የራስዎን ሥራ ይጀምሩ

 ምን አይነት ሥራ ልጀምር ?

ምን ልስራ ?›› የሚለው ጥያቄ ድንቅ ጥያቄ ነው፡፡ ትክክለኛ ምላሽ ሚፈልግ ውብ ጥያቄ፡፡የሰው ዘር እስካለ የሚኖር ቋሚና አስፈላጊ ጥያቄ፡፡ ጊዜ የማያልፍበት፣ በየትኛውም ስፍራ ሚነሳ ጠቃሚ ጥያቄ፡፡

እርግጥ ነው የሆነ ስራ እየሰራህ ሊሆን ይችላል፡፡ምናልባትም ስራህን ትወደው፣ ወይም ጠልተኸው ይሆናል፡፡

በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ‹‹ምን ልሥራ ?›› የሚለው ጥያቄ  በውሥጣችን ከተፈጠረ፣ የአንዳች ፍላጎት ምልክት አድርገን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ምናልባትም የለውጥ፣ምናልባትም የሥኬት፣ምናልባትም የብልፅግና፣አልያም እንዲሁ አንዳች ነገር የማከናወን ፍላጎት፡፡

ይህ በ ሁለት የተለመዱ ቃላት የተሰነዘረ ግዙፍ ጥያቄ ‹‹ ይህን ሥራ›› ‹‹ያን አትስራ ›› በሚሉ ሁለት ተመጣጣኝ ቃላት ብቻ የሚመለስ ጉዳይ አይደለም፡፡

አጥጋቢና ትክክለኛውን ምላሽ ለማግኘት፣ የጋለ ፍላጎት ያስፈልጋል፡፡ምናልባትም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተፃፉ ፅሁፎችን ማገላበጥ ፣ ጥቂት የጥሞና ጊዜያት መመደብ ፣ከሌሎች ሰዎች ጋር መወያትን የመሳሰሉ ተጨማሪ ጥረቶች ይጠይቅ ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ታዋቂ ምግብ ቤት ነበረች፡፡ምንጊዜም በደንበኞች ስለምትጨናነቅ መቀመጫ ቦታ ለማግኘት ጥቂት ደቂቃዎች ቆሞ መጠበቅ ያስፈልጋል ፣ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን የሚለቀቁ ቦታዎችን በንቃት መከታተልና ተጠቃሚዎቹ ሲነሱ ቶሎ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ በረንዳና  ጓሮ፣ ጥጋጥጉም በተመጋቢዎች ይሞላል፡፡

እርግጥ ምግቡ ግሩም ፣ዋጋውም ቅናሽ ሊባል ሚችል ቢሆንም፣ አገልግሎት አሰጣጧ ፈፅሞ ምቹ አይደለም፣ ጫጫታው፣የተመጋቢው ትርምስ፣ የቤቷ መጥበብ፣በፍጥነት ተመግቦ ቦታ የመልቀቅ ህጉ በጣም ያስጨንቃል፡፡

አንድም ነገር ሳይለወጥ ፣ከዕለት ወደ ዕለት ገበያዋ እየደራ፣የደንበኞች ቁጥር እየጨመረ፣ጭንቅንቁም እየባሰ፣እውቅናዋ ከፍ እያለ መሄዱን ለዓመታት ቀጠለ…

ምግብ ቤቷ በበርካታ ሆቴሎች፣ሬስቶራንትና፣ ግሮሰሪዎች የተከበበች ናት፡፡ ሁሉም ማለት ይቻላላል ከሷ የተሻለ ህንፃ፣ንፅህና፣ስርዓት ቢኖራቸውም አንዳቸውም የሷን ግማሽ ያህል ሽያጭ የላቸውም፡፡

ከዓመታት በኋላ እቺ ባነስተኛ ቤት ውስጥ የደራ ገበያ ያላት ምግብ ቤት መሰረታዊ ለውጥ አደረገች፡፡ የዱሮው ቤት ፈርሶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ ህንፃ ተገነባ፣ጥራት ባላቸው መጠቀሚያ ቁሳቁስ ተደራጀ፣የማብሰያ ክፍሉ፣የመፀዳጃው ንፅህና ግሩም ሆነ ፡፡ ውስጣዊ ዝግጁትን ሚገልፅ ጥሩ ሥያሜ ተሰጥቷት ባለ መብራት ማስታወቂያ ደጃፏ ላይ ተሰቀለ፡፡ ዘመናዊ አስተናጋጆች ተቀጠሩ፣በርካታ የምግብ ዝርዝር የያዙ ሜኖዎች በየጠጴዛው ላይ ተደርድረው ተመጋቢ ይጠብቁ ጀመር…

ዝር ያለ ሰው አልነበረም፡፡

ምግብ ቤቷ በተሻሻለ መልኩ ሥራ መጀመሯን  ደጋግመውአሳወቁ ፡፡

ጥቂት ደንበኞች መጡ፡፡

ምግብ አዘዙ ፣አቀራረቡ ላይ ለውጥ አለ፣ምጣኔውም እንደበፊቱ አይደለም፣ ጣዕሙም ትንሽ ተቀይሯል፣ ዋጋምው ጨምሯል፣ተመግበው ወጡ ተመልሰው ግን አልመጡም፡፡

አልፎ አልፎ አዳዲስ ደንበኞች ብቅ ቢሉም ያን ያህል አጥጋቢ እንቅስቃሴ ሊፈጠር አልቻለም፡፡ ለምን ይሆን?

ምግብ ቤቷ ያረገችው ማሻሻያ ሁሉ በራሱ ሚደነቅ ቢሆንም የደንበኞቿን ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ አልነበረም፡፡

በሂደትም ተዘግቶ ህንፃው ለቢሮነት ተከራየ፡፡

ተመጋቢው ከያለበት እየተጠራራ ወደዛች ምግብ ቤት ይተም የነበረው ለምንድነው?

በአካባቢው ያለ አብዛኛው ተጠቃሚ ቅድሚያ  ለዋጋው ሁኔታ የሚሰጥ  በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የንዕህና፣የምቾት፣ የዘመናዊነት ጥቅም ሳይገባቸው ቀርቶ አይደለም ፡፡

ሰዎቹ ያችን አነስተኛ ምግብ ቤት እንዲመርጡ የሚያስገድዳቸው በቂ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ነበራቸው፡፡

የማንኛውም ቢዝነስ ስኬታማነት፣ የሰዎችን ፍላጎት መገንዘብና ትክክለኛ መፍትሄ በማቅረብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዘህ፡-

የት መስራት ልጀምር ?

‹‹ በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ውስጥ  ችግሮችን እየተጋፈጡ ለማደግ መጣጣር፡፡ ወይም የወደፊቱን ጊዜ አጨልመው እያሰቡ ካሉበት ሳይነቃነቁ፣ ችግሮች በቀላሉ እንዲያጠፉን መጠበቅ ›› ብዙውን ጊዜ ከነዚህ ሁለት ምርጫዎች አንዱን እንድንመርጥ እንገደዳለን፡፡

ለስኬት በምታደርገው ጉዞ ላይ በርካታ ውጣውረዶች ሊያጋጥሙህ  እንደሚችሉ አይካድም፡፡

ውስብስብ ችግሮችን ሁሉ መተንተን ባይቻልም፣ በየትኛውም ሀገር የሚገኝ ጀማሪ ስራ ፈጣሪን

የሚፈታተኑ ፣  የት ይደርሳል  የተባለ ታታሪን አደናቅፈው የሚያስቀሩ 4 ታዋቂ መሰናክሎች አሉ፡፡

የአንድን ችግር ምክንያት ማወቅ የመፍትሄውን 50% እንደማግኘት ነውና  በየትኛውም ቦታ እየተከስቱ

ሊያሰናክሉህ ስለሚችሉ ለምን ተዘጋጅተህ አትጠብቃቸውም?

 መቼ ነው መጀመር ያለብኝ?

በስራው ዓለም  ከሚያስፈልጉ ጥሬ ሀብቶች ሁሉ የጊዜን ያህል ውድ ዋጋ ያለው ምንም ነገር የለም፡፡ ስኬታማነትህ በጊዜ አጠቃቀምህ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ሁሉም ነገር በጊዜ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ እንደመሆኑ መጠን በየትኛው ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብህ ጠንቅቀህ ልትረዳ ይገባል፡፡

ጆን ማክስዌል የተባለው ታዋቂ የአመራር መፃህፍት ደራሲ ይህን ሀቅ እንዲህ ያስቀምጠዋል፡-

ትክክለኛ ባልሆነ ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ብትወስን ተቀባይነት ታጣለህ፡፡

ትክክለኛ ባልሆነ ጊዜ የተሳሳተ ውሳኔ ብትወስን ውድቀትን ትቀምሳለህ፡፡

በትክለኛው ጊዜ የተሳሳተ ውሳኔ ብትወስን ስህተትን ትሰራለህ ፡፡

በትክክለኛው ጊዜ ትክክለኛ ውሳኔ ብትወስን ስኬታማ ትሆናለህ፡፡

ይለናል፡፡ልትሰራው ያሰብከውን ስራ ከጊዜ አኳያ ገምግም፡፡ አጣዳፊ  የሆነውን አስቀድም፡፡ አጣዳፊ ያልሆኑትን አስከትል፡፡ጠቃሚውን ጠቃሚ ካልነው ለይና በቅደም ተከተል ተግብር፡፡ስለዚህ በቅድሚያ ለምታከናውነው ነገር ሁሉ ጥሩ ዕቅድ አውጣ፡፡

ዕቅድህ በጎ እምነት ይፈጥልሃል፡፡

በጎ እምነትህ፣ቀና አመለካከትን ይፈጥርልሃል፡፡

ቀናው አመለካከትህ ፣ ተነሳሽነትን ይፈጥርብሃል፡፡

ተነሳሽነትህ ፣ጠንካራ ድርጊት ውስጥ ያስገባሃል፡፡

ድርጊትህ፣መልሶ ከፍተኛ ተነሳሽነት ይፈጥርብሃል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ ‹‹መቼ ›› ‹‹ምን›› እንደምትሰራ በቀላሉ ግልፅ ይሆንልሃል….

እንዴት ልስራው?

እንዴት ልስራው? የሚለው ጥያቄ በብዙ መልኩ የሚውጠነጠነው እዚህ ክፍል ነው፡፡አስተዳደሩን እንዴት ባዋቅረው ነው ቀልጣፋና ውጤታማ አሰራር በድርጅቴ ውስጥ ሚሰፍነው? ባለሙያዎቼ የቴክኒክ ስራቸውን እንዴት ቢያከናውኑት ነው የተሻለና ጥራት ያለው ምርት ወይም አገልግሎት ማቅረብ የምንችለው? የሚሉት ጥያቄዎች እዚህ ይነሳሉ፡፡

ማንኛውም ሥራ የራሱ የሆነ የአሠራር ዘዴ እንዳለው ሁሉ ያው ስራ በብዙ መንገዶችም ሊከናወን ይችላል፡፡ የወቅቱ ሁኔታ፣የመስሪያ መሳሪያው ሁኔታ፣የሰራተኛው ልምድ፣ ዕውቀትና የክህሎት ደረጃ፣ ሊገኝ የታሰበው ውጤት፣ ሥራው በተለያ መልኩ እንዲሰራ የሚያደርጉ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡

አንድ ስራ በብዙ መንገድ ሊከናወን ይችላል ሲባል፣ሁሉም የአሰራር ስልቶች አንድ ዓይነት ውጤት ያስገኛሉ ማለት እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ተጨባጩን  ሁኔታ መሰረት አድርጎ እንዴት ቢሰራ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል የሚያስረዳ የአሰራር ስልት መንደፍ ራሱን የቻለ ስራ ነው፡፡

በሙከራ የሚገኝ የአሰራር ስልት አለ፡፡በተለምዶ የተወረሰ የአሰራር ስልት አለ፡፡ቀስ በቀስ እየተሻሻለ የሚመጣ የአሰራር ስልት አለ ፡፡

አስቀድሞ በማጥናት ለስራው የሚመጥን የአሰራር ዲዛይን ማውጣትን የመሰለ ምርጥ ስልት ያለ አይመስለኝም፡፡

ምክንያቱም በፍጥነት ከሚለዋወጡ የገበያ ሁኔታዎች ፣ከተወዳዳሪዎች እንቅስቃሴ፣ከደንበኞች ፍላጎት  ጋር በአስተማማኝ ሁኔታ ተጣጥሞ ሊጓዝ የሚችለው ይህ በጥናት ላይ ተመስርቶ ዲዛይን የሚደረግ የአሰራር ስልት ነውና፡፡

እርግጥ ነው የቀሩት የአሰራር ስልቶችም የራሳቸው የሆነ ጠንካራ ጎን ይኖራቸዋል፡፡ያም ሆኖ በጥናት ላይ ተመስርቶ ዲዛይን የሚደረገው የአሰራር ስልት የተሻለ ውጤት ያስገኛል፡፡ምክንያቱም የአሰራር ስልቱ ላይ መጠበብ ያስፈለገበት ወንኛ  ዓላማም  የተሻለ ውጤት ማስገኘት ነውና፡፡

‹‹አንድ ዛፍ ለመቁረጥ የአንድ ሰዓት ጊዜ ቢሰጥህ፣ አርባ አምስት ደቂቃውን መጥረቢያህን ለመሳል ተጠቀምበት›› የሚለውን   አባባል እዚህ ላይ መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »