የራስዎን ሥራ ያስፋፉ

የራስዎን ሥራ ያስፋፉ

የንግድ ሥራን ማስፋፋት

የንግድ ሥራ ድርጅቶች አንዴ ከተቋቋሙ በኋላ ባሉበት ሁኔታ የንግድ ሥራቸው የመቀጠል እድል የላቸውም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የውድድር መኖር ነው፡፡ ደንበኞች የሚፈልጉትን ምርት የራሳቸው መመዘኛዎችን በማውጣት የበለጠ ፍላጎታቸውን ሊያሟላ የሚችል ምርት የያዘውን ድርጅት እንደሚመርጡ ግልጽ ነው፡፡ የምናመርተው ምርት በደንበኞች ዘንድ ተፈላጊ እንዲሆን የደንበኞችን ፍላጎት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የደንበኞች ፍላጎት ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ይህንን ተለዋዋጭ የሆነውን የደንበኞችን ባህሪ ተከትሎ ፍላጎታቸውን ለማሟላት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና አሰራሮችን እንዲሁም አዳዲስ አገልግሎቶችንና አቀራረቦችን ተከታታይ በሆነ ሁኔታ መፍጠርና ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡

አዳዲስ ቴክኖሎዷዎችንና አሰራሮችን ለማመንጨትም ይሁን የተፈጠሩ ቴክኖሎጂዎችን ተቀብሎ ተጠቃሚ ለመሆን የድርጅቱ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል፡፡

የንግድ ድርጅቶች ራሳቸውን የወቅቱ ገበያ ከሚፈልገው ሁኔታ ውጭ በሆነ መንገድ ገበያው ውስጥ መቆየት አይችሉም፡፡ ስለዚህ ሁል ጊዜም ራሳቸውን ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም በየጊዜው የሚፈጠሩ መልካም አጋጣሚዎችን በተገቢው መጠቀም የንግድ ሥራቸውን ማስፋፋትና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

የንግድ ሥራ እድገት ሲባል በብዙ መልኩ ሊገለጽ የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ የንግድ ሥራችንን ለማሳደግ ከሚከተሉት በአንዱ ወይም ሁሉንም ስትራቴጂዎች በአንድ ልንጠቀም እንችላለን፡፡ እነዚህ ስትራቴጂዎችም፡-

 • የገበያ ድርሻ /Market Share
 • የሽያጭ መጠን /Sales
 • የትርፍ መጠን /Profit
 • የሰው ሃይል /Staff numbers
 • ተርን ኦቨር /Tumover ማሳደግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

                ምርትና ገበያን ማሳደግ /Product-Market growth/

 • በገበያው ውስጥ ለመቆየት /Surivival/ ፡- የገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት አንድ የንግድ ድርጅት ራሱን በየጊዜው የሚያሳድግና የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ምርቱን ማሻሻልና ማሳደግ ይኖርበታል፡፡ የሚያመርተው ምርት ሁልጊዜ የደንበኞቹን ፍላጎት መሰረት አድርጎ መሻሻሎችን የማያደርግና ገበያውንም ለማሳደግ የማይፈልግ የንግድ ሰው በገበያው ውስጥ ረጅም ጊዜ ሊቆይ አይችልም፡፡
 • ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም /Economics of Sealse/፡- በትልቅ አቅም የሚመረት ምርት በአነስተኛ ካፒታል ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በላቀ ደረጃ ሀብትን በቁጠባ ለመጠቀም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በቀን አስር ካርቶን ሳሙና የሚያመርት ድርጅትና በቀን ሃምሣ ካርቶን የሚያመርት ድርጅት በምርት ደረጃ ልዩነታቸው ሰፊ ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱ ድርጅቶች የሚጠቀሙት የሰው ሃይል፣ ለአስተዳደራዊ ወጭዎች የሚያዎጡት እና የመሳሰሉትን ብንመለከት ብዙም የተራራቀ አይሆንም፡፡ ይህም ድርጅቱን በገበያው ውስጥ በቀላሉ ተወዳዳሪ እንዲሆን አቅም ይፈጥርለታል፡፡ የመግዛትና የመደራደር አቅማቸውንም ያየን እንደሆነ በምርት ግብዓት ግዥ ወቅት እነዚህ ሁለቱ ድርጅቶች እኩል የመደራደር አቅም የላቸውም፡፡

ከሁለቱ የተሻለ የመደራደር አቅም ያለው በቀን ሃምሳ ካርቶን ሳሙና የሚያመርተው ሲሆን ግብዓት አቅራቢ ተቋማት ለማንኛውም ደንበኛ ከሚሸጡበት በተወሰነ ደረጃ የዋጋ ቅናሽ በማግኘት ተጠቃሚ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡

 • የገበያው መለጠጥ /Expansiion of market/፡- በጊዜ ሂደት የህዝቡ ቁጥር መጨመር ወይም የደንበኞች ገቢ መጠን ማደግ አና የመሳሰሉት ክስተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ክስተቶች በገበያው ውስጥ ያለውን የሸቀጦችና አገልግሎቶች ፍላጎት ያሳድጋል፡፡ ፍላጎት ሊያድግ ደግሞ የምርት እጥረት እና የዋጋ መናርን ስለሚፈጥር አምራቾች ብዙ በማምረት ያለውን ገበያ እንዲጠቀሙ ያበረታታቸዋል፡፡
 • የባለሃብቶች ፍላጎት /Owners Mandate/፡– የንግድ ድርጅት ባለሃብቶች ከንግዱ የሚገኘውን ትርፍ ወይም ድርጅቱ ለህብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን የላቀ አገልግሎት በመረዳት ድርጅታቸው እንዲያድግና እንዲስፋፋ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ ሌሎች እስካሁን የተመለከትናቸውና ቀጥሎ የምንመለከታቸው ምክንያቶች ቢኖሩም የድርጅቱ ባለቤቶች ፍላጎት ካላሳዩ የድርጅቱ ምርትና ገበያ ማሳደግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ምክንያቶች አንዳሉ ሆነው የባለሃብቶች ፍላጎትም ከፍተኛ ሚና ያለው እንደሆነ እንረዳለን፡፡
 • ቴክኖሎጂ /Technology/፡- አንዳንድ ድርጅቶች ምርትና ገበያቸውን ለማሳደግ የሚጥሩት በየጊዜው የሚፈጠሩትን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለመጠቀም ነው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም የገንዘብ አቅም ወሳኝነት አለው፡፡ እነዚህን ቴክኖሎጂዎች አለመጠቀም ደግሞ በተለይ በዚህ ዘመን በገበያው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ አያስችለንም፡፡ እንዲያውም አዳዲስ ግኝቶችን ለመፍጠርና ጥናቶችንም ለማካሄድ ብዙ ገንዘብ የሚያወጡ ድርጅቶች በመስፋፋት ላይ ናቸው፡፡
 • ግርማ ሞገስ ለማግኘት/Prestige and Power/፡- አንዳንድ ግለሰቦች በህብረተሰቡ ውስጥ ባላዠው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶች ሁሉ ክብር ለማግኘት፣ በልጠው ለመታየትና ተሰሚነትን ለማግኝት ወዘተ. ከመፈለጋቸው አንፃር የንግድ ድርጅታቸው እንዲያድግ ጠረት ያደርጋሉ፡፡
 • የመንግስት ፖሊሲ /Government Policy/:– መንግስት በሚያከናውናቸው አንዳንድ ኢኮኖሚያዊ አንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ተጠቃሚ ለመሆን የንግድ ድርጅቶች የተሻለ አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ የተሻለ አቅም ያላቸው ድርጅቶች የመንግስት መመዘኛዎች በማሟላት ፈቃድ የማግኘትጀ፣ የኮታ ተጠቃሚ የመሆን እና የመሳሰሉትን እድሎች ማግኘት ይችላሉ፡፡ እነዚህን እድሎች ለመጠቀም ሲሉ የድርጅታቸውን አቅም ለማሳደግ ጥረት የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡
 • ራስን ለመቻል /Self – Suficiency/:- ድርጅቶች በራሳቸው አቅም የማያከናውኗቸውን ተግባራት በሌሎች አካላት የተዘጋጁትን በመግዛት አልያም ከፍለው በማሰራት ወዘተ. ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ሁሌ አዋጪ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን የሌለው የእንጨት ሥራ ድርጅት ማሽኑን ለመግዛት አስከሚችል ድረስ ማሽኑ ካላቸው ተቋማት ዘንድ በመሄድ በክፍያ በማሰራት ደንበኞቹን ሊያገለግል ይችላል፡፡ ነገር ግን የራሱ የተሟላ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ቢኖረው የበለጠ ደንበኞቹን ማገልገል ይችል ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ ድርጅት ጠንክሮ በመሥራት የራሱን ድርጅት በተሻለ ሊያደራጅ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ጥሬ ዕቃዎችን ለማግኘት ሁሌ የሚቸገር አንድ የንግድ ድርጅት ራሱን በማሳደግ የጥሬ ዕቃውን ምንጭ በቁጥጥሩ ስር ሊያደርገው ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን የንግድ ድርጅቱ አቅሙን መገንባት ከቻለ ብቻ ነው፡፡

የድርጅቱ እድገት ሲታሰብ ምርትንና ገበያን የማሳደግ ስትራቴጂ

ብዙ ድርጅቶች የወደፊት የድርጅታቸው ህልውና ላይ ሲመክሩ ገቢንና ትርፍን ማሳደግ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ነገር ግን የድርጅት እድገት ሲታሰብ ምርትንና ገበያን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረጉ የበለጠ ውጤታማ እንድንሆን ያደርገናል፡፡ በቅድሚያ ድርጅቱ አሁን እያመረተ ወይም እያቀረበ ያለውን ምርት በሚገባ ማጤን ያስፈልጋለ፡፡ ከዚያም አሁን ባለበት ሁኔታ ይቀጥል? ወይስ አሁን ያለንበት ሁኔታ ይሻሻል? ወይም ደግሞ እንደ አዲስ እናደራጀው እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች አንስተን ጥናት ላይ በመመስረት ውሳኔያችንን በአንዱ ላይ እናሳርፋለን፡፡ ይህንን ስናደርግ ቀጥለን የምናያቸው ምርትና ገበያን የማሳደግ ስትራቴጂዎች ሊያግዙን ይችላሉ፡፡

 • አሁን ያሉት ደንበኞች የበለጠ እንዲገዙን ማድረግ /Market Penetration/:- ይህ ስትራቴጂ አሁን ያለው ምርት ሳይቀየር በብዛት በማምረት አሁን ላሉ ደንበኞች ፍላጎታቸውን በማሳደግ የበለጠ እንዲገዙን የማድረግ ስልት ወይም ስትራቴጂ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ምርቱን በስፋት በማስተዋወቅ፣ ምርትን የሚታይ ቦታ በማስቀመጥ፣ ምርትን በተለያየ መጠን በማሸግ፣ የአቅርቦት ቦታዎችን በማስፋፋት ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡
 • የገበያ እድገት ስትራቴጂ/Market Development/:– ይህ ስትራቴጂ አሁን ያለውን ምርት ለሌሎች አዳዲስ ደንበኞች የማቅረብና አዳዲስ ደንበኞችን የማፍራት ስትራቴጂ ነው፡ ይህንን ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችን ለንጠቀም እንችላለን፡፡ ከእነዚህም መካከል አዳዲስ ደንበኞች ዘንድ ለመድረስ ዋጋን ዝቅ አድርጎ መግባት፣ ስለምርቱ ጥራትና አጠቃቀም ትምህርት መስጠት፣ ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ለምሳሌ፡- አዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረ አንድ የልብስ ስፌት ድርጅት ቀደም ሲል ያቀርባቸው የነበሩ ምርቶችን በክልሎች ሊያስተዋውቅ ይችላል፡፡ ይህንንም ሲያደርግ አዲስ አበባ ላይ ያለውን ስምና ዝና ሊጠቀም ይችላል፡፡ ወደ ገበያው ሲገባ ሰፊ የማስተዋወቅና ለተወሰኑ ወራት የዋጋ ቅናሽ እና ሌሎች ስልቶችን ተግበራዊ ሊያደርግ ይችላል፡፡

 • የምርት/አገልግሎት እድገት ስትራቴጂ /Product development/:- ይህ ስትራቴጂ አዳዲስ ምርቶች/አገልግሎቶችን ወይም ነባር ምርቶች/ አገልግሎቶችን አሻሽሎ በአዲስ መልክ ወይም በአዲስ አቀራረብ ለነባር ደንበኞች የማቅረብ ስትራቴጂ ነው፡፡

አሁን በሀገራችን ያሉት የተለያዩ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች እያቀረቧቸው ያሉት አዳዲስ መርቶች እና ነባር ምርቶችን በተለያየ መጠንና አስተሻሸግ ማቅረባቸው ለዚህ አይነቱ ስትራቴጂ ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው፡፡

 • አዲስ ምርት፣ አዲስ ገበያ ስትራቴጂ /Diversification/ ፡-

ይህ ስትራቴጂ አዲስ ምርት ይዞ ለአዳዲስ ደንበኞች የማቅረብና የማስተዋወቅ ስትራቴጂ ሲሆን ከሌሎች ስትራቴጂዎች ሁሉ እጅግ አደገኛው ስትራቴጂ በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ድርጅቱ ከዚህ በፊት አምርቶ የማያውቀውን ወይም አቅርቦ የማያውቀውን አገልግሎት ባህሪያቸውን የማያውቃቸው አዳዲስ ደንበኞች ዘንድ ለማድረስ የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ነው፡፡

ለምሳሌ በሆቴል ንግድ የሚታወቅ አንድ ነባር ድርጅት ከተወሰኑ አመታት በኋላ ከሆቴል ንግዱ ጎን ለጎን የህፃናት ማቆያ ወይም አፀደ ህፃናት ለመክፈት ቢያስብ እስካሁን ያካበተው ልምድ፣ ያሉት ደንበኞች፣ የሚያስተዳድራቸው ሰራተኞች ወዘተ. የሆቴል እንጂ ከህፃናት ጋር ግንኙነት የሌለው በመሆኑ ወደ ገበያው ሲገባ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡

ገበያ ሁሌም ተለዋዋጭ ነው፡፡ የንግድ ድርጅቶች ደግሞ የገበያውን ተለዋዋጭነት ተከትሎ ራሳቸው ከሁኔታዎች ጋር በማስማማት ብቁና ተወዳዳሪ ሆነው መገኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸውን ስትራቴጂዎች በተገቢው ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል የንግድ ድርጅቶች ራሳቸውን ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር እንዲጓዙ እና ምርትና ገበያን በማሳደግ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋልዋል፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »