የላቀ አመራር ችሎታ ባለቤት

የላቀ አመራር ችሎታ ባለቤት

ተመዝግቦ የተቀመጠ ነገር ባለመኖሩ መቼ እንደተወለደ ቀኑንና ዓመተ ምህርቱን እንኳን እሱ ወላጆቹም ጭምር በትክክል ለይተው አያውቁትም፡፡ ምክነያት ቢባል ደግሞ ከወላጆቹ አንዳቸውም ማንበብና መፃፍ አይችሉም ነበርና ነው፡፡ እንዲያውም በኋላኛው ዘመን ደርግ አናትና አባቱን ቀለም ለማስለየት፣ ፊደል ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ እና ስማቸውን እንኳ ማንበብና መፃፍ ሳይችሉ ነበር ያለፉት፡፡ ይሁንና የወላጆቹን ግምትና ሌሎች ሊያውቁት ይችላሉ የተባሉ ሰዎችን ጠይቆ ጣሊያን በገባ በሁለተኛው አመት ላይ ነኁወ የተወለድከው ስለተባለ በዚህም፣ በዚያም ተብሎ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 6 ቀን 1930 እንደ ኤውሮጳ ደግሞ ጃንዋሪ 14 ቀን 1938 ዓ.ም የልደት ቀኑ ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡
የተወለደው ትምህርት ከዲቁናና ከቅስና በላይ በማይኬድበት፣ ከገበሬ ህዝብ መሀል መርሀቤቴ ውስጥ ባለች ማቁር ሚካኤል በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ ከመንደሩ ልጆች ዕጣ ፈንታ ባልተለየ ሁኔታ የከብት ጭራ በመከተል ነው የልኁደነት ሕይወቱን የጀመረው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ወላጅ እናቱ ታማሚ ስለነበሩ ከመርሀቤቴ ደብረሊባኖስ ገዳም በታች ወደሚገኘው ወደ ኮራ ገዳም ተክለሃይማኖት የሚባል ፈዋሽ ጠበል ስለነበር ይጠመቁ ተብሎ ወደዚያ ይላካሉ፡፡ የዕምነት ጉዳይ ሆነና ጤንነታቸው መሻሻል ሲያሳይ፣ “ከጤናዬ የሚብስ ምን ኖሮ? እዚሁ ተቀምጨ ገዳሙን አገለግላለሁ” ብለው በመወሰናቸው ልጁም በለስ ቀንቶት እዚያው ገዳሙ ውስጥ እየኖረ በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ጊቢ ትምህርቱን ጀመረ፡፡
ወላጆቹ ውርዴ ስለነበሩ ከአምስት ልጆች ውስጥ እንደ ዕድል የተረፈው እሱ ብቻ ነበር፡፡ በሀገር ቤት እምነት መሰረት እንደሌሎቹ ልጆች እሱንም ሞት ጠልፎ እንዳይወስድባቸው በማሰብ ሞትን ለማታለል እንደ ደንቡ በአርባ ቀን ሳይሆን ቆይቶ ሰው መለየት ሲጀመር ነው እንኮኮ ብለው ለብቃ ኢየሱስ ወስደው ክርስትና ያስነሱት፡፡ ያኔ ታዲያ “ይሄ የኢየሱስ ወርቅ ነው፣ የኢየሱስ ሀብት ነው” ሲሉ በምክንያቱ ስም አወጡለት፡፡
ለመሆኑ ኢየሱስወርቅ ዛፉ ማነው?… ምን የሚወራ ታሪክ አለው? ስኬቱና ከስኬቱ በስተጀርባ ያለው ምስጢር ምን ይሆን?…
ድንቅ ለሆነ ታሪኩን የማስታወስ ችሎታው፣ አተራረኩና መረጃ አያያዙ ምስጋናዬን እያቀረበኩ ታሪኩን እነሆ በአንደበቱ…
  
ልጅነት
በልጅነቴ ፈጣን፣ ኩራተኛና እልኸኛ እንደነበርኩ አልረሳውም፡፡ አንድ ሰው የማይጥም ነገር ተናግሮኝ እንዲያው ዝም ብዬ ያለፍኩት ቀን ሞቴ ነበረች፡፡ እናቴ ታማሚ በመሆኗ ብዙ ችግር ብንቀምስም፣ የፈታይ እየፈተለች፣ እህል በሚወቃበት አውድማ ሄዳ እህል እየለመነች ብታሳድገኝም፣ ተንኮልና ትእቢት አልወቅ እንጂ ራሴን የላስደፍር ኩሩ ነበርኩ፡፡ አንድ ጊዜ ትዝ ይለኛል ከአጎቴ ልጅ ጋር የየራሳችንን ከብቶች እየጠበቅን ሳለን የእኔን ላም ወደዛ ገፍቶ የሱን ከብቶች ሲያጠጣ ብው ብዬ በክትክታ ዱላ ደረቱ ላይ መትቼው ተዘረረ፡፡ መቼም ያኔ ያለማወቅም አለ… ብቻ እግዜር አተረፈው፡፡ እናቴ ጥጥ ስትፈትል ጥፍጥሬውን ፈልቅቃ ካወጣች በኋላ ያ ጥፍጥሬ ተጨቅጭቆ የሚወጣው ፈሳሽ ተንተክትኮ ሙቅ ነው የምንለው አንዱ ትልቁ ምግቤ እሱ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ታዲያ ስኳር የሚባል ነገር አናውቅም ነበር፡፡ ኧረ መኖሩንም ያወቅኩት አዲስ አበባ መጥቼ ነው፡፡
እናትና አባቴ ተለያይተው የመኖራቸው ምስጢር በጊዜው ባይገባኝም እናቴ ከጊዜ በኋላ እዛው ቅርብ ዜጋመል ማርያም ለሚኖር አንድ ደብተራ ልጅ መውለዷ ይከነክነኝና ያስከፋኝ ነበር፡፡ እኔ ከአባቴ ጋር አብረው እንዲሩ ነበር ምኞቼ፡፡ ለካ አባቴ ደሴ ሄዶ የራሱን ኑሮ መስርቶ ኖሯል፡፡ መቼስ እህል ውሃ ካለቀ ምን ይደረጋል?! ኮራ ገዳም ሀሁ ብዬ ጀምሬ በስድስት ወር ዳዊት መድገሜ፣ የቀለም ትምህርት ደግሞ ማታ እያጠናሁ ውዳሴ ማርያሙንም ሌላውንም … በፍጥነት መያዜ መምህሮቼን ያስደንቃቸው ስለነበር “መዝገቡ፣ የቀለም ቀንድ” የሚል ቅጽል ስሞች አውጥተውልኝ ነበር፡፡ ከብት ከመጠበቅ፣ ከመማር የዘለለ ነገር ስላልነበረኝ ችግራችንን ለማሸነፍ እናቴን የምረዳበት እድል አልነበረኝም፡፡ ቆቅ ማጥመድ እወድ ስለነበር ዜጋመል ማርያም አስቀድሼ ስመጣ ወጥመዴ ትልቅ ቆቅ ይዞልኝ አገኘሁና ደስ አለኝ፡፡ በእውነቱ አንበሳና ነብር እንደገደለ ጀግና ነበር የተጎማለልኩት፡፡ ለነገሩ ቆቁ ትልቅ ነበር፡፡ ወዲያውም ለናቴ ወስጄ ሰጠሁና “ጓደኞቼን ስለምጠራ ቆቁ በደንብ ይሰራልኝ” ብዬ አስራ ሁለት ጓደኞቼን ጠርቼ ከተፍ አልኩ፡፡ እናቴ ይሄን ነገር እያነሳች “ለቆቅ ግብዣ ይኸን ያህል ሰው የምትጠራው ፍሪዳ የጣልክ መሰለህ?” በማለት ትቀልድብኝ ነበር፡፡
አባቴ ከብዙ ጊዜ በኋላ ከደሴ ወደ መርሀቤቴ ሲመጣ በዜጋመል ማርያም በኩል አድርጎ መጣና ሁኔታዬን አይቶ ዲቁና መቀበል እንዳለብኝ ወስኖ እስከ ደብረሊባኖስ መታጠፊያ ውሻ ገደል ድረስ በእግሬ ይዞኝ ከሄደ በኋላ ውሻ ገደልጋ ስንደርስ ድምጻቸው የሚያስፈራ፣ እርጀት ያሉ መኪኖችን ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ፡፡ አባቴም ወደ አንዷ ደካማ መኪና ሲያስገባኝ ኡኡታዬን ለቀቅኩትና አምልጩ ለመጥፋት ሞከርኩ፡፡ እዚህ ነገር ውስጥ እንዴት አገባለሁ ብዬ አስቸገርኩ፡፡ ትዝ ይሉኛል አንዲት እናት እንዳቀፉኝ አልቅሼ፣ አልቅሼ እንቅልፍ ጥሎኝ ኖሮ አዲስ አበባ መግባቴን ነበር የማስታውሰው፡፡ ያም ሆኖ ግን አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ዲቁናዬን ወሰድኩና ግራም፣ ቀኝም ሳልወላውል ተመልሼ ወደ ኮራ ገዳም ሄድኩ፡፡ ለተወሰነ ጊዜም ኮራ ገዳም ከቀደስኩ በኋላ እኔና እናቴ ዜጋመል ማርያም ገባን፡፡
ሀገሩ ከገባሁ በኋላ “እንግዲህ ደቁነህ ከመጣህማ እዚሁ ትቀድሳለህ፣ በወር ስድስት ሽልንግ እንከፍልሃለን አሉኝ፡፡ በሱ ተስማምቼ በአንድ ወገን ትምህርቴን እየተማርኩ (ድጓ ድረስ ደርሼ ነበር) መቀደሴን ተያያዤው ሳለሁ የሰራሁበትን ስጡኝ ብል እምቢ አሉኝ፡፡
በእውነት እናቴም በጣም አዘነች፡፡
እኔም በዱላም ተማትቾ መብቴን የማላስከብርበት በመሆኑ እጅግ ሀዘን እንዳገባኝ፣ ስንታየሁ የሚባል የዜጋመል ዲያቆን ከኔ ትንሽ ነፍስ አወቅ የነበረ ልጅ ቀድሞ አዲስ አበባ ደርሶ የተመለሰ ነበርና እሱም አንድ ቀን “እንዳው እኮ አዲስ አበባ ብንሄድ በወር 100 ሽልንግ ድረስ መቀጠር እንችላለን ይለኛል፡፡ እኔ በዲቁናው ጥሩ ድምጽ ስለነበረኝ፣ እንግዳ መጣ፣ ቄስ መጣ የተባለ እንደሁ እንድቀድስ ተፈልጌ ነው የምጠራው፡፡ ለምን አንሄድም ታዲያ? አልኩት፡፡
እሱ ከመሀል ከተማው ዘመድ ስለነበረው ይቸግረናልም ብለን አላሰብን፡፡ እሱ የዚያቦታ ተወላጅ እና ከቆላ መሬቱ ከሚተክለው ጌሾም፣ ሙዝም ይነገድ ስለነበር፣ ትንሽ ብር ቋጥሮ በእግራችን ከፍቼ ከተማ ተነስተን ሁለት ቀን ከተጓዝን በኋላ በሁለተኛው ቀን ማታ እንጦጦ የሚሊኒክ ማርያም ጋ ደረስን፡፡
ወደታች አዲስ አበባን ስናያት መብራቱ ተብለጭልጦ አይኔን ሲማርከው “ገነት ማለት ይሄ አይደለም ወይ?” ብዬ አሰብኩና ከልጁ ጋር ተያይዘን ደጀ ሰላሙ ሳር ላይ ተኝተን አደርን፡፡
ማንተማሪያም ባዩ ሲየሱስወርቅ
በበነጋው ዶሮ ማነቂያ ያለች መጠጥ ቤት ያላት ዘመድ ጋ ሄድን፡፡ ለዲቁና አዲስ አበባ መጥቼ ወደያውኑ ተመልሼ በመሄዴ አዲስ አበባ ከተማን ሳላውቃት ቀርቼ ነበር፡፡ ለዶሮ ማነቂያ ቅርብ ወደ ሆነው አራዳ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ስሄድ የከተማው ዲያቆኖች ጨርሶ አያስጠጉም፡፡ ያቺኑ የደጀ ሰላሟን ጉርሻ ባገኝ ብሎ ነበር አልተሳካም፡፡ አብሮኝ ጠፍቶ የመጣው ስንታየሁ አዲስ አበባ ከአሁን ቀደም መጥቶ ይወቅ እንጂ ስለ ሥራ ማግኘት ጉዳይ ምንም የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን ቆይቶ ተረዳሁ፡፡
የስንታየሁ ዘመድ ቤት ማድቤት የመሰለ፣ ቀን ቡና የሚፈላበት ክፍል ውስጥ ነበር ሰሌን አንጥፈን የምንተኛው፡፡ ታዲያ አንድ ምሽት ያለችኝን አንድ ነጠላ፣ ረጅም ሱሪና እጀ ጠባብ ለብሼ ጋደም እንዳልኩ እንቅልፍ የወሰደኝ መስሏቸው ስንታየሁና ዘመዲቱ ሲነጋገሩ እሰማለሁ፡፡ ባለቤቲቱም “ያንተ አልበቃ ብሎህ እንዴት ጓደኛህን ይዘህ ትመጣለህ? አሁን እዚህ ምን ልትሆኑ ነው?” ትለዋለች፡፡ ይህን በሰማሁ በበነጋው እንደወጣሁ ሳልመለስ በዛው ቀረሁ፡፡ ያን ጊዜ እንዳሁኑ ብዙ ለማኝ፣ ብዙ የሰው መጨናነቅ ስላልነበር በየቦታው እየዞርኩ፣ መኪናም እየተጠጋሁ መለመን ጀመርኩ፡፡
ስለምን ከዋልኩ በኋላ ማታ አራዳ ጊዮርጊስ ደረጃዋ ላይ ሄጄ ከሌሎች የኒቢጤዎች ጋር ስንከባለል አድር ጀመር፡፡
የት መሄድ፣ ምን ማድረግ እንዳለብኝ በማላውቅበት ሁኔታ ውሰጥ እያለሁ አንድ ቀን ከሰዓት በኋለ አንድ ጠጅ ቤት በራፍ ላይ ቆሜ፡፡
“ምንተስለማርያም፣ ስለቸሩ እግዚአብሔር ብለው?” እያልኩ ስለምን በሩ ወገን ብሎ ተከፈተ፡፡ አድሩስ ሲጨስ፣ ቡና ከነረከቦቱ አየሁ፡፡ እዛ የተቀመጡት ሴቶች “ግባ” አሉኝ፡፡ ከመሀከላቸው እመቤት የመሰሉት ሴት ከየት እንደመጣሁ ሲጠይቁኝ ዋሽቼ ዲቁና ልቀበል ከዜጋመል መጣሁ ብዬ የመጣሁበትን በዝርዝር አስረዳኋቸው፡፡ አዲስ አበባ የማውቀው ዘመድ እንዳለ ሲጠይቁኝ ዘቢደር የምትባል ኮማሪት ዘመድ እንዳለችኝ መስማቴንና ግን የት እንደምትኖር እንደማላውቅ ነገርኳቸው፡፡ ብርዝ ሰጥተውኝ እሷን እየጠጣሁ ሳወራቸው የሀገሬ ሰዎች ሆነው ተገኙና እዚያው እነሱ ጋ እንድኖር ጠየቁኝ፡፡ ያቺን ጣፋጭ ብርዝ ከቀመስኩ በኋላ እዚሁ ኑር ሲሉኝ ደስታዬ ወሰን ነበር ያጣው፡፡
በኋላ በዘመዶቻቸው አማካይነት የድሮ ሲኒማ ኢምፒር በታች ፖሊስ ጣቢያ ነበር እዛ ዘመዶቹ እንዲፈለጉለት ብለው ለፖሊስ ያስመዘግቡልኛል፡፡ ከትንሽ ጊዜም በኋላ መርሀቤቶችንማ መፈለግ ፍርድ ቤት ነው፡፡ ወይ በነፍስ ግዳይ ወይ በመሬት ተከሰውና ከሰው ሲጨቃጨቁ ይገኛሉ፡፡ ይባልና አራዳ ጊዮርጊስ አጠገብ ያለው ፍርድ ቤት እወሰዳለሁ፡፡ እዛም የኔ ጉዳይ ተነስቶ ጠፍቶ የመጣ ነው ሲል ፖሊስ ያስረዳል፡፡ “እነ ፊታውራሪ ገዝሙን ታውቃለህ?” ተባልኩ፡፡ ይሄን ስም አባቴ ሲያነሳ ሰምቼ አውቅ ስለነበር “አዎ” አልኩኝ፡፡ “እንግዲያውማ ወደ እሳቸው ጋ ይሂድ፣ የሳቸውን ስም ካወቀ ዝምድና ይኖር ይሆናል” አሉና ወደዛ ወተወሰድኩኝ፡፡ እዛ ስሄድ የዛፉ ልጅ መጣ ብለው ጉድ ተባለ፡፡ ለካ ከአባቴ ጋ ይተዋወቁ ኖሯል፡፡ በመጨረሻም ኮማሪቷ ዘመደ ዘቢደር መርካቶ እንዳለች ታውቆ ወደዛ ተወሰድኩ፡፡
ምንም እንኳን ዘቢደርጋ ስኖር ማሩና ብርዙ ሞልቶ ኑሮው ሁሉ ጥሬ ቢሆንም፣ ምን መሆን እንዳለብኝ እያሰብኩ እጨነቅ ነበር፡፡ “ወታደር ልሁን? ወይ ሲግናል የሚማሩ ዘመዶች ነበሩና አለባበሳቸው ስለሚማርከኝ ከነሱ ጋር ልግባ ይሆን?” እያልኩ ስጨነቅ አንድ እሁድ ጠዋት ቡና እየተፈላ እንዳለ እዛው ቁጭ ብዬ ሳፈጥ ጠጅ ቤቱ ካሉት ሠራተኞች አንዷ “ኢየሱስወርቅንማ እኔ አገባውና ኑሯችንን እዚህ እንመሰርታለን እንጂ አገር ቤት ምን ሊያረግ ይሄዳል? እያለች ስትል፣ ስለ እንደዚህ አይነቱ ቀልድ ለማገናዘብ የሚያስችል የእድሜ ብስለት አልነበረኝምና “ቱ! እንዴት አይነት ሰይጣን ነሽ? ዲቁናዬን ልታፈርሽብኝ?” ብዬ እውነት ይህን ነገር ልታደርገው እንዳሰበች ተሰምቶኝ ቡራ ከረዩ አልኩና በማግስቱ ከዘቢደር ቤት ተነስቼ ወጣሁ፡፡
በእግሬ ወደ እንጦጦ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ እንጦጦ ስደርስ አንድ ትንሽ መኪና አየሁና ለመንኩ፡፡ መቼም እድሜ ለአደስ አበባ ልመናውን እንደሁ ተክኜበታለሁ፡፡ ልመናዬ ተቀባይነት አገኘና መኪናው ጫንጮ ድረስ ሸኘኝ፡፡ ከዛም ደብረ ጽጌ የሚባል ቦታ ዘመዶች እንዳሉኝ አውቅ ስለነበር እዛ አድሬ ተስተናግጄ በማግስቱ ወደ ዜጋመል ተመለስኩ፡፡
የፊታውራሪ ገዝሙ ሰዎች ለአባቴ ወረቀት ጽፈው ይልካሉ፡፡ አባቴ ደሴ መብራት ኃይል ዘመበኛ ሆኖ ነበር የሚሰራው፡፡ ወረቀቷ ስትደርሰው ለሰው ያስነብባታል፡ መልእክቷም “ልጅህ አዲስ አበባ ገብቷል ከእንግዲህ እግር ካወጣ የትም ቀልጦ ይቀራል” የምትል ነበረች፡፡ አቤቴ ከሌላ የወለደው ልጅ አዲስ አበባ መጥቶ ሲያጣኝ ዜጋመል ማርያም ይመጣል፡፡ በቁመት ከእኔ አጠር የሚለው አባቴ (ለዛም ነው ዛፉ የተባለው) ሀይለኛና የሚፈራ ሰው ነበር፡፡ ያኔ በወር ስድስት ሽልንግ ተስማምቼ የቀደስኩበት ያልተከፈለ ገንዘቤን የስድስት ወር 36 ነጭ ሽልንግ አፍንጫቸውን ይዞ ተቀበለልኝና ይዞኝ ወደ ደሴ ሄድን፡፡
እየሱስወርቅ ጠንቋይ ነው
በአስር አመቴ ነው ደሴ ሄጄ መንግሥት ትምህርት ቤት የገባሁት፡፡ ኤቢሲ አላውቅ፣ አንድ ሁለት ሦስት እያሉ ቁጥር መጻፍ አልችል፡፡ ከዜሮ ክፍል እንድጀምር ተደረገ፡፡ ደግነቱ ቶሎ፣ ቶሎ የሚፈጥን ተማሪ በየተርሙ ነበር ከአንድ ክፍል ወደ ሌላው የሚዛወረው፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ አራተኛ ክፍል ደረስኩ፡፡ ከዚያም መምህር አካለ ወልድ ትምህርት ቤት ሁለት አመት ከተማርኩ በኋላ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስድኩና እንደአጋጣሚ ከኛ ትምህርት ቤት የመጀመሪያውና አንዱ ሆኜ ጥሩ ውጤት አምጥቼ እድሜዬ 14 በመሆኑ እድሜውም ይፈቅዳል ተብሎ ያኔ ጀነራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነበርና ወደዛ ተላኩ፡፡
ደሴ እያለሁ ጫማ የሚያደርጉ ልጆች ሳይ ጫማ ለማድረግ ፍላጎቱ ስለበረኝ መርፌ፣ መርፌ ቁልፍ፣ ምላጭ (የቤሳ ምላጭ) እየገዛሁ ያቺን በየገበያውና በተለያዩ ቦታዎች ቅዳሜና እሁድ፣ እየዞርኩ እየሸጥኩ የመጀመሪያ ሸራ ጫማዬን ገዛሁ፡፡ ያኔ የቀለም ፋውንቴን ፔን(ብእር) ሀገር ውስጥ በብዛት ይገባ ነበር፡፡ ብእሩ ወዲያው ነበር የሚበላሸው፡፡ እና እኔ የተሰባበረውን ሁሉ በአምስትም፣ በአስርም ሳንቲም እየገዛሁ አንዱን ለአንዱ እያገጣጠምኩ እሰራውና አስርም፣ አስራ አምስትም ሳንቲም እያተረፍኩ እሸጥ ነበር፡፡
ትዝ ይለኛል አንድ የደሴ ፖሊስ አዛዥ የሚስታቸው ወንድም የሆነ ዮሐንስ የሚባል ለእኔ ነፍስ ያወቀ ወጣት ነበር፡፡ እሱ ባለባበሱም፣ በትምህርቱም በሁኔታውም ከሌሎቻችን ከፍ ሰለሚል አንድ ቀን እንደሱ እሆናለሁ እያልኩ ነበር የማስበው፡፡ እና እሱና ሌሎች ሁለት ጓደኞቹ “ኢየሱስወርቅ ጠንቋይ ነው፡፡ አለበለዚያ እንዴት እኛን በትምህርት ይበልጠናል?” ይሉ ነበር፡፡ እኔ ያችን የቄስ ትምህርቷን በቃል የመሸምደድ ልምድ ስለነበረኝ ነገሮችን ቶሎ እጨብጣለሁ፡፡ ስለዚህ በክፍል ውስጥ ጎበዝ ስለነበርኩ እንደዚያ ስም ሰጡኝ፡፡ እኔም “መርፌ በጉንጩ አሳልፋለሁ” ብዬ በእውነትም ሳሳልፍ ደንግጠው ጠንቋይ መሆኔን አረጋግጠው አረፉት፡፡
ዊንጌት አዳሪ ት/ቤት ስገባ ኑሮዬም ሻል አለ፡፡ በሁለት አንሶላ መሀል ገብቶ መተኛትን ታደልኩ፡፡ ሰዎች በቂጣቸው ቁጭ የሚሉበት ሽንት ቤት ላይ እኔ ወጥቼ በእግሬ ቂጢጥ ብልበትም ለዘለቄታው ህይወቴ አመራርና ሁኔታ መሰረት የጣሉ ነገሮችን ሁሉ ቀስሚበት በሁሉም ዘርፍ በኳሱም፣ በፐብሊክ ስፒኪንጉም፣ በአሎሎና ጠጠር ውርወራውም፣ በእንግሊዝኛ ሊትሮቸሩም ብዙ ተሳትፎ እያደረግኩ ጥሩ ውጤት ይዤ ነበር የጨረስኩት፡፡ በተለይ ከ1-3 የሚወጡ ተማሪዎች ሽልማት ይሰጣቸው ስለነበር የአንድ ዓመት ተሸላሚ ሆኜ ከአልጋ ወራሹ ሽልማት ለመውሰድ የዊንጌትን ጥቁር ጃኬት፣ በግራና በቀኝ ቢጫ መስመር ያለችባትና ሰማያዊ ቁምጣ ሱሪ ለብሼ ጫማ ባይኖረኝም እግሬ ፎከታም እንዳይሆን በሳሙና በደንብ ታጥቤና በአረፋው ወልውዬ፣ በትሬንታ ኳትሮ መኪና ተጭነን ወደ ሽልማቱ ቦታ የሄድኩበትን ጊዜና አንዳንድ ጊዜ የሚያስተምሩን እንግሊዛዊ መምህራኖቻችን በምጽፈው ድርሰት ላይ “አንድ እንግሊዛዊ ይህን ቢመለከት በአንድ ኢትዮጵያዊ መሳፉን ፈጽሞ ሊያምን አይችልም” እያሉ የሚጽፉትን ሳስታውስ የዊንጌት ዘመኔን በጥሩ አስታውሰዋለሁ፡፡
የዊንጌት ትምህርቴን እንደጨረስኩ ጫማ፣ የምለብሰው ደህና ልብስና በአጠቃላይ የግል ጽዳቴን ለመጠበቅ እንኳን የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበረኝ ዩኒቨርስቲ መግባት አልቼልኩም ነበር፡፡
የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ደግሞ ቆንዶ ብሌዘር የነበራቸው፣ ግሬይ ሲሪ ከከረባት ጋር የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ እኔ ደግሞ ለእግሬ እንኳን ጫማና ንጽህናዬን ለመጠበቅ የተመቻቸ ሁኔታ የሌለኝ ነበርኩ፡፡ እንዲያውም ከዚያን በፊት አባቴ “በል እዚህ ከደረስክ አሁን ደግሞ እዚሁ አስራ አንደኛ ክፍል ላይ አቁምና አስተማሪነት አንድ አመት ተምረህ ታማሚ እናትህን እርዳ፡፡ እኔ እንደሆንኩ ከዚህ በኋላ ልረዳህ አልችልም” ብሎኝ እኔም “ግድ የለህም ከ11ኛ ክፍል አቋርጩ አንድ አመት አስተማሪነት ተምሬ ሥራ ከምፈልግ፣ 12ኛን ልጨርስና ብፈልግ ይሻላል” ብየው ነበር፡፡ አባቴ እሱ ባለው መንገድ ጨርሰን 11 ባውንድ በወር የሚያገኙትን ስለሚያውቅ ነበር እንዲያ ያለኝ፡፡ አሰራ ሁለቷን ከጨረስኩ በኋላ ግን ከላይ ባነሳሁዋቸው ምክንያቶች ዩኒቨርስቲ መግባት የማይታሰብ ነበርና ሥራ ማፈላለጉን ተያያዝኩት፡፡
ስራ ፍለጋ
መጀመሪያ ሥራ ፍለጋ የሄድኩት ትምህርት ሚኒስቴር ነበር፡፡ እዚያም ሰዎች “ኤርፎርስ (አየር ሀይል)የፀሐፊነት ሥራ ችሎታ ያለው ይፈልጋልና እዛ ሄደህ ለምን አታመለክትም?” አሉኝ፡፡ ኤርፎርስ ደብረ ዘይት እንደመሆኑ በሎንችና ደርሶ ለመመለስ ራሱ 1 ብር ከ50 ሣንቲም ያስፈልግ ስለነበር ዊንጌት ትምህርት ቤት ነርስ ለነበረው ብርሃነ ገብርኤል ጉዳዩን ሳጫውተው አንድ አሮጌ ኮት፣ አንድ አሮጌ ጫማና መሳፈሪያ አድርጎ ሰጠኝ፡፡
ሎንችን ልይዝ ስሄድ ማን ከእኔ ሊወዳደር ይመጣል አግደው ከበደ፡፡ መቼም ስለሱ ለማሰረዳት መለስ ብዬ ስለዊንጌት ያለውን አንድ ነገር ማጫወት አለብኝ፡፡ ዊንጌት 12ኛ ክፍል ስንገባ የአመራር ችሎታ (Leadership quality)ን ተማሪዎችን የሚያሰለጥኑበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከመጨረሻ ዓመት ተማሪዎች መካከል አስተዳደሩ የሚያስቀምጣቸውን መስፈርት ያሟሉ አሥራ ሁለት ተመርጠው ፐርፌክት ሆነው ይሰየማሉ፡፡ ከመካከላቸውም አንዱ “ሃድ ቦይ” ይባልና የፐርፌክቶች ሰብሳቢና ተጠሪ ይሆናል፡፡ ከ”ሄድ ቦይ” ቀጥለው አራት “ሃውስ ካፕቴንስ” ተብለው የሚሰየሙ በአራት የቀለም ዓይነት ለተሰየሙ (ቢጫ ፣ሰማያዊ፣ አረንጓዴና ቀይ) እያንዳንዳቸው እስከ ሰማኒያ ተማሪዎች የሚያስተኙ መኝታ ቤቶች ኃላፊ ይሆኑ ነበር፡፡ ሀውስ ካፕቴን የሚሆኑት በትምህርት ጎበዝ የሆኑ፣ በፀባይ ጥሩ የተባሉ መሆን አለባቸው፡፡ አልፎ ተርፎም በስፖርቱም፣ በመጠኑም ቢሆን መካፈል የቻሉ መሆን አለባቸው፡፡ እና የመምራት ችሎታ አለው የሚባለው የሀውስ ካፕቴን ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ አግደው (ሄድ ቦያችን) ፣እኔ ደሞ የብጫው መኝታ ቤት ሃውስ ካፕቴን ነበርኩ፡፡
ምንም እንኳን በትምህርት ውጤት ብበልጠውም በቁመናው፣ በግርማ ሞገሱ፣ ከአለባበስ ጀምሮ በብዙ ሌሎች መስፈርቶች ይበልጠኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ከሱ ጋር ሥራው ላይ ለማመልከት አብረን ሆነን ነው ደብረዘይት የሄድነው፡፡
ለሥራ ውድድሩ ስንገባ የሚጠይቁን የነበሩት አቶ ታደሰ ምህረቱ የሚባሉ ነበሩ፡፡ አግደው መጀመሪያ ገባና ኢንተርቪው አድርጎ ወጣ፡፡ ሲመጣም እንዲህ እያለ ነበር “እኔ አግደው ነኝ ደግሞ በ200 ብር የምቀጠረው? ይቀልዳሉ እባክህ፡፡ እኔ ከሱ ቀጥዬ የምገባ ስለነበርኩ የብሩን መጠን ስሰማ ልቤ በኃይል ትመታ ጀመር፡፡ አባባ ለ11 ባውንድ በእንዳላሰበኝ 20 ባውንድ ልቀጠር በመሆኑ ጓጉቼ ገባሁ፡፡ ፈታኙ አቶ ታደሰ እንድቀመጥ ካደረጉኝ በኋላ በእንግልዝኛና በአማርኛ ስሜን፣ ቀኑንና ዓመተ ምህረቱን እንድጽፍ ጠየቁኝ፡፡ በእውነቱ አሁንም ጽህፈቴ መጥፎ አይደለም፡፡ በተለይ ያኔ ቆንጆ ስለነበር በደንብ ቅሽር አድርጌ ፅፌ ሰጠኋቸው፡፡
ሌላው ነገር ጠይቀውኝ ከመላለስኩ በኋላ ልጅ ነህ ምንም አይደል ቀስ እያልክ ታድጋለህ 180 ብር እንቀጥርሀለን አሉኝ፡፡
ደነገጥኩ! ተናደድኩ!
ሥራውን በእርግጥ በጣም እፈልገዋለሁ፡፡ ግን ለአግደው 200 ብር እንቀጥርሃለን ብለው ለምን ለእኔ 180 ብር አሉኝ? ልጅ ነህ ሲሉ ምናልባት የጓደኛዬን አካላዊ ገጽታ ተመልክተው እንጅ እኔ ለሥራው ልጅ እንዳልሆንኩ አውቃለሁ በሚል ሃሣብ ውስጥ እየዋኘሁ፣ ጌታዬ ሥራው የአዕምሮ ሥራ ነው ወይስ የጉልበት ስራ? ብዬ ጠየቅኋላቸው፡፡ መቼም ንዴቱ ሰውነቴን ውርር ነበር ያደረገኝ፡፡ በትምህርቱ በኩል ከአግደው እኔ እበልጥ ስለነበር የጥያቄዬ ዓላማ ሳይገባቸው አልቀረም፡፡ ጥያቄዬን ሰምተው እሳቸው ፈገግ ሲል፣ እኔ በአዕምሮዬ ብሯን ደጋግሜ ሳሰላስል የሦስት ወር የሙከራ ጊዜህን አይተን እንጨምርልህ ይሆናል አሉኝ፡፡ በልቤ ሁለት ወር ዕረፍቴንስ ሠርቼ ብለቅ? አባባ ከአሁን ወደያ ሥራ ይዘህ እናትህን እርዳ፡፡ እኔ አብቅቻለሁ ስላለ ወደ ደሴ መሳፈሪያም አላከልኝም” ስለዚህም የተሻለ መሄጃ ስላልነበረኝ ባይሆን የሙከራ ጊዜው ሁለት ወር ብቻ ይሁንልኝ ብዬ ጠየቅኩ፡፡ አሁንም ፈገግ እያሉ እሺ አሉኝና ተስማማሁ፡፡
የወር ደሞዜን 18 ባውንዷን አሰብኩና በለጠ ሆቴል 50 ብር በወር መኝታና ምግብ ተነጋገርኩ፡፡ ጋሽ በለጠ የኤርፎርስ ወጥ ቤት ሰራተኛ ስለሆነ የሚዘጋጀው ምግብ ሌላ ነበር፡፡ በቃ እዛ ተኮናተርኩና አዲስ ኑሮ ጀመርኩ፡፡ ሁለት ወሯ ልታልቅ ስትል ደሞዜ 210 ብር መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ዘጠኝ በሯ ታክስ ትሆንና 210 ብር ንፁህ ገቢ አገኘሁ ማለት ነበር፡፡ መቶ ብር እቁብ ገባሁና 101 ብሯን ለመኖሪያዬና ለሚያስፈልገኝ ሌላ ላ ወጪ አድርጌ ቅብርር ብዬ አንድ ዓመት ሰራሁ፡፡ እቁቧንም የገባኋት ልክ ዓመቷ ላይ እንድታልቅ አስቤ ስለነበር እሷም ሃብቴን በመቶ ሳይሆን በሺ ለመቁጥር አበቃችኝ፡፡
በዚያን ጊዜ ኤይር ፎርሶች የምሽት በረራ (ናይት ፍላይት)፣ ልምምድ እየተባለ ኤደን ይሄዳሉ፡፡ ኤደን በቀረጥ ነፃ ነበረችና አንዳንድ ዕቃዎች እየገዙ ይመጡ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ከፀሐፊነት ወደ ረዳት ደመወዝ ከፋይነት አድጌ ደሞዝ ከፋይ ነበርኩና ብዙ ወዳጆችን አፈራሁ፡፡ እነሱም ኤደን ሲሄዱ ጨማ፣ ካኪ ልብስና የመሳሰለውን በርካሽ ዋጋ ያመጡልኝ ነበር፡፡ በዘጠና ስድስት ብርም ከስዊዲን አገር ኮንትሮ ፔዳል የሆነች ቆንጆ ብስክሌት ለሠራተኛው መመላለሻ ተብሎ ከሚመጣው አንድ ገዛሁና ዓለሜን መቅጨት ጀመርኩ፡፡
ሰው ሁሉ አይይ ኢየሱስ አሁንማ ይቺን፣ ይቺን ለምዶ የት ይሄዳል?” ሲባል እኔ ግን ዓመቴን ጠብቄ የሥራ መልቀቂያ አስገባሁ፡፡ ለምን ትለቃለህ? ሲሉኝ ለመማር ነው ስል መለዮ ልበስና እኛ እናስተምርሃለን አሉኝ፡፡ ባለፈው ዓመት ይችን እድል ባገኝ ኖሮ አንድ ዓመት ጓደኞቼ አይበልጡኝም ነበር፡፡ አሁን ግን ጥሪትም ስለያዝኩ በራሴ ነው የምማረው ብዬ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሊከፈት 15 ቀናት ሲቀር (ከኤርፎርስ) ከአየር ኃይል መሥሪያ ቤት ተሰናበትኩ፡፡
ያለችኝን አጭር ጊዜም በመጠቀም አሥር ዓመት ወደ አላየኋት እናቴ ጋ ስሄድ ከዜጋመሉ ደብተራ ስዩም ወልደጊዮርጊስ የወለደቻት እህቴ አድጋ አገኘኋት፡፡ እናቴ ነፍሷን ይማርና የምትወደውን የወይን ጠጅ ቀለም ያለው ቀሚስና ኩታ፣ ለእህቴም የጊዜውን ቆንጆ ልብስ ገዝቼ አልብሼ፣ ጅንስ ለባሽ የሰለጠነ ሰው ሆኜ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ገባሁ፡፡ በእውነቱ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለእኔ ሌላው የኑሮ ብስለት የገበየሁበት ቦታ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ወንድ ለወንድ እየተያያዝን ዳንስ መማር፣ እንዲያም ሲል ውቤ በርሃ መግባትም ጀመርን ይሁንና በትምህርቱ በኩል ጥሩ ውጤት ነበረኝ፡፡ ትምህርቱ በተርም ነበር ተከፋፍሎ የሚሰጠን፡፡ ሁለቱን ተርም በጣም ጥሩ ውጤት ይኑረኝ እንጂ ሦስተኛውን ተርም የመጀመሪያ ዓመት ጨርሶ አልተማርኩም፡፡ በፋሲካ እረፍታችን ጊዜ ከተማሪዎችና አስተማሪዎች ጋር በሱልልታ መንገድ ሙሉ ፋርም የሚባል ቦታ ሄደን ሳለ ዊንጌት እና ዩኒቨርስቲ ኮሌጅም ማትማቲክስ አስተማሪያችን የነበረው ጂም ማርሻል ውስኪ ይጠጣ ስለነበር፡ ስማ ጂም፣ ይቺን ውስኪ የምትባል ነገር ስትጠጣ የሚሰማህ ስሜት ምንድነው? አልኩት፡፡ ሰውየው ወዳጆቹን ሲሳደብ “ጉን” ነበር የሚለው እና ‘Yo Goon, you don’t have to ask me because I have the Whiskey here’ ብሎ ከሻንጣው አውጥቶ ለምን አትቀምሰውም? ይለኛል፡፡ ብቃወመውም ቀድቶ ሲሰጠኝ እንዲያው መቅመሱ አጓጉቶኝ ስቀምሰው አይጣፍጥም፡፡ አይ ጂም ይሄማ አይጣፍጥም ስለው አንተ ቢጣፍጥ ባይጣፍጥ ምንቸገረህ? ዊስኪ ስትጠጣ ምን ይሰማሀል ነውና ያልከኝ የሚሰማኝን እንድቃወቅ ዝም ብለህ ጠጣው” ሲለኝ እንደ ውሃ ጠጣሁት፡፡
እና በደረቴ ተደፍቼ ቀረሁ፡፡
ህመሙ ጠናብኝና በ3ኛው ቀን ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ሆስፒታል ተኛሁ፡፡ የዩኒቨርስቲው ኮሌጅ የፋክሊቲ ዲን ቱርዶ (Trudeau) ይባል ነበር፡፡ ሆስፒታል ድረስ መጥቶ አትጨነቅ የመጀመሪያ ሁለት ተርም ውጤትህ በጣም ጥሩ ስለሆነ ሦስተኛው ተርም ባትማርም የዩኒቨርስቲው ፋኩልቲ ወደ ሁለተኛ ዓመት እንድታልፍ ፈቅዷል አለኝ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ሁለተኛ ዓመቴን በጥሩ ሁኔታ ጨረስኩና ሦስተኛው ዓመት ላይ ኘሮግራሙ ‘Foreign Student Leadership Project’ የሚባል የአሜሪካን ተማሪዎሽ ስኮላርሺፕ ተመራጭ ሆንኩ፡፡ የመሪነት ችሎታ አላቸው ተብለው በኮሌጅ የሚመርጡ ተማሪዎችን ስኮላርሺፕ ይሰጡና ከአሜሪካ ተማሪዎች ጋር የመተዊወቅና ልምድ የመለዋወጥ ትምህርት ለአንድ አመት ለመውሰድ ከኢትዮጵያ ከእኔ ጋር ሦስት ተማሪዎች ተላክን፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ተመራጭ የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረአብ ሲሆን 3ኛው ደግሞ በወቅቱ የቀ.ኃ.ሥ ስኮላርሺፕ የነበረ አሞጊ ካሌብ የተባለ ኬንያዊ ተማሪ ነበር፡፡ ሦስተኛ ዓመቴን አሜሪካ ተማርኩ፡፡
አሜሪካን አገር የ3ኛ ዓመት ኮሌጅ ተማሪ ሆኜ የሂሣብ ትምህር (Accounting) ነበር የምማረው፡፡ እዚያም እያለሁ ብዙ ቦታ ንግግር እንዳደርግ እጋበዝ ነበር፡፡ ስለ ሀገሬና ስለ አፍሪካ ብዙ ውይይት በማድረግ ጊዜዬን አሳልፍ ስለነበር ሳስበው እዚህ መጥቼ እንደገና ሁለት ዓመት ኮሌጅ መቆየት በእውነቱ ለእኔ አንዱን አመት ያለአግባብ እንደማቃጠል ስለቆጠርኩት ሦስቱን አመት በሂሳብ ልመረቅ ከሰራሁ በኋላ አራተኛው ዓመት ላይ በአስተዳደር አዛውሩኝ ብዬ ማመልከቻ አስገባሁ፡፡ መጨረሻ ዓመት ላይ ወደ አስተዳደር አዛውሩኝ የምትለው እንዴት አድርገህ ትችለዋለህ? ተባልኩ፡፡ ሆኖም ያለፋት ዓመታት ውጤቶች ጥሩ ስለነበሩ ፋካልቲ ካውንስሉ ማመልከቻዬን መርምሮ ፈቀደልኝ፡፡ ሲፈቅድልኝ ግን በአስተዳደር 3ኛ ዓመት ላይ መወሰድ የነበረባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ማታ በኤክስቴንሽንና በግል አጥንቼ ፈተናዎቹን መውሰድ ግዴታዬ ተደርገው ነበር፡፡
ያ ዓመት ብዙ ጭንቅንቅ የሞላበት ሆነ፡፡ በአንድ በኩል መደበኛ የ4ኛ ዓመት ትምህርትንና 3ኛ ዓመት ያልወሰድኳቸውን አስፈላጊ የአስተዳደር ኮርሶች በተጨማሪ መማርና ማጥናት፣ በሌላ በኩል ከእኔ የተሻለ ም/ፕሬዚዳንት አታገኙም ብዬ ከሃገሬ ልጆችና ከስኮላርሺፕ ተማሪዎች ጋር ተወዳድሬ ስላሸነፍኩ በተማሪዎች አመራር ውስጥ ተሳታፊ ሆንኩ፡፡ ጓደኛዬ ንዋይም በበኩሉ ለተማሪዎች ምክር ቤት ዋና ፀሐፊነት የተሻለ አታገኙም ብሎ ተወዳድሮ አሸንፎ የካውንስሉ አባል ሆኖ ነበር፡፡
  
በገበየሁ ፍራሳ የተመራው የዚያን ዘመን የተማሪዎች ካውንስል በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች ላይ የታሪክ አሻራ ጥሎ ያለፈ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ አንዱን ድርጊት እንደምሳሌ ብንመለከተው፣
ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ በየዓመቱ የዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ቀን የሚባል በዓል ነበረው፡፡ በዕለቱም ግጥሞች፣ ቅኔዎች፣ የተለያዩ የሥነ-ፅሁፍ ስራዎች ይዘጋጁና በሀገሪቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ በሳል ሰዎች መጥተው ስራዎቹን ከገመገሙ በኋላ ነበር ለኮሌጅ ቀን ሥራዎቹ የሚቀርቡት፡፡ የነመንግስቱ ነዋይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራን ተከትሎ የዩኒቨርስቲ ተማሪው ስላሉት ችግሮች በግልፅ ይወያይ፣ ስለ መንግስት ድክመት ይነጋገር ጀምሮ ነበር፡፡
እንደ አውሮጳ አቆጣጠር ግንቦት 1961 ዓ.ም በተከበረው የኮሌጅ ቀን ላይ ስለሀገር፣ ስለደሀው ህብረተሰብ፣ ስለጭቁኑ ገበሬ ኑሮ አውስተው በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የልማት አለመፋጠንና የህዝብ ኑሮ የተመሰቃቀለ ስለመሆኑ የሚያንፀባርቁ ግጥሞች ቀርበው ስለነበር ከዚህ በመነሳት በቀጣዩ የ1962 የኮሌጅ ቀን አከባበር ላይ የሚቀርቡ ስራዎችን የመንግስት መረጃ ክፍሎች ሳይገመግሙ መቅረብ አንደማይችልና ተማሪው የሚቀርበውን ፅሁፍ ለማስገምገም ፈቃደኛ ካልሆነ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት በኮሌጅ ቀን ላይ የተገኙት ግርማዊ ጃንሆይ እንደይማገኙ ጥብቅ ማሳሰቢያ ይሰጣል፡፡
በወቅቱ ኢየሱስወርቅ የተማሪዎች ማማክርት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመርጦ ነበር፡፡ ዩኒቨርስቲው የትምህርት ነፃነት ስላለው ፅሁፉን ቀደሞ በማስገምገም ላይ የመማክርቱ አባላት ሀሳቡን ስላልተቀበሉት ለማስገምገም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ በዚ ክርክር ቢካሄድም ወግባባት ላይ ስላልተደረሰ በዩኒቨርስቲው ኮሌጅ ቀን ግርማዊነታቸው ሳይገኙ ቀሩ፡፡ ይሁንና በዓሉ በተገቢው መንገድ ተከናውኖ ነበር፡፡ ያኔም ግዛቱን የሚቃወሙ፣ ብዙ ነቃፊ ግጥሞች በነዩሀንስ አማሱ ጭምር ቀርቡ፡፡ ይሄን ተከትሎ ይመስላል እኛው አንድ ቤት ውስጥ እየቀለብን እያስተማርን እንዲህ እያዶለቱ አስተደደሩን መቃወም የሚመጣ ከሆነ አዳሪነቱን መበተን ነው የሚሻለው የሚል ሀሳብ የኮሌጅ ቀን ተከብሮ እንዳለቀ አዳሪነት እንዲቀር ተወሰነ፡፡
ይህ ውሳኔ ሲተላለፍ ወዲያውኑ ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ፣ አለማያ ኮሌጅ፣ ሕንፃ ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ፣ ቅድስተ ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ጎንደር የጤና ኮሌጅ በመተባበር ሃሳቡንና ውሳኔውን በመቃወም ከቻንስለሩ (ጃንሆይ ጋ) ለመነጋገር ሚኒሊክ ቤተ መንግስት ቀጠሮ አገኙና ለስብሰባው ተሰየሙ፡፡ ኃ/ስላሴ በጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተለያዩ ሚኒስትሮች፣ በጦር መኮንኖች ግራ ቀኝ ተከበው የተማሪዎች ተወካይ የሆኑት የፅሁፍና በአንደበት አዳሪነት እንደመብት የሚታይ ባይሆንም እንኳ ውሳኔው ግን በዚህ ሰዓት መወሰድ የለበትም፣ ከጊዜ በኋላ የሚቀርብ ቢሆን የሚያስገርም አለመሆኑን ጠቅሰው ለማሳመን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ፀሀፊ ትእዛዝ አክሊሉም “እኛ በምንማርበት ወቅት በአኩፋዳ ኮቾሮና ቆሎ እየለመንን፣ እየቋጠርን፣ እሱን እየበላን ነበር የተማርነው፡፡ እናንተ ዛሬ በተመቻቸ አልጋ፣ ሁሉ ነገር ሳይጓደልባችሁ እየተንቀባረራችሁ…” እያሉ በአጭሩ ጠገባችሁ የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡
ያኔም ጃንሆይ ስንቱን የደሀ ልጅ ልናስተምርበት የምንችለውን ገንዘብ በናንተ ላይ ብቻ ማፍሰስ አግባብ አይደለም” ከማለት የዘለለ አልተናገሩም፡፡ ልጅ ይልማ ደሬሳ ግን “እንኳን እኛ ሀገር፣ ሜትሮፖሊታን ኒውዮርክ እንኳን አዳሪነት የለምና አዳሪነት ይቀጥል ብሎ እንዲህ አይነት አቋምና ክርክር ማቅረብ በፍፁም አግባብ አይደለም” ይላሉ፡፡ ኢየሱስወርቅም ለጥ ብሎ እጅ ይነሳና፡-
“ክቡር ፀሀፊ ትዕዛዝ አክሊሉ፣ እኛ እንማር የነበረው በአኩፋዳ ኮቾሮና ቆሎ እየለመንን ነበር ብለዋል፡፡ እዚህ ላይ ምንም ቅዋሜ የለኝም፡፡ እኛ ዛሬ እዚህ የቀረብነው ተማሪዎች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ት/ቤት በሄዱበት ጊዜ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የተማሩትን ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የምንማር ብንሆን ኖሮ እናንተ ያለፋችሁበትን ሁኔታ ማለፍ ግን ባለን ነበር፡፡ ነገር ግን ዛሬና ያን ጊዜ የተለያየ በመሆኑ ነገሮች ተለዋውጠዋዋ፡፡ በሌላ በኩል ክቡር የገንዘብ ሚኒስትር ኒውዩርክንና ኢትዮጵያን ማወዳደርዎ ሁለት የማይገናኙ መስመሮችን ለማገናኘት እንደመሞከር ይቆጠራል” ሲል የተማሪዎች ማመክርት አባላት ሳቃቸውን ይለቁታል፡፡
“ይሄም ትልቅ ድፍረት ነው” ብለው ጃንሆይ ተቆጥተው መለስ ሲሉ ኢየሱስወርቅም ንግግሩን ይቀጥላል “…ኢትዮጵያን ማወዳደር ያለብን ይልቁንስ ከራሳችን አህጉር፣ ከኛ የኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር የሚቀራረቡ አገሮተን ነው…” ሲል፣ ግርማዊነታቸው ጣልቃ ይገቡና “…እነ ጋናን ልትለን ይሆናል!፡ ይሉታል፡፡ እውነትም እንደ አጋጣሚ ሆኖ በዛን ጊዜ የአፍሪካ ወጣቶች ንቅናቄ ስብሰባ ላይ ለመካፈል የኢትዮጵያ ወጣቶች ወክሎ ኮናክሪ ጊኒ ደርሶ መመለሱ ስለነበር የንኩሩማ ፓርቲ የወጣት ክንፍ ድርጅት እንግዳቸው አድርገው አንድ ሳምንት ሀገሪቱን አዙረው አስጎብኝተውትም ነበርና “አዎ ግርማዊነትዎ…” ይላል፡፡ ወቅቱ እነ ንክሩማ፣ ጋማል አብድልናስር፣ ኔሬሬና እና ሴኮቱሬ አፍሪካን እንመራለን የሚሉበትና ንጉሠ ነገሥቱ ደግሞ “ከኛ የተሻለ ለአፍሪካ መሪ እንዴት ይታሰባል?” የሚሉ ስለነበር በኢየሱስ ወርቅ ንግግር ቅር ይሰኛሉ፡፡ የተማሪዎችም ማመልከቻና ጥያቄዎች ተቀባይነት ሊያገኙ ቀርቶ አዳሪነት የሚባል ነገር ከዚያን ጊዜ በኋላ ተግባራዊ እንደማይሆን ተነግሯቸው ይመለሳሉ፡፡
ውሳኔው ተግባራዊ በሆነበት ወቅት ኢየሱስወርቅ ለምረቃ የሚዘጋጅበት ጊዜ ነበር፡፡ እንደሀሙስ ምረቃ ሆኖ ረቡዕ ማታ የመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ ትልቅ የተማሪው ስብሰባ በተማሪዎች ዲን አማካይነት ተጠራ፡፡ በየዓመቱ እንደሚደረገው ሁሉ በትምህርት ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ስማቸውና ውጤታቸው እየተነገረ ከየዲፓርትመንቱ አንድ ተማሪ ተሸለመ፡፡ በመጨረሻም በዚያን ዓመት የኮሌጅ ትምህርታቸውን ከሚያጠናቅቁት መካከል በትምህርቱ፣ በጠባዩ፣ ለኮሌጁ ሕብረተሰብ የሰጠው አመራርና አገልግሎት በተማሪዎች ዲን፣ በፋኩልቲ ዲንና አስተማሪዎች ተገምግሞ አንደኛ ለወጣ ተመራቂ ተማሪ “የልዑል መኰንን መታሰቢያ ሽልማት” ይሰጥ ነበርና የዚያን ዓመት ተሸላሚ ኢየሱስወርቅ ሆነ፡፡
በበነጋው ለምረቃው ፕሮግራም ስድስት ኪሎ የልደት አዳራሽ በር ላይ ተማሪዎች ተሰልፈው ሳለ አንዱ ተማሪ መጥቶ ኢየሱስወርቅን ከሰልፉ መሀል “ትፈለጋለህ” ብሎ ያወጣውና የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ፀሀፊ ቢሮ ቁጭ ብሎ እንዲጠብቅ ይነገረዋል፡፡ ቁጭ ብሎ የሚሆነውን እየጠበቀ እንዳለ ሌሎች ጓደኞቹ ፈልገው ያገኙትና “ባንተ ምክንያት 45 ደቂቃ ምረቃው ዘገየ!” ይሉታል፡፡ “ምን ተፈጥሮ?” ሲልም “ዲግሪህ ከጃንሆይ ዥጅ አይሰጥህም ስለተባለ ተማሪዎችም፣ አስተማሪዎችም እሱ የማይሰጠው ከሆነ እኛም አንገባም ብለዋል፡፡ በል ና አሁን አንተ ስትገባ ተማሪውም ይገባል “ብለው ያስገቡታል፡፡
ቦታውን ይዞ ከተቀመጠ በኋላ ስሙ ለምርቃት ሲጠራ ይነሳል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ መሰረት በመጀመሪያ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ታስሉን አስተካክሎ አርዴይን ካደረገ በኋላ ነበር ከጃንሆይ እጅ ዲፕሎማ የሚወሰደው፡፡ “ኢየሱስወርቅ ዛፉ በማዕረግ” ተብሎ ሲጠራ ቤቱ ተናጋ፡፡ ወደ መድረኩም ወጥቶ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ታስሉን እያደረጉለት ሳለ “ዲፕሎማህ በኋላ ይላክልሀል” ሲሉ ሹክ ይሉታል፡፡ የልደት አዳራሽ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር፡፡ በዛ ሁኔታ ችግር መፍጠር አልታየውም ነበርና ይህን ላለማጨናገፍ ቀስ ብሎ ወደ ጃንሆይ ዞር ይልና ካባውን በሁለት እጆቹ እንደማጣፋት አድርጎ ዝቅ ብሎ እጅ ነስቶ የተቀበለ በማስመሰል ያልፋል፡፡ ያኔ ሁሉም ተማሪ ዲፕሎማውን ያገኘ ነበር የመሰለው፡፡
ምረቃውም እንዳለቀ ተመራቂዎችና የተገኙ ወላጆቻቸው ግብር ሲገቡ በሁኔታው እንዳያዝንና እንዳይበሳጭ በማሰብ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ወደ ቤቱ ወስዶ ከቤተሰቡ ጋር ምሳ አብልቶና አጽናንቶ ወደማታ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ (አራት ኪሎ) ይመልሰዋል፡፡
ወደያውም ያዩት ተማሪዎች የሳይንስ ፋካልቲ ዲን ሚስተር ማክፋርሌን ዲፕሎማውን ሊሰጠው ይፈልገው እንደነበር ይነግሩታል፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎችም በኋላ ሚስተር ማከፋርሌን ዲፕሎማውን አምጥቶ ያስረክበዋል፡፡
  
የኢንሹራንስ ደላላ መሆን
በአስተዳደር ተመርቁ ሥራ ለመያዝ በምሞክርበት ጊዜ አንዳንድ ችግሮች ገጠሙኝ፡፡ መጀመሪያ ሥራ ልይዝ የፈለግኩት መብራት ሀይል ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን ነበር፡፡ ለተባለው የሥራ ቦታ አንድ ሰይቼንቶ መኪና ከነቤንዚኗ ይሰጥ ስለነበር ተምሬ እንደጨረስኩ መኪና መያዙ አጓጉቶኝ ነበር፡፡ በመሥሪያ ቤቱ የጽሁፍ ፈተናም በዲፓርትመንታችን በኩል እንዲሰጥ ጠይቆ ስለነበር ተፈተንኩ፡፡ አንደኛ ወጥቼ ማለፌ ተነገረኝና አቶ እንግዳ ጀማነህ ወደ ሚባል ሹም ቢት ተጠርቼ ቀረብኩ፡፡
በጣም ጥሩ ውጤት ነው፡፡ ደስ ብሎናል አሉና አሁን የኛ ውሳኔ በህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ቦታ ሳይሆን ፐርሶኔል ኦፊሰር ሆነህ እንድትሰራ ነው አለኝ፡፡ ፐርሶኔል ኦፊሰር መኪና የለውም፣ ቤንዚን የለውም፡፡ ሰማህ አቶ እንግዳ የፈተናችሁኝ ለህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ቦታ ነው እንጂ ፐርሶኒል ኦፊሰር ብላችሁ አይደለም፡፡ እኔን ምርጫ እንዳደርግ እድሉን በመስጠት ፋንታ እናንተው ባልጠየቅሁት ቦታ ላይ ሰይማችሁኛል፡፡ ገና ሳልቀጠና እንዲህ እንደፈለጋችሁ የምታሽከረክሩኝ ከሆነ ከተቀጠርኩ በኋላማ ምን ልታደርጉኝ ነው? ብዬ ብድግ አልኩና የቢሮውን በር እንደጉድ ደርግሜው ወጣሁ፡፡
ቀደም ሲል በዘመኑ የሃገሪቱ ተጠባባቂ አቃቤ ሕግ ዶ/ር በረከተአብ ኃ/ሥላሴ ዩኒቨርሲቲም የሕገ መንግሥት አስተማሪ ስለነበሩና ከተማሪዎች ጋር ቅርበት ስለነበራቸው ከቢሮዋቸው ጠርተው መንግሥት መሥሪያ ቤት እንዳትቀጠር የደህንነት ሰዎችም በዓይነ ቁራኛ እንዲከታተሉህ ትዕዛዝ ስላለ ድምፅህን አጥፍተህ በግል መሥሪያ ቤት ተቀጥረህ እንድትሠራ እመክርሃለሁ ብለውኝ ነበር፡፡ ይህችን ምክር በማጤን የሥራ ፍለጋ ትኩረቴ ወደ ግል ድርጅቶች ሆነ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሳለሁ የወባ ማጥፊያ ድርጅት ለኢንተርቪው ጠሩኝ፡፡ ዋናው ኃላፊ ዶ/ር ቻንድ የተባሉ ሕንድ የቃል ጥያቄ አድርገውልኝ መልስ ከሰጠሁ በኋላ በወር 478 ብር ደመወዝ ሊከፍሉኝ ዝግጁ እንደሆኑ ሲነግሩኝ አስቤ መልስ እሰጣለሁ ብዬ ተሰናበትኩ፡፡
ቀጥዬም የኮሌጅ የአስተዳደር ዲፓርትመንት ኃላፊው ዶ/ር ስዩም ገ/እግዚአብሔር ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ወደሚባል ኩባንያ ሄደህ ዋና ሥራ አስኪያጅን ሚስተር ሴሲል ጆስን አነጋግር ብለውኝ ስለነበር ወደዚያ አቀናሁ፡፡ ከመሥሪያ ቤቱ ደርሼ ለዋናው ሥራ አስኪያጅ ፀሐፊ የመጣሁበትን ምክንያት ካስረዳዋት በኋላ ወደ ሚስተር ዶስ ቢሮ አስገባችኝ፡፡ በሁኔታው በተለይም በቁንንነቱ ጄኔራል ዊንጌት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከነበረው ፒኮክ እያልን በቅጽል ስም ከምንጠራው ከሚስተር ሄረንግ የማይተናነስ እንግልዛዊና ከእርሱ ያላነሰ አለባበስ ዘናጭ ሕንድ(አቤድ ፒታልዋላ) በአንድነት ቃለ መጠይቅ አደረጉልኝ፡፡ እኔም የሚቻለኝን መለስኩ፡፡ ብዙም የሀሳብ ጭንቀትና ማወላወል ሳይኖርብኝ በእውነት ሥራ ከሰጡኝ ብዙ ሳልከራከር እቀበላለሁ፡፡ ኩርት፣ ኮስተርና ቁርጥ ቁርጥ ያለ አነጋገራቸው፣ አለባበሳቸውና ጠቅላላ ሁኔታቸው ይሰማማኛል ብየ በውስጠ ሕሊናየ ወሰንኩ፡፡
ሚስተር ጆስ በዘርፉ የሰለጠንክ ባትሆንም ትንሽ እናሰለጥንሃለን፡፡ 500 ብር ደሞዝም እንከፍልሃለን ይለኛል፡፡ አነጋገሩ ማራኪ እንደው ተክ፣ ተክ የሚችል ሰው ነበር፡፡ ምንም ላስብበት እንኳን ሳልለው እሺ አልኩት፡፡ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ባቋቋሙት ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ካምፓኒ ኦፍ ኢትዮጵያ ሐሙስ ጁላይ 12 ቀን 1962 ተመርቄ ጁላይ 16 ሰኞ ሥራ ጀመርኩ፡፡
  
አቤድ ፔታልዋላ፣ ኤል አ ይ ሲ (ላይፍ ኢንሹራስ ካምፖኒ ኦፍ ኢንዲያ) የነበረ ዝንጥ ያለ ቁንን ካዥዋል ህንድ ነበር ስራዬ ብሎ በደንብ ያሰለጠነው፡፡ ሰዎችን በደንብ ቀርቦ ጤፍ በሚቆላ ምላስ ስለማናገር፣ ስለሚጥማቸው ችግር አሳማኝ በሆነ መንገድ አውርቶ የላይፍ ኢንሹራንስ እምነት እግዜር ያውቃል በሚባልበት ኢትዮጵያ፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል በሚደገምበት ሀገር ሃሳቡን አስረድቶ፣ አሳምኖ እንዲገዙ ማድረግ እጅግ ፈታኝ ስራ ነበር፡፡ ያ ኢየሱስወርቅን በደንብ አድርጎ ያሰለጠነው፡፡
ስልጠናውን ሲጨርስ የስድስት ወር የሙከራ ጊዜ ሰጠው፡፡
በተሰጠው የጊዜ ገደብ ልክ የተሰጠውን የኢንሹንራስ ፖሊሲ እንዴትም ብሎ ቢሆን ሸጦ ከጨረሰ ላይፍ ሴልስ ሱፐር ኢንተንዴንት የተሰኘውን ቦታ ሊሰጠው ቃል ገባለት፡፡ ይህንን ቦታ ለማግኘት ግን ስድስት ወሯን በአግባቡ ተጠቅሞ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ ለስራው የሚረዱት ነገሮች ተብለው አንዲት ጠርማሳ ቦርሳ፣ የኢንሹራንስ ማመልከቻ ፎርሞችና ፓምፍሌቶች ተሰጠው፡፡ እነዚህን ይዞ በየቦታው እየሄደ፣ በር እያንኳኳ ኢንሹራንስ ግዙኝ ማለት ጀመረ፡፡ አንዳንድ ከሱ ጋር አብረው ከዩኒቨርስቲ ኮሌጅ የተመረቁና መንግስት መስሪያ ቤት የገቡ “አይ ኢየሱስ! ከዩኒቨርስቲ ወጥተህ የኢንሹራንስ ደላላ ሆነህ እንዲገለፅ ስላልፈለገ አንዴ ከጀመርኩማ ከግብ ማድረስ አለብኝ የሚል ዕምነትና ግፊት ስለነበረው ወደኋላ ማፈግፈግ አልፈለገም፡፡
ስራው ግን አድካሚና አስቸጋሪ ነበር፡፡
አስር ሰው አናግሮ አንድ ኢንሹራንስ ነበር ለሁለት ወራት እየሸጠ የነበረው፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀጠል የሚችል መሆኑን እስኪጠራጠር ድረስ ተቸገረ፡፡ ተስፋ መቁረጥ ውስጡ እየተንሰራፋ ባለበት ሁኔታ ነበር አንዲት ቅፅበት የሰውየውን ሕይወት ከቶ ምን ሲደረግ ከኢንሹራንስ ውጭ ያንተ ሕይወት? ያለችው፡፡
አንድ ቀን ከአራት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ ለመሄድ ታክሲ ሲጠብቅ ታክሲዎች ከላይ ሰው እየጫኑ ይመጡና የቀራቸውን አንድ ወይም ሁለት ቦታ ለመሙላት እሱ ጋ ሲደርሱ “ካዛንቺስ?” ሲላቸው መስመራቸው ስላልሆነ ጥለውት ይሄዳሉ፡፡ ብዙ ታክሲዎች እንዲህ ተመሳሳይ ድርጊት ውስጥ ሲያልፉ ነው መታዘብ የጀመረው፡፡ ከላይ ሞልተው አንድ ሰው ፍለጋ ይመጡና እሱጋ ሲደርሱ ቆመው ይጠይቁታል፡፡ መስመራቸው ለየቅል መሆኑን ሲረዱ ይሄዳሉ፡፡ እንደዚህ እያደረጉ በየሃያ እና ሰላሣው ሜትር ለሌላ ሰው ይቆማሉ፡፡ ያኔ ነው ታክሲ ነጂው በመንገድ ላይ የቆመ ሁሉ የሱን ግልጋሎት ፈላጊ እየመሰለው እየቆመ፣ እየጠየቀ ሳያገኝ ሲሄድ ከሱ አንድ ኢንሹራንስ ለመሸጥ አስር ሰው ከማነጋገር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን የተገነዘበው፡፡
ይሄ ታክሲ የቀረውን አንድ ሰው ፍለጋ በያለበት የሚያቆም ከሆነ እኔ እንዴት ልሰለች ይገባኛል? ሲል ራሱን ጠየቀው፡፡
መልሱ ፈፅሞ ባለመሰልቸት ላይ ጠንካራ አቋም መውሰድ ነበርና በአቋሙ ገፋበት፡፡ በሚገርም ሁኔታም ለስድስት ወር የተሰጠውን የሥራ ድርሻ በሶስት ወር ጨርሶ የኢምፔሪያል ኢንሹንራስ ሴልስ ሱፐር ኢንቴንዳንት ሆነ፡፡
ከዚህ በኋላ ነው ቮልስ መኪና ገዝቶ ስራውን በደንብ የተያያዘው፡፡
  
ሁለት ዓመት ከሰራሁ በኋላ በዚህ ሁኔታ ዝም ብሎ ከምቀጥል ሀሳቤ ሳይደክም ማስትሬቴን ማግኘት አለብኝ ብዬ ስኮላርሺፕ ማፈላለግ ጀመርኩ፡፡ አሜሪካን ኢንፎርሜሽን ሰርቪስ ሄጄ አንዳንድ መረጃ አገኘሁና የእንግሊዝኛ ብቃትን የሚመዝን ፈተና ስለነበር ወስጄ ጥሩ ውጤት አገኘሁ፡፡ በቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ በነበሩት በዳግ ሐመርሸልድ ስም በተቋቋመ ፌሎሺፕ ድጋፈ ስኮላርሺፕ አግኝቼ አንድ ዓመት ተኩል አሜሪካን ሀገር ተምሬ ማስትሬቴን ስጨርስ ወደ ሃገሬ ከመመለስ ሌላ ምኞትና ፍላጐት አልነበረኝም፡፡ በዚህም ምክንያት የሴክቸረር አሲስታንት ሺፕ እንስጥህና ዶክትሬትህን ቀጥል ሲሉኝ እኔ እንደሆነ አስተማሪ አልሆን፣ አገሬ ደካማ እናት፣ ሽማግሌ አባት፣ አሮጊት እናት፣ ያልተማረች እህት፣ ያልተማረ ወንድም አሉኝ፣ ለነሱም ኃላፊነት አለብኝ…” ብዬ እንቢ በማለት አርብ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስና ፕላኒንግ ማስትሬቴን ማግኘቴን አረጋግጨ ቅዳሜ ወደ ሀገሬ ጉዞ ጀመርኩ፡፡
ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ እንደምመለስ ጠብቀው ነበርና በተለይ የቦርዱ ሊቀመንበርና የብሔራዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ክቡር አቶ ምናሴ ለማ እኛው ጋ ነው የምትሰራው አሉኝና ሞኤንኮ ሄጄ ቆንጆ ኦፔል መርጩ እንዳወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶልኝ አጠቃላይ የኩባንያው ሱፐር ኢንቴንዳንት አድርገው ሾሙኝ፡፡
የ/ቀ/ኃ/ሥ በጐ አድራጐትና የስኮላርሺፕ ጉዳይ
ስኮላርሺፕ ሳስብ ትዝ የሚለኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ በዚያን ዘመን የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ በጐ አድርጐት ድርጅት በጥሩ ውጤት የመጀመሪያ ዲገሪያቸውን ላገኙና ትምህርት መቀጠል ለሚፈልጉ ስኮላርሺፕ ይሰጥ ነበር፡፡ እኔም የመጀመሪያ ድግሪዬን በማዕረግ አጠናቅቄ ስለነበር ስኮላርሺፕ ልመና ማመልከቻ አስገብቼ መልስ አጥቼ ነበር የዳግ ሐመርሽልድን ፌሎሺፕ ድጋፍ ያገኘሁት፡፡
ትምህርቱን አጠናቅቄ ተመለስኩና ሥራ ይዤ የተወሰነ ጊዜ ከቆየሁ በኋላ አንድ ቀን በድንገት ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በጐ አድራጐት ድርጅት ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ ይዘው ቀደም ሲል ለከፍተኛ ትምህርት የስኮላርሺፕ ድጋፍ መጠየቅዎ ይታወሳል፣ ጥያቄዎ ከደረሰን የሰነበተ በመሆኑ ጥያቄዎች ማደስ ከፈለጉ ሌላ ማመልከቻ ያስገቡ የሚል ነበር፡፡ የድርጅቱን አስተዳዳሪዎች ቅር አሰኘ የተባለው መልስ ደግሞ የመጀመሪያ ማመልከቻየ ከደረሳችሁ እስካሁን ብዙ ነገሮች ሆነዋል፡፡ ከሆኑት ነገሮች ውስጥም አንዱ የዳግ ሐመርሽልድ ፌሎው ሆኜ በመመረጥ ወደ አሜሪካ ሄጄ ከፍተኛ ትምህርቴን አጠናቅቄ ሁለተኛ ዲግሪየንም አግኝቼ ተመልሻለሁ፡፡ ስለዚህም ለዓመታት መልስ የተነፈገውን ማመልከቻ የማደስ ፍላጐትም፣ ምክንያትም እንደሌለኝ በትህትና አስታውቃለሁ የሚል ነበር፡፡
ትዳርና ስደት
አንድ ዓመት ከሰራሁ በኋላ ኢምፔሪያልን ለቅቄ ብሉናይል ኢንሹራንስ በዛው ደረጃ መስራት ጀመርኩ፡፡ በእውነቱ ከኢምፔሪያል የለቀቅኩት አዝማሚያው ስላለማረኝና የተሻለ ለመስራት ይኼኛው አማራጭ ጥሩ በመሆኑ ነበር፡፡ እውነትም ትንሽ እንደሰራሁ ረዳት ማኔጀር እንዲያ ሲልም ዴፒውቲ ጄኔራል ማኔጀር ሆንኩ፡፡ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ እያለሁ ውቤ በረሃ መሄድ ጀምሬ ነበር፡፡ አንድ ቆንጆ ሴትም አይቼ በወጣትነቴ ፍቅር ይዞኝ አግብቼያት ሦስት ዓመት ግድም ያህል እንደቆየን በተለያዩ ምክንያቶች መግባባት ባለመቻላችን ተፋታን፡፡ ከዛ በኋላ ነው ከአሁኗ ባለቤቴ ጋር የተገናኘነው፡፡
ከዊንጌት ትምህርት ቤት ጓደኛዬ እህት ነበረች፡፡ ያኔ ገና እቴጌ መነን ለመግባት ከጎንደር መጥታ ነው ያየኋት፡፡ በወቅቱ ልጅ ነበረችና እንደ ጓደኛየ እህት ከማየት አልዘለልኩም ነበር፡፡ ኑሮ በየራሳችን መንገድ ሲያኳትነን ቆይቶ እኔ አግብቼና ፈትቼ ልጅቱ አድጋ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጠረችና የኔ መኪና ግጭት ደርሶባት ስለነበር የተበላሸውን እቃ ከውጪ እንድትገዛልኝ ጠይቄያት አመጣችልኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ መቀራረብ ጀመርን፡፡ ስንቀራረብም በዚሁ የአየር መንገድ ስራ እስከመቼ የመቆየት ሀሳብ እንዳላት ጠየቅኳት፡፡ የመማር እድሉ ከገጠመኝ እፈልጋለሁ አለች፡፡ ማግባትስ? ብዬ ስጠይቃት ፈቃዷ መሆኑንና አንድ ቀን የራሷን ቤተሰብ የመመስረት ፍላጎት እንዳላት ነገረችኝ፡፡ እኔ በበኩሌ ስለጋብቻ ያለኝን አስተሳሰብ ግልጽ አድርጌ አጫወትኳት፡፡
እንደ እምነትና የጋብቻ ሕይወት መመሪያዬ፣ ስንጋባ ከሞት በስተቀር ምንም ሌላ ነገር ሊለየን አይገባም ብዬ እንደማስብ፣ ይሄ ማለት ግን እንድንለያይ የሚያደርገን ምንም ምክንያት የለም ማለት እንዳልሆነና የምንለያይም ከሆነ የህይወት መጨረሻ አለመሆኑን ሁለታችንም በቅድሚያ ብንገነዘብ ጥሩ ነው አልኳት፡፡ በዚህ ተማምነን ፓስተር ሄደን ጤናችንን ተመረመርን፡፡ ጤነኛ መሆናችንንና ጤነኛ ልጆች መውለድ እንደምንችል አረጋገጥን፡፡ ያለችግር ጤነኛ የማርገዝና የመገላገል እድል ከገጠማት በመጀመሪየ ሁለት ልጆች ብቻ እንደምንፈልግ፣ መኖሪያ ቤታችንን ከሰራን በኋላ የኢኮኖሚ አቅማችንን አይተን ጥሩ ከሆነ ሁለት ተጨማሪ ልጆች ለመውለድ ተስማምተን ቅልብጭ ባለች የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ተጋባን፡፡
ሁለት ልጆች ካፈራን በኋላ ባልነው መሰረት ዳግመኛ ከሃያ፣ ሰላሳ ዓመት በኋላ እንዲህ ባደረግነው ኖሮ፣ ይሄን በጨመርንበት የማያሰኝ ጥሩ ቤት እንደምኞታችን ሰራን፡፡ በ67 ዓ.ም የገንዘብ ተቋማት በሙሉ ባንኮችም፣ኢንሹራንሶችም በደርግ ሲወረሱ የእኛም በዓባይ ኢንሹራንስ ውስጥ የነበረን የአክሲዮን ድርሻ ተወረሰ፡፡ ወደያውም የተወረሱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን አንድ ተቋም አድርጉ ተብለን አንድ ስድስት ሰዎች ተመረጥን፡፡ ከአምስት ሌሎች የተመረጡ የኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን ሌት ተቀን ሰርተን የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን አቋቋምን፡፡ እዛም ላይ የመጀመሪያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኜ ተሾምኩ፡፡ ከእኔ የተሻሉ እንዳሉ ብጠቁምም በፍጹም ይሄ አብዮቱን መቃወም ነው ነበር የተባልኩት፡፡ ትንሽ እንደቆየሁ ግን በእኔ ቦታ ሌላ ሰው በሥራ አስኪያጅነት መሾሙን በሬዲዩ ሱነገር ሰማሁ፡፡ ቀድሞም ወደ ውጪ መውጣት ፈልጌ ነበርና እድሉን ላገኝ ነው ብዬ ደስ ቢለኝም ወደ ውጪ መውጣቱ ቀላል አልሆነም፡፡ ነገሮ አስፈሪ ደረጃ ላይ እየደረሱ፣ የለውጥ ሂደቱም በእኔ እይታ ጥሩ አልሆን እያለ መጣ፡፡
የለውጥ ሀዋርያ የሆነው ሻለቃ ሽፈራው ወርቁ የመድንን ቢሮ ስናቋቁም ሳምሶናይት ሻንጣ እያያዘ ነበር የሚመጣው፡፡ አንድ ቀን በዛ ሳምንሶናይት ውስጥ ኢዚ እየያዘ እንደሚንቀሳቀስ ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ወቅቱ በስመ ሞክሼ እንኳን ሰው የሚሰተሰርበት ነበር፡፡ ይሄንን ሳስብ ከባለቤቴ ጋር ቁጭ ብለን ተማከርንበት፡፡ ታሰረህ ማየት አልፈልግም፡፡ አንድ ቀን ደግሞ ሰንቅ ማመላለስ አይቻልም ተብሎ ሞትህን መስማት አልፈልግም፡፡ ለልጆቹም ቢሆን አባታችሁ ሞቷል ከምል አንድ ቀን ታገኙታላችሁ ብል ይሻላል፡፡ በሃገራችሁ ከመጣው መቅሰፍት ዞር ማለቱ አይከፋም፡፡ እኔ ልጆቹን ማሳደግና ማስተዳደር አይቸግረኝም አለችኝ፡፡ በዚህ ተስማምተን አንዳንድ ወዳጆች ከኛ ጋር ሥራ ሲሉኝ መጀመሪያ እረፍት መውሰድ እፈልጋለሁ ብዬ ከዚህ ጎንደር፣ ከጎንደር መተማ ገባሁ፡፡ ታዲያ ረፋድ ላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ድንበር ይገቡና ቆንጆ ቅመም ያለው ቡና ጠጥተው ይመለሳሉ፡፡ ሱዳኖቹ ደሞ ወደ ኢትዮጵየ ገብተው ካቲካላ ይጠጡ ነበር፡፡ እኔም ከሀገሬ ሰዎች ጋር ብና ለመጠጣት ወደ ሱዳን ቦርደር ገባሁ፡፡
ስደት ወደ ሱዳን
አንዲት ቡና ቤት ቁጭ ብዬ ቡናዬን ስጠጣ ቆየሁ፡፡ አንድ ፖሊስ ነበር እዛ አብሮኝ ቡና የሚጠጣ እና ዝም ብለን ተፋጠን ቁጭ አልን፡፡ ብዙ ጊዜ ስለቆየሁበት ተነስቶ ወጣ፡፡ እሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ እኔ ወደ ሱዳን ቀጠልኩ፡፡ ከድንበሩ ትንሽ እልፍ ብሎ ፖሊስ ጣቢያ ነበር፡፡ እነሱ ጋ ገብቼ የሪፊዩጂ ፈቃድ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ፡፡ መጀመሪያ መመርመር አለብን አሉኝ፡፡ እንግሊዝኛ በደምብ የማይችሉ ዝቅተኛ ሹሞች ነበሩና እኔ የኢንሹራንስ ጄኔራል ማናጀር ነበርኩ ስላቸው እነሱ ግን የኢትዮጵያ ኤርፎርስ ማናጀር ያልኩ መስሏቸው የኢትዮጵያ የጦር አውሮፕላኖች ድንበር እየዘለሉ እየመጡ እዚህ የሚያስፈራሩትና ቦምብ የሚጥሉበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ሲሉ ጠየቁኝ፡፡ ኧረ እኔ አላውቅም አልኳቸው፡፡ አንተ የኤርፎርስ ሥራ አስኪያጅ አይደለህ እንዴ? አሉኝ፡፡ በብዙ ውጣ ውረድ ማንነቴን ካስረዳሁ በኋላ ማታ የነሱን ኪስራ የሚባል የማሽላ እንጀራና ሞሎሂያ በሚባል የሱዳኖች ወጥ በልቼ አሸዋዬ ላይ ተኛሁ፡፡ ከዚያ ተነስቼ በአንድ ከባድ የጭነት መኪና ተጭኜ ወደ ገዳሪፍ የምትባል ቦታ ሄድኩ፡፡ እዛ ፖሊስ ጣቢያ አስቀምጠውኝ እነሱ ወሬያቸውን ይቀዱ ጀመር፡፡
ኧረ እኔ ደክሞኛል ማረፊያ እፈልጋለሁ? ስል ይኸው አሸዋው ላይ ተኛ አሉኝ፡፡ እንዴት? ማረፊያ አልጋ ያለበትን አሳዩኝ ስል የኢትዮጵያ መንግሥት እዚህ ስለሚሰልል ላንተ ለደህንነትህ ጥሩ አይደለም አሉኝ፡፡ ኧረ ግድ የላችሁም እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም አልኩ፡፡ ትፈርማለህ? አሉኝ፡፡ አዎ ብሎ ፈርምኩና እዛው ቅርብ ያለ ሴቲት የሚባል ሆቴል አልጋ አከራዩ ጋ ሄጄ ተመዘገብኩና ሰውነቴ ላይ ያለውን አቧራ ታጠቤ፣ ቀዝቃዛ ኮካ ኮላ መጠጣት አሰሀንቶኝ ነበርና ቁልፍ ስጠኝ ስለው ቁልፍማ አልሰጥህም አንዱ ክፍል እኮ አራት አልጋ ነው ያለው አለኝ፡፡ በእውነቱ የአንዱ አልጋ ኪራይ አንድ የሱዳን ፖውንድ አይሞላም ነበርና ለአራቱም ከፍዬ ቁልፉን ሊሰጠኝ ተስማማሁ፡፡
ወዲያው ገላየን ታጥቤ በህይወቴ የማልረሳትን ያቺን ቀዝቃዛ ኮካ ኮላ ጠጥቼ አንድ ቀን አንዱ አልጋ ላይ ሌላ ቀን ሌላኛው ላይ እያልኩ የስደት ኑሮዬን ተያያዝኩት፡፡
የተወሰነ ጊዜ ቆይቼ ካርቱም ሄድኩ፡፡ እዛ ኦኤዩ የሚሰራ አብድላዚዝ ፋራጅ የሚባል አሜሪካን አገር ተማሪ ቤት እያለሁ ያገኘሁት የቆየ ወዳጄ ቤተሰብ ቤት ተጠግቼ ትንሽ እንደቆየሁ አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሥራ አገኘሁ፡፡ እዛው ጥቂት እንደቆየሁ እግዜር ይስጣቸው መቸስ ሱዳኖች ሲበዛ ጥሩ ሰዎች ናቸው፣ ሞንታዝ ዛፉ መባል ጀመርኩ፡፡ የኢንሹራንስ ኤክስፐርት ዛፉ ተብዬ ጥሩ ስም አገኘሁ፡፡
እዛው እያለሁ እንግሊዞች መጥተው ናይጄሪያ ውስጥ ኩባንያ ስላለን እዛ ሄደህ የቃል መጠይቅ አድርግ አሉኝ፡፡ ትኬት ላኩልኝና ሄጄ ቃለ መጠይቁን አድርጌ በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉኝ፡፡ ሱዳኖቹን ተሰናብቼ ተነስቼ ወደ ናይጀሪያ ሄድኩ፡፡ እንግሊዞቹ ከናይጄሪያውያን ጋር በመሆን ላቋቋሙት አዲስ ብሮኪን ኩባንያ የቴክኒክ አማካሪ አድርገው ነበር የወሰዱኝ፡፡ ከጥቂት ጊዜም በኋላ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅና ዳይሬክተር አደረጉኝ፡፡ ያኔ ነው ቤተሰቤን፣ ባለቤቴንና ልጆቼን መናፈቅ የጀመርኩት፡፡ ባለቤቴ እኔን ስታገባ ኢትዮጵያ አየር መንገድ መስራቱን አቆመች እንጂ እኔ ካገር ከወጣሁ በኋላ ተመልሳ ሥራውን ጀምራ ነበር፡፡
  
ከሱዳን ወደ ናይጄሪያ ከመሄዱ ጥቂት ጊዜ አስቀድሞ በርካታ የሥራ ጥያቄዎች ቀርበውለት ነበር፡፡ ነገር ግን ከእንግልዞች ጋር ተስማምቶ ስለነበር ጥያቄውን ተቀብሎ ማስተናገድ እንደማይችል ከምስጋና ጋር ይመልስላቸዋል፡፡ ጥያቄውን ካቀረቡለት ድርጅቶች አንዱ ጓደኛው የሚሰራበት ላይቤሪያ ውስጥ ኢምፔሪያል ኢንሹራንስ ላይፍ ኢንቴንሽንስ የሚባል ድርጅት መጥቶ እንዲጎበኛቸው ግብዣ አቀረቡለት፡፡ አጋጣሚውን ሊጠቀምበት ስለፈለገ ወደዛው አቀና፡፡ የላይቤሪያ ቆይታውን ጨርሶ ሲመለስ በጋና አክራ በኩል አድርጎ ነበር ለመመለስ የፈለገው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ አየር መንገድ አክራ በረራ እንዳለው ስለሚያውቅ አንዳንድ ኢትዮጵያኖችን አግኝቶ የሀገር ናፍቆቱን ሊወጣ ነበር፡፡
በኤርፖርት ብዙም በማይርቅ ኮንትኔንታል በተባለ ሆቴል አልጋ እንደያዘ ሀገር ውስጥ ብሉናይል ኢንሹራንስ ኮምፖኒ አለቃው የነበረውን አቶ አባተን እዛ አፍሪካ ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን ውስጥ ተቀጥሮ ስለነበር እሱ አልጋ የያዘበት ሆቴለ እሱም አልጋ ይዞ ያገኘዋል፡፡ አንዳንድ አጋጣሚዎች የሚደንቅ ክስተት ፈጥረው ያልፋሉና የቀድሞ አለቃውን ማግኘቱ ሲደንቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ በሚኖረው ወቅት ሆቴል የሚይዙት እዛ ነበርና “ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጡና የሚያድሩ ሰዎች አሉ ወይ?” ብሎ ሲጠይቅ “አዎ” የሚል መልስ ያገኛል፡፡ ካለመሞከር ደጃዝማችነት ይቀራል እንዲሉ ከመኝታ ቤቱ ውስጥ ያለውን ስልክ አንስቶ ሪሴፕሽን ደውሎ ሚስስ የዛብነሽ ታደሰ የምትባል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰው መኖር አለመኖሯን ሲጠይቅ አለች” ይለዋል፡፡ ሆቴሉ ከሚያድሩት ሰዎች አንዷ ባለቤቱ ነበረች፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ አገኛት፡፡ አቶ አባተ ክፍል ተገናኝተው ማታውኑ ወደ አዲስ አበባ ትመለስ ነበርና ልጆቹን ይዛ ከሃገር ለመውጣት ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ ባለቤቱ ከሀገር እንዳትወጣ ያገዳት አንዱ ምክንያት የእናቷ በጠና መታመም እንደሆነም በጥሞና ተመካከሩ፡፡ በዚያች ወቅት የሆነው ሆኖ ከሀገር መውጣት እንድትችል ሁለቱም የሚችሉትን ለማድረግ ተስማምተው ተለያዩ፡፡ አጋጣሚ ሆነና ብዙም ሳይቆይ እናቷ አረፉ፡፡ ኢየሱስወርቅም ወዲያኑ ጣልያን ሀገር በሚገኝ ኩባንያ ስም ሌተር ሄድ ተጠቅሞ የቅጥር ደብዳቤ አዘጋጅቶ ላከላት፡፡ የተላከላትን ሰነድ ጣሊያን ኤምባሲ አስገብታ ቪዛዋን አገኘችና ጣልያን ሀገር ገባች፡፡ ጣሊያን ሀገር እያለች ለረዥም ጊዜ የምታውቃት ጓደኛዋ ጋ አስራ አምስት ቀናት ቆየታ ከነልጆቻቸው ወደ ናይጄሪያ አቀናች፡፡
የኢየሱስወርቅ ግዙፍ ስኬትም ናይጄሪያ ውስጥ ነው የተከወነው፡፡
  
የአፍሪካ ሪኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆን
ቤተሰቦቹን እንዳገኘ፣ሁኔታዎች መሻሻል ሲጀምሩ፣ ህይወት መረጋጋት ስትይዝ ነው የአፍሪካ መንግስታትና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያቋቋሙት ልክ እንደ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሙሉ ዲፕሎማቲካዊ አወቃቀር ያለው የአፍሪካን ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን በከፍተኛ ኪሳራ አደጋ ውስጥ መውደቁ የታወቀው፡፡ ዋና መስሪያ ቤቱ ናይጄሪያ የሆነው ይኸው የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኮርፖሬሽን የመንግስታቱ ተወካዩችና ቦርዱ በከፍተኛ ክፍያ ፕራይስ ወተር ሐውስ ኤንድ አሶሴትስ የሚባሉ የማኔጅመንት አማካሪዎች ይቀጥሩና ኦዲት ተደርጎ ሲያበቃ በአንድ ድምፅ “ይሄ ድርጅት ትንሽ እንኳን ህልውና እንዲያገኝ በአዲስ ማዋቀሩና አዲስ አመራር መሾም አማራጭ የሌለው እርምጃ መሆኑ ስለታመነበት አዲስ ሰው ለመቅጠር ማስታወቂያ ይወጣል፡፡
የወጣውን አለም አቀፍ ማስታወቂያ የሰሙና ኢየሱስወርቅን የሚያውቁት ሁሉ “ለምን አታመለክትም?” ይሉት ጀመር በዛ ቦታ ላይ ተወዳድሮ ሀላፊ መሆን ማለት ሙሉ ዲፕሎማቲካዊ መብት የሚያሰጥ ነበር፡፡ ችግሩ ግን እጩ ሆኖ ለመቅረብ መጀመሪያ የተወዳዳሪው ግለሰብ ሀገር መንግስት ባይደግፈው እንኳን አለመቃወሙን ማሳወቅ አለበት፡፡ ኢየሱስወርቅ ደግሞ ለምን እንደማይወዳደር ያውቀዋል፡፡ እሱ ኬላ ሰብሮ የወጣ፣ የኢትዮጵያ ፖስፖርት የሌለውና በሪፊውጅ ፈቃድ ወዲያ ወዲህ የሚል ሰው ነው፡፡ መመረጥ አይደለም ማሰቡስ ራሱ አያስገምተውም? ነገሩ ግን እንዲህ አልሆነም፡፡ ሰውየው በአጋጣሚዎች ሰጦታ የታደለ ሰው ነበር ቢባል አልተጋነነም፡፡
የ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ማስታወቂያ በወጣበት ሰሞን ሲሰራበት በነበረው ድርጅት በኩል አፍሪካን የሚነካ የኢንሹራንስ ጉባኤ ሲኖር ተወክሎ ይላክ ነበር፡፡ በዚሁ ምክንያት ሲሼልስ ውስጥ ለስብሰባ ሄዶ ገባኤው እንዳለቀ በናይሮቢ አፍሪካን ኢንሹራንስ ኦርጋናይዜሽን የሚባል ድርጅት ሴክሬታሪ ጀነራል የሆነ ዮሴፍ አሰፋ የሚባል ጓደኛው ዘንድ ያመራል፡፡ ዮሴፍ ጋ እና ሌሎች የሚያውቃቸው ጓደኞቹ ዘንድ አንድ ሳምንት ያህል አርፎ ለመሄድ ብሎ ነበር ወደዛ ያቀናው፡፡ እዛም እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ታደሰ ገብርኪዳን አሩሻ ለስብሰባ ቆይቶ በኬንያ በኩል ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ናይሮቢ ይገባል፡፡ የኢየሱስወርቅ ጓደኞችም የብሔራዊ ባንክ ገዥውን መምጣት አውቀው ስለነበር ራት አብረውት ሲበሉ ቀጠሮ ይይዙና ከአቶ ታደሰ ጋር ራት አብረን እንበላለንና በማስታወቂያ ለወጣው የአፍሪካ ሪኢንሹራንስ የዋና ሥራ አስኪያጅነት ቦታ ለመወዳደር እንደምትፈልግና በኢትዮጵያ በኩል ተቃውሞ ስለመኖርና አለመኖሩ ጠይቀው” ይሉታል፡፡ ከስንት ዓመታት በኋላ አሁን ሳገኘው እንዴት እንዲህ ብሎ እጠይቀዋለሁ? በማለት ኢየሱስወርቅ ፡አልጠይቅም” ይላል፡፡
አጋጣሚ ራቱ አልቆ ወደየማረፊያቸው ሊለያዩ ሲሉ የባንኩ ገዥ አቶ ታደሰ መኪናው ውስጥ ገብቶ ጉዞ ሊጀምር ካለ በኋላ ከመኪናው ወርዶ “ኢየሱስ አንድ ነገር ብልክህ ትተባበረኛለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ኢየሱስወርቅም “ምን ችግር አለው? ምን ልተባበርህ?” ይለዋል ሙሉ ፈቃደኝነቱን በሚገልፅ ትሁት አቀራረብ፡፡ “እባክህ ናይጀሪያ ያለው አቶ አባተ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ውስጥ አሁን እየመጣ ባለው የማኔጅመንት ለውጥ የኢትዮጵያ መንግስት የሚደግፈኝ ከሆነ ለምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅነት ልወዳደር ብሎ ጠይቆ ነበርና ይህ አይነቱ ድጋፍ ሊሰጠው እንደማይችል ንገረው፡ ይለዋል፡፡ ይሄኔ ቅሬታውን ሳይሸሽግ “አይ አቶ ታደሰ ይቅርታ አድርግልኝ እንዲህ አይነቱን መልዕክት ማድረስ ያስቸግረኛል፡፡ አንደኛ መምዕክቱ ጥሩ አይደለም፡፡ ሁለተኛ እኔ እኮ ምናልባት ትቸገር እንደሆነ ብዬ ከስንት ጊዜ በኋላ ሳገኝህ አላስቸግርህም ብዬ ነው እንጂ፣ እኔ ራሴ ለዋና ሥራ አስኪያጅነት ቦታ እንድወዳደር ጓደኞቼ ሲጠይቁኝ የኢትዮጵያ መንግስት ላይደግፈኝ ይችላል ብየ ነው ዝም ያልኩት” ይለዋል፡፡ አቶ ታደሰ ስለጉዳዩ በደምብ እንዳላወቀ ጠቅሶ “እንደሱማ ከሆነ እንፄዳት እንዲህ ያለ መልእክት ታደርሳለህ? በል ተወው፡፡ ለምንድን ነው ግን አንተ የኢትዮጵያ መንግስት ይደግፈኛል ወይ ብለህ የምትጠራጠረው? ምን አደረግክ? አገር ጥለህ በመሄደህ ኢትዮጵያ ነች እንጂ የተጎዳችው አንተ ምን አደረግክ? በል አሁን ሙሉ ድጋፍ በፈለግከው በኩል ስለምታገኝ አመልክት” አለው፡፡
የነገሩን ጨርሶ ባልተጠበቀ ሁኔታ መምጣት የእግዜር ስጦታ ያህል ነበር የቆጠረው፡፡
ውድድሩ ከባድና አንድ መቶ አስራ አሰባት አፍሪካውያን ተወዳዳሪዎች የተካፈሉበት ነበር፡፡ ኢየሱስወርቅን እንደተወዳደሪ ደግፎ ያቀረበው የናይጄሪያ መንግስት ነበር፡፡ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዩንኬይማ ነበሩ የድጋፍ ፈቃድን የፈረሙበት፡፡ ከተፍተኛ ውድድር ከተካሄደበት ከዚያ ምርጫ በሚደንቅ ውጤት በሙሉ ድምጽ በመመረጥ ኢየሱስወርቅ የአፍሪካ ሪኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ (ዲይሬክተር ጀነራል) ሆነው፡፡ ያኔ ታዲያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ታደሰ ኢትዮጵያ የማትቃወም መሆኑን ግልፁልን ሲባሉ አለመቃወም ብቻ ሳይሆን እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ብቃት እንዳለው የምናምንበት ዜጋችን ነው ሲሉ ነበር የፃፉለት፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንደሆነመ የኢትዮጵያ መንግሥት የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ሰጠው፡፡
በህይወቱ እንደ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ፊታኝ ስራ እንዳልገጠመው ያምናል፡፡ እንደተባለው ተስፋ የሌለው ድርጅት መሆኑን ይበልጥ ማስረገጥ ወይ ደግሞ ከተመናመነ ተስፋው መንጥቆ አውጥቶ ህይወት ሊዘራበት ምርጫው በሱ ብቃት ላይ ነበር የሚወሰነው፡፡
ሌት ተቀን መስራት ነበረበት፡፡ ይሄ ሌት ተቀን የሚለው ቃል ግን ለዘልማድ ያህል የተጠቀሰ ሳይሆን የተግባሩ ተክክለኛ መገለጫ ቃል ነው፡፡ የመጀመሪያውን ሶስት አራት ዓመት ድርጅቱን የማቃናት ስራ ላይ ተወጠረ፡፡ በጣም ብዙ ጉድፍ የነበረበትን ያን ድርጅት ሙሉ በሙሉ ማፅዳት ነበረበት፡፡ እዛው ናይጄሪያ ውስጥ በናይጄሪያ ነጋሪት ጋዜጣ የድርጅቱ ስታተስ እንዲታወጅና ከናይጄሪያ ያለውንም የሪኢንሹራንስ ሥራ በቀጥታ ያለማንም ኤላ ደላላ ጣልቃ ገብነት መስራት እንዲችል የሚያደርገውን አዋጅ እንዲታወጅ አስደረገ፡፡ እጅግ ባለሰለሰ ጥንቃቄና ጥረት ባካሄደው ትግል ተስፋ የለውም የተባለለት ድርጅት ከተሰፋም አልፎ በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማትረፍ ጀመረና ጉድ አሰኘ፡፡ ከዚያ በኋላ አፍሪካ ሪ እያሳየ የመጣው ለውጥ ለኢየሱስወርቅ ትልቅ ኩራት ሆነው፡፡ አፍሪካ ሪ እንደተሾመም ስሞን ኬላ ሰብሮ እንዳልወጣ ሰተት ብሎ ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ ያኔ በደንብ በቀይ ምንጣፍ (ሬድ ካርፔት) አይነት አቀባበል ነበር የተደረገለት፡፡ በቅርብ የሚያውቁትም ብዙ ወዳጆቹ “ኬላ ሰብሮ በእግሩ የወጣ ኮብላይ በቦሌ ቪአይፒ (VIP) በቀይ ምንጣፍ ተመለሰ” እያሉ ያሾፉብታል፡፡
የአፍሪካ ልማት ባንክ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ባለአክሲዮን ነው፡፡ እንደሚታወቀው የአፍሪካ ልማት ባንክ ራሱ በአፍሪካ መንግሥታትና አፍሪካዊ ባልሆኑ መንግሥታት ሕብረት የተያዘና የሚተዳደር ድርጅት ነው፡፡ ታዲያ አፍሪካዊ ያልሆኑት አባላት አፍሪካውያኖቹን “ሁል ጊዜ የምታቋቁሟቸው ድርጅቶች ፖለቲካዊ ግብ ያላቸው ናቸው፡፡ ቢዝነስ አታውቁም፡፡ በያለበት ኪሣራ ነው፣ በያለበት ሙስና ነው…” እያሉ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ እየከሠረ በነበረበት ጊዜ እንደምሳሌ ይጠቅሱት ነበር፡፡ ገፅታውን ቀይሮ በትርፍ ሽቅብ ሲወጣ ደግሞ አፍሪካ ልማት ባንክም አፍሪካ ሪኢንሹራንስን እንደ አንድ ጥሩ ምሳሌ ሊያነሳው ተገደደ፡፡ አልፎ ተርፎም በየዓመቱ አቡጃ በሚያካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ኢየሱስወርቅን ስለ ኢንሹንራስና ኢንቨስትመንት ወረቀት እንዲያቀርብ ይደረግ፣ በየሄደበት የሀገር መሪዎች፣ የገንዘብ ሚኒስትሮች… የላቀ ከበሬታ ይቸሩት ጀመር፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን ኢየሱስወርቅን የስኬቱ ጥግ አድርጎ አላቀመውም፡፡
አፍሪካ ሪኢንሹንራስ የአፍሪካ መንግስታት ሲያቋቋሙት ለኩባንያው የሚያዋጡትን ገንዘብ ሃምሳ በመቶውን ብቻ ነበር የከፈሉት፡፡ እሱ ሊገባ ሲል ኩባንያው አደጋ ውስጥ በመሆኑ ተጨማሪውን ሃምሳ በመቶ መክፈል እንዳለባቸው ተጠይቀው እየከሰረ ባለ ድርጅት ውስጥ ተጨማሪ ገንዘብ ማስቀመጡ አልታያቸውም ነበርና ከወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ችግር ጋር በተያያዘም የሚጠበቅባቸውን ተጨማሪ ገንዘብ ሳይከፍሉ ቀሩ፡፡ ትርፍ መስራቱ ሲገርማቸው ለነበሩት ሁሉ ”ሊታመን የማይችል” የሚለውን ቃል በሙሉ አግራሞት ታጀበው እንዲያወጡት ከማድረግ አልዘገየም ነበር፡፡ መንግስታት ሊከፍሉት የሚገባውን ሁለተኛውን 50 በመቶ እዳቸውን ከትርፉ ላይ ከፍሎላቸው ቁጭ አለ፡፡ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ከተስፋ ማጣት እጅግ ሊያስደንቅ በሚችል ስኬት ላይ ተፈናጠጠ፡፡ ኢየሱስወርቅ መድህን ሆነው!
ያኔ አባል ያልሆኑ የአፍሪካ መንግስታት የአባልነት ጥያቄ ሲቀርብላቸው ፈገግታ ባጀበው ደሰታ አበል ይሆኑ ጀመር፡፡ አፍሪካ ሪኢንሹራንስ ውስጠ በአንድ ጊዜ ለ5 ዓመት ነበር አንድ ተመራጭ የሚሰራው፡፡ ኢየሱስወርቅ የመጀመሪያውን አምስት አመት ከጨረሰ በኋላ ለሁለተኛው አምስት አመት በድጋሚ ተመረጠ፡፡ ያኔም የካፒታሉን 67 በመቶ እንደገና ትርፍ ሰርቶ በሼር መልክ ለመንግስታቱ አከፋፈል፡፡ የአፍሪካ ኢንሹንራስ ኩባንያዎች ብሎ ፖሊሲው እንዲስተካከል ብዙ ክርክርና ውዝግብ ከተደረገ በኋላ እንዲቀበሉት በማድረግ አቅም ያላቸው የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አባል እንዲሆኑ አደረገ፡፡
አፍሪካ ሪኢንሹራንስን በሁለት እግሩ ከማቆምም በላይ እንደልቡ እንዲሮጥ ካስቻለው በኋላ ሁለተኛው የተመረጠበት አምስት አመት ሊሞላ አንድ አመት ሲቀረው ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ደርግን ይታደጋል፣ ስህተቶችን ያርማል፡፡ እንዲያም ከሆነ ሃገር እንደገና ጥሩ ሥራ ሊሠራባት ይቻላል፣ እኔስ ብሆን በሰው ሃገር ተንደላቅቄ ከመኖር ሃገሬ ገብቼ ለ20ኛ ለ50 ሰው የሥራ ዕድል መፍጠሩ አይበልጥም ወይ? ብሎ ራሱ ላነሳው የሕሊና ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሰጥቶ የሥራ ኩንትራቱንም ሳይጨርስ ወደ ሃገሩ ተመለሰ፡፡

  
ወደ ሀገር ቤት መመለስ
ወደ ሀገሬ ከመመለሴ በፊት ኢንሹራንስ ለማቋቋም የሚያስችል ህግ በመረቀቅ ላይ እንደነበር አውቅ ነበር፡፡ ባይኖርመ ሌሎች ኢንሹራንስ ነክ ሥራዎችን ለማቋቋም እችል ይሆናል፣ ህጉም የወጣ እነደሁ በርካታ ነገሮችን መስራት እችላለሁ ብዬ ብመጣም ስድስት ወር ያህል ህጉ ሳይወጣ ዘገየ፡፡ በወጣበትም ዓመት ያደረግኩትን ጥናት ለተወሰኑ ሰዎች ሳቀርብላቸው በወረቀት የምትሰጠን ሳይሆን ሥራውን አንተ የምትጀምረው ከሆነ ሁላችንም ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ ነን አሉ፡፡ እኔም ባይሆን አቋቁሜው ሌላ ድርጅቱን የሚያንቀሳቅስ ሰው እንዲተካኝ በማድረግ እኔ ሌላ የምፈልገውን እሰራለሁ ብዬ ኩባንያው እንዲመሰረት አደረግኩ፡፡ ኢንሹራንሱ ሲቋቋም ትልቁና ዋነኛው ነጥብ የሥራ እድል መፍጠርም ነው የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡ ብዙዎችም በኢንሹራንሱ መመስረት ላይ ኢንቨስት ስላደረጉ ስሙን ሕብረት ኢንሹራንስ ብለነው ፈቃድም በጠየቅን በሁለት ቀናት አግኝተን ለማቋቋም ያደረግነውን ወጪ ገንዘብ በሙሉ መልሰን ወሰድን፡፡ አሁን ኢንሹራንሱ ትርፋችን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከኢንሹራንሱ ትርፈ ከሚገኝ ገንዘብ ወጭ ተደርጐ ያም እንደ እርሾ ሆኖ የዛሬውን ሕብረት ባንክን ለማቋቋም ተቻለ፡፡ አሁን በኢንሹራንሱና ባንኩ አነሰ ቢባል ስምንት መቶ የሚጠጋ ሠራተኛ አለ፡፡ ለዚህ አይነት የሥራ እድል መፈጠር አንዱ ምክንየት ነኝ ብዬ ስለማምን የኔ ትልቁ ሽልማቴና ሜዳልያዬ ብዬ የማስበውና ከስኬቶቼም እንደ ዋነኛው አድርጌ የምቆጥረው ይህንን ነው፡፡
ከዚህ መደበኛ ሥራዬ ውጪ ከአንድ ሁለት ኢትዮጵያኖች ጋር ሆነን ማጂክ ካርፔት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚል አንድ ትምህረት ቤት ገዝተን አሁን ወደ አራተኛ ዓመት ሆኖታል፡፡ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትም ውስጥ በምክትል ፕሬዝዳንትነት እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡ ሌላው እኔና ባለቤቴ ከብዙ በሕመሙ የተነኩ ቤተሰቦችና የአእምሮ ጤና ሐኪሞች ጋር በመሆን አእምሮ ጤና ክብካቤ ማህበር ኢትዮጵያ የሚባል ሃገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አቋቁመን ባለቤቴ በፈቃደኛ ኃላፊነት (ያለምንም ዓይነት ጥቅምና ክፍያ) እየመራቸው ይገኛል፡፡ በእውነቱ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል፣ እኔ የምመኘውን፣ ፈልጌ ያላገኘሁትን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል የምለው፣ አገር የሚያደንቀው ልጄ ኒውዮርክ ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሮችስተር ማትማቲክስና እስታትስቲክስ (ጥምር ሜደርስ) አጥንቶ ለመመረቅ ተቀብለውት እዛ ትምህርት ቤት እያለ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ በሚያስቸግር ሁኔታ፣ የአእምሮ ጤና ችግር ገጠመው፡፡ አሁን እንግደህ እዚሁ እኛ ጋር ነው ያለው፡፡ ከህመሙ ለማዳን ያልገባንበት፣ ያላደረግነው ጥረት የለም፣ አይኖርበትምም፡፡ ከዚህም የተነሳ ነው ማህበሩን የማቋቋም ጥረቱን ተቀላቅለን እኔና ባለቤቴ የበኩላችንን አስተዊጽኦ እያደረግን ያለነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እዚሁ ከኛ ጋር ሲሆን የሚኖረው ተገቢውን እንክብካቤ እያደረግንለት ነው፡፡
ፈረንጅ ‘Ambition Should never die!’ እንደሚለው ሁሉ ህይወት እንዲህ እያለች ትቀጥላለች፡፡ በቃኝ ያልኩ እለት እንደምሞት ስለማውቅ ጥረቴን ማቆምን ጨርሶ አላስበውም፡፡ ህይወትም ጣዕም ያለው ትግሉ ሲቀጥል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከውዷ ባለቤቴ የዛብነሽ ታደሰና ከአእምሮ ታማሚው ልጃችን ፍጹም ኢየሱስወርቅ ጋር ደርግ የወረሰብን ቤት ተመልሶልን እዛ ውስጥ እየኖርን ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ዓቢይ ኢየሱስወርቅ የኮምፒውተር ፕሮግራመር ሲሆን የሁለት ሴቶች ልጆች አባል ሆኖ አሜሪካን ሀገር ይኖራል፡፡ የልጅ ልጅ ለማየትም የታደልኩ በመሆኑ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ እንደ ትናንቱ ህይወትን በብሩህ ገጽታዋ እያየኋት እኖራለሁ፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »