እህል በእህል– በቀድሞ ዘመን ኢትዮጵያውያን በእህል በከብት ቢበለፅጉም የገንዘብ ችግር ስለነበረባቸው በገንዘብ ከሚገበያዩ ይልቅ አንዱን ነገር በአንዱ መለወጥ ይቀላቸው ነበር። ለምሳሌ ቃሪያ (በርበሬ) በገንዘብ ከሚገዙ በእህል፣ በሱፍ፣ በስንዴ፣ በልዩ ልዩ ጥራ ጥሬ ይለውጡ ነበር፤ ለምሳሌ ጤፍን በምሥር፣ ሌላውን እህል ወይም ተክል እንዲሁ እንደተፈላጊነቱ ይለዋወጡ ነበር። እንደጊዜው ሁኔታ አንድ ጊዜ እኩል ለእኩል ይለዋወጣሉ፤ አንዳንድ ጊዜም ደግሞ አንዱ ይወደድና 3 ለ 1 ወይም እንዲህ እየተባለ ይለዋወጣሉ። በጠቅላላው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በዚህ መልክ ይገበያዩ ነበር፤ የቀረው ቀርቶ ጥጡ ሳይቀር በእህል፣ እህሉም በጨው ይለወጥና ይገዛ ነበር። ጨው – እህል በእህል ከሚለወጠው ጋር በሁሉም ዘንድ የታወቀው የወል ዋጋ የነበረው፣ እንደዛሬ ብር በኢትዮጵያ ዋጋ ሆኖ የታወቀው ጨው ነበር። ማለት እያንዳንዱ ሰው ብዙ ሊያተርፍ የሚቻለው በጨው የነገደ ሲሆን፣ ውድ የሆነውን ነገር ሁሉ የሚገዛ በጨው ነበር። እዳም ቢኖርበት የሚከፍለው በጨው ነበር፤ የቀረው ቀርቶ ባርያ ይሸጥበት በነበረ ጊዜ እንኳን በዚህን ያህል ጨው የተገዛ ባሪያ እየተባለ የነገር ነበር። የጨውም የዋጋ ግምት የተለያየ ደረጃ ነበረው፤ ማለት ዝቅተኛው አይነት “እየሌ” እየተባለ ይጠራ ነበር። ከዚያም ቀጥሎ የነበረው “ልመደው” የተባለው ከባድ አይነት ጨው ነበር። የመጨረሻው ደግሞ “ጋንፋር” የተባለ ነበር። የሆነ ሆኖ፣ ከነዚህም ውስጥ እየተሸረፈ “ግማሽ እየሌ” “ግማሽ አሞሌ” እየተባለ ይሸጥበት ወይም ይገዛበት ነበር። ጥይት – የብር ያህል ዋጋ ኑሮት ሁሉም ደስ ብሎት የገበያይበት ይለዋወጥበት የነበረ ልዩ ልዩ ዋጋ የነበረው ጥይት ነው። ስለዚህ ለሳበው ጠበንጃ ከሚያገለግለው ባሩድ ጀምሮ፣ የወጡትን ጠበንጃዎች ጥይቶች ሁሉ እንደ አይነታቸው፣ እንደ ተወዳጅነታቸው ዋጋ ነበራቸው፤ ይሸጡባቸው ይገዛባቸውም ነበር። እንዲያውም ከሌላው አይነት ማለት ጨውን ከመሰለ ዋጋ ይልቅ ጥይት ለአያያዝ ተስማሚ ስለሆነ፣ ከእህልና ጨው ይልቅ በጥይት መሸጥ ይወዱ ነበር። ምክንያቱም በአንድ በኩል ላያያዙ ይመቻል፣ ሁለተኛ የጦርነት ጊዜ ስለነበር በየጠረፉ ጠላት ስለሚያስቸግር፣ አንዱ ጎሳም ከሁለተኛው ጋር መጋጠም እንደ ጉብዝና ስለሚቆጠር ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጠበንጃ መያዝና ጥይት መግዛት ይወድ ስለነበር ጥይት በጣም ውድ ዋጋ የነበረው፣ ለመሸጥም ለመግዛትም ትንሹም ትልቁም የሚፈልገው ነበር። ምንጭ ማህበራዊ ኑሮ በኢትዮጵያ (ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ )