኑ እንጂ የእንግሊዝና የአሜሪካ ኩባንያዎች ማናጀሮችና የላቀ ትምህርት ከሀብት ጋር ያካበቱ ነበሩ፡፡
እሱን የጠቆሙት ኮካ ኮላ ኢንተርናሽናል፣ ኦሪሶች ካምፓኒ ዩኤስ ኤ እና ሌሎችም “ያለው የህዝብ ግንኙነት ሰፊ ነው… የኛን ማስታወቂያ ይሰራል፣ አይጠጣም፣ አይሰክርም.. ሰፊ ተሰጥኦም አለው” ብለው ነበር ለእጩነት ያበቁት፡፡ ከዚያም በኋላ ሸላሚው ድርጅት በእሱ ላይ ጥናት ማድረግ ጀመረ፡፡ ጥናቱ ታዲያ “በየባንኮኒው ላይ ይደገፋል ወይ? እንዴት ነው የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሊሆን የቻለው?” የሚል ነበር፡፡
…በዩኒቨርሲቲ እንኳን ሳይመረቅ በራሱ ጥረት ገና ከማፉ ገበያ፣ ከዘጠኝ አመቱ ጀምሮ ሙያውን እንዴት እንደ ጀመረና የሰራቸው ሁሉ ከግምት ገቡና በአፍሪካ የመጀመሪያው በህዝብ ግንኙነትና በማስታወቂያ ስራ የጐልድ ሜርኩሪ ኢንተርናሽናል አዋርድ AD HONOREM ተሸላሚ ለመሆን በቃ፡፡ ውብሸት በትምህርቱ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲ ያገኘው ደፕሎማና ዲግሪ አይኑር እንጂ የተዋጣለት የፈጠራና የህዝብ ግንኙነት ሰው ተብሎ በመላው ዓለም ስሙ ቦታ አግኝቷል፡፡ ራሱን በራሱ ያስተማረና የፈጠራ ሰው መሆኑ ነበር ከተማሩት በላይ እንኳን ያደረገው፡፡ በጎልድ ሜርኩሪ ኢንተርናሽናል አዋርድ ተሸላሚነቱ በተጨማሪ በአሜሪካ አገር ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት በ18 ዓይነት የማስታወቂያ ማሰራጨትና ፈጠር ችሎታ ተሸላሚም ሆኗል፡፡ ያቀረባቸው 18 አይነት ይትብሃሎች ፈጠራዎቹ መሆናቸው ሰውየው ምን ያህል ለሙያው የተሰጠ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡
ከበርካታ ሀገሮች ነጭ ወርቅና ቀይ ወርቅ ከመሸለሙም በላይ ስለሽልማት ከተነሳ እስራኤል ሀገርም “ኳሊቲ ኦፍ ላይ” የሚል የአድቨርታይዚንግ ስብሰባ ላይ በ”ወጥ” (Original) ማስታወቂያ ስራ ተሸላሚና ያቀረበው ሀሳብ አንደኛ ደረጃን እንዲያገኝ ያስቻለው መሆኑ የማይዘነጋ ነው፡፡ እዛ ላይ ታዲያ በሽልማት ያበቃውን ሀሳብ ያቀረበው “ጠላ አለ” የሚል የጣሳ ምልክት ብቻ ተጠቅሞ ነበር፡፡ ወጪ የሌለበት ቀላልና በደንብ ሀሳብን የሚገልፅ ማስታወቂያ፡፡ እጅግ የተደራጀ አቅም፣ እውቀትና ልምድ ካላቸው የማስታወቂያ ምሁሮች ጋር ተወዳድሮ ለማሸነፍ ያበቃው አገሩ ውስጥ እንደተራ የሚታየውን ሀሳብ ብቻ ነበር ያነሳው፡፡
“ስልጣን ይቀናኛል.. ብር ነው የማይቀናኝ፡፡ ስልጣን “እልል” እያለ ይመጣል፡፡ ብር ደግሞ ከአጠገቢ “ኡኡ!” እያለ ይሸሻል፡፡” የሚለው ውብሸት ከማስታወቂያ ስራው ጐን ለጐን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ብሄራዊ ማህበር፣ በባድሜንተን ፌዴሬሽን በቦርድ አባልነትና በሊቀመንበርነት፣ በአዲስ አበባ ወወክማ ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም በልዩ ልዩ ማህበራት በሊቀመንበርነት ሰርቷል፡፡ በአዲስ አበባ የንግድ ምክር ቤት ም/ፕሬዝዳንት፣ ከዛም የባርድ አባል፣ ብሎም ከቦርድ አባልነት ም/ፕሬዝዳንት እያለ ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅታል፡፡ በድጋሚ በተደረገው ምርጫም በአንድ ድምፅ ተመርጦ የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች ፕሬዝዳንት ሆኖ 8 አመት በአጠቃላይ በሁለቱም ንግድ ምክር ቤቶች 12 አመት በመሪነት ሰርቷል፡፡ በንግድ ምክር ቤት ውስጥ በፕሬዝዳንትነት መስራቱ እሱ እንዳለው ህዝብ ነውና የመረጠው ከግል ጥቅሙ ይልቅ ለመረጠው የንግዱ ማህበረሰብ ማገልገሉ ቢያስደስተውም የምክር ቤቱንና የማስታወቂያ ድርጅቱን ስራ ማጣጣም እጅግ ተስኖት ድርጅቱ አደገኛ ኪሳራ ውስጥ እስከመግባት ደርሶ ነበር፡፡ የድርጅቱ ሰራተኞች በአንድ ድምፅ የምክር ቤቱ ተመራጭ መሆኑን ቢያወግዙትም በነገሩ እየተጨነቀ ከማለፍ በቀር የወሰደው እርምጃ አልነበረም፡፡
ምክር ቤቱ ውስጥ በነበረው ቆይታ ከአፄ ኃይለስላሴ በስተቀር በስልጣን ላይ የሌን ያህል የቆየ የለም የሚለው ውብሸት በንግድ ምክር ቤቶቹ ሲሰራ ደስተኛ አንደነበርና በርካታ እንግዶችን በመቀበል፣ ከ5 በላይ የንግድ ፕሮቶኮል ስምምነቶችን በመፈራረም እንዲሁም ኢትየጵያ በኤግዚቢሽን በየቦታው አንደኛ እንድትሆን በባህሏ፣ በእምነቷና በቀደምትነቷ ኮርታ እንድታሸንፍ በማድረጉ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡
“የመላው አፍሪካ እግዚቢሽን ሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ላይ የኢትዮጵያ የወቅቱ ጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊና የሞዛምቢኩ ፕሬዛዳንት ቺሻኖ በተገኙበት በተካሄደው ኤግዚቢሽን ላይ ለመሳተፍ ቡናና አገራችን ያለውን ነገር ይዘው ሄደን ነበር፡፡ ታዲያ ለእኛ የተሰጠው ቦታ ላይ EAST AFRICA ተብሎ በእንግሊዘኛ ተፅፎ ነበር፡፡ ባየሁት ነገር ተበሳጭቼ አዘጋጆቹን በመጥራት አስፈረስኩት፡፡ ወዲያውም በአማርኛ “ኢትዮጵያ” በሚል ከፃፍኩ በኋላ በግራና በቀኝ ደግሞ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ አስፅፌ አስለጠፍሁ፡፡ አምስት ኪሎ ቡናም አስቆላሁና በቡና ሽታ አካባቢው ግጥም አድርጌ አሳጠንኩት፡፡ ዳኞች ለመገምገም ሲመጡም “ይሄ ምንድነው? ይላሉ፡፡ እኔም ኢንሳይክሎፒዲያ በማቀበል “እዩት… የራሳችን መለያ ያለን ነን፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ኢትዮጵያ ብቻ ናት የራሷ ፊደል፣ የቀን አቆጣጠር ቀመር ያላት..” ብየ አስረዳኋቸውና ይዘን የሄድነውን የሀገራችንን ወይንና የተፈላውንም ቡና አጠጥቻቸው “ይሄ የኢትዮጵያ ቡና ነው፡፡ ኮፊ ማለት ከፋ ከሚባለው የሀገራችን ክልል የተገኘ ስያሜውም ከዛ የመጣ ነው፡፡ በማለት ታሪክ አጣቅሼ በማቅረብ ማብራሪያ ሰጠኋቸው፡፡ በውድድሩም ከሁሉም በልጠን አንደኛ በመውጣታችን ደስታየ ልክ አልነበረውም..”
ከንግድ ምክር ቤቱ ሀላፊነት በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ተመርጦ በሀላፊነት ይሰራ እንጂ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያውለው በማስታወቂያ ስራው ነው፡፡ በ1967 ዓ.ም የተቋቋመው አንበሳ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ድርጅት በአሁኑ ሰዓት አዲስ ከተቋቋመው ቡድን (Mobile Publicity) ጋር በጋራ ሀያ አራት ሰዎችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ይህ አሀዝ በትርፍ ጊዜ የሚሰሩትንና ሞዴል የሚሆኑትን ሳይጨምር ነው፡፡
አንበሳ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ድርጅት በዓለም አቀፉ የማስታወቂያ ማህበር (International Advertising Association) አባል የሆነው፣ ውብሸት አሜሪካ ሀገር ተጋብዞ በሄደበት ወቅት ነው፡፡ ከዚያም ውቤ ቱርክ ኢስታንቡል ለስብሰባ እንደሄደ በስብሰባው ላይ የተዋጣለት ንግግር በማድረጉ የማህበሩ የቦርድ አባል መሆን ቻለ፡፡ ለድርጅቱ ስያሜ የሰጠው ከልጅነቱ ገጠመኝ ጋር አያይዞ ነበር፡፡
የእናቱ ልጅ ታላቅ ወንድሙ አቶ ተሰማ አዳኝ ስለነበር የ12 አመቱን ውብሸት ጠመንጃ አስይዞ ወንድነት እንዲማር አደን ይዞት ይሄድ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በበቅሎ አፈናጦት ሲሄዱ ሁለት ሴትና ወንድ አንበሶች መንገዱን ዘጉትና ቅስቅስ አልልም አሉ፡፡ እነሱም ዝም ብለው ቆሙ፡፡ ውብሸትም ወንድሙን “እንውረድ!” ይለዋል፡፡ ወንድሙም “አይሆንም ከተንቀሳቀስን ይዘላል” ይለዋል፡፡ ይሄ ነገር ውስጡ ይቀርና ለድርጅቱ ስያሜ እስከመሆን ይበቃል፡፡ እንደ ሌላው አውሬ አንበሳ ሾካካ ባለመሆኑ ይወደዋል፡፡ እሱ በጣም የሚጠላው አውሬ፣ በህልሙ ሁሉ ሳይቀር የሚያቃዠው እባብ ነው፡፡ ሾካካ ሰውና እባብ አይወድም.. ከሰው ስም አጥፊ፣ ሾካካ፣ አስመሳይ- ከአውሬ ደግሞ እባብን ጨርሶ አይወድም፡፡
ውብሸት በርካታ የፈጠራ ስራዎችን በማስታወቂያው ዘርፍ ሰርቷል፡፡ የቅብብሎሽ፣ ግጥምና ሙዚቃ አቀፍ ማስታወቂያ (ጂንግል) በመስራትም ስልጣኔውን ለማከተል የጣረ ሰው ነው፡፡ ፊልም በቪዲዩ ካሴት በማቅረብ የመጀመሪያው መሆኑን ይናገራል፡፡ ይኸው “የክትነሽ” የሚለው የቪዲዮ ፊልሙ በአሜሪካን ሀገር ነበር የተዘጋጀው፡፡ በሸክላ፣ በሲዲ ማስታወቂያ ቀርፆ ለማውጣትም ቀዳሚው ነው፡፡ ከ3 መቶ በላይ የማስታወቂያ ጂንግሎችን (ማስታወቂያውን የሚያጅቡ ሙዚቃዊ ቅንብሮችን) ሰርቷል፡፡ አዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ ጠቃሚ ተግባራትን የከወነ ሲሆን ብዙ ጊዜ ሌሎች ሀሳቡን ተከትለው ሲረባረቡበት ተወት አድርጐ የተለየ ሀሳብ ለመፍጠር እንደሚሞክር የሚናገረው ውብሸት ሀሳብ የሚመጣለት እብድ ሲያይ፣ ከእብድ ጋር ሲነጋገር፣ ከሰው ጋር ሲጨዋወት መሆኑ ለየት እንዲል ያደርገዋል፡፡
“…ሀሳብ የሚመጣልኝ ብቻየን ስሄድ ወይም እብድ ሰው ሳገኝ ነው፡፡ ከእብድ ሰው ብዙ ነገር አገኛለሁ.. ወይ ደግሞ የተለየ መልክ ያለው ሰው፣ ትከሻው ሰፊ ወይም ግንባረ ሰፊ ሰው ሳይ … ሀሳቦች ይግተለተሉልኛል፡፡ በተለይ ሰካራም ሳይ እፈነድቃለሁ… በጣም ነው የምወደው… ሀሳቦች ከሰካራም በጣም ነው የሚገኙት፡፡ አንድ ጊዜ በደብረዘይት ሳልፍ አንድ እብድ ድንጋይ ይዞ ሲያስፈራራ አየሁና “እሱን አስቀምጥና ና!” ስለው እንዳልኩት አደረገና መጣ፡፡ ሻይ አስመጥቼለት መጨዋወት ጀመርን፡፡ ከዚያም አድራሻ ተለዋወጥን፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ እሱ የሰጠኝ አድራሻ የጐረቤት ነበር፡፡ “ምን ያህል ይርቃል?” ብለው “ጐረቤቱ ነው?… አምስት ኪሎ ሜትር …” አለኝ፡፡ “ታዲያ እንዴት ይጠሩሀል?” ብለው “ከፈለግህ ጥራኝ ካልፈለግህ ተወው?!” አለኝ፡፡ እሽ ብየው ተለያየን፡፡”
የሚገጥሙትን ሁኔታዎች ወደሚፈልገው መንገድ ይዞ የመሄድ ልዩ ችሎታ አለው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአንድ ወቅት ገጠመኙን ለማንሳቱ በቂ ምስክር ይሆናል፡፡
ወደ አንድ ክፍለ ሀገር ፊልም እያሳዩ ፊሊፕስን ለማስተዋወቅ ይሄዳሉ፡ ፊልሙም ጃንሆይ አሜሪካንን ሲጉበኙ የሚያሳይና የፊሊፕስ የማስታወቂያ ፊልም ነበር፡፡ በበነጋው ስራቸውን ጨርሰው ወደመጡበት ሊመለሱ ሲሉ አንድ ሰውየ ለውብሸት ማመልከቻ ይሰጠዋል፡፡ ማመልከቻውም “ለተከበሩ ወጣት ውብሸት ወርቃለማሁ የፊሊፕስ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መተከል አውራጃ…” ይላል፡፡ እና ማመልከቻው ሊስቱን ስለቀማበት፣ በዚያ ቁጭት ከስራ ስላባረረው የወረዳ ገዥ አቤቱታ የሚያቀርብ ነበር፡፡ ሊጠቀልለው “ሌላ ምንም አልፈልግም… ይህንን ባለጌ በአዳባባይ ላይ፣ ህዝብ በተሰበሰበበት፣ በዚያ በገበያ ቀን ተናግራችሁ ካሳፈራችሁልኝ፣ ኮወረዳችሁልኝ፣ እንደፅድቅ እቆጥረዋለሁ” የሚል ነበር፡፡
ውብሸትም የመኪናውን ማይክራፎን በመጠቀም “አቶ እገሌ አሉ? … ማመልከቻውን አንብበነዋል.. በጣም የሚያሳዝን ነው… እኛም ልባችንን ተነክቷል… ነገር ግን በዚህ በገበያ መካከል አንድ ከተማ ውስጥ ተንናግርልዎት ትንሽ ሰው ነው የሚያዳምጥልዎት፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ስመለስ በወናው በንጉሰ ነገስቱ ሬዲዮ ጣቢያ ስለምናገርና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚሰማው ያኔ ነው አንጀትዎ የሚርሰው… ግን ይህንኑ ወሬ፣ ዜናውን ለመከታተል ብርቄ የተባለችውን የፊልፕስ ሬዲዮ ሱቅ ሄደው ይግዙ፣ ወኪላችንም አቶ እከሌ፣ እከሌ ነው” ሲል ሰውየውም ደስታ አጥለቅልቆት “በሬዬንም ሸጨ ቢሆን ይህችን ብርቄ ሬዲዮ እገዛለሁ!” ብሎ እየፎከረ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡
ሙያውን የሚወደውን ያህል ተገቢውን አክብሮት ከመስጠት ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡ የሙያ ስነ ምግባሩን በመጠበቅም ላይ ምስጉን ነው፡፡ “እኔ የማምነው የሙያውን ሥነ-ምግባር በሚገባ በማክበርና በመጠበቅ ደንበኞቼን ከፍ ማድረግን እንጂ ሁሉንም ነገር በግርድፉ ጥሩ ነው ማለትን አልደግፍም፡፡ ፈፅሞ ሙያዊ ሥነ-ምግባሩም አይደለም፡፡ በሙያው ውስጥ እስካለሁ ድረስ ለሙያው መገዛት አለብኝ፡፡ ስነ-ምግባሩን ማክበር አለብኝ፡፡ እኔ ጋ የሚያሰሩት ድርጅቶች የስራ ቁርኝታቸው ቢቋረጥ ለስድስት ወር መጠበቅ አለብኝ፡፡ ተመሳሳይ ድርጅቶችን ባደባልቅ አልከብርም፡፡ መቼም የሀገራችን ፀጉር አስተካካይና የማስታወቂያ ሰራተኛ አንድ ነው፣ ፆሙንም አያድርም፣ አይከብርምም፡፡ ካልራብኝ ለምን ሙያውን ላበላሽው? እኔ ሀብት ማጋበስ ምኞቼ አይደለም፡፡ የምኖረው እንኳን ሳር ቤት ውስጥ ነው፡፡ እንደ አገሬ ሳር ቤት ሰርቼ ነው የምኖረው፡፡ ውስጡ ጥሩ ሊሆን ይችላል ግን ሳር ቤት ነው፡፡ እኔ የማመነው ህዝብን በማስተባበር፣ ጥሩ ስራ በመስራት ነው፡፡ ገንዘብ የተባለ እንደሁ አይጠጋኝም፡፡ ለበጐ ስራ በሌለሁበት እንኳ ሳይቀር እመረጣለሁ፡፡ ገንዘብ ያለበት ቦታ ግን ተመርጨ አላውቅም፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ሃብቴና ሙያየ ከህዝብ ጋር ያለኝ ቁርኝት ነው፡፡ ሀብቴ ሀገሬ ናት፡፡ በተረፈ ሀብት ላጋብስ ብል ግን በአንድ አመት ሚሊየነር መሆን እችላለሁ፡፡ እንዴት እንደሚመጣም አውቀዋለሁ፡ ያ ደግሞ የኔ ጠባይ አይደለም፡፡ በተረፈ ግን በሙያዬ፣ በኑሮዬ እግዚያብሄር እንደ እኔ ያሳካለት ሰው የለም፡፡ ከአለማዬ ውጭ ሳልሆን፣ ሳልቀላምድ፣ ሳላስመስል እዚህ ደረጃ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ ከገንዘቡ በበለጠ ለሙያዬ ክብር አለኝ. ሰው አርጐልኛልና…” ውብሸት ጠንካራ ስብዕናን ያዳበረ ሰው ነው፡፡ አይጠጣም፣ አያጨስም፣ ምቀኝነት የሚባሉ በሽታዎች የሉበትም፡፡ የአሉባልተኛና የሀሜተኛ በሽታ ልክፍት፣ ከሱካርና ከጉበት በሽታ አይለይም ብሎ ስለሚያምን ከነዚህ የፀዳ ነው፡፡ ለተስፋ መቁረጥ ሁሌ በሩ ክፍት አይደለም፡፡ “ዩሴፍ መቃብር ስገባ ብቻ…” ስለሚል ለተስፋ መቁረጥ ከቶም ቦታ አይሰጥም፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን ለነገሮች ሁሉ አድናቆት አለው፡፡ የማንንም ሙያ አይንቅም፡፡ ለሰዎች እኩል ክብር አለው፡፡ ጥሩ አስለቃሽና እንጀራ ጋጋሪ ሳይ እንኳን ያለኝ አድናቆት ልባዊ ነው፡፡ በሰዎች ስራ አድናቆት በመስጠትና በማበረታታት እንጂ በመተቸት አላምንም ይላል፡፡ ሰው ስኬታማ ለመሆን ንፁህ ልብ፣ እምነት፣ በስራ መተማመንና ማንነቱን ማወቅ እንደሚያስፈልገውና በዘርፉ እውቀቱን ማዳበር እንዳለበት ያምናል፡፡”ማንኛውም ሰው ለሰው ንፁህ ማሰብ አለበት፡፡ አገሩን፣ ወገኑን ከሁሉም በላይ መውደድ አለበት፡፡ የሚከተለውን ሰው፣ አብሮት የሚሰራውን ሰው ማወቅ አለበት፡፡ ሰው በትዕቢት ተወጥሮ ካየው ሊፈነዳ መድረሱ ነውና ራቅ ብሎ ሊጠብቀው ያስፈልጋል፡፡ በቻለው አቅም ሁልጊዜም እስከመጨረሻው የደም ጠብታ በሙያው ላይ መጣር፣ መታገል አለበት፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለበትም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ትልቁ ድክመታችን ምቀኝነታችንና ማድነቅ አለመቻላችን ነው፡፡ ይህን ማስወገድ መቻል በራሱ ስኬት ነው፡፡”
ውብሸት ወርታለማሁ የተሳካለት ሰው ነው፡፡ በሄደበት ሁሉ የሰው ፍቅር አለው፡፡ በሙያው ታዋቂ ነው… ለመመረጥ የታደሰ… ገብቶ በወጣበትም ሁሉ የሚሳካለት፡፡ ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ ላይ ኬንያውያን እንዳሉት ‘The man with a Golden touch’ “የነካው ሁሉ ወርቅ” የሚሆንለት ሰው ነው፡፡ አርባ አንድ ሀገሮችን አይቷል፡፡ ‘Iam Successful Every where’ የሚለው ውብሸት በህይወቱ ደስተኛ ነው”…ሁሉ በእጄ ነው…እግዚአብሔር ይመስገን የማንንም በር እንኳኩቼ የማይከፍትልኝ የለም፡፡ የመጨረሻው የስኬት ደረጃ ደግሞ ይሄ ነው፡፡ በዚህ ላይ እኔ ደግሞ በ25 ሳንቲም ሻይ ተደስቼ መዋል የምችል ሰው ነኝ፡፡ ይህ እምነት፣ ይህ ስኬት ያለ ውጣ ውረድ እንዲሁ የተገኘ አይደለም፡፡ በጠንካራ እምነት፣ ሪስን ለዓላማ ፅናት በማሰልጠንና በመትጋት የመጣ ነው…” ይላል፡፡ የተፈተነባቸውም አጋጣሚዎች ይህንኑ የሚያፀኑ ናቸው፡፡ ከፈተናዎቹ አንዱ በመርከብ ከአንዱ አገር ወደ ሌላ አገር ግንድ የጀመረ ጊዜ ሰዎች ተመሳጥረው አዘቅት የከተቱት ገጠመኝ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ ለመክበር ፈልጎ በጀመረው ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር በመርከብ መነገድ በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያየ ጊዜ አንድ ሚሊዮን ተኩልና ግማሽ ሚሊየን በማድረግ ራሱን በሁለት ሚሊየን ብር እዳ ውስጥ ዘፍቆት ቁጭ እንዲል ምክንያት ሆነው፡፡ ያን ጊዜ ነው ባልተመረጡበት ስራ መሰማራት ደካማነትን ማወጅ መሆኑ የገባው፡፡
ሁለት ሚሊየን ብር እዳ በገባበት ወቅት “አለሁልህ!”ብለው ከጎኑ የቆሙለት የሚያምነው ባንክና ተሾመ በቀለ የሚባል ጓደኛው ናቸው፡፡ ባንኩ ያለፊርማ፣ ያለምንም ማወላወል ነበር እዳውን ከፍሎ ነፃ ያወጣው፡፡ ይሁን እንጂ ውብሸት በኪሳራ አማካይነት ያጋበሰውን እዳ እስካሁን በመገፍገፍ ላይ ይገኛል፡፡ ችግሮች እንዳይነሳ አድርገው ሊጥሎት ቢመጡም እንዲህ እያለ ነበር እየተቀበለ የሚያስተናግዳቸው፡-
“…ወይ ጊታ! ደግሞ ይህንንም ልታሳየኝ ነው?” መከራውን ዋጥ ያደረገው… እጅግ ከከፋ ተስፋ መቁረጥ ጋር ግብ ግን ገጥሞ ነው ግን አሸንፏል! ዛሬ ከቀረበት የገንዘብ እዳ ውጭ ሁሉም ትዝታ ሆኗል፡፡
በእግዚአብሔር ያለው እምነት ከፍተኛ እርዳታው ነው፡፡ መከራዎችን ሁሉ በፅናት እንዲቋቋም የረዳውም ይኸው የዕምነቱ ፅናት ነው፡፡ ጠንካራ እምነት ስላለውም “.. እኔ ሰባት ቀን መሬት ብተኛና ብፀልይ የፈለግሁትን አገኛለሁ…” ይላል፡፡ ሁልጊዜ ፀሎቱ እንዲህ ነው “…ጤንነቴን ስጠኝ፣ የሰው መውደድ ስጠኝ፣ በሰላም አውለኝ፣ ሀጢአቴን ይቅር በለኝ፣ ለዚህ ያበቃኸኝ አምላክ ሆይ ተመስገን.. ከክፉ ነገር ሰውረኝ.. የሰጠኸኝን ልጆችና ሀገሬን ባርክ፣ ጠብቅልኝ…”
መከራ ካስመከረውም ተለምዶ ይሆናል ቢሮው ላይ እንዲህ የሚል፣ እንደነፍሱ የሚወደው ጥቅስ ተሰቅሏል፡፡ “አለኝ ብለህ አትኩራ፣ የለኝም ብለህ አትፍራ፣ ህቡፅ ነውና የአምላክ ስራ፡፡” እሱነቱ በአምላኩ እጅ እንዳለ ስለሚያምን ነገሩን ሁሉ በእሱ ላይ ጥሎ ነው የሚታገለው፡፡ ቤቱ ውስጥ የፀሎት ቤት ስላለው ሁልጊዜ ጠዋት ፀሎት ያደርጋል፡፡ ከሴት ጋር አድሮ ከሆነ ብቻ ፀሎት ቤቷ ሳይገባ በረንዳው ላይ ሆኖ ይፀልያል፡፡
ሌላው መለያው ሁሉን ነገር በማሻሻል ማመኑ ነው፡፡ የማያምንበትን ነገር ግን ባለመቀበልም ላይ ግትር ነው፡፡ ቀዩም ቀይ፣ ጥቁሩም ጥቁር ነው በሱ ዘንድ፡፡ ፍቅር እንጅ ሌላ የሚገዛው ነገር እንደሌለ ያስረግጣል፡፡ መፅሀፍ ቅድስ ማንበብ ላይ ግን ፈሪ ነው፡፡ አንቀፅ ባንቀፅ የሰፈረው መልእክት የሚያሰጋ ነው… ሰለሚል ደከም ይላል፡ አስርቱን ቃላት ወዳጅና ከአንዷ አታመንዝር በስተቀር በደንብ የሚያምንባቸው ናቸው፡፡ ያቺን የሚጥሳትን “አታመንዝር” ህግ እድል ፋንታ እንደሰጣት ማለፍን ስለማይፈልግ ታጥቦ፣ ታጥኖ፣ ስጋወ ደሙን ቀምሶ ለማለፍ የሚመኘውና ሊያደርገውም የሚፈልገው ነው፡፡
ውብሸት ቀን ሶፋ ላይ ወይም ባገኘበት እንደተቀመጠ ለ10 ደቂቃ እንቅልፍ ሸለብ ካለደረገው ሲያነጫንጨውና ሲደብተው ነው የሚውለው፡፡ ማታ ላይ በመከራ ነው እንቅልፍ የሚመጣለት፡፡ ለምሳ እና እራት ብዙም ግድ የሌለው ውብሸት ቁርስ ነፍሱ ነው፡፡ በተለይ ግፍልፍል ሽታው ብቻ ይበቃዋል በፍቅር ነው የሚወደው፡፡ ውቤ አንድ ጊዜ ቁርስ ላይ ከተቀመጠ በአቦ በስላሴ ተብሎ በገላጋይ ነው የሚነሳው ቁርስ ይበላል የሚለው ቃል ብቻ አይገልፀውም፡፡
የጠንካራ ጎኖቹን ያህል ሊወዳደሩ ፈፅሞ የማይችሉ ገን ደግሞ ጥቂት የማይባሉ ደካማ ጎኖች እንዳሉት እሱም ሳይቀር ጠንቅቆ ያውቃቸዋል፡፡ ቶሎ ቱግ ይላል፣ ይናደዳል፡፡ ሲናደድ ደግሞ ነስር ይነስረውና ንዴቱንና ቱግታውን ያሳብቅበታል፡፡ ከሰው ጋር ሲጣላ እንባው መቅደም፣ መቆጣት፣ መሳደብና እቃ መስበር ከችኩልነትና ቀዥቃዣነት ጋር ሀብቱ ናቸው፡፡ ንዴቱ፣ በቁጣና ስድቡ ካልወጣለት ቂመኛ ነው፡፡ የቂም ምርኮኛነቱ ግን በቀል ወልዶበት አያውቅም፡፡ ምናልባትም ተፈጥሮው ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ አቅዶ ትንሽ መስራትም በተለይ የዛሬ ጊዜው መሰናክል ሆኖ አስቸግሮታል፡፡ ከሁሉ የባሰው ድክመቱ ለሴት ያለው ፍቅር መብዛቱ ነው፡፡ ሲናደድ እቃ መስበርም የጀመረው ከሴት ጋር በተያያዘ ገጠመኙ ነው፡፡ በጉርምስናው ወቅት ሴቶች በቮልስ ዋገን መኪናው ጭኖ ወደ ፖርቲ ቤት ጉዞ እንደተጀመረ መኪናዋ ወገቤን ትላለች፡፡ ብትባል፣ ብትሰራ፡፡ ውርደት! ውቤ ታዲያ ያኔ ያደረገው እንዲህ ነበር የመኪናዋን መስታወት በዱላ አመድ ማድረግ፡፡ ሴትን በወርቅ፣ በማርቼዲስና በቢኤም ደብሊው መግዛት አይቻልም፡፡ በፍቅርና በስነምግባር እንጂ የሚለው ውብሸት ለሴት ያለው ፍቅር የበዛ ነው፡፡ የሚገርመው እንዲያም ሆኖ የራሱ የሆነ መመሪያ ያለው መሆኑ ነው፡፡
“የሰው ሚስት፣ ሰው ወዶ ያስቀመጣትን፣ አብራ የምትሰራን ሴት፣ የጐረቤትን ሴት፣ የጋደኛየን እህት አልፈልግም፡፡ የፈለገችው ሞናሊዛም ብትሆን ከነዚህ ጋር መቅበጥ ከጀመርህ ጠላት ነው የምትገዛው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሴት፣ መጠጥና ስልጣን ስትጋራው አይወድም፣ ለሌላው ግን ግድ የለውም፡፡ ከዚህ ውጪ ግን አዎ ትንሽ ትንሽ ቀበጥ የምል ይመስለኛል…”
ምናልባት ለትዳሩ ስኬታማ ሆኖ ያለመቆየት ተጠቃሹ ግር ለዕንስቶች ያለው ስሜት ሊሆንም ይችላል፡፡ ምንም እንኳን ትዳሩ እስካሁን ዘልቆ ስኬታማ ባይሆንም ለአንድ የሴቶች በጎ አድራጎት ማህበር ወጣት ሴቶችን ለመመልመል ከጓደኞቹ ጋር በተላከ ጊዜ ነበር የትዳር አጋሩ ከሆነችው ወጣት ጋር ሊተዋወቅ የቻለው፡፡
ለኢትዮጵያ በጐ አድራጐት ሴቶች ማህበር የአባላት ቁጥር ለመጨመር እንደያስችል እነልዕልት ሰብለና ወ/ሮ ሉሌ ወጣቶችን ማርኩልን፣ ወዲያ እንዲመጡ አግባቡልን ብለው ከላኳቸው መሀል ውብሸት አንዱ ነበር፡፡ ውብሸት የወጣለት የትምህርት ቤት እጣ ስም ከሚፈለገው ጋር አንድ መሆኑ ደግሞ አስገራሚ ነበር፡፡
ከስራ እንደወጣ በ11 ሰዓት ሴቶች ተማሪዎች ፊት ቀርቦ ንግግር ለማድረግ ሁሌ ሩጫ ነበር፡፡ ሴቶቹ የማህበሩ አባል እንዲሆኑና የሀገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ሰናይ ተግባር ለመተግበር እንዲችሉ ማሳመን ነበር፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ የፍቅር ጉድኝት ለመፍጠር በአንድ ክትፎ ነገሩ የማያልቅ በመሆኑ ደብዳቤ ለጉርፎ በመፃፃፍ፣ ልቤ በፍቅርሽ ጦር ተወጋ ለማለት ጦሩን ከነልቡ ስሎ መናዘዝን የሚጠይቅ ነበር፡፡
ከእለታት ባንዱ ቀን ምድቡ የደረሰበት ሴንቲሜሪ ትምህርት ቤት ሄዶ ንግግር ሲያደርግ አንዲት ቆንጆ አይኑ ትገባና ንግግሩን እስከማስጠፋት ልቡን ትሰውረዋለች፡፡ አይኑ እንደተንከራተተ፣ ልቡ እንደቋመጠ ምንም እርምጃ ሳይወስድ ይመለሳል፡፡ አጋጣሚ ይሆንና ልቡን ያጠፋችው ልጅ ስለ አባልነቱ ለማናገር ከጓደኛዋ ጋር ሆና ቢሮው ትመጣለች፡፡ መቀራረቡ ሲፈጠር በዘዴ የልጅቱን ጓደኛ የእናት ልጅ አድርጐ ይቀርባታል፡፡ የሌላቸውንም ዝምድና በባሌም በቦሌም ብሎ ዘር ቆጥሮ የአንድ አያት ልጅ አድርጓት ቁጭ ሲል እሷም “ወንድሜ!” ብላ ትቀበለዋለች፡፡ እሱም”በይ እንግዲህ ወንድሜ ማለት ብቻ ዋጋ የለውምና ይችን ጓደኛሽን መላ በይኝ” አላት፡፡ እሷ የልጅቱን ልብ ስታሟሟ፣ እሱ ደሞ መኪናውን እያስጮኸ፣ እያስጓራ ላይ ታች በማለት የልጅቷን ቀልብ ለመሳብ ጣረ፡፡ ተሳካለትና እጁ ላይ ወደቀች፡፡
ተቀራርበው አንድ አመት እንደቆዩ ሽማግሌ ይላክ ትልና ሀሻብ ታቀርባለች ውቤም ሽማግሌዎች ላከ፡፡ የልጅቱ አባት ስለ ውብሸት ሰልለው ኖሮ “ያ አውሮራ ቡና ቤት በራፍ ላይ ሴቶች እያየዘ ማኪያቶ ሲልስ የሚውለው አይደል?” ይሉና በሽማግሌዎቹ ላይ ውሻ ፈትተው ያባርሯቸዋል፡፡
በኋላም ይበልጥ ስለውብሸት ስራ ሲያጣሩ ፊልፕስ ነው የሚሰራው፣ በሬዲዮ ማስታወቂያ ይሰራል… እየተባለ ሲዘረዘርላቸው “ይሄ ባትሪ ድንጋይ ግዙ እያለ የሚያስተዋውቀው ነው?” ይላሉ አዎ ሲባሉ “ባትሪ ድንጋይ ግዙ እያለ ለሚያሻሽጥ ደላላማ ልጄን አሳልፌ አልሰጥም” ይላሉ፡፡ በኋላ ግን በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩ የተከበሩ ሰዎች ሲዳሞ ዲላ ድረስ ሲላክባቸው ደንግጠው አደግድገው ተቀበሉና “የእናንተ ዘር መሆኑን መች አውቄ? ታዲያ ለምን ዳይሬክተር ምናምን አታደርጉትም ነበር? እዚያ የፈረንጅ ባትሪ ከሚያስተዋውቅ? ብለው ጋብቻውን ተቀበሉት፡፡ ቆይተውም ተጋቡ፡፡ በትዳራቸውም ሁለት ልጆችን አፈሩ… አሀዱ ውብሸትንና ዳግማዊ ውብሸትን፡፡ ሁለቱ ልጆቻቸው የአምስትና የሁለት አመት ህፃን እያሉ ተፋቱ፡፡ ውብሸት እንደሚለው ልጆቹን በእንጀራ እናት ላለማሳደግ ለራሱ በገባው ቃል መሰረት ከትዳሩ ዓለም ርቆ ቆየ እስካሁን፡፡
ልጆቹን በራሱ ምሳሌ ለመቅረፅ ይመስላል ስለሀገር ፍቅርና አደን ሲያስተምርና ሲመክር ነው ያሳደጋቸው፡ “የወንድ ጠባይ፣ ያበሻ ወኔ አላቸው፡፡ ወኔያቸው ሌላ ነው፡፡ ወኔ ካለህ ትግልህ ቶሎ አይቀዘቅዝም…” ይላል፡፡ የመጀመሪያ ልጁ አሀዱ ሜሪላንድ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው አሜሪካን ዩኒቨርስቲ በኢንተርናሽናል ፋይናንስ ማስትሬቱን አግኝቶ እዛው ዲሲ ፋኒሜ ባንክ የሚባል ውስጥ የአንድ ክፍል ሹም ሆኖ በኃላፊነት ይሰራል፡፡ ሁለተኛው ልጁ ዳግማዊ ስኮላር ሽፕ ከዱክ ዩኒቨርስቲ አግኝቶ ባችለሩን ከያዘ በኋላ ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲም ስኮላርሽፕ አግኝቶ ማስትሬቱን በክብር ወስዶ ፒ ኤች ዲውን ለማጠናቀቅ ዓመት ያልሞላ ጊዜ ይቀረዋል፡፡
ከየትኛውም ፍቅር ይበልጥ ከልጆቹ እንኳን ለሀገር ፍቅር ያለው ስሜት እጅግ የላቀና የውብሸት መለያው ነው፡፡ “ከሁሉም በፊት የሀገር ፍቅር ይቀድማል” ነው የሚለው፡፡ ቢሮው የኢትዮጵያ ባንዲራ ጐልቶ ይታያል ቤቱ ሳሎን ውስጥ የኢትዮጵያ ባንዲራ ተገማሽሮ ይገኛል፡፡ በተጋበዘበት ቦታ ሁሉ የሚለብሰው የሀገር ልብስና ካባ ሀገርን የሚያንፀባርቅ ነው በዚህ የቃለመጠይቅ ወቅት እጅግ በጋለ ስሜት ሲናገር የነበረውና ብዙ ታታም የፈጀው በሀገር ፍቅር ላይ ነው፡፡
“… የተፈጠርሁባት ምድር የሰው ልጅ መጀመሪያ የተፈጠረባት፣ እነሉሲ (ድንቅነሽ) የተገኙባት ሀገር ነች.. በጥላ ስር ትክክለኛ ፍርድ ይሰጥበት የነበረው፣ ተጠይቅ ልጠይቅ፣ በላ ልበልሃ የሚባለው የት ነው? በኢትዮጵያ ምድር ነው.. ከኋላ ቀርነታችን፣ በስልጣኔ ካለመመንደጋችን በቀር.. እ … እሱም ወደ ፊት የሚመጣ ነው.. ምን ጐድሎን? እንጀራ በወጥ የሚጣፍጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው… ጣዕም እንኳን ያለው ምግብ ዶሮና ሎሚ የእኛ ነው.. እ? ዶሮአቸውን ብትል ጣዕም የለው… ሎሚያቸው ብትል ጣዕም የለው… የነጮቹ እንቁላላቸው እንኳን ውስጡ ነጭ ነው… የእኛ ግን ቢጫና ጣዕም ያለው ነው… እትብቴ የተቀበረው እኮ እምየ ምድር ነው… ልሀድ የወለድሁት፣ ያስተማርሁት.. አሜሪካም ድረስ ልኬ የማስተምረው እኮ ሀገር ስላለኝ ነው… ፈረንጆች በቀስተ ደመና የሚመስሏት፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ያላት፣ የሚያኮራ ስልጣኔ በነላሊበላ፣ አክሱም፣ ሶፍዑመርና ጎንደር.. ያላት ምርጥ ሀገር ስላለችኝ እድለኛ ነኝ፡፡ ለሀገር ጥሩ ፍቅር ኖሮህ እኮ ከተነሳህ ስኬታማ ትሆናለህ… ችግሯን፣ መከራዋን፣ ደስታዋን መካፈል አለብህ፡፡ … ይገባሀል? የኢትዮጵያ ህዝብ እወዳለሁ…በርበሬውን እወዳለሁ… ፍርፍሩን እወዳለሁ… ሁሉ ነገሩ ደስ የሚልህ ሀገርህ ውስጥ ነው… ብዙ ችግሮች የሉም ብየ አይደለም፣ ብዙ ድክመቶች ጠፍተውኝ አይደለም… ግን እትብትህ ማለት አንተ ማለት ነው… ሀገርህ ማለት አንተ ማለት ነው… ታሪክ እኮ አለን… የዘመኑን ዕውቀት ለመገብየት ዘግየተን ይሆናል እንጅ ስልጣኔ እኮ አለን …ሳውና ባዝ ድሮ የነበረን ነን… ነጭ በጥቁር ያውም በኋላ ቀር መሳሪያ የተሸነፈበት እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው… እኔ ወደ 17 ጊዜ አሜሪካን በተለያየ ጉዳይ ሄጃለሁ… አንድ ወር ስቀመጥ እጅ፣ እጅ አይደለም እግር፣ እግር ነው የሚለኝ.. አልወደውም! አሁን አሁን የባህላችን መውደቅ ያሳዝነኛል… ስንቱ ሀገር የባህል ድርቅ ሲያሰቃየው እያየን እንኳን ለባህላችን ግምት አለመስጠታችን ያበግነኛል፡፡ በኛም በማስታወቂያ ሰራተኞች በኩል ባህሉን እየገደልነው ነው… ከላይ በእንግሊዘኛ፣ ቀጥሎ በአማርኛ…ቅኝ እንደተገዙ ሀገሮች እንዴት በባዕድ ቋንቋ እናስቀድማለን? … መጀመሪያ የምወደው ሀገሬን ነው… ልጅ ወለድኩ ልጆቼን እወዳለሁ… ዘመዶቼን፣ ጓደኞቼን የኢትዮጵያን ህዝብ እወዳለሁ…”
ለሀገር ፍቅር ካለው ስሜትም ይመስላል ካባ መለያው የሆነው፡፡ ይህንን ያሳደረ፣ በልቡናው ያሰረፀ ደግሞ ሌላ ገጠመኝ አለው፡-
ኃይለስላሴ ነብይ ዘወጠኖ መፅሀፈ ሚኒሊክ አዳም “ነብዩ ሚኒሊክ የጀመረውን ኃይለስላሴ እየፈፀመው ነው” የሚለውን ቅኔ አፄ ኃይለስላሴ ዘንድ ቀርቦ በመቀኘቱ ንጉሰ ነገስቱ “እኛስ የጀመርነው የለም?” ሲሉ ፈገግታ ለበስ ቁጣ ካቀረቡ በኋላ “ምን ያምርሃል ምን ትፈልጋለህ?” ብለው ቅኔ ተቀኝውን ውብሸትን ይጠይቁታል፡፡ ከአፋቸው ቀልቦም “የእርስዎን ካባ፣ ጃንሆይ የእርስዎን ካባ ነው” ይላል፡፡ “አንተ ወስላታ ደፋር!” ይባላል፡፡ ውቤም እጅ ይነሳል፡፡ በጃንሆይ ትዕዛዝ የመጣለት ካባ ልኩ አልሆን ይላል፡፡ ጃንሆይም ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት “ይልበሰው!” ይላሉ አስቂኝ ነበር፡፡ ጃንሆይም ሳቁና የልዩ ግምጃ ቤታቸውን ምክትል ቀኛዝማች አመኑ ገብረሃናን አስጠርተው “ለዚህ ልጅ ካባ ይሰጠው፣ ለወደፊትም የክብር ልብሱ ይሆናል!” ብለው አዘዙ፡፡ አንድም የጃንሆይ ስጦታ ስለሆነ … በሌላም በኩል አባት፣ አያቱን ቅድመአያቱ ስለሚለብሱት፣ የሀገሩም የክብርና የኩራት ልብስ ስለሆነ፣ ትንበያው ሰመረና የክብር ልብሱ ሆነ፡፡ ውብሸት በተጋበዘበት የክብር ግብዣ ሁሉ የባህል ልብሱ ከካባ ጋር የሌለበት አንድስ እንኳን የለም ቢባል ፈፅሞ ማጋነን አይሆንም፡፡ ውብሸት ከዚህ በኋላ ተግባራዊ ቢያደርጋቸው የሚመኘውን መኖሩም የበለጠ ትርጉም የሚያገኘው የሚፈልጋቸውን ሶስት ነገሮች ያሳካ እንደሁ ነው፡፡
የመጀመሪያው ችግረኛን የሚረዳበት፣ አንድ በጐ ተግባር ከውኖ የሚያልፍበት መንግስታዊ ያልሆነ ለበጐ አላማ የሚሰራ ድርጅት (NGO) ቢያቋቁም፣ ሁለተኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ቢሆን ነው፡፡ ይህንንም ለማሟላት ብቃትና ተሰጥኦው አለኝ ባይ ነው፡፡ “…ራዕዩ አለኝ፡፡ እኔ ራሴን ጠብቄ ሰካራም ሳልሆን፣ ሌባና ወራዳ ሳልሆን ነው የቆየሁት፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እኔን በፕሬዝዳንትነት ቢመርጠኝ እሱም አያወላዳ፣ እኔም አላወላዳ፡፡ እኔ የአደባባይ ሰው ነኝ፡፡ ደግሞም በየቦታው በንግድ ምክር ቤት፣ በልዩ ልዩ ማህበራት ፕሬዝዳንት እየሆንሁ ልምዱን ስላካበትሁት በግማሽ መሳቁንም፣ ማኩረፉንም፣ አቀባበሉንም አውቅበታለሁ፡፡ እንደውም የሚሆነኝ ቦታ እሱ ይመስለኛል…” የመጨረሻው ምኞቱም የእግዜሩን ጥሪ በፈገግታ ለመቀበል ገዳሙን መጐብኘት ነው ስጋወደሙን መቀበል፡፡
  
ከሆስፒታል ከወጣ በኋላ ሰው እየታቀፊው ካልሆነ በስተቀር መንቀሳቀስ አልቻለም ነበር፡፡ ዶ/ር ፖርትማን ቤት ለማገገም ያህል አንድ ወር ተቀመጠና ከዚያም ወደ ጣሊያን አገር ሄደ፡፡ መቶ አለቃ ገ/የስ በቀለና ባለቤቱ ሂሩት ካሳየ የተባሉ ወዳጆቹ ጋ ሄዶ ለ15 ቀናት ከቆየ በኋላ ከዊልቸር የተሻለ መሳሪያ በመጠቀም ሀገሩ ተመለሰና በማግስቱ ናዝሬት ሶደሬ ሄዶ እዛ ተቀመጠ፡፡ የሰው ሀብት የተትረፈረፈለት ውብሸት ወርቃለማሁ መታመሙንና በዊልቸር ካልሆነ መንቀሳቀስ አለመቻሉን የሰሙት የሶደሬ መድሀኒዓለም ቤተክርስቲያን ምዕመናን ወቅቱ ከፍልሰታ ፆም ጋር የተያያዘ ስነበር ፊት ሌት ከቀን እንባ እየተራጩ ፀሎት ያዙለት፡፡
  
“ትድናለህ… ግን ህይወትህን በዊልቸር ላይ ሆነህ ልትገፋ ትችለለህ”
ቃሉን ሲሰማ የውብሸት ወርቃለማሁ ፊት ከሞት ያልተናነሰ ሀዘን ነበር የደበበበት፡፡ ህይወት ከዚህ በኋላ በዊልቸር ላይ ልትገፋ የመሆኑ መሪር ዜና ከሞት መርዶ ባልተናነሰ ቅስሙን ሰበረው፡፡
ስዊዘርላንድ ውስጥ ለታከመበት የሚከፈለውን ከ75ሺ ብር የበለጠ ገንዘብ መንም እንኳን ባለውለታው የሆኑት የኦሪስ ኩባንያ ባለቤት ለሆስፒታሉ ቢከፍሉለትም ሰርቶ ገንዘቡን በየወሩ እየከፈለ መጨረስ ነበረበት፡፡ በወቅቱ ድርጅቱን በረዳት ሥራ አስኪያጅነት ይመሩ የነበሩት ወ/ሮ ስመኝሽ አይችሉህምና ባለቤታቸው ዶ/ር ካሳዬ ቀፀላ ባይኖሩ እቢሮው መመለስ ባልቻለ ነበር፡፡ ባለውለታዎቹ ናቸው፡፡
እሱ ግን እስካሁን በዊልቸር ላይ ነው ያለው፡፡
በዊልቸር ላይ ሆኖ ህይወትን መግፋት ከባድ ሆነ፡፡ ኑሮ እየከፋ ሄዶ ትዳር ተበጠበጠ፡፡ ድህነት አስፍስፎ ሊውጠው ቀረበ፡፡ ትዳር ላይ ስምምነት መጥፋቱም ሶስት ሚሊዮን ሊያወጣ የሚችል ቤት በሶስት መቶ ሺ ብር አሸጠ፡፡ ነገሮች ተተረማመሱ፡፡
  
ቅስሙ ስብር ብሎ ሴት ቀን አምላኩን ከዚህ ስቃይ እንዲያድነው መለመን ግድ ሆነበት…
መከራው ከእግዚአብሄር ጋር አቀራረበው… በጣም አቀራረበው፡፡
ለአንድ ወር ያህል ሶዳሬ ጤንነቱን እየተከታተለ፣ በተያዘለትና እርሱም አጥብቆ በጀመረው ፀሎት ገፍቶበት ልመናው ሰመረና በእግዚአብሄር ሀይል ለውጥ ታየ!
በዊልቸርም፣ በከዘራም፣ እያነካከሰም የሚገርም ለውጥ አመጣ፡፡
ከሁለት ልጆቹ ጋር በተረፈችው ትንሽ ገንዘብ ጊዎን ሆቴል ጊዮን ሪቪየራ ቤት ተከራየና እየተፍጨረጨረ ለመስራት መሞከር ጀመረ፡፡ በከዘራ ሆኖ ስራውን አንድ ሁለት እያለ ሳለ ፈፅሞ ያልተጠበቀና እሱ የእግዚአብሄር ስጦታ ያለው የጎልድ ሜርኩሪ ሽልማት እጩ የመሆኑ ዜና በካራካስ ቬንዙዌላ ላቲን አሜሪካ ደረሰው፡፡
ያኔ በደንብ ዳነ!
የህክምና እዳውን መክፈል ቻለ!
ህይወት ከሞት አፋፍ ተመለሰች፡፡ ያቺ ከነጥልቅ ስቃይዋ ያንዣበበችበት መራራ ፈተና እንኳን የውብሸትን ፈገግታና ቀልደኝነት መቀማት አቅቷት ተሸነፈች፡፡
እናም እሱ ሊወስደው ያሰፈሰፈውን ሞት በፅኑ እምነቱ ነክቶ ወደ ወርቅ የቀየረው ልዩ ሰው ነው ውቤ !!!

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »