ከመጀመርዎ በፊት

የራስዎን ሥራ ከመጀመርዎ በፊት

ከወራት በፊት ከአንድ ጓደኛዬ ጋር በአንድ መዝናኛ ስፍራ ቁጭ ብለን ስንጨዋወት ያለኝ ነገር መቼም ከውስጤ አይጠፋም፡፡ ይህ ጓደኛዬ ከዩኒቨርስቲ ተመርቆ ከወጣ በኋላ በቀሰመው ዕውቀት የራሱን ስራ ፈጥሮ በመስራት ላይ ነው፡፡ በወቅቱ ሞቅ ባለ ጨዋታ መሀል በቅጽበት ከጨዋታችን ርእስ ውጪ የሆነ አንድ ጥያቄ ያነሳል፡፡

“ደመወዝህ ስንት ነው?”  ግራ ገባኝ ለቅጽበት ትኩር ብዬ ከተመለከትኩት በኋላ ያችን የተለመደችዋን መልስ ሰጠሁት “የወንድ ልጅ ደመወዝና የሴት ልጅ እድሜ አይጠየቅም”፡፡ ቀጠለ “እኔ ግን እነግርሀለው በወር እስከ 15ሺህ ብር ድረስ አገኛለሁ” አለኝ፡፡ ንግግሩ አግራሞት ፈጥሮብኝ እኔም ጥያቄዬን ቀጠልኩ “ማን ይከፍልሀል ላንተ ደግሞ? ማንቀጥሮህ? “ ራሴ ለራሴ እከፍላለሁ” ሲል መለሰልኝ፡፡

“ከደመወዜም በላይ አንተ የሌለህን ግን ደግሞ እኔ ያሉኝን ሶስት ነገሮች ልንገርህ” አለና ቀጠለ።አሁን ጉንጮቼን ተደግፌ ከማዳመጥ ውጪ አማራጭ የለኝም፡፡የጊዜ ነጻነት፣ የገንዘብ ነጻነት እንዲሁም የአዕምሮ ነጻነት ከአንተ በተሻለ መልኩ አለኝ፡፡

አየህ እኔ የራሴን ስራ ስሰራ የግሌ ፍላጎትና የውስጤን ትእዛዝ በመከተል ከፈለኩ በተመቸኝ ሰአት እሰራለሁ።የስራ ሰአት የምወስነው እኔው ነኝ።ይህ የጊዜ ነጻነቴን ማሳያነው፡፡ወደገንዘብ ነጻነት ስመጣልህ ደግሞ የምፈልገውን ገንዘብ በፈለኩት ቀን እወስዳለሁ።ለፈለኩት አላማም አውላለሁ።አንተ ግን ወር ጠብቀህ ነው ደመወዝ የምትቀበለው፡፡ሌላው ደግሞ የራሴን ስራ እቅድ የማወጣው እኔው ነኝ። የራሴም አለቃ እኔው ነኝ።አሁንስ ተረዳኸኝ ? አለኝ፡፡

ምን ይመስላቹኃል የራሳችን ሥራ ብንጀም ?

ማንኛውም ሥራ ሊሰራ ሲታሰብ ዓላማ ያስፈልገዋል፡፡ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ደግሞ ዕቅድ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለዕቅድ በድንገት ተነስቶ የሚጀመር ሥራ ውጤት አልባ ሊሆን ይችላል፡፡

ዕቅድን በተግባር አውሎ ዓላማን ማሳካት ብዙ ውጣ ውረድ አለው፡፡ ያለ ውጣ ውረድ ስኬት አይኖርም፡፡ ስኬታማ መሆን የሚቻለው ትክክለኛ የሆነ ግብ መርጦ የግቡን አቅጣጫ በትክክል መከተል ሲቻል ብቻ ነው፡፡ማንኛውም ሰው ዘመኑ የሚፈቅደውን የአሠራርና የአመራር ዕውቀትና ክህሎት በማግኘት የግል ሥራ ለመፍጠር ብቃት ሊኖረው ስለሚችል እርሰዎም ቆም ብለው ራስዎን መፈተሽ ይኖርብዎታል፡፡

የግል ሥራ ይሆንዎታል?

ሥራ ፈጣሪ ሰው ለፈጠረው ሥራ (ለመሠረተው ድርጅት) ሙሉ ኃላፊነት ያለበት ሰው ነው፡፡ በግል ለሚመሠረት ድርጅት ከባለቤቱ የበለጠ ተቆርቋሪና ለድርጅቱ ጠቃሚ ሰው የለም፡፡ ድርጅቱን በአግባቡ በመምራት ውጤታማ የማድረግ ኃላፊነት የባለቤቱ ብቻ ነው፡፡ ውጤታማ ለመሆን ይህንን ኃላፊነት መወጣት ግዴታ ነው፡፡ ኃላፊነትን መወጣት እርካታን ያጎናጽፋል፡፡ የግል ሥራ መፍጠር ትልቅ እርምጃና ከባድ ውሣኔ ሲሆን፣ ጠንክሮ ለመሥራት ስኬታማ መሆን ሕይወትን ይለውጣል፡፡ በየቀኑ ረዥም ሰዓቶችን በሥራ በመጠመድ ማሳለፍ የሚከብድ ቢሆንም መጨረሻው አስደሳችና ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡

የሥራ ውጤት ሊገኝና ሊያድግ የሚችለው በግላዊ ባህሪያት፣ በአካባቢ ምቹ ሁኔታዎችና በባለሙያ ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ የእርስዎም የሥራ ወዳድነት ባህሪዎና ሙያ ባደገ ቁጥር የድርጅትዎ ውጤታማነት የላቀ ይሆናል፡፡ ሊኖርዎ የሚገባው የሥራ ወዳድነት ባህሪና ሙያ ለመመስረት ካቀዱት የድርጅት ዓይነት ላይጣጣም ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በድርጅትዎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ የቤተሰብዎ ድጋፍና የገንዘብ አቅምዎም ድርጅቱን ከመመስረት በፊት ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጠቃሚ ነገሮች ናቸው፡፡

ምንም ይሁን ምን ለመሥራት የሚፈልጉትና የሚወድት አንድ ዓይነት ሥራ አለ፡፡ ይህንን ሥራ ሠርተው ከትልቅ ደረጃ ለማድረስ የሚያበቃዎ ባህሪና ፍላጐትም አለዎት፡፡ ምንም እንኳ ለሥራው አስፈላጊ የሚባሉ ሁሉም ዓይነት ባህሪያትና ሙያ ባይኖርዎትም ባህሪይዎንና ሙያዎን በሥልጠናና ጥናት ማሳደግ ይችላሉ፡፡ መሻሻል ያለባቸው ባህሪያት በመለየት አመለካከትዎንና አሠራርዎን መለወጥ ይችላሉ፡፡ የራስዎን የገንዘብ አቅም ማደራጀት ወይም ከቤተሰብ የገንዘብ አቅም ጋር በማቀናጀት ወይም በማናቸውም ሁኔታ ለሚጀምሩት አዲስ ሥራ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይችላሉ፡፡ አስፈላጊውን የሙያ ሥልጠና ለማግኘት ደግሞ ባለሙያ ሠራተኛ በመቅጠር ወይም በሌላ መንገድ ራስዎን ማሰልጠን ይችላሉ፡፡

ሥራ ፈጣሪና የውጤት ባለቤት ለመሆን ኃላፊነት የሚሸከሙ፣ በራስዎ የሚተማመኑ፣ ተስፋ የማይቆርጡ፣ የማይሰላቹና አቅምዎን አሟጠው የሚሠሩ ሥራ ወዳድ ይሁኑ፡፡ ለውጤት ይሥሩ፡፡ ለማቀድ፣ ለመወሰን መረጃ ይጠቀሙ፡፡ ግልፅ ራእይ ይኑርዎ፡፡ በጥንቃቄ ያቅድ፡፡ አጋጣሚዎችን ይጠቀሙባቸው፡፡ በይሉኝታ አይሸነፉ፣ ዕቅድዎንና ተግባርዎን ሁልጊዜ ይገምግሙ፡፡ ከስተትዎ ይማሩ፡፡ ሰዎች የሚሰጡዎትን አስተያየት ያድምጡ፡፡ ጠቃሚ አስተያየቶችን ለይተው ይጠቀሙባቸው፡፡ አሻሚ ጉዳዮች ሲያጋጥሙዎ ያቻችሉአቸው፡፡ ግትር አይሁኑ፣ ሰዎችን አሳምነው ወደራስዎ ለማምጣት ይጣሩ፡፡ በአግባቡ ይቆጥቡ፡፡ አሥር ብር አትርፈው አሥራ አንድ ብር አያባክኑ፡፡ ከነዚህ ባህሪያቶች አብዛኛዎቹን ከተላበሱ ለመሥራት የሚያቅትዎ ምንም አነገር አይኖርም፡፡

እስቲ ራስዎን ይመዝኑ፤

የራስዎን ሥራ ለመጀመር ከመወሰንዎ በፊት ግላዊ ባህሪዎን፣ ሙያዎንና የአካባቢዎን ሁኔታዎች ይፈትሹ፡፡ ድርጅትዎን ለመምራትና ትክክለኛ የሥራ ሰው መሆንዎን ለማረጋገጥ ባህሪዎን፣ ሙያዎንና የአካባቢዎን ሁኔታዎች በሚገባ ይገምግሙ፡፡ እያንዳንዱ ሁኔታዎ በድርጅትዎ ላይ በጥንካሬም ይሁን በድክመት የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ይለዩ፡፡ ለምሣሌ፣ ድርጅት ለመምራት የሚያስችል እውቀት ካለዎ ጥንካሬዎ ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔዎችን ለመወሰን የሌላ ሰው ድጋፍ የሚያስፈልግዎ ከሆነ ድክመትዎ ነው፡፡

ከዚህ በታች ያለው መጠይቅ የትኛውን ሙያ ወይም ግላዊ ባሕሪ ማሻሻል እንደሚያስፈልገዎ እንዲለዩ ይረዱዎታል፡፡ መጠይቁን ሲመልሱ የራስዎን ባህሪያት በጥንካሬም ሆነ በድክመት ለይተው በሣጥኖቹ ውስጥ x ምልክት ያድርጉ፡፡ ባህሪዎን፣ ሙያዎንና የአካባቢዎን ሁኔታዎች በጥንካሬ ወይም በድክመት ለመፈረጅ እውነተኛና ትክክለኛ ይሁኑ፡፡

1. ሙያን በተመለከተጥንካሬድክመት
ሀ. ሙያ /ክህሎት/፡-
ሙያ /ክህሎት/ ማለት በድርጅትዎ ውስጥ በሙያዎ ሠርተው ለሚያመርቱት ምርት ወይም ለሚሰጡት አገልግሎት ያለዎት የተግባር ችሎታ ማለት ነው፡፡ ለምሣሌ የሚጀምሩት ሥራ የብረት በር መሥራት ከሆነ ብረት መለካት፣ የመቁረጥና መበየድ የሙያ ብቃት ሊኖርዎ ይገባል፡፡ ለመሥራት ላቀዱት ሥራ ተፈላጊ የቴክኒክ ሙያዎ ጠንካራ ነው ወይም ደካማ? ለመሥራት ካቀዱት ሥራ ጋር የሚዛመድ ሙያ ከሌለዎ በድክመት ይውሰዱት፡፡
ለ. ድርጅት የማስተዳደር ብቃት፡-
ድርጅት የመምራት ሙያ ማለት ድርጅትዎን በብቃት ለመምራት የሚያስፈልግዎ ችሎታ ማለት ነው፡፡ የድርጅትዎ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን የመግዛት፣ ምርትዎን ወይም አገልግሎትዎን የመሸጥ ችሎታ በጣም የሚያስፈልጉ ሙያዎች ናቸው፡፡ እንዲያውም ድርጅት የመምራት ሙያና ብቃት ለስኬት ከሚያስፈልጉ ችሎታዎች ዋነኛው ነው፡፡ ለምሣሌ ለምርትዎ ወይም ለሚሰጡት አገልግሎት ዋጋ መተመን፣ ገቢዎንና ወጪዎን በመዝገብ የመያዝ ችሎታዎች በጣም አስፈላጊ ናቸው በነዚህ ብቃቶች ጠንካራ ነዎት ወይም ደካማ?
ሐ. መሠረታዊ ዕውቀት፡-
ለመጀመር ላቀዱት ሥራ የሚያስፈልግ መሠረታዊ ዕውቀት በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ መሠረታዊ ዕውቀት ማለት ለመሥራት ላቀዱት ሥራ ያለዎትን አጠቃላይ ግንዛቤና ንቃተ ህሊና ማለት ነው፡፡ ስለሚጀምሩት ሥራ ያለዎ መሠረታዊ ዕውቀት በላቀ ቁጥር ውጤታማነትዎ የተረጋገጠ ይሆናል፡፡ በሥራዎ ላይ የሚያጋጥሙ ስህተቶችንና ድክመቶችን ለማስወገድ ያስችልዎታል፡፡ ተወዳዳሪዎችዎን ለመለየት ይረዳዎታል፡ መሠረታዊ ዕውቀትዎና ንቃትዎ ጠንካራ ነው ወይስ ደካማ?
1. የራስዎ ባህሪዎና ሁኔታዎች፡-
ሀ. በራስ መተማመን፡-
ሥራዎትን ውጤታማ ለማድረግ በራስዎ ይተማመኑ፡፡ በራስ መተማመኑ፡፡ በራስ መተማመን ማለት ሥራዎን ለመሥራትና ለመምራት ያለዎ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት ማለት ነው፡፡ ድርጅትዎን በብቃት የመምራትና ኢንቨስትመንትዎን የማሳደግ ውሣኔና አቋምዎ ማለትም ነው፡፡ በራስዎ ይተማመናሉ?
ለ. ግብ ይኑርዎ፡-
የግል ሥራዎን ለመጀመር የተነሱት ለምንድነው? ከየት ተነስተው የት ለመድረስ ነው? የቅርብና የሩቅ ዓላማዎችዎን ይለዩ፡፡ ሥራዎ ተግባራዊ መሆን የሚችሉ ዕቅዶች ብቻ ይመራ፡፡ የንግድ ወይም የሥራ ጽንሰ ሃሳብ (Business idea) ይኑርዎ፡፡ የሚጀምሩት ሥራ ጊዜያዊ ችግርዎን ለማቃለል ብቻ መሆን የለበትም ደመወዝተኛ እስከሚሆኑ ድረስ በግልዎ ለመሥራት አቅደው ከሆነ ሥራው ውጤት አይኖረውም፡፡ ከመቀጠር ይልቅ በራሴ የፈጠርኩት ሥራ ይጠቅመኛል ብለው ይነሱ፡፡ ሥራዎን ሲሠሩ የራስዎ አለቃ ይሁኑ፡፡ በነዚህ አቋሞች ጠንካራ ነዎት ወይም ደካማ?
ሐ. ኃላፊነትን መወጣት ፡-
ድክመት የማይኖረው ወይም ስህተት የማያጋጥመው የሥራ መስክ መፍጠር አይቻልም፡፡ ሁልጊዜ ድክመቶችና ስህተቶች በሥራ ላይ ይከሰታሉ፡፡ የሚያጋጥሙ የሥራ ድክመቶችና ስህተቶች ለማረምና ለማስወገድ፣ ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ይሁኑ፡፡ በሥራዎ ላይ ለሚከሰቱ ስህተቶች ሁሉ ኃላፊነት የሚወስድ ሰው እርስዎ ብቻ መሆንዎን ይመኑ፡፡ ኃላፊነት መቀበልና በብቃት መወጣት ጥንካሬዎ ነው፡፡ በኃላፊነት መሸሽ ወይም መወጣት አለመቻል ውድቀትዎን ያፋጥነዋል፡፡ በዚህ ረገድ እርስዎን በምን ይመዝናሉ?
መ. ውሣኔ ሰጪ ይሁኑ፡-
በድርጅትዎ ጉዳይ ላይ ውሣኔ ሰጪ እርስዎ ብቻነዎት፡፡ በሥራዎ ላይ ውሣኔ የሚሰጥ ሌላ አካል መሆን የለበትም፡፡ ለሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የሚሰጡት ውሣኔ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ቢሆን እንኳ ሥራዎን ለማከናወን ጠቃሚ ነውና ከመወሰን አይቆጠቡ፡፡ ሲወስኑ ብልህ ይሁኑ፡፡ ለውሣኔዎ ምን ምላሽ እንደሚሰጥ አስቀድመው ይተንብዩ፡፡ ይህ ችሎታዎስ እንዴት ነው?
ሠ. የቤተሰብ ተሳትፎ፡-
ድርጅትዎን ውጤታማ ለማድረግ ሙሉ ጊዜዎን በሥራ ላይ ያሳልፋሉ፡፡ የጊዜ እጥረት ሊያጋጥምዎ ይችላል፡፡ ይህንን ችግር ለማቃለል በድርጅትዎ ሥራ ውስጥ የቤተሰብዎ ተሳትፎ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ለመሥራት ያቀዱትን ሥራ ቤተሰብዎ የሥራዎን ዕቅድ ከደገፉ ሊረዱዎና ሥራውንም ሊያግዙዎ ይችላሉ፡፡ የቤተሰብ ድጋፍ አለዎት?

ረ. የገንዘብ አቅም፡-
ለድርጅትዎ ማቋቋሚያ የራስዎ ገንዘብ ካለዎትና የገንዘብ እጥረት ከሌለብዎ ጠንካራ ጐን አለዎት ማለት ነው፡፡ የራስዎ ባለሆነ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ወይም ከሌላ ምንጭ ላገኙት ገንዘብ ከፍተኛ ወለድ የሚከፍሉ ከሆነ ወይም ገንዘቡ በድንገት ባልጠበቁት ጊዜ የሚወስድብዎ ከሆነ በድክመት ይውሰዱት፡፡ የገንዘብ አቅምዎ እንዴት ነው?
በሳጥኖቹ ውስጥ ያሉትን ምልክቶች ቆጥረው ስንት ጠንካራና ደካማ ጐኖች እንዳሉ ይጻፏቸው፡፡
የነጥቦች ድምር

በመቀጠል የጥንካሬዎና የድክመትዎን ብዛት ይመልከቱ፡፡ያሉዎትን የጥንካሬዎችና ድክመቶች የትኞቹ እንደሆኑ በጥንቃቄ ይመርምሩአቸው፡፡

ጥንካሬዎ ከድክመትዎ ይበልጣል ?

ጥንካሬዎ በበዛ ቁጥር የራስዎን ሥራ ለመጀመር ምቾት ይሰጥዎታል ፡፡ያለብዎትን ድክመት ለማሻሻል እንደሚችሉ ማመን አለብዎ፡፡

ድክመተዎን ወደ ጥንካሬ ለመቀየር

-የሌሎች ሰዎችን እርዳታ ይጠይቁ (ቤተሰብ፤ጉደኛ፤ የቢዝነስ ሰዎች..)

-አጫጭር ኮርሶች መማር (የሂሳብ መዘገብ አያያዝ፤..)

-ስኬታማ ሰዎችን ማየት

-ጠቃሚ መረጃዎችን /ድህረ ገፆች/ በመመልከት ( yerasbusiness.com )

የራስዎን ሥራ ለመጀመር ምቾት ይሰማዎታል ?

      ይሰማኛል           አይሰማኝም

 መልሶ ይሰማኛል ከሆነ

ማንኛውንም የንግድ ስራ ለመጀመር በየትኛው ዘርፍ ልሰማራ ብለው ለመወሰን የትኛው ስራ ያዋጣል፣ ምንብሰራ ቶሎ ትርፋማ እሆናለው እና የትኛው ስራ ነው በአካባቢዬ ሰዎች ሰርተውት ትርፋማ የሆኑበት ብለው በማሰብ እንዳይጀምሩ አደራ እንሎታለን። እስከዛሬ ድረስ ሰዎች ከላይ በዘረዘርኩት መልኩ ወደ ንግድ ይገባሉ ነገር ግን ለዘላቂ ስኬታማ የንግድ ስራ ትክክለኛ አመራረጥ ከዚህ እንደሚከተለው ቢሆን ይመረጣል።
ሊሰሩ ያሰቡትን የንግድ ስራ ዘርፍ በእነዚህ መስፈርቶች ይመዝንዋቸው።

1. ምን አይነት ሀብት አለኝ፡- ወደስራ ከመግባቶ እንዲሁም ሚሰሩትን ስራ ከመምረጦ በፊት እርሶ ያሎት የገንዘብ ፣ የእውቀት፣ የልምድ ፣ የውጫዊ እና የአስተሳሰብ ስጦታዎን ይመልከቱ። ከላይ የተዘረዘሩት እያንዳንዳቸው ኢንቨስት ሊደረጉ የሚችሉ ሀብቶች ናቸው እርሶ የትኛው ነው ያሎት? እውቀቶትን አልያም ልምዶትን በመሸጥ ወደ ስራ መሰማራት ይችላሉ፣ የመልክና ቁመና አልያም የፈጠራ ስጦታ ካሎት በፊልም ሞዴሊንግ የጥበብ ስራዎች ውስጥ ቢሰማሩ እንዲሁም መነሻ ሚሆን ገንዘብ ካሎት እሱን በአግባቡ በመጠቀም ስራውስጥ መግባት ይቻላል። በአጠቃላይ ወደራስዎ በመመልከት ሌሎች ሰዎች ጋ የሌለ የእርሶን ልዩ ስጦታ አልያም ልምድ ወደገንዘብ ሊቀየር በሚችል መልኩ ለይተው ያውጡ።

2. ስራውን ይወዱታል፦ ሊሰሩ ያሰቡት ስራ ሌሎች ሰርተውት ስለተሳካላቸው ወይም ሰዎች ይህስራ ያዋጣል ስላሎት ሳይሆን ይህን ስራ ምን ያህል እወደዋለው ብለው እራስዎን ይጠይቁ። ሰው የህይወት ዘመኑ አላማው የተፈጠርኩት ለዚህ ነው የሚለው ጉዳይ ላይ ቢሰራ ውጤታማነቱ አያጠራጥርም፡ በሚወዱት ወይም አላማዎ የሆነዉ ስራ ላይ ቢሰማሩ ከስራው ከሚያገኙት ትርፍ በበለጠ የሚያገኙት እርካታ ጠንክረው እንዲሰሩ ብርታት ይሆኖታል።

3. ትርፉማነቱ፡ የአንድ ንግድ ሚዛን መስፈርያው ትርፋማ ነው ወይስ አይደለም የሚለው እንደሆነ አያጠራጥርም። የንግድ ዋናው አላማ ትርፍ ነው ቢባልም በዚህ ዘመን ግን Social marketing concept እንደሚለው አንድ ንግድ ከትርፋማነቱ ባሻግር ማህበራዊ ጠቀሜታው፣ ተፈጥሮን የማይጎዳ፣ ደንበኞችን የሚያረካ፣ ሰራተኞችን፣ መንግስትን በአጠቃላይ ሁሉንም አካላት ጠቅሞ የሚያስመሰግን መሆን እንዳለበት ይደነግጋሉ።
የአንድ ንግድ ትርፋማነቱ የሚለካው በዋናነት Return on Investment ማለትም ንግዱን ለመጀመር ያወጣነውን ወጪ በስንት ጊዜ እንመልሰዋለን በሚል ስሌት ሲሆን የተለመደው ትርፋማነትን መመዘኛ መንገድ ደግሞ በወር ውስጥ ምንያህል ገቢ እንዲሁም መጪ አለ ተብሎ ተሰልቶ የሚገኝ ነው።

4. ማህበራዊ ጠቀሜታው፡- ትልቁ የንግድ ስራችንን መለኪያ መሆን ያለበት ማህበራዊ ጠቀሜታው ነው። ማህበራዊ ጠቀሜታው ምን ያህል ነው? የሰዎችን ችግር ፈቺነው ወይ? ከትንሽ ተነስቶ ትልቅ ቦታ መድረስ ይችላል ወይ? በዚህ አጋጣሚ ማንኛውም የንግድ ስራ ሀሳብ መነሳት ያለበት ከችግር ነው ከግለሰቦች እንዲሁም ከማህበረሰቡ አልያም በአካባቢችን ካሉ ሰዎች ቾግር ተነስተን የንግድ ስራ ሀሳብ ማመንጨት እንችላለን።

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »