ከባንኮች ብድር ማግኛ መስፈርቶች
ከባንኮች ብድር ማግኛ መስፈርቶች
- የንግድ ባንኮች ብድር አሰጣጥና ለመበደር የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች
ያለጥርጥር ንግድን ለመጀመር ወይም ለማስፋፋት የሚያስፈልግን ገንዘብ ለማግኘት ጠንካራ
ጥረትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡ ንግድዎን ለመጀመር ወይም ለማስፋፋት ሲያቅዱም
የገንዘብ እጥረት ከፍተኛ እንቅፋት ሊሆንብዎት ይችላል፡፡
እስካሁን ድረስ በሀገራችን ውስጥ 18 ባንኮች ተቋቁመው በስራ ላይ ያሉ ሲሆን የሚሰጡት አገልግሎትም ገንዘብ የማስቀመጥ፣ ካስቀመጡት ገንዘብ የማውጣት፣ ገንዘብ የማስተላለፍ እና የብድር አገልግሎቶችን ነው፡፡ ከባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በሀገራችን ያሉ የንግድ ባንኮች የሚሰጡትን ብድር፣ ብድሩን ለማግኘት ያሉትን ሂደቶች፣ ከብድር ጋር በተያያዘ የሚነሱትን ጉዳዮች፣
ሀ) ጊዜ ላይ የተመሰረተ ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ደንበኞች ቀድመው በተዋዋሉት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚያልቅ እና ወለድ የሚከፈልበት ነው፡፡ ብድሩም በየወሩ፣ በየሩብ ዓመቱ፣ በግማሽ ዓመት እና በየዓመቱ ወይም ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም ብድር በአንድ ጊዜ በመክፈል ሊከናወን ይችላል፡፡ ይህ የሚወሰነውም በድርጅቱ የገንዘብ ፍሰት እና በድርጅቱ ሁኔታ ላይ በመመርኮዝ ነው፡፡ የጊዜ ሂት ላይ በመመስረትም ይህንን የብድር ዓይነት በሦስት መክፈል ይቻላል፡-)
- የአጭር ጊዜ ብድር (በአብዛኛው ከ2 ዓመት ያነሰ)፡- ይህ የብድር ዓይነት የአጭር ጊዜ የገንዘብ ፍላጎትን (የመስሪያ ገንዘብ ፍላጎትን) ለማሟላት የሚሰጥ ብድር ነው፡፡
- የመካከለኛ ጊዜ ብድር (ከ2-5 ዓመት)፡- ይህ የብድር ዓይነት ለመካከለኛ ጊዜ የሚፈለግ የገንዘብ እጥረትን ለማሟላት የሚሰጥ ብድር ነው፡፡
- የረጅም ጊዜ (ከ5 ዓመት በላይ)፡- ይህ የብድር ዓይነት የረጅም ጊዜ የገንዘብ ፍላጎትን ለማሟላት የሚሰጥ ብድር ሲሆን ከእነዚህም መካከል ለኘሮጀክቶች፣ ለሰፋፊ ግንባታዎችና ለመሳሰሉት የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው፡፡
በጊዜ ላይ የተመረኮዘ ብድሮች ምሳሌ፡-
መጠን 200,000
የወለድ መጠን 10%
የመክፈያ ጊዜ በየወሩ
ብድሩ የሚያልቅበት ጊዜ 3 ዓመት
|
ለብድር የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ከተሟሉ እና ብድሩ ከተከፈለ በኋላ የብድር መጠኑ ወደ ደንበኛው ሂሣብ ይገባለታል፡፡ ከዚያም ደንበኛው እኩል የሆነ ክፍያ በየወሩ ብር 6,453.44 ለሦስት ዓመታት ይከፍላል፡፡ አጠቃላይ ክፍያውም ዋናውን ብድር እና ወለዱን ያካትታል፡፡
ለ) የኦቨር ድራፍት ብድር (ከተቀማጭ ሂሳብ በላይ የሚሰጥ)፡-
ይህ የብድር ዓይነት ደንበኛ በባንክ ካስቀመጠው (ካለው) ገንዘብ በላይ እስከተወሰነ መጠን ድረስ ለእለት እንቅስቃሴው ብር እንዲያወጣ ነው፡፡ ይህ የብድር ዓይነት በጊዜ ላይ ተመርኩዞ ከሚሰጥ ብድር በሁለት ባህሪያት ይለያል፡፡
የመጀመሪያው ብድሩን ለመክፈል ቀድሞ ኘሮግራም የተያዘለት አለመሆኑ እና ሁለተኛው ደግሞ የመክፈያ ጊዜው ክፍት መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ባንኩ በድርጅቱ እንቅስቃሴ ያልረካ ከሆነ በፈለገው ጊዜ ብድሩ እንዲመለስለት ይጠይቃል፡፡ የወለድ መጠኑ የሚሰላውም በወሩ ውስጥ አንድ የኦቨር ድራፍት ደንበኛ ከባንኩ ያወጣው እና ወደ ባንክ ሂሳቡ ያስገባው መጠን ልዩነት ነው፡፡
ምሳሌ፡–
የብር መጠን 200,000.00
የወለድ መጠን 9%
የመክፈያ ጊዜ ገደብ የለውም
ብድር የሚያልቅበት ጊዜ በ1 ዓመት ወይም በ6 ወር የሚታደስ
አንድ ደንበኛ የኦቨር ድራፍት ደንበኛ ከሆነ ገንዘቡን ወደ ሂሳብ ከማስገባት ይልቅ እስከ ብር 200,000.00 ድረስ ሂሳቡ ላይ ምንም ባይኖረውም እንዲያወጣ ይደረግና ባንኩ በየቀኑ ደንበኛው ያወጣውን ተጨማሪ ገንዘብ በወሩ ውስጥ አስልቶ ወለዱን በወሩ መጨረሻ ያስከፍለዋል፡፡
ሐ) ኦቨር ድሮዋል (ተጨማሪ ወጭ)፡-
ይህ የብድር ዓይነት በኦቨር ድራፍት ላይ በተመደበለት ብር በላይ ለአስቸኳይ እና ያልተገመተ የገንዘብ እጥረት ማቃለያ የሚፈቀድ የብድር ዓይነት ነው፡፡
ድርጅትዎ የኦቨር ድራፍት የብድር ዓይነት ከተመቻቸለት በኋላ ባልጠበቁት ሁኔታ የገንዘብ እጥረት ቢገጥምዎ የኦቨር ድሮዋል ብድር እንደገና ሊመቻችልዎት ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ለዚህ ብድር የሚከፍሉት የወለድ መጠን ከላይ ካየናቸው የብድር መጠኖች ከፍ ያለ ነው፡፡
መ) የሸቀጥ ብድር /መርቻንዳይዝ ብድር/፡-
ይህ ዓይነቱ ብድር ሸቀጦች ተገዝተው በግምጃ ቤት ውስጥ ከተከማቹ በኋላ የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም እነዚህ ሸቀጦች እስከሚሸጡ ድረስ ለሚፈጠር የገንዘብ እጥረት ማቃለያ የሚሰጥ ብድር ነው፡፡ ለዚህ ብድር በዋስትና መያዣነት የሚያገለግሉት እነዚሁ ሸቀጦች ናቸው፡፡
በክምችት ያሉትም ሸቀጦች በባንኩ እና በድርጅቱ በጋራ የሆነ ቁጥጥር ይጠበቃሉ፡፡ ከዚህ ክምችት ውስጥ የተወሰነ ሲሸጥ ይኸው ገንዘብ ከነወለዱ ለባንኩ ይከፈላል፡፡
ሠ) ቅድሚያ ጭነት ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ቡና ላኪ ላልሆኑ ላኪዎች የሚሰጥ ብድር ሲሆን ይህም 80% የሚሆነውን ዋስትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ /የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚሰጥ ሆኖ ጥሬ እቃው ተገዝቶ የምርት ሂደቱን ጨርሶ ያለቀለት ምርት ሆኖ እስከሚወጣ እና ተመልሶ ወደ ውጭ ለመላክ እስከሚጫን ድረስ የሚያስፈልግ የገንዘብ እጥረት የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው፡፡
ረ) ለማስመጣት የሚሰጥ የመተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት)፡-
ይህ ዓይነቱ ብድር አንድ አስመጪ ውጭ ሀገር ካለ ላኪ ጋር እቃ ለማስመጣት ይዋዋልና እቃውን ውጭ ያለው ድርጅት መጫኑን የሚያሳይ ሰነድ ለባንኩ ሲያቀርብ ባንኩ አስመጪውን በመወከል የሚከፍልበት የብድር ዓይነት ነው፡፡ ጠቅላላ የግዢና ሽያጭ ውለታዎች የሚፈጸሙት ለአስመጭና ላኪዎች ይሆናል፡፡
ሰ) በማስመጫ ሰነድ ላይ የሚከፈል ቅድሚያ ክፍያ ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት አንድ አስመጪ እቃውን አስመጥቶ ከወደብ እስከሚለቀቅለት ድረስ የሚሰጥ ብድር ነው፡፡ ሆኖም የሰነድ ስራዎች በ1 ወር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ማለቅ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ከፍ ላለ የወለድ ክፍያ ይዳርጋል፡፡
ሸ) ወደ ውጪ ለመላክ የሚሰጥ ቅድሚያ ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ለላኪዎች በመቶኛ ተሰልቶ የሚሰጥ ብድር ሲሆን በመቶኛ የሚሰላውም እቃውን ልኮ ከሚሰበስበው ገንዘብ ላይ ነው፡፡
ቀ) ወደ ውጪ ለመላክ የሚከፈት የመተማመኛ ሰነድ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ቅድሚያ የሚሰጥ ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ላኪዎች ከሀገር ውጭ ባለ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚሰጥ ብድር ነው፡፡
በ) የሕንፃ/የቤት ግንባታ ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ለቤት እና ለንግድ ግንባታ የሚሆን የገንዘብ እጥረት ሲያጋጥም ይህንን እጥረት ለማስወገድ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም የሚከፈለው በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ብድር ይሆናል፡፡
ተ) የባንክ የዋስትና ብድር፡-
ይህ የብድር ዓይነት ባንኩ የተወሰነ ገንዘብ ለሚመለከተው ግለሰብ/ድርጅት ለመክፈል ዋስትና የሚገባበት ሲሆን ይህን ክፍያ ሊፈጸም የሚችለው አመልካች/ ተበዳሪው በውለታው መሰረት ለመፈጸም የገባውን ቃል ሳያከብር ሲቀር ነው፡፡
በንግድ ባንኮች የሚሰጡ የዋስትና ሰነዶች፡-
- የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና
- የጨረታ አፈጻጸም ዋስትና
- የአቅራቢዎች ዱቤ ዋስትና
- የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና
- የቀረጥ ክፍያ ዋስትና እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ቸ) የንግድ ቅንሽ ሰነድ፡-
ይህ የብድር ዓይነት አዲስ የብድር ዓይነት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ በዱቤ ሽያጭ ለሚያከናውኑ ነጋዴዎች ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ድርጅትዎ የጥሬ ገንዘብ እጥረት ሲያጋጥመው የዱቤ ሽያጭ ውሉን ለባንኮች በማቅረብ የሚሰጥ የብድር ዓይነት ነው፡፡
- ብድርን ከመውሰድ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች
የንግድ እቅድ፡- የንግድ እቅድ የንግድዎን አቅም የሚገልፅ ሰነድ ሲሆን በንግድዎ ላይ የሚኖሩትን አዎንታዊና አሉታዊ ተፅእኖዎች ከግምት ያስገባል፡፡
የዋስትና ማስያዢያ፡- ይህ ማለት አንድ ተበዳሪ ለሚበደረው ገንዘብ የሚያስይዘው ዋስትና ሲሆን ይህም ተበዳሪው ባልተጠበቀ መንገድ የወሰደውን ብድር ሳይከፍል ቢቀር ባንኩ የያዘውን የዋስትና ንብረት ሽጦ ገንዘቡን ይወስዳል፡፡
የዋስትና ማስያዢያ ሽፋን ንጽጽር፡- ይህ ንጽጽር ለዋስትና ያስያዙት ንብረት ከተበደሩት ገንዘብ ጋር ያለው ንጽጽር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ያስያሪት ንብረት
100% ቢሆን ሊበደሩ የሚችሉት 100% ከ100% የበለጠ
ወይም ያነሰ ሲሆን ይችላል፡፡
ወለድ፡– ይህ ማለት ተበዳሪው ለተበደረው ገንዘቡን በመበደሩ
ምክንያት የሚከፍለው ዋጋ ሲሆን በአብዛኛው በዓመታዊ
ብድር መቶኛ ይገለጻል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ያሉ ባንኮች
ብድር የሚሰጡበት የወለድ መጠን ከ8.5% አስከ 15% ድረስ ይሆናል
ንጹህ ብድር/ ክሊን ሎን/፡- ይህ የብድር ዓይነት ማንኛውም የብድር ዓይነት ሆኖ የድርጅቱ/ የተበዳሪው/ ጥንካሬ እንጂ ያለው የማስያዢያ ዋስትና ግምት ወስጥ የማይገባበት ነው፡፡
የእፎይታ ጊዜ፡- ይህ ጊዜ ተበዳሪዎች ገንዘቡን ተበድረው በመክፈል እስከሚጀምሩበት ድረስ ያለው ጊዜ ሲሆን ተበዳሪዎች በዚህ ጊዜ ውሰጥ ወለድ ብቻ እንዲከፍሉ ይገደዳሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የእፎይታ ገዜ በሩብ ዓመት ግማሽ ዓመት እና በዓመት ሊገለጽ ይችላል፡፡
ብድሩን እንደገና ማየት፡- ይህ ማለት የብድሩን ማብቂያ ጊዜ እንደገና መከለስ ሲሆን ይህም የወለድ መጠኑን በመጨመርና በመቀነስ፣ የብድሩን መክፈያ ጊዜ እና መጠን በመቀየር ማስተካከል ሲሆን ከዚህ በኋላ እንደገና የተሰራ የብድር አከፋፈል ሰንጠረዥ እንዲደርስዎት ይፈልጋል፡፡ ይህ የሚጠቅመው
- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ያልተከፈሉ ብድሮችን ለማስተካከል
- የብድሩን ዕድሜ ለማራዘም/ብድሩ ተከፍሎ የሚያልቅበትን ጊዜ ለማራዘም
- አዲስ የገበያ ሁኔታ ለመፍጠር ነው፡፡
ያልተከፈለ ብድር፡- ይህ ማለት ተበዳሪው በተቀመጠለት ኘሮግራም መሰረት ብድሩን ሳይከፍል ለ90 ቀናት ሲቆይ ማለት ነው፡፡ ይህም የተበዳሪው ፋይል ወደ ያልተከፈለ ብድር ይዛወራል ማለት ነው፡፡ ከዚያም በውለታው መሰረት ላልተከፈለው ገንዘብ ቀድሞ ከሚከፍለው ተጨማሪ 3% ወለድ እንዲከፍል መክፈል ካቆመበት ቀን ጀምሮ ይታሰብበታል፡፡
- ህጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችና አጠቃላይ መስፈርቶች
ማንኛውንመ ብድር ከባንክ ለመውሰድ የሚፈልግ ሰው የሚከተሉትን ህጋዊ መስፈርቶች ማሟላት ይገባዋል፡፡
- የታደሰ የንግድ ፈቃድ፣
- ማንኛውም ዓይነት ብድር ከባንኩ የሚጠይቁ ጊዜ የታክስ ከፋይ መለያ ቁጥር ያስፈልግዎታል፣
- ግብር የከፈሉበትን ሰርተፍኬት ማቅረብ አለብዎት፣
- የገንዘብ አጠቃቀም ዝርዝር መረጃ፡
- ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች በባለቤትነት የተያዘ ንግድ ከሆነ የመተዳደሪያ ደንብና የመመስረቻ ፅሁፍ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
- የተንቀሳቃሽ የሂሳብ መዝገብ ላይ ምንም ዓይነት ጥሩ ያልሆነ የሥራ አካሄድ መኖር የለበትም፡፡
- የሌላ ባንክ ያልተከፈለ ብድር ሊኖር አይገባም፡፡
- ማንኛውንም ባንኩ የሚጠይቃቸውን ሰነዶች ማቅረብ ግዴታ ነው፡፡
- የሚጀምሩት የንግድ አንቅስቃሴ በገንዘብ አዋጪ፣ በኢኮኖሚም ቢሆን ትርጉም የሚሰጥ፣ በሕግና በአካባቢ ጥበቃ ተቀባይነት ያለው እንዲሁም በማህበረሰቡ የሚፈለግ መሆን አለበት፡፡
- ብድር ለመውሰድ የሚከናወኑ ተግባራት
- ብድር ለመጠየቅ ለባንኩ የማመልከዎ ደብዳቤ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ በደብዳቤዎ የሚበደሩት ገንዘብ መጠን፣ የሚከፍሉበትን ጊዜ (ለምሳሌ በወር፣ በሩብ ዓመት፣ በግማሽ ዓመት ወይም በሌላ) እንዲሁም ብድሩ የሚቆይበትን የጊዜ መጠን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡
- ቅድመ-ቃለ መጠይቅ፡- ከባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የብድሩን ዓይነት፣ ለምን ግልጋሎት እንደሚውል እና የብድሩን መጠን በቅድመ-ቃለ መጠይቅ ያካሂዳሉ፡፡
- ድጋፍ ሰጪ የሆኑ መረጃዎች ከማመልከቻ ደብዳቤው ጋር ተያይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡- የንግድ ፈቃድ፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት፣ በመያዣነት የሚያሲዙት ቋሚ ንብረት ሲሆን የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እና ሌሎችን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡
- የባንኩ ባለሙያዎች የሥራ ጉብኝት እና የቋሚ ንብረት ግምት፡- የድርጅትዎ የሥራ እንቅስቃሴ በባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ይጎበኛል፡፡ ይህም የድርጅቱን የንግድ ልውውጥ (እንቅስቃሴ) እንዴት እያካሄዱት ነው የሚለውን ለመገምገም ባንኩ ይጠቀምበታል፡፡
- የባንኩ የምህንድስና ባለሙያ በመያዣነት የተጠቀሙትን ቋሚ ንብረት ከተለያየ አቅጣጫ በማየት ግምት ያወጣል፡፡ ለምሳሌ፡- ያስያዙት ቋሚ ንብረት ግምታዊ ዋጋ፣ የሚገኝበት ቦታ፣ ያለው ጠቀሜታ፣ የንብረቱ ሁኔታ እና ሌሎች ጉዳዮችን ያጣራል፡፡
- የብድር አሰጣጥ ምዘና፡- ባንኩ ቀደም ብሎ በተጠቀሱት መረጃዎች መሰረት የተጠየቀው ብድር ይገባል አይገባም የሚለውን ያጣራል፡፡
- የባንኩ ውሳኔ
በመጨረሻም በደብዳቤ ውሳኔውን ያሳውቃል፡፡
- ባንኩ ማንኛውም የኮንትራት ውል ያጠናቅቃል፣ ምዝገባ ያካሂዳል እንዲሁም የተያዘውን ቋሚ ንብረት የኢንሹራንስ ሁኔታ ያጣራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ
- ባንኩ የተፈቀደውን ብድር መመሪያ እና ቅድመ ሁኔታዎች በተከተለ ሁኔታ ወደ እርስዎ የባንክ መዝገብ ያስተላልፋል፡፡
- ከብድር በኋላ ያሉ ሁኔታዎች፡- የተበደሩትን ገንዘብ በተቀመጠልዎ የጊዜ ገንዘብ በተፈራረሙት ኮንትራት መሰረት መክፈል ይኖርብዎታል፡፡
- ብድር ለመጠየቅ የሚወስደው ጊዜ፡- በንግድ ባንኮች በአማካይ 15 ቀናት ይወስዳል፡፡
በተመረጡ የንግድ ባንኮች ብድር ለመውሰድ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ባንኩ የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች
- የተጨማሪ ክፍያ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ብድር
- የአንድ ጊዜ የዕቃ ግዢ ብድር
- ቀጣይ የዕቃ ግዢ ብድር
- ለአስመጪዎች የሚሰጥ የመተማመኛ ሰነድ
- ቀጣይ የላኪዎች ብድር አገልግሎት (ፋሲሊቲ)
- የዋስትና ደብዳቤ
- የጊዜ ገደብ ብድር
- ለተሽከርካሪዎች መግዣ ብድር
- የግንባታ ማሽኖች
- የግብርና ምርት ማካሄጃ የጊዜ ገደብ ብድር
- ለጥቃቅንና አነስተኛ የብድር ተቋማት የሚሰጥ ብድር
- ለደንበኞች የሚሰጥ ብድር
- ለተሽከርካሪ ግዢ
- ለግንባታ ማሽኖች ግዢ
- ለቤት መግዣ ወይም መስሪያ
- ለቤት መኪና ግዢ
- ለጋራ መኖሪያ ቤቶች ግዢ
- ለትምህርት የሚሰጥ
- ለግል ጥቅም የሚውል
በመያዣነት የሚቀበላቸው ቋሚ ንብረቶች
- ሕንጻ
- ተሽከርካሪዎች
- የንግድ ቤቶች
- ተቀማጭ የባንክ ሂሳብ በመያዣነት የሚቀበላቸው
- የማጠራቀሚያ ሂሳብ
- ተንቀሳቃሽ ሂሳብ
- የጊዜ ገደብ ተቀማጭ ሂሳብ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ማረጋገጫ የማረጋገጫ ሰነድ
- በስምምነት የሚቀበላቸው
- የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶች
- የመንግስት ቦንድ
- የኢንሹራንስ ፖሊሲ የጥሬ ገንዘብ ዋጋ
- የጋራ ንብረት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት
- ዋስትና (ባንኮችን ወይም ግለሰብ)
- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ተጠቃሚዎች፡- የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ዋነኛ ተጠቃሚ ናቸው፡፡
ወለድ መጠን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዓመት ባበደረው ገንዘብ መጠን 7.5 በመቶኛ ወለድ ይሰበስባል፡፡ ባንኩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በማሰጠው መመሪያ መሰረት በወለድ መጠኑ ሊለያይ ይችላል፡፡ ሌሎች ባንኮች እንደሚያደርጉት ሁሉ የእፎይታ ጊዜ እንደኘሮጀክቱ ባህሪይ ታይቶ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚሰጣቸው የብድር
ዓይነቶች፡-
- የረጅም ጊዜ ብድር
- ለ20 ዓመት የሚቆይ ብድር ማንኛውንም የእፎይታ ጊዜ ጨምሮ
- ከ5-15 ዓመት ባሉት ጊዜያት ተከፍሎ የሚያበቃ ቋሚ የሥራ መስሪያ ካፒታል ብድር
- የመካከለኛ ጊዜ ብድር
- የሥራ ማስኬጃ ብድር፡- ይህም
የሥራ ሂደት ለማራዘም፣ አቅምን
ለመገንባት ወይም ለማሳደግ አና
በአጭር ሊከሰት የሚችል የገንዘብ
እጥረትን ለመሸፈን ይጠቅማል፡፡
- የጋራ ገንዘብ ማውጣት ወይም ለጋራ ጥቅም አብሮ ገንዘብን ወጪ ማድረግ፡፡
- የዋስትና አገልግሎት፣ ይኸውም ለላኪዎች የሚሰጥ የዋስትና አገልግሎት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መንግስት በሰጠው ትኩረት መሰረት ለመካከለኛ እና ለረጅም ጊዜ ወለድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች፡-
- ለንግድ ተግባር የሚውል የግብርና እንቅስቃሴ
- ለአምራች ኢንዱስትሪዎች
- ለግብርና ምርት ውጤት ኢንዱስትሪዎች
የወለድ መጠን፡- ከላይ ለተጠቀሱት የንግድ ዘርፎች 8.5 በመቶኛ ሲሆን ከእነሱ ውጪ ላሉት ግን 1 በመቶኛ ተጨማሪ ወለድ ያስከፍላል፡፡
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው፡- ባንኩ በመጀመሪያ መሰረት የሚያደርገው የኘሮጀክቱን አዋጪነት ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብድሩን ለመጠበቅ ሲባል ባንኩ የኘሮጀክቱን የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ሊጠይቅ ይችላል፡፡
ብድር ለመውሰድ የሚወሰደው ጊዜ፡- ብድር ለመውሰድ በዛ ቢባል 32 ቀናት ይወስዳል፡፡
- አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
- የተለመዱ የብድር ዓይነቶች፡
- ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- በመያዣነት የሚቀበላቸው ንብረቶች ከሌሎች የግል ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- ዳሸን ባንክ አ.ማ.
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች
- ተጨማሪ ክፍያ (ለሥራ ማካሄጃ ካፒታል)
- የጊዜ ገደብ ብድር (የአጭር ጊዜ እና ኘሮጀክት ማገዣ)
- የጥሬ ዕቃ መግዣ ብድር
- የአስመጪዎች ሰነድ ቅድሚያ ክፍያ
- ቀጣይ ተቀማጭ ሂሳብ በላይ የሚሰጥ ብድር (ወደ ውጭ የሚላኩ ዕቃዎች ሰነድ)
- ለውጭ ንግድ የዋስትና ደብዳቤ
ባንኩ በመያዣነት የሚከፍላቸው ንብረቶች፡- ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የተለመዱ የብድር ዓይነቶች፡-
- ለግብርና
- ለአምራቾች
- ለላኪና አስመጪነት ብድር
- ለንግድና አገልግሎት
- ለግንባታና ኮንስትራክሽን
- ለትራንስፖርት
- ወጋገን ባንክ አ.ማ.
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች፡-
- የጊዜ ገደብ ብድር
- የአጭር ጊዜ ብድር
- የመካከለኛ ጊዜ ብድር
- የረጅም ጊዜ ብድር
- የተጨማሪ ክፍያ
- ብድር ማሳወቂያ ደብዳቤ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ
- የቤትና መኪና መግዣ ብድር
- የዋስትና ማረጋገጫ ደብዳቤ
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው ንብረቶች
- የመኖሪያ ወይም የንግድ ቤቶች
- የንግድ ማካሄጃ መሣሪያዎች
- የጥሬ ዕቃ
- ተቀባይነት ያለው ዶሴ
- የአቢሲኒያ ባንክ አ.ማ.
- የጊዜ ገደብ ብደር
- የአጭር ጊዜ ብድር
- የመካከለኛ ጊዜ ብድር
- የረዥም ጊዜ ብድር (ኘሮጀክት ማስፈጸሚያ)
- ተጨማሪ ክፍያ
- የብድር ማረጋገጫ ደብደቤ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ብድር
- ወደ ውጭ በሚልኩ የንግድ ሰነዶች ተመርኩዞ የሚሰጥ ቅድመ ክፍያ
- ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የንግድ ሰነዶች ተመርኩዞ የሚሰጥ ቅድመ ክፍያ
- የዋስትና ማረጋገጫ ደብዳቤ
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው ንብረቶች
- ሕንፃዎች
- ተሽከርካሪዎች
- የንግድ ቤቶች
- በመያዣነት የሚቀበላቸው ተቀማጭ ሂሳቦች
- የቁጠባ ሂሳብ
- ተንቀሳቃሽ ሂሳብ
- በጊዜ ገደብ ተቀማጭ ሂሳብ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ሰነድ
- በስምምነት የሚቀበላቸው ሰነዶች
- የመንግስት የግምት ቤት ሰነዶች (ትሬዠሪ ቢል)
- የመንግስት ግዢ ቦንድ
- የኢንሹራንስ ፖሊሲ ጥሬ ገንዘብ ዋጋ
- የአክሲዮን ማህበር የምስክር ወረቀት
- ዋስተና (ባንክ ወይም ግለሰብ)
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ሰነድ
- በስምምነት የሚቀበላቸው ሰነዶች
- የመንግሰት የግምጃ ቤት ሰነድ
- የመንግሰት ግዢ ቦንድ
- የኢንሹራንስ ፖሊሲ የጥሬ ገንዘብ ዋጋ
- የአክሲዮን ማህበር የምስክር ወረቀት
- ዋስትና (ባንክ ወይም ግለሰብ)
የባንኩ የብድር አገልግሎት ዋነኛ ተጠቃሚዎች በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ባንኩ ለሚከተሉት የንግድ ዘርፎች ብድር ይሰጣል፡-
- በአገር ውስጥ ንግድ ለተሰማሩ
- በትራንስፖርት ለተሰማሩ
- አስመጪዎች
- ባለ ኢንዱስትሪዎች
- በግንባታ ለተሰማሩ
- ለላኪዎች
- በግብርና ለተሰማሩ
- የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ለሚነግዱ
- ሕብረት ባንክ
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች እላይ ከተጠቀሰው ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የባንኩ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች፡ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች የባንኩ ዋኒኛ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ ከእነሱ በተጨማሪ
- በአገር ውስጥ ንግድ የተሰማሩ
- በውጭ ንግድ የተሰማሩ
- ባለፋብሪካዎች
- በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ
- በትርንስፖርት ዘርፈ የተሰማሩ
- በግንባታ ሥራ የተሰማሩ
- በሆቴሎችና ቱሪዝም
- ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
በመያዣነት የሚቀበለባቸው ንብረቶችና ሰነዶች እንደዚህም የተለመዱ የብድር አገልግሎቶች እላይ ከተጠቀሱት ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች፡- አንበባ ባንክ ብድሩን በማስፋት በሁለቱም ማለትም በጊዜ ገደብ እንዲሁም በተጨማሪ ክፍያ ለባለሀብቱ (ኢንቨስተሩ) እና ለንግዱ ማህበረሰብ በማንኛውም መስክ ቢንቀሳቀሱ የብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዋነኛ የባንኩ አገልግሎቶች
- ከሂሳብ ተቀማጭ በላይ ተጨማሪ ክፍያ
- የጊዜ ገደብ ብድር
- የአጭር ጊዜ
- የመካከለኛ ጊዜ
- የረዥም ጊዜ
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ብድር
- ለግለሰብ የሚሰጥ ብድር
- ለአስመጪዎች የሚሰጥ የብድር አገልግሎት
- ለላኪዎች የሚሰጥ ቀጣይና ከጭነት በፊት የሚሰጥ ብድር
- የዋስትና ደብዳቤ
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው ንብረቶችና ሰነዶች
- ንብረቶች (ይዞታ፣ ሕንጻዎች እና መኖሪያ ቤቶች)
- ተሽከርካሪዎች
- ጥሬ ዕቃ (ሸቀጣ ሸቀጥ)
- የግንባታ ማሽኖች
- የባንክ ዋስትና ደብዳቤ
- የባንክ ተቀማጭ
በስምምነት የሚቀበላቸው ሰነዶች
- የመንግስት የግምጃ ቤት ጨረታ ሰነድ
- የኢንሹራንስ ፖሊሲ የጥሬ ገንዘብ ዋጋ
- የመንግስት ቦርድ
- የሌሎች ባንኮች የአክሲዮን የምስክር ወረቀት
- በሊዝ የተገዛ መሬት እና ሌሎችም
- የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ አ.ማ.
የኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ የብድር አገልግሎቱን በማስፋት በሁለቱ ማለትም በጊዜ ገደብ እና በተጨማሪ ክፍያ በማንኛውም መስክ ለሚሰሩ የንግዱ ማህበር አባላት የብድር አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ዋነኛ የሚሰጣቸው አግልግሎቶች፡-
- ከተቀማጭ ሂሳብ ተጨማሪ ክፍያ
- ኦቨር ድሮዋል
- የጊዜ ገደብ ብድር
- የአጭር (1 እስከ 3 ዓመት)
- የመካከለኛ (3 እስከ 5 ዓመት)
- የረጅም (ከ5 ዓመት በላይ)
- የጥሬ ዕቃ ግዢ ብድር (የአንድ ጊዜ ወይም)
- የአስመጪዎች መተማመኛ ሰነድ
- የላኪዎች ብድር
- ለላኪዎችና አስመጪዎች የቅድሚያ ክፍያ
- የዋስትና ሰነድ
ባንኩ ከዚህ በተጨማሪ
- በአገር ውስጥ ንግድ
- በግብርና
- በግንባታ
- በውጭ ንግድ
- በትራንስፖርትና በመሳሰሉት ለተሰማሩ ነጋዴዎች የብድር አገልግሎት ይሰጣል፡፡
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው ንብረቶችና ሰነዶች
- የታገደ ጥሬ ገንዘብ
- ንብረቶች (ይዞታ፣ ሕንጻዎች እና መኖሪያ ቤቶች)
- ሕንጻዎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶች
- ተሽከርካሪዎች (ሸቀጣ ሸቀጥ)
- የግንባታ ማሽኖች እና መገልገያዎች
- የባንክ ዋስትና ደብዳቤ
- የባንክ ተቀማጭ
- በስምምነት የሚቀበላቸው ሰነዶች
- የመንግስት የግምጃ ቤት ጨረታ ሰነድ
- የኢንሹራንስ ፖሊሲ የጥሬ ገንዘብ ዋጋ
- የመንግስት ቦርድ
- የሌሎች ባንኮች የአክሲዮን የምስክር ወረቀት
- የዋስትና ደብዳቤ (ከግለሰብ)
- የዋስትና ደብዳቤ (ከማህበራት)
- በሊዝ የተገዛ መሬት እና ሌሎችም
የእፎይታ ጊዜ፡- ከባንኩ የእፎይታ ጊዜ ለማግኘት ገንዘቡ ለታቀደለት መርሃ-ግብር መዋል አለበት፡፡ እስከ ዓመት የሚቆይ የእፎይታ ጊዜ ባንክ ይሰጣል፡፡
የክፍያ ጊዜ፡- በየወሩ ወይም በየዓመቱ ሊከፈል ይችላል እንዲሁም በአንድ ጊዜ ክፍያ ሊሆን ይችላል፡፡
የወለድ ክፍያ መጠን፡- ከ8.5 እስከ 12 በመቶኛ በግብርናው ዘርፍ ያስከፍላል፡፡
- ዘመን ባንክ አ.ማ.
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች፡-
- ንግድን በተያያዘ የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች፡-
- የሥራ ካፒታል (ከ1 እስከ 2 ዓመት)
- ለኘሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚሆን ብድር
- ለሀገር ውስጥ ለውጭ ባንኮች የዋስትና ማረጋገጫ
- የቤት ግንባታ ብድር (ለግንባታም ሆነ ለመግዛት) (ከ1 እስከ 5 ዓመት)
- የመኖሪያ ቤት ግንባታ
- የንግድ ቤት ግንባታ
- የሸማች (የተጠቃሚ) ብድር (ከ1 እስከ 3 ዓመት)
- ለግል ዕቅድ የሚውል
- የቤት መኪና ለመግዛት
- ለሕክምና ወጪ እና ለሌሎች የሚውል ብድር
ባንኩ በመያዣነት የሚቀበላቸው፡- ከኦሮሚያ የሕብረት ሥራ ባንክ አ.ማ. ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- ባንኩ በተለይ ብድር የሚሰጥባቸው ዘርፎች
- ለግብርና
- ለአምራቾች
- አስመጪና ላኪ ንግድ
- ንግድ እና አገልግሎት
- ለሕንጻ እና ግንባታ
- የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
የሚሰጣቸው የብድር ዓይነቶች፡- ከሌሎቹ የግል ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
በመያዣነት የሚጠቀማቸው ንብረቶችና ሰነዶች፣ ከሌሎቹ የግል ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- ብርሃን ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
ባንኩ የሚያቀርባቸው የብድር ምርቶች፡- ብርሃን ባንክ በሀገራችን አዲስ ከተቋቋሙት ባንኮች አንዱ ሲሆን በጊዜ ገደብ ብድርንና ከተቀማጭ ሂሳብ በላይ ተጨማሪ ክፍያ አገልግሎቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለሚሠሩ ነባርና አዲስ ደንበኞቹ ያቀርባል፡፡ ባንኩ የሚሰጣቸው ዋና ዋና የብድር አገልግሎቶች አብዛኞቹ የንግድ ባንኮች ከሚሰጧቸው ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ተቀባይነት ያላቸው ማስያዣዎች፡- ከኦሮሚያ የህብረት ሥራ ባንክ አ.ማ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
የእፎይታ ጊዜ፡- በብርሃን ባንክ ለብድር እፎይታ ለማግኘት ብድሩ ኘሮጀክቶች ላይ መዋል አለበት፡፡ ማሽን ለመገንባት ከሆነ የእፎይታ ጊዜው ከ1 እስከ 2 ዓመታት ሊረዝም ይችላል፡፡
መልሶ የመክፈያ ጊዜ፡- ከወርሃዊ እስከ ዓመታዊ ሊረዝም ይችላል፡፡
የወለድ መጠን፡- በባንኩ የሚከተሉትን ዝቅተኛ የወለድ መጠኖች ሊያገኙ ይችላሉ፡-
- 5% ለውጭ የመላኪያ ብድር
የማስያዣ ሽፋን መጠን፡- እያበበ ያለ ንግድ ከሆነ ያለዎት ከጠየቁት ብድር 20% ያህሉን በማስያዣነት ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡
የብድር ሒደት እንቅስቃሴዎችና መስፈርቶች፡- ከብርሃን ባንክ ብድር ለማግኘት የሚከተሉትን ማድረግ ያስፈልጋል፡-
- የብድር ጥያቄ ማቅረብ
- የቅድሚያ ቃለ ምልልስ ማካሄድ
- መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ማሟላትና የማመልከቻ ደብዳቤ ማዘጋጀት
- ጥቁር መዝገብንና ብድር መክፈል ያለመቻልን አስመልክቶ የብድር መረጃን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መውሰድ
- አጠቃላይ መስፈርቶችን ማሟላት፡ የንግድ ፍቃድ፣ የግብር መለያ የምሰክር ወረቀት፣ ከግብር ነፃ ወረቀትና የመሳሰሉት
አጠቃላይ ማስረጃዎችን ማቅረብ፡- የባለቤትነት የምስክር ወረቀት፣ ዕቅድና ለኘሮጀክቶች የንግድ ዕቅድ
የንግድ ዕቅድን ማቅረብ፡- የንግዱ ዳራ፣ በገቢና ወጪ ማመሳከሪያ (በባላንስ ሺት) የተደገፈ የመጪ ጊዜ የገንዘብ ዕቅድ፣ የገንዘብ ፈሰትና የገቢ መግለጫዎች የተካተቱበት የንግድ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የታሰበው ንግድ የፍላጎትና የአቅርቦት መጠን ሊገለፅ ይገባል፡፡
አዲስ ንግድን ለመጀመሪያነትና ነባሩን ለማስፋፊያነት የሚሆን ብድርን የመስጠት ፈቃደኝነት፡- ያለው ብቸኛ ችግር የአዲሱን ንግድ አዋጭነት መለካት ላይ ነው፡፡ አዋጭነቱ ከተለካ በኋላ ግን ብርሃን ባንክ ብድር ሊሰጥ ይችላል፡፡
ለተበዳሪው የሚሰጥ ምክር፡- ብድሩ ተከፍሎ እስከሚያልቅ ድረስ ብድሩን ከታሰበለት ዓለማ ውጪ መጠቀም አሳሳቢ እንቅስቃሴ ነው፡፡
ለጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች የተዘጋጀ ልዩ መመሪያ፡- እስከ አሁን ድረስ በባንኩ ለንግድ ድርጅቶቹ የሚሠራ ልዩ መመሪያ የለም፡፡ ነገር ግን ብርሃን ባንክ ከጀርመን ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራርመው ለንግድ ድርጅቶቹ ከፊል የብድር አገልግሎት ከሚሰጡት ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡
- ቡና ኢንተርናሽናል ባንክ አ.ማ.
ባንኩ የሚያቀርባቸው የብድር ምርቶች፡- ቡና ባንክ በሀገራችን አደስ ከተቋቋሙት ባንኮች አንዱ ሲሆን የጊዜ ገደብ ብድርንና ከተቀማጭ ሂሳብ ተጨማሪ የሚከፈል አገልግሎትን በተለያዩ ዘርፎች ለሚሠሩ ነባርና አዲስ ደንበኞቹ ያቀርባል፡፡ በምርት ዓይነትና በዘርፍ ባንኩ የሚሰጣቸው ዋና ዋና የብድር አገልግሎቶች እላይ ከተጠቀሰው የኦሮሚያ የህብረት ሥራ ባንክ ኢ.ማ ከሚሰጣቸው ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡
ተቀባይነት ያላቸው ማስያዣዎች፡- ከኦሮሚያ የህብረት ሥራ ባንክ አ.ማ ጋር ተመሳሳይ ናቸው፡፡
የእፎይታ ጊዜ፡- ለማሽን ግንባታ ከ1 እስከ 2 ዓመት ይደርሳል
መልሶ የመክፈያ ጊዜ፡- ከወርሀዊ እስከ ዓመታዊ
የማስያዣ ሽፋን መጠን፡- ቡና ባንክ ማስያዣ ሲያቀርቡ ማስያዣዎ ከ85% እስከ 115% ሊገመት ይችላል፡፡
የብድር ሒደት አንቅስቃሴዎችና መስፈርቶች፡- እላይ ከተጠቀሰው ከብርሃን ዓለም አቀፍ ባንክ አ.ማ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡
- አዲስ ባንክ አ.ማ.
ባንኩ የሚያቀርባቸው የብድር አይነቶች፡- አዲስ ባንክ የጊዜ ገደብ ብድርንና ከተቀማጭ ሂሳብ ተጨማሪ የሚከፈል አገልግሎትን በተለያዩ ዘርፎች ለሚሠሩ ነባርና አዲስ ደንበኞቹ ያቀርባል፡፡ የኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ከሚያቀርባቸው የብድር አገልግሎቶች በተጨማሪ አዲስ ባንክ ከመተማመኛ ሰነድና ከሽያጭ ኮንትራት ቅድሚያ የሚሰጡ አገልግሎቶች (አድቫንስ አጌንስት ሪቮኬብል ኤልሲ እና አድቫንስ አጌንስት ሴልስ ኮንትራክት) አሉት፡፡
በዘርፍ ሲታይ አዲስ ባንክ የሚከተሉትን ያቀርባል፡-
- በሀገር ውስጥ ንግድ አገልግሎቶች – የመጓጓዣ፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ
- በዓለም አቀፋዊ ንግድ፣ ማስመጣት/መላክ፣ የመተማመኛ ሰነድ
- ግብርና
- የጭነት መኪና
- ግንባታና ሌሎችም
ተቀባይነት ያላቸው ማስያዣዎች፡- ከኦሮሚያ የህብረት ሥራ አ.ማ ጋር ተመሳሳይነት ነው
የእፎይታ ጊዜ፡- ለመሥሪያ ካፒታልነት የተለቀቀ ብድር ላይ ምንም የእፎይታ ጊዜ የሌለ ሲሆን ለግንባታ ግን እስከ አንድ ዓመት የእፎይታ ጊዜ ይሰጣል፡፡
የመልሶ መክፈያ ጊዜ፡-
- ወርሃዊ፡-ለሀገር ውስጥ ንግድ አገልግሎቶች
- በየ3 ወሩ፡- ለግንባታ
- በየ6 ወሩ
- በየዓመቱ፡- ለግብርና
- በጥቅሉ
ብድሩ የሚያተኩርባቸው ደንበኞች፡-
- ባንኩ የሚጠይቃቸውን አጠቃላይና ውስን የብድር መስፈርቶች እስካሟሉ ድረስ እንደ ግለሰብ፣ ኃ.የተ.የግ.ማ፣ ማህበርና ሌሎችም የባንኩን የብድር አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
- ባንኩ አዲስ ለሚቋቋሙ ንግዶችም ሆነ መስፋፋት ለሚሞክሩ አትራፊ ንግዶች በመርሆ ደረጃ ለማበደር ፈቃደኛ ነው፡፡
- የባንኩ የብድር አገልግሎት በወኪሎች በኩል ሊሰጥዎት ይችላል፡፡
- ቢያንስ የአንድ ዓመት ልምድ እንደ ብድር መስፈርት ሊጠየቅ ይችላል፡፡ ለብድር ብቁነት፣ ሕጋዊነት፣ ፈቃደድና የግብር ነፃነት ግዴታ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
የወለድ መጠን፡- የሚከተሉትን ዝቅተኛ የወለድ መጠኖች ሊጠየቁ ይችላሉ፡-
- 8% ለውጭ መለኪያ ብድር
- 15% ለጭነት መኪና ብድር
- 5% ለመሥሪያ ካፒታል
- 75% ለግንባታ ብድር
የማስያዣ ሽፋን መጠን ከአዲስ ባንክ ብድር ለማግኘት ያቀረቡት ማስያዣ በ95%፣ 90%፣ 70% እና 65% ቅናሽ ሊኖረው ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- ሕንፃው አደስ ከሆነ ከፍተኛው ቅናሽ የሆነውን 95% ሊያገኝ ይችላል፡፡
የብድር ሒደት እንቅስቃሴዎች፡ ከአዲስ ባንክ ብድር ለማግኘት የሚከተሉትን እንቅስቃሴዎች ማድረግ ሊጠበቅባችሁ ይችላል፡-
- የብድር ጥያቄ ማቅረብ
- የቅድሚያ ቃለ ምልልስ ማካሔድ
- መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ማሟላትና የማመልከቻ ደብደቤ ማዘጋጀት
- ጥቁር መዝገብንና ብድር መክፈል ያለመቻልን አስመልክቶ የብድር መረጃን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባነክ መውሰድ
- አጠቃላይ መስፈርቶችን ማሟላት
- የንግድ ዕቅድ ማቅረብ
ብድሩ የሚያተኩርባቸው ደንበኞች፡-
የብድር ዓይነት | ኢላማ (ገጠር፣ከተማ፣ ሴቶች፣ ማህበራት፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት ወ.ዘ.ተ) |
ተቆራርጦ የሚከፈል ብድር | ሁሉም ብቁ ናቸው |
የጊዜ ገደብ ብድር | “ “ |
በጥቅል የሚከፈል ብድር | “ “ |
የግብአት ብድር | “ “ |
አዲስ ለሚጀምሩ ንግዶች ለማበደር ያለ ፈቃደኝነት፡- ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያቋረጡ፣ የካሌጅ ተመራቂዎችና ተመሳሳይ ቡድኖች
ተቋማዊ ፖሊሲዎች የሚከለሱበት ድግግሞሽ፡- ውስጥ የድግግሞሽ ጊዜ የለም
የቁጠባ አይነቶች፡- የቁጠባ ደብተር ሂሳብ (6% ወለድ) እና የጊዜ ተቀማጭ (6-7%)
ሌሎች አገልግሎቶች፡- ሥልጠና፣ ሀዋላ፣ የጡረታ ክፍያ
የአገልግሎት ማቅረቢያ፡- በቅርንጫፍ/ንዑስ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል፣ የገበሬ ማህበራት፣ ወረዳዎች፣ ቀበሌዎችና የደንበኞች ቤት ድረስ በመሔድ
አደስ የሚተዋወቁ የብድር አይነቶች፡- የመጠለያ ብድር
የብድርና ቁጠባ ተቋማት
- አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም
የብድር አገልግሎቶች/ምርቶች፡-
- በጊዜ ገደብ የሚሰጥ ብድር
- በተከፋፈለ ጊዜ የሚከፈል የቋሚ ክፍያ ብድር (ኢንስቶልመንት)፡ በጊዜ ገደብ የሚሰጡና በተከፋፈለ ጊዜ የሚከፈሉ የቋሚ ክፍያ (ኢንስቶልመንት) የጥቃቅን የንግድ ድርጅቶች ብድር፣ የቡድን ብድር፣ የግለሰብ ብድር፣ የህብረት ሥራ ብድር፣ ህብረተሰብን መሠረት ላደረጉ ድርጅቶች የሚሰጥ ብድርና የንግድ ብድር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ዓመታዊ የማበደሪያ መጠን፡
- የጊዜ ገደብ ለሚሰጡ ብድሮች 12% ከተጨማሪ 3% ዓመታዊ የአገልግሎት ክፍያ ጋር
- ለኢንስቶልመንት ብድሮች 10% ከተጨማሪ 3% ዓመታዊ የአገልግሎት ክፍያ ጋር
ለጥቃቅን ኢንተርኘራይዞች ብድር የብድር መጠን፡
ኡደት (ዙር) | መጠን (ብር) |
1ኛ | እስከ 2000 |
2ኛ | 3000 |
3ኛ | 4000 |
4ኛ | 5000 |
5ኛ | 5000 |
የንግድ ብድር የብድር መጠን፡
ኡደት (ዙር) | መጠን (ብር) |
1ኛ | 5000 |
2ኛ | 6000 |
3ኛ | 7000 |
4ኛ | 9000 |
5ኛ | 10000 |
የብድር ጊዜ፡- ከፍተኛው የብድር ጊዜ 36 ወራት ሲሆን ዝቅተኛው የብድር ጊዜ ደግሞ 7 ወራት ነው
እስካሁን የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገባቸው ያሉ ምጣኔ ሀብታዊ (ኢኮኖሚያዊ) እንቅስቃሴዎች
- የመግዛትና መሸጥ እንቅስቃሴዎች
- የሴት ፀጉር ሥራ/ የውበት ሳለንና የወንድ ፀጉር ቤት
- ልብስ ስፌት
- ትንሽ ምግብ ቤቶች
- የቧንቧ ሥራና የኤሌክትሪክ ዕቃዎችና የጫማ ጥገና እንዲሁም ልብስ ማጠብ
- ሜካኒክ፣ የጋሪ መጓጓዣ
- ዕደ ጥበብና የማምረት እንቅስቃሴዎች
- የጥልፍ ሥራ
- የእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ
- ሽመና
- የቆዳና የቀርከሀ ሥራ
- የወርቅና የብር አንጥረኝነት
- የወረቀት ቦርሳ ማምረት
- ሻማ መምረት
- ምድጃ ሥራ
የእፎይታ ጊዜ፡- ለማንኛውም ዓይነት ብድር የ30 ቀናት የእፎይታ ጊዜ አለ
የብድሩን ሒደት ለመጨረስ የሚያስፈልግ ጊዜ፡- ለቡድን ብድር 15 ቀናትና ለግለሰብ ብድር ቢበዛ 7 ቀናት
የንግድ ዕቅድን ማቅረብ፡- አዲስ የብድርና ቁጠባ አ.ማ ተበዳሪዎች እንደ ንግድ ዕቅድ ሊያገለግሉ የሚችሉ የማመልከቻ ፎርሞች እንዲሞሉ ይጠይቃል፡፡
ብድሩ የሚያነጣጥርባቸው ደንበኞች
- የጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶችና የራሳቸውን ሥራ ለመሥራት ቁርጠኛ የሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችና ሴቶች
- በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ የህብረት ሥራ ማህበራት
- እንደ እድር ያሉ ህብረተሰብን መሠረት ያደረጉ ድርጅቶች፡፡ እድሮቹ ከአባሎቻቸው መካከል በጣም ደሀ የሆኑትን ይመርጣሉ
- ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን፣ ኮሌጅ እንዲሁም ዩኒቨርሲቲን የጨረሱ ተመራቂዎች ገቢ ማስገኛ እንቅስቃሴዎች ውስጥ እስከተሳተፉና በቡድን ማስያዣ ብድር ለመውሰድ እስከፈለጉ ድረስ አዲስ የጀመሩት ንግዶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ተበዳሪዎች በሚመለከተው የቀበሌ የብድርና ቁጠባ ኮሚቴ የሚመለመሉ ወይም የሚመረጡ ይሆናሉ፡፡
አዲስ ለሚመሰረት ንግድ ለማበደር ያለ ፈቃደኝነት፡- ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ላቋረጡ፣ የኮሌጅ ተመራቂዎችና የመሳሰሉት ቡድኖች አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ የሥራ ፈጣሪነቱ ቁርጠኝነት እስካላቸው ድረስ ሥራ አጥ ለሆኑና አዲስ ንግድ ለሚጀምሩ አገልግሎቱ ይሰጣል
ለብድሩ ብቁ የሚያደርጉ መስፈርቶች፡- የብድር ደንበኛ የሚሆኑ ሁሉ የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል
- የአዲስ አበባ ነዋሪ መሆን
- ከ18 ዓመት እድሜ በላይ መሆን
- በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ መሆን ወይም ለመሰማራት ዝግጁ መሆን
- ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው መሆን፣ ሰርቲፊኬት፣ ፈቃድ
- የቴክኒክና የሙያ ሥልጠና ተመራቂ ሆኖ ለህብረት ሥራ ማህበር ወይም በንግድ ቡድን የተደራጁ መሆን
- የተቋሙን ሕጎችና መመሪያዎች ለመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጁ መሆን
- ቋሚ የሥራ ቦታ መኖር
ለተበዳሪዎች የሚሰጥ ምክር፡- የተቋሙ ሁሉም ደንበኞች በተለይም የብድር ደንበኞች ብድር ከመውሰዳቸው በፊት የማሳወቂያ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ የማሰወቂያ ሥልጠና በብድሩና በአሰጣጡ ዓይነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
የቡድን/የህብረት ሥራ ብድሮች፡- የሚያስፈልገው የማሳወቂያ ሥልጠና ለቡድን/የህብረት ሥራ አባላት ከ15 ቀናት ላላነሰና ከወር ላልበለጠ ጊዜ በአራት የግንኙነት ጊዜያት ይሰጣል
የግለሰብ ብድር ደንበኞች፡- የተቋሙን ዓላማዎች፣ የደንበኛውን መብቶችና ግዴታዎች፣ የብድር ዓይነቶች፣ ወዘተ አስመልክቶ ከአንድ ሰዓት ያልበለጠ የማሳወቂያ ሥልጠና ይሰጣል፡፡
የብድር አገልግሎት አይነቶች፣ ወለድና የብድር ጊዜ፡
የምርት ዓይነት | መስፈርት | ዝቅተኛ መጠን (በብር) | ከፍተኛ መጠን (ብር) | ከፍተኛ የብድር ጊዜ (ወራት) | የወለድ መጠን | የአገልግሎት ክፍያ | የመድህን መጠን/ ዓመት |
ጥቃቅን ብድር |
በአነስተኛ
ንግድ፣ ምግብን በሒደት ውስጥ ማሳለፍ ወዘተ የተሰማሩ |
700 |
5000 |
24 |
9% |
2% |
1% |
አነስተኛ ብድር |
መነሻ ካፒታሉ ከ5000 ብር በላይ የሆነ፡፡ የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ንግዶች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡ |
5000 |
250000 |
36 |
9% |
2% |
1% |
የፍጆታ ብድር |
በቡድን ማስያዣ ብድር ይሰጣል፡፡ ለመንግሥት ቋሚ ሠራተኞች |
700 |
1000 |
24 |
10% |
— |
1% |
የግብርና ብድር |
እንስሳት እርባታ፣ ማደለብ፣ ግብርና ወዘተ |
700 |
250000 |
18 |
9% |
2% |
1% |
የጥቃቅን ኪራይ ብድር | ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና የህብረት ሥራ ማህበራት |
— |
250000 |
36 |
9% |
2% |
2% |
የአጭር ጊዜ ብድር |
በማንኛውም ሕጋዊ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች |
30000 |
100000 |
6 |
1.5/ወር |
— |
1% |
የቤት ብድር | የቤቱ ሕጋዊ ባለቤትነትና ቋሚ ገቢ |
700 |
50000 |
60 |
10% |
2% |
2% |
ማስያዣዎች፡ ተቋሙ ለሚሰጣቸው ብድሮች የተለያዩ ዓይነት የብድር ዋስትናዎችና የንብረት ማስያዣዎችን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ እነዚህም፡
የትብብር ቡድን ማስያዣ
የጓደኛ ተፅዕኖ ማስያዣ፡ ይህንን የዋስትና አማራጭ የሚጠቀሙ የብድር ደንበኞች ከ3 እስከ 5 አባላት ያሉት ቡድን ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ አሠራር እያንዳንዱ የቡድን አባል ማንኛውም የቡድን አባል ያልከፈለው ቀሪ ብድር ላይ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡
የቡድን መሪ ዋስትና/ማስያዣ፡ ከላይ ከተገለፀው ዘዴ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን ላልተከፈለው ቀሪ ብድር ለቡድኑ መሪ ተጨማሪ ኃላፊነት በመስጠቱ ይለያል፡፡ በዚህ አሰራር የቡድነ መሪ የተወሰነ ንብረት ወይም አብሮ የሚፈርም ሰው ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡
የአንዱ ለሌላው የሚሆን (ክሮስ) ዋስትና/ማስያዣ፡ በዚህ አሠራር ሁሉም የቡድኑ አባላት ቤተሰብ ወይም ሌላ ማንኛውንም ሰው እንደ ዋስትና ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ላልተከፈለ ቀሪ ብድር ቅድሚያ ኃላፊነቱ ለቡድን አባላት ቢሰጥም ይህንን ዓይነቱን ዋስትና የፈረመው ሰው ኃላፊነት አለበት፡፡
ጥቃቅን የክራይ ብድር ዋስትና፡ በማንኛውም ሶስተኛ ወገን ወይም ደንበኛ በስምምነት ከተወሰነ ቦታ ለማሽን/ለመገልገያዎች እንቅስቃሴ ከለላ የሚሰጥ ግለሰብ፣ ድርጅት ወይም ማንኛውም ሌሎች ተቋማት
የግል ዋስትና፡ በቀጣሪው የጽሁፍ ስምምነት ላይ ተመስርቶ ብድሩ ለደንበኛው ይሰጣል፡፡ ልዩ ውሳኔ ካልተሰጠ በስተቀር በዚህ መንገድ የሚሰጥ ብድር ከ50 ሺህ ብር አይበልጥም፡፡
የንብረት ማስያዣ፡ በንብረት ማስያዣ ላይ ተመስርቶ ብድር ይሰጣል፡፡ የዚህ ዓይነቶ ማስያዣ የተለያዩ አማራጮች አሉ፡-
የቤት ማስያዣ፡ የብድር ፍላጎታቸው ከ50 ሺህ ብር ለሚበልጥ ግለሰቦች እንዲሁም ኢንተርኘራይዞች ቤቱ ከዋና ከተማው ውስጥ ወይም አዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ እስካለ ድረስ ማስያዣውን ከራስ ንብረት ወይም ማንኛውም ሶስተኛ ወገን ማድረግ ይቻላል፡፡
ተሽከርካሪዎች፡ በአዲስ አበባና በአቅራቢያው ባሉ የኦሮሚያ ዞኖች የትራንስፓርት ባለሥልጣን መ/ቤቶች በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች እንደ ማስያዣ ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡
ማሽኖች፡- ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ የማይንቀሳቀሱና በንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች የተመዘገቡ ማሽኖች እንደ ማስያዣ ያገለግላሉ፡፡ የማሽኑ ዋጋ ከብድሩ 50% በላይ መሆን ሲኖርበት የተገዛበት ጊዜ ደግሞ 5 ዓመት ወይም ከዚያ ወዲህ መሆን አለበት፡፡
የቁጠባ ማስያዣ፡ ሁሉም የተቋሙ የቁጠባ ደንበኞች ቁጠባቸውን እንደ ማስያዣ በመጠቀም ብድር ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ በዚህ መንገድ የሚሰጠው ብድር መጠን ከቁጠባው 125% በላይ መሆን አይችልም፡፡
ከተቋሙ ውጭ ሌሎች ባንኮች ውስጥ ያለ የቁጠባ ተቀማጭ፡- ከተቋሙ ብድር የሚፈልጉ በማናቸውም የንግድ ባንኮች የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን ቁጠባዎች እንደ ማስያዣ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይህንን አማራጭ ለመጠቀም ባንኩ በቅድሚያ ተቋሙ ማረጋገጫ አስካልሰጠው ድረስ የቁጠባው አስቀማጭ ወጪ እንዲያደርግ እንደማይፈቅድ የጽሁፍ ማረጋገጫ ሊሰጠው ይገባል፡፡
የሚወሰድ ገንዘብ፡ ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ማንኛውም ዓይነት ገንዘብ የሚቀበል ግለሰብ/ቡድን ወይም የህብረት ሥራ ማህበር በቀጣሪው የጽሁፍ ማረጋገጫ ከሚቀበለው ገንዘብ እስከ 75% ድረስ ብድር እንዲወስድ ይፈቀድለታል፡፡
ቼክ ከሌላ ማስያዣ ጋር፡ ይህ ዓይነቱ ማስያዣ ለአጭር ጊዜ የብድር ዓይነት ብቻ ይፈቀዳል፡፡ በዚህ አሠራር የብድር ደንበኛው ወይም ማንኛውም ሌላ ሰው ብድሩ ተከፍሎ ማለቅ ባለበት ቀን ለአዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም የሚከፈል ቼክ ይፈርማል፡፡ ፈራሚውም በሒሳብ ውስጥ የተወሰነ የገንዘብ መጠን በየብድሩ የጊዜ ገደብ ማለቂያ ላይ ማጠራቀም ይኖርበታል፡፡
የትምህርት ማስረጃ አብሮ ከሚፈርም ቤተሰብ ጋር፡ የቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ወይም ማንኛውም ሌላ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂዎች የትምህርት ማስረጃቸውን እንደ ማስያዣ በመጠቀም እስከ 5 ሺህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ሊበደሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኮሌጁ አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም እስኪነግረው ድረስ ለብድር ደንበኛው ዋናውን የትምህርት ማስረጃ ሰነድ እንደማይሰጥ ለተቋሙ ለማረጋገጥ ፈቃደኛ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በላይ የብድር ደንበኛው ቤተሰብ ኃላፊነት ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆን አለበት፡፡
የንግድ ማስያዣ፡ ጊዜያቸው ጠብቀው ብድራቸውን የሚከፍሉ በመሆናቸው የሚታወቁ ተደጋጋሚ ተበዳሪዎች እስከ 5 ሺህ ብር ለሚደርስ የሶስተኛ ወገን ብድር ዋስ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ ደንበኞች የንግድ ካፒታላቸው ከ50 ሺህ ብር በላይ መሆኑ የሚገመት ከሆነ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር የንግድ ንብረታቸውን አስይዘው ሊወስዱ ይችላሉ፡፡
የመድህን ቦንድ፡ አንድ ደንበኛ ታዋቂ ከሆነ የመድህን ድርጅት የዋስትና ሽፋን ያለው ከሆነና የመድህን ድርጅቱ ደንበኛው በተያዘው ዕቅድ መሠረት መልሶ መክፈል ባይችል ያልተከፈለውን ቀሪ እንደሚከፍል የጽሁፍ ማረጋገጫ የሚሰጥ ከሆነ ደንበኛው የመድህን ሽፋኑን 75% እንዲከፍል ይፈቀድለታል፡፡
ሕጋዊ ተቋማት፡ እድሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም ማናቸውም ሕጋዊ ተቋማት ብድር መውሰድ ወይም ዋስ መሆን ይችላሉ፡፡
ሌሎች አገልግሎቶች
የቁጠባ አገልግሎት
አስገዳጅ ቁጠባ፡ ይህ ቁጠባ የብድር ደንበኞችም ሆኑ የብድር ያልሆኑ ደንበኞች የተቋሙን የብድር አገለግሎቶች ለማግኘት ብቁ ለመሆን ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቁጠባ ነው፡፡ አስገዳጅ ቁጠባ የደህንነትና ወርሀዊ ቁጠባ ሊሆን ይችላል፡፡
የኮንዶሚኒየም የቅድሚያ ክፍያ ቁጠባ፡ ለኮንዶሚኒየም ቤት የተመዘገቡና ቢደርሳቸው የቅድሚያ ክፈያውን ለመክፈል አቅም የሚያጥራቸው ሰዎች ለዚህ ዓላማ በተቋሙ ቁጠባ ያላቸው ከሆነ ብድር ይሰጣቸዋል፡፡ ደንበኛው የአስገዳጅ ቁጠባውን 1% በየወሩ ቢያንስ ለ12 ወራት መክፈልና የቅድመ ክፍያውን ቀሪ በአንዴ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡
በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቁጠባ
ተበዳሪ ደንበኞች፡- ሁሉም የተቋሙ ደንበኞች ለብድሩ የተሰጣቸውን የሒሳብ ደብተር በመጠቀም በመደበኛነትም ሆነ በሌሎች መንገዶች በተቋሙ ቁጠባ ሊያካሒዱ ይችላሉ፡፡
ተበዳሪ ያልሆኑ ደንበኞች፡- ማንኛውም ሰው በተቋሙ ከ5 ብር ጀምሮ የቁጠባ ሒሳብ መክፈት ይችላል፡፡
የኘሮቪደንት ፈንድ ቁጠባ፡- ማንኛውም መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ይህንን መንገድ ሠራተኞቹ የተሻለ ገንዘብ እንዲያገኙ ሊጠቀምበት ይችላል፡፡ ቀጣሪው ከሠራተኞቹ የሰበሰበውን ገንዘብ እንደ ኘሮቪደንት ፈንድ ያጠራቀመ ከሆነና የቁጠባው መጠን ቢየንስ ለአንድ ዓመት ያህል የማይቀንስ ሆኖ የድርጅቱ አንድ ሠራተኛ በሚሞትበት አጋጣሚ በቁጠባው ላይ ከሚሰላው መደበኛ ወለድ በተጨማሪ የሟች ቁጠባ ላይ ተመስርቶ ተጨማሪ 1 በመቶ ለአንድ ዓመት ያህል ለቤተሰቡ ይሰጣል፡፡
የቁጠባ ሳጥን፡- ተቋሙ አገልግሎቱን ለሚፈልጉ ደንበኞች ከእንጨት የተሰሩ የቁጠባ ሳጥኖችን ያቀርባል፡፡ ይህ አገልግሎት የቀን ገቢያቸውን የተወሰነ መጠን ሊያጠራቅሙ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ትናንሽ የንግድ ድርጅቶች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
ተንቀሳቃሽ ቁጠባ፡- የኤዲሲኤስአይ ሠራተኞች በየሳምንቱ የንግድ ቦታዎች ድረስ በመሔድ ከደንበኞችና ደንበኛ ሊሆኑ ከሚችሉ አካላት ተንቀሳቃሽ ቁጠባ ይሰበስባሉ፡፡
የማስቀመጫ ጊዜ፡- ቢያንስ ለሶስት ወራት የተጠራቀመ ቁጠባን ይመለከታል፡፡ በመሆኑም ቁጠባው በዓመት ቢያንስ 4.5 በመቶ ወለድ ይጨምራል፡፡
የመድህን አገልግሎት፡- የብድር ደንበኞችንና ቤተሰቦቻቸውን ለመደገፍ ሶስት ዓይነት የመድህን አገልግሎቶችን ይሰጣል፡-
የሕይወት መድህን፡- የብድር ደንበኛው በውጫዊ ምክንያቶች በሚሞትበት ጊዜ ያልተከፈለው ቀሪ ገንዘብ በመድህን ከለላው የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ይህ እንዲሆን ደንበኛው የብድሩን 1 በመቶ የአርቦን ክፍያ (ኘሪምየም) መክፈል አለበት፡፡ ይህ ተግባራዊ የሚሆነው በቡድንና በግል ብድሮች ላይ ብቻ ነው፡፡
የንግድ ድርጅቶች መድህን፡- ይህ ዓይነት መድህን በኃ.የተ.የግ.ኩ ወይም በህብረት ሥራ ማህበራት መልክ ብድር ለሚወስዱ ደንበኞች የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ ዓይነት መድህን ተግባር ላይ የሚውለው የመድህን ገዢዎች ንብረት ከራሳቸው ቁጥጥር ውጭ በሆኑ አደጋዎች በሚጠፉበት ጊዜ ነው፡፡ የንግድ ድርጅቱ የብድሩን 1 በመቶበአንድ ዓመት በመክፈል መድህኑን ይገዛል፡፡
የንብረት መድህን፡- ይህ መድህን የቤት ብድር ደንበኞችን የሚሸፍን ነው፡፡ የመድህን አገልግሎቱ የሚሰጠው ቤቱ ላይ አደጋ ሲደርስ ወይም ተበዳሪው ሲሞት ነው፡፡ የዚህ መድህን ተጠቃሚዎች የብድሩን 2 በመቶ በዓመት መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡
የፈንድ አስተዳደር፡- ጡረታ የወጡ የመንግሥት ሠራተኞች የማህበራዊ ደህንነት ፈንድ ክፍያ፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የአገልግሎት ክፍያ ስብሰባ፣ መንግሠታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ዓለም አቀፋዊ መንግሥታዊ ኤጀንሲዎች ፈንዶችን ማስተዳደር እና ሌሎች ከዚህ ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን የሚያካትቱ የሦስተኛ ወገን የፈንድ አስተዳደር አገልግሎቶች በፈንድ አስተዳደሩ ስር ይካተታሉ፡፡ ዝርዝር ስምምነቶቹ በተቋሙና በሦስተኛው ወገን መካከል ይደረጋሉ፡፡
የሥልጠናና የምክር አገልግሎት፡- አመራራዊ፣ ግብይታዊ፣ ቴክኒካዊና አስተዳደራዊ ምክሮችን ለደንበኞች መስጠትና በእነዚህ ዘርፎች አገልግሎት እንዲያገኙ እገዛ ማድረግን ያካትታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መዝገብ አያያዝ፣ ጥሬ ገንዘብ አያያዝ፣ ወ.ዘ.ተ ላይ ለደንበኞች ሥልጠና ማመቻቸት ይካተታሉ፡፡