እጅግ በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች 7 ልምዶች

Published by Abreham D. on


ከአስራ አምስት ሚሊዮን ቅጂ በላይ ተሽጧል፤ በሰላሳ ቋንቋዎች ተተርጉሞም ለንባብ በቅቷል፤ በእኛው አማሪኛ ቋንቋም ተተርጉሞ መታተሙንም አውቃለሁ፡፡ ይህ መጽሐፍ “The 7 Habits of Highly Effective people” ይባላል:: “እጅግ በጣም ስኬታማ የሆኑ ሰዎች 7 ልምዶች” ብለን ቃል በቃል እንተርጉመው፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ ይባላል፡፡ ይህ መጽሐፍ በግለሰብ ደረጃ ብልፅግናን (Personal development) ለመፍጠር እንዲረዱ ታስበው እስከ ዛሬ ድረስ ከተጻፉ መጽሐፍት መካከል ወደር የማይገኝለት ነው፡፡ ካላነበባችሁት እንድታነቡት እመክራለሁ፡፡ ያነበብነውም ደግመን ልናነበው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡የዚህ ድንቅ መጽሐፍ ደራሲ ስቴቨን ኮቬይ “ውስጣዊ ድል ከውጫዊ ድል ይበልጣል” ይላል፡፡ እዚህ ምድር ላይ ማግኘት የምንፈልጋቸውን ነገሮች በሙሉ ለማግኘት አስቀድመን ራሳችንን ማሸነፍ፤ የህይወታችን ሾፌር መሆን፤ ውስጣዊ ማንነታችንን መቆጣጠር ወዘተ አለብን ማለት ነው፡፡ “ከተማን ከሚመራ ሰው ይልቅ ራሱን የሚመራ ሰው ይበልጣል” ይላል ጠቢቡ ሰለሞን፡፡ ራስን ማሸነፍ ሌሎች ውጫዊ ነገሮችን የማሸነፊያ ቁልፍ ነው፡፡ በመቀጠል በቅደም ተከተል የምንመለከታቸው 7 ልምዶች ማንኛውም ሰው የግል ህይወቱ መሪ እንዲሆን በእጅጉ የሚያግዙ ናቸው፡፡ አሁን ቦታውን ለእነዚህ ልምዶች ለቀቅ እናድርግ እስኪ፡፡1. ኃላፊነት ውሰዱጅብ ከሄደ በኋላ የውሻ መጮህ ምንም ው.ጤት አያመጣም፤ ትርፉ ድካም ነው፡፡ ውጤት የሚያመጣው ጅቡ ከመምጣቱ በፊት አስቀድሞ በማነፍነፍ ድምጽ ማሰማት ነው፡፡ ሁኔታዎችን፣ ሌሎች ሰዎችን፣ ዓለምን ወዘተ የሚወቅሱ ሰዎች በህይወታቸው የረባ ቁም ነገር አያከናውኑም፤ ሁልጊዜም ኃላፊነትን የሚያሸክሙት ከእነሱ ውጪ ላለ ሌላ አካል ነው፡፡ ኃላፊነትን መሸከም ስንችል ነው የህይወታችንን ጉዞ አቅጣጫ መወሰን የምንችለው፡፡ የተሸከርካሪውን መሪ ለሌላ አካል አሳልፈን ሰጥተን የምፈልገው ቦታ አይደለም የደረስኩት፤ በፈለኩት ፍጥነት አይደለም እየተጓዝኩ ያለሁት ወዘተ ልንል አንችልም፤ ብንልም ዋጋ የለውም፡፡ የጉዞውን አቅጣጫ፣ ፍጥነት እና አድራሻ የሚወስነው አሽከርካሪው ነው፡፡ ልምዳችን መውቀስ፣ ጣት መጠቆም፣ ራስን መከላከል ወዘተ ከሆነ እውነቱን ለመናገር የሚወቀስ ነገር ማግኘት አይከብድም፡፡ ዘወትር የእናቴ መቀነት አደናቅፎኝ ነው ማለት ህይወታችን ባለህበት እርገጥ እንዲሆን በር ወለል አድርጎ ይከፍታል፡፡ ስለዚህ ለውጥ ለማምጣት፣ የራሳችን ሰዎች ለመሆን፣ ውስጣችንን ድል ለማድረግ ወዘተ ሁልጊዜም ለገዛ ራሳችን ህይወት ሙሉ ኃላፊነት እንውሰድ፡፡ ቃላችንን የምናከብር፤ በአልንበት ቦታ የምንገኝ፤ በገዛ ራሳችን ጥረት የምንፈልገውን ማንኛውንም ዓይነት ነገር እጃችን ለማስገባት መጓዝ ያለብንን ያህል ርቀት መጓዝ የምንችል ሰዎች እንሁን፡፡ “ስራ እኮ ጠፋ! እኔ ምን ላድርግ?!” ከማለታችን በፊት ስራ ለማግኘት የምንችለውን ድንጋይ በሙሉ መፈንቀላችንን እርግጠኛ እንሁን፤ ቀጣሪዎች የሚፈልጉትን ዕውቀት እና ክህሎት ይዘን ለመገኘት ጥረት እናድርግ፤ የተለመደውንም ያልተለመደውንም አማራጭ እንፈትሽ፡፡ ሳይኮሎጂስቶች “Life is 10 % what happens to us and 90 % how we react to it” ይላሉ፡፡ የህይወታችንን አብዛኛውን (90 %) ክፍል በምንፈልገው መልኩ መስራት እንችላለን ማለት ነው፡፡ የምናጭደው የዘራነውን ነው፡፡2. የምትፈልጉትን ነገር አስቀድማችሁ እወቁስቴቨን ኮቬይ “ነገሮች ሁለት ጊዜ ይፈጠራሉ” ይላል፡፡ የመጀመሪያው ፈጠራ የሚጠናቀቀው አእምሮአችን ውስጥ ነው፡፡ ከቤት ከመውጣታችን በፊት የምንሄድበትን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ከአንድ እና ሁለት፣ አምስት እና አስር ዓመት ወዘተ በኋላ ምንድን ነው ማግኘት፣ ማድረግ፣ መሆን ወዘተ የምንፈልገው? ለእነዚህ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት ነገሮቹ በተጨባጭም ወደ ህይወታችን የሚመጡበትን ዕድል ከፍ ያደርጋል፡፡ “We rise to the level of our expectations” ይባላል፡፡ የምናገኘው የምናስበውን ነው፤ የምንደርሰው እንደርሳለን ብለን የምናስበው ከፍታ ድረስ ነው፡፡ ግባችንን ማወቃችን ትኩረታችንን ለመሰብሰብ ይረዳናል፤ ከነፈሰው ጋር አንነፍስም፤ በፈተና መካከል ጸንተን እንቆማለን፡፡ ሳይኮሎጂስቶች የህይወታችንን ግብ በቅጡ ለመለየት የሚረዳን አንዱ ሁነኛ መንገድ “የቀብራችን ዕለት እንዲነበብ የምንፈልገውን የህይወት ታሪካችንን መወሰን ነው” ይላሉ፡፡ ቁጭ ብለን ልናስብበት ይገባል፡፡3. ቅድሚያ ለሚገባቸው ነገሮች ቅድሚያ ስጡ“ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት” ይባላል፡፡ ቅድሚያ መስጠት ላለብን ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን፡፡ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም፡፡ ኮቬይ እንዲህ ይላል፡- “ራሳችሁን ከእነዚህ ሶስት አጉል ልምዶች በአንዱ መውቀስ ቢኖርባችሁ በየትኛው ነው የምትወቅሱት? (1) መስራት ያለብኝን ነገር በቅደም ተከተል መለየት አልችልም፤ (2) በአስቀመጥኩት ቅደም ተከተል መሰረት መስራት አልችልም፤ (3) በወሰንኩት ቅደም ተከተል መሰረት ለመስራት አስፈላጊው ቁርጠኝነት የለኝም፡፡ ብዙ ሰዎች ቁርጠኝነቱ የለኝም ነው የሚሉት፡፡ ጠለቅ ብለን ከመረመርነው ግን እውነቱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እውነቱ ቅደም ተከተሉ ውስጣችን በጥልቀት አለመስረጹ ነው፡፡ ልምድ 2ን ማለትም የህይወት ግባችንን አስቀድመን በሚገባ ለይተን በሚገባ ውስጣችንን መቅረጽ አለመቻላችን ነው”::4. በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ ተመሩከተቃራኒ ፆታ ጀምሮ እስከ የንግድ ስራ ግንኙነት ድረስ በጋራ እኩል ተጠቃሚነት መርህ መመራት ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ “አዎ! በሚገባ አምንበታለሁ፡፡ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ነው ህይወቴን የምመራው፡፡” ትሉ ይሆናል፡፡ እንደምትሉት እንደምትኖሩ ግን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ለማሸነፍ ከመጣር ይልቅ እንዴት በጋራ እኩል ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት አድርጉ፡፡ የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ከሌላው ከፍ ብሎ ለመታየት፣ ልክ ሆኖ ለመገኘት ወዘተ ከመጨነቅ ይልቅ በጋራ እኩል እንዴት ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ማሰብ እና ይህንን መርህ በየትኛውም የግንኙነታችን መረብ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይበልጥ ውጤታማ ያደርገናል፡፡5. መጀመሪያ ለመረዳት ጥረት አድርጉመጀመሪያ ስንረዳ የሚረዱንን እናገኛለን፡፡ ብዙ ጊዜ ግን በአንጻሩ ጊዜያችንን የምናጠፋው ሰዎች እንዲረዱን በመፍጨርጨር ነው፡፡ ቆም ብለን  “ምንድነው እስኪ እያሉ ያሉት? ልክ ይሆኑ ይሆን? በየትኛው ማዕዘን ነው እነሱ ጉዳዩን ያዩት?” ወዘተ ብሎ በቀናነት ማሰብ እና ሰዎችን ለመረዳት ጥረት ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ሰዎችን የመረዳት ችሎታችን ጥሩ ሲሆን የሚረዱንን ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል፡፡6. 1 + 1 = 3“ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” ትልቅ መልዕክት ያለው አባባል ነው፡፡ በጋራ የሚሰሩ ስራዎች በግል ከሚሰሩ ስራዎች ይልቅ የላቀ ውጤት ያመጣሉ፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ ሩጫን በመሰለ የግል ጥረትን በከፍተኛ ሁኔታ በሚጠይቅ የውድድር ዘርፍ እንኳን አትሌቶቻችን ሲተባበሩ የሚያስመዘግቡትን አንጸባራቂ ድል እናውቀዋለን፡፡ በየትኛውም አጋጣሚ በጋራ የመስራትን መንፈስ ማዳበር ጠንካራ ያደርጋል፤ የበዛ ፍሬም ያፈራል፡፡ አብረን መብላት ብቻ ሳይሆን አብረን መስራትንም ባህላችን እናድርግ፡፡ ስቴቨን ኮቬይ እንደሚለው “አንድ ሲደመር አንድ ከሁለት በላይ ነው”፡፡
7. መጋዛችሁን ሳሉስቴቨን ኮቬይ መጽሐፉ ውስጥ ግሩም አፈ ታሪክ አለ፡፡ አንድ ተጓዥ መንገደኛ በአንድ ጫካ ውስጥ አቋርጦ ሲያልፍ አንድ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ላቡ ጠፍ እስከሚል ድረስ ያለምንም እረፍት እንጨት ሲቆርጥ ይመለከታል፡፡ ተጓዡ መንገደኛ ቆም ይልና የመጋዙን መደነዝ አስተውሎ ኑሮ “ወዳጄ! ለምን መጋዝህን ዕረፍት ወስድህ አትስለውም?” ይለዋል፡፡ ልፋ ያለው እንጨት ቆራጭ “አይ ለሱ እንኳን ጊዜ የለኝም” የሚል የዋህ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡ ይኼ ምስኪን እንጨት ቆራጭ ዕረፍት ወስዶ መጋዙን ቢስል በተሻለ ቅልጥፍና ብዙ እንጨት መቁረጥ እንደሚችል አልተረዳም፡፡የተራ ቁጥር ሰባት ልምድ መልዕክት ቀላል እና ግልጽ ነው፡፡ በቂ ዕረፍት ምንጊዜም አድርጉ ነው፡፡ ከስራ በኋላ ራሳችሁን ዘና የማድረግ ልምምዱ ይኑራችሁ፡፡ መዝናናት ለጊዜው ከሚሰጠው ደስታ ባሻገር ለቀጣይ ስራ ያዘጋጃል፡፡ ሁልጊዜም እንደምለው ትልልቅ ኩባንያዎች ወጪ ችለው፣ ወርሃዊ ደሞዝ መክፈላቸውን ሳያቋርጡ ሰራተኞቻቸውን የሚያዝናኑት በጣም ቸር ስለሆኑ አይደለም፡፡ ይልቁንም የተዝናና ሰራተኛ ይበልጥ ውጤታማ እንደሚሆን እና እነሱንም ይበልጥ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው፡፡አንድ አንድ ሰዎች “እኔ መዝናናት አይሆንልኝም” ይላሉ፡፡ “መዝናናት ራሱን የቻለ ችሎታ ነው” ይላል አንድ ሌላ ወዳጄም፡፡ በመሆኑም “እንዴት እንዝናና?” የሚል ጥያቄ ያላችሁ ሰዎች እነዚህን የመዝናኛ አማራጮች እንድትፈትናቸው እጋብዛለሁ፡- ዋና ዋኙ፤ ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፉ፤ ዮጋ ስሩ፤ ዳንስ ደንሱ፤ ከከተማ ከተቻለም ከሀገርም ወጣ ብላችሁ ጎብኙ፤ ደስታ ይሰጠኛል ብላችሁ የምታስቡትን የትርፍ ጊዜ የመዝናኛ አማራጭን (Hobby) ሞክሩ፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »