በተተከለበት የሚያድግ
በተተከለበት የሚያድግ
ከሰባት አመት በፊት
ሀሳቡ እንዴት እንደመጣለትም አያውቀው፡፡ ዩጋንዳ ውስጥ እያለ ድብርቱን ለማስለቀቅ ያህል ለሚቀርበውና እዚያው ድጋንዳ ውስጥ ለሚገኘው ጓደኛው እንደቀልድ አድርጎ ደብዳቤ ይፅፍለታል፡፡ የደብዳቤው መንፈስ ሲጠቀለል የሚከተለው ነበር፡፡
ለ ግዛው ሽብሩ
(የማይታወቅ ድርጅት ሀላፊ)
ለአመልካሽ ሰለሞን ግዛው በተለያዩ የበረራ ድርጅቶች ውስጥ የሰራሁ ሲሆን ሀገሪ ኢትዮጵያ ውስጥ የግዴ የሆነ የበረራ ድርጅት ከፈቼ የተለያዩ መድሀኒቶችን ለህብረተሰቡ ለማመላለስ፣ የቱሪዝም መስኩን ለማስተዋወቅ፣ የተለያዩ ቱሪስቶች ሀገራችንን በቀላሉ እንዲጎበኙ በማስቻል ረገድ መስራት ስለምፈልግ፣ የእርስዎ ኤንጂኦ የፍላጎቴን ማሟላት እንድችል ትብብር ያደርግልኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
ከሰላምታ ጋር
(የማይነበብ ፊርማ)
ጓደኛው ለቀልድ በተፃፈለት ደብዳቤ ሆዱ እስኪቆስል ስቆ “እብድ!” ሲል ነበር ነገሩን ያለፈው፡፡ ሰውየው የፃፈውን ደብዳቤ ያነበበና አንድ ሚሊዮን ብር እንኳን የሚሞላ ገንዘብ የሌለው መሆኑን ያወቀ ማንም ሰው “እብድ!ሳይለው ቢቀር ነው የሚገርመው፡፡
የተወለደበትን መንደር ስም በየቀኑ ስንሰማው የኖርነው አይደለም፡፡ ምናልባትም ጥቂቶቻችን እንዲህም የሚባል ስም አለ እንዴ? ልንል እንችላለን፡፡ የዛን ጊዜውን አያድርገውና ከማሻ ወደ ትውልድ መንደሩ ቄቶ ለመድረስ ስድስት ሰአት በበቅሎ ወይም ረዥም ጉዞ በእግር መሄድ ግድ ነበር፡፡ የመጨረሻ መጨረሻ የሚባል-የምድር ሆድ የተባለለት ቦታ ነው የተወለደው- ሰለሞን ግዛው፡፡ የትውልድ መንደሩን የምድር ሆድነት ለማጉላት የምናወራለት ሰው አምስተኛ ክፍል አንደደረሰ ድረስ መኪና አይቶ የማያውቅ መሆኑን መጥቀስ ጨዋታችንን ያሞቀዋል፡፡ አስራ አንደኛ አመቱን ሲቆጥር አንዲት ላንድሮቨር አየና ነፍሱ ተመንጥቃ ልትወጣ ደረሰች- አይቶ አያውቅማ፡፡ ደግነቱ መፅሄት ምናምን ላይ ስዕል ያይ ስለነበር እንደምንም ግራ እንዳልተጋባ ተደርጎ ሊወሰድለት ይችላል፡፡ ያቺን ላንድሮቨር ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እያባረራት ሁለት ሶስት ኪሎ ሜትር ሮጠ፡፡ ከዛ በኋላማ የልቡ ደርሶ ሞተር ያለው ነገር ፍቅር አስይዞት ቁጭ አለ- ማን ነበሩ ዘመድ… አለ መለከፍ ነው ያሉት?
አጅሬው ድሮ ባያውቀውም አሁን ሲገባው ግን ከጎሬ ወደ ጋምቤላ የሚሄድ አውሮርላን ይመስለዋል… ሲበር ድምፁን ይሰማል- ለማየትማ መታደልን ይጠይቃል፡፡ ልዩ የሞተር ድምፅ የሚሰማበትን ቀንና ሰአት አእምሮው ሰሌዳ ላይ ክትብ አድርጎ ይዞ መናፈቅ ስራው ሆነ፡፡ አውሮፕላን እንዴት እንደሚሰራ አይወቅ እንጂ እድሜ ደጉ መኪና ሰው ጭኖ እንደሚሄድ አሳውቆታል፡፡ እንጂማ “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ… በዘፈን አንደኛ ጥላሁን ገሰሰ” ሲባል እየሰማ የልጅ ነገር ይሄኔ አብሮም ዘፈኑን አስነክቶት ሊሆን ይችላል፡፡
ምንድነው ግን አውሮፕላን? ምንድነው የሚሰራው? መስመር ስቶም እኮ ሲሄድ በአካባቢው አይቶ ሊሆን ይችላል… ግን ይሄ አውሮፕላን የሚባለው ነገር.. ለሱ ምንድነው? እንዲሁ የሚናፈቅ የሞተር ድምፅ ያለው በዓየር ላይ የሚበር ነገር?… ሌላማ ምን ሊያውቅ ይችላል? ሆሆይ… ድምፁን መስማቱ ራሱ ፍሰሀ ነው እቴ.. እንኳን እየጮኸ የሚያልፍና የሚያገድምበትን ቀንና ሰአት አወቀ እንጂ “ኧኧኧኧ! አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ..” ማለት ነው፡፡
ሩህሩህ፣ ማንም ልጅ የሚያዘው፣ ሰው አክባሪ፣ ተንኮል የሚባል ያልፈጠረበት ጥሩ ልጅ እንደ ነበር ያስታውሳል፡፡ ቄቶ የምትባል የትውልድ መንደሩ እስከ አራተኛ ክፍል ተማረ፡፡ ከዚያዋ ወላጆቹ ወደተሻለ… በሱ ቤት ትልቅ ከተማ መሆኗ ነው… ወደ ማሻ ዘመድ ዘንድ ተላከ፡፡ ያሌ ነው እግዜሩ ብሎለት ያቺን ላንድሮሸር ያየው፡፡
እዚያ ዘመድ ቤት ጥሩ አኗኗር ስለነበራቸው (መቼም በኛ ሀገር የምግብ ብዛት አይደል ጥሩ የሚያሰኝ?) እኛ… ጥሩ ይበላ ነበር፡፡ ለነገሩ ሰዎቹም በጣም ጥሩ ነበሩ፡፡ ትንሽ ብቻ ሰውየው ፍርድ ቤት አካባቢ ስለሚሰሩ ቀን ቀን እስረኞች ሲያስሩ፣ ሲፈቱ የዋሉትን እንጨት ማታ እየተመላለሰ እንዲያመጣ የሚያዙት እሱን መሆኑ ከፋ እንጂ፡፡ ያንን እንደጨረሰ ደግሞ በአማካይ አምስት ወይም ስድስት ጊዜ ሮጥ፣ ሮጥ እያለ ከወንዝ ውሀ መቅዳቷ ላይም መለገም የለበትም፡፡ ተወንዟ ውሀውን ቀድቶ ሲጨርስ ያው ሰውየው ቤት የሚሸጥ ጠጅ ስላለ እሱን ለጠጪዎች መለስ ቀለስ እያለ መቅዳት ግዴታው ነበር፡፡ ምናላት… መላላክ፣ መታዘዝ ለሚወድ ልጅ?! ህም!አለ ያገሩ ሰው፡፡ ብቻ እንዳህያ ነበር የሚሰራው፡፡ አይ እናቴ ሆዴ ጉድሽን አላየሽ ነው የሚባለው? አሃ! ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ እንደመሆኑ እንደብርቅ ነዋ ይታይ የነበረው … እዚህ በጠጅ ሽታ “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” ማለት እንደሁ አይፈቀድለት!
ሳይደግስ አይጣላ አንዲሉ ቤተሰቦቹ ችግሩን ሰሙለትና ጎሬ ወደነበረው የሚሲዮን ሆስቴል ወሰዱት፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ከሚሲዮኖቹ ጋር የመገናኘት የቻለው፡፡ እሱን የሞተር ድምጽ እየሰሙ፣ መኪና ነገር እያሳዩ ገደል መክተትም ቢሆን አይከብድ፡፡ እሱም ራሱ ነገሩን ሲያከብደው “ሞተር እያሳየህ ሀይማኖቴን ልታስለውጠኝ ትችላለህ” ነው የሚለው፡፡ እዛ…ሚሲዮኖቹ ግቢ ያሉትን ላንድሮቨርና ሞተር ብስክሌት እያየ ደርሶ የሚበላው ያጣ ይመስል አይኑን ከርተት፣ ከርተት ሲያደርግ አይተው በጥቂት ፊት ሰጡት፡፡ ትንሸም ቢሆን ስራ እየሰጡት ማንነቱን ማየት ጀመሩ ወጉስ በብዙ ልትሾም በትንሽ ትታያለህ አይደል?አዩታ፣ ለዚህ ሁሉ ግን ምክንያት የሆነው ሚሲዮኖች ያሉበት ግቢ የመኖሩ እውነታ ነው፡፡
ያለው ፍላጐት ከታየ በኋላ እንደው አጋጣሚ ነሸጥ ያረጋቸው እለት የሚወዳትን የውሀ ፓውፕ ሞተር አስነሳ ይሉታል፡፡ እንዲህ የተባለ ቀን የሚሊዮን ብር ሎተሪ የደረሰው ይመስል ሲፈነድቅ፣ ደርሶ እንደግዳይ ጣይ ጀግና ጉራውን ሲቸርችር ነው የሚለው፡፡ የሱ እኩዮች ትምህርት ቤት ሲሄዱም ሆነ ቴኒስ ሲጫወቱ እሱ ግን ያቺን ሞተር ሲነካካ፣ ሲያስነሳ፣ በግራሶ ሲለዋወስ መዋሉን የመጨረሻ ደስታው አድርጎ ነው ቁጭ ያለው፡፡ ከትምህርት ጥናትና ከፀሎት ፕሮግራም በስተቀር ሙሉ ጊዜውን እዛችው ባለችው ጋራዥ ውስጥ ከሚሲዮናዊው ጋር ሲሰራ፣ ሲጎረጉርና በዘይት ሲጥቆረቆር ነበር የሚውለው፡፡ ዕድሜ ደጉ እዛው እያለ ከላንድሮቨር መኪና ማየት አስከ ሞተር ማስነሳት፣ መካኒክነቷንም ለወጉ መሞካከር፣እንዲያ ሲልም አውሮፕላን እስከ ማየት፣ አልፎ ተርፎም የአውሮፕላን መሪ ይዞ አለምን የዞረ ያህል እስኪመስለው ድረስ መሪ ለመጨበጥ ሳይቀር ታድሏል፡፡ መቼም ሰው ብርቱ ካላልን በቀር ናላውን ያዞረው የአውሮፕላን ፍቅር ደርሶ ተማርኮለት መሪ እስከመጨበጥ ሲደርስ ልቡ በደስታ ቀጥ ብላ “አውሮፕላን አፍቃሪው መሪ ሲጨብጥ ጭልጥ አለ! አለመባሉ ራሱ ያስገርማል፡፡
ማመስገንም ከተገባው አኮስትራን ነው፡፡ እኚህ ሚሲዮናዊ የአውሮፕላን ማረፊያውን ሜዳ እንዲጠርግ ከማድረጋቸውም በላይ ባለውለታው ናቸው፡፡ በቴፒ ከተማ አሜሪካ በቀል የሆነውን የሚሲዮናዊ ድርጅት በበላይነት የሚመሩት እሳቸው ነበሩ፡፡ የድርጅቱ አውሮፕላን ደጋግሞ ከመጣ በኋላ አንድ ጊዜ አብራሪው ፓይለት ማክስ ጎቭ ሰለሞንን ይጭነውና በአየር ላይ እየበረሩ ሳለ መሪውን አስይዞ አውሮፕላኑን ያስነዳዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፕላን መሪ ሲይዝ በአእምሮው ለቅፅበት የሰፈነው የዓለሙ ሁሉ ጌታ የሆነ ያህል ነው፡፡ ብቻ ያንን መሪ ይዞ ለጉድ ፈሰሰው፡፡ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም ተሳስቶ ግን “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” ሳይል አልቀረም፡፡
ከዚያ በኋላ መላ ሀገሪቱን እያዳረሰ የነበረው የለውጥ ማዕበል የእድገት በህብረት ዘመቻ ይዞ በመምጣቱ የወጣቱ ሰለሞን እና የሚስዮናዊው ድርጅት ግንኙነት መቋረጥ ግድ ሆነ፡፡ በዘመቻው ማእበል ላለመወሰድ ላይ ታች ማለት፣ ቦታ መቀያየር ተጀመረና ሞተርና ድምፁ መረሳት ጀመሩ፡፡
ከሰባት አመት በኋላ
አዲስ አበባ
መኪናው ወደ ቦሌ ኤርፖርት እያመራ ነው…
እነዚህ ሁለት ሰዎች ድንገት በሆነ አጋጣሚ ዳግመኛ ካልተገናኙ በስተቀር ይሄ የመጨረሻ መሰነባበቻቸው ሊሆን ነው፡፡ መጀመሪያውኑ ግን ካፒቴን ሰለሞን አስራ አንድ አመት ከሰራበት የአሜሪካን ሀገሩ ሚሽን አቭየሽን ድርጅት ስራውን ለቅቆ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቅረት መወሰኑ ለአብዛኞቹ እንደ እብደት የሚታይ ሀሳብ ነው፡፡ ደርሶ የተንደላቀቀ ኑሮ መኖር፣ የተሻለ ደሞዝ፣ የተሻሉ አውሮፕላኖች፣ ስልጣኔ በተትረፈረፈላቸው ሀገሮች እጁን እየተሳመ መስሪት እየቻለ እንዲህ ያለ ውሳኔ መወሰኑ ትንሽ ግራ ያጋባል፡፡
የሆነው ሁሉ ሆነና ካፒቴን ሰለሞን ከአለቃው ጋር ወደ ኤርፖርት እየሄዱ ነው! ያው እንዲህ ሀገሬ… ሀገሬ ማለት ያበዛው ኢትዮጵያ አየር መንገድ ተቀጥሮ ለመስራት ሳይሆን ይቀራል? ፍላጎቱ ከሆነ እስከፈለገ ድረስ ይፈነጭበታል፡፡ ሌላማ ምን ሊሰራ ይችላል? ያው የውጭ ሀገር ኑሮ መርሮት ሀገሩ ተመለሰና ሲሰራ ኖሮ… የሚል… እንዳው ሀገሩን የረሳ ዜጋ እንዳይባል ህይወት ታሪክ ለማሳመር ያህል እዚህ መቅረቱ ደግ ነው፡፡
ምን እንደነሸጥው ባይታወቅም አንድ ተራ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ጫር ጫር አድርጎ ለአለቃው አሳየው፡፡
አለቃው ወረቀቱ ላይ ያለውን ሀሳብ ገረፍረፍ አድርጎ አየውና ወደ ካፕቴን ሰለሞን ዞርም ብሎ ሳያይ “ሀገርህ አይደል? ትችላለህ! አለው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ካፒቴን ሰለሞን ይሄንን ሀሳብ ትንሽ ከቀልድነት በዘለለ ስሜት ውስጥ ሆኖ ያብላላው ጀመር፡፡
በእውነቱ ለአገሩ የመቆርቆሩ ነገር የሚገርም ነው፡፡ የዛሬ ሰባት አመት ለጓደኛው እንደቀልድ የፃፈውን ደብዳቤ ነው ዛሬም እንደቀልድ ለአለቃው ጫጭሮ ያሳየው፡፡ ይሄ ሰውዬ በደንብ እየለየለት ይሆን እንዴ?
እነዛ ሚሲዮኖች ሄደዋል፡፡ ሰለሞንም ሞተር ሳይክል ማስነሳት፣ በዘይትና በግራሶ መጥቆርቆር ቀርቶበታል፡፡ መቼስ የተለመደ ነገር ሲቀር ቅር ፣ ቅር ማለቱ አይቀርም፡፡ መተከዝ ምን ዋጋ አለው? ሰው ያጣውን እያሰበ ሲብሰለሰል ቢኖር ምን ይፈይዳል? በማጣት ያገኘውን ብቸኝነት ማጣጣም ነው፡፡ ቅርጥፍ፣ ቅርጥፍጥፍ፣ምጥጥ፣ ዋጥ ማድረን ነው፡፡ ህይወት እንደሆነ ከነጣጣ ፈንጣጣዋም ቢሆን መገፋቷ አይቀር፡፡
በዚያው የዕድገት በህብረት ዘመቻ ምክንያት አንዴ ጅማ፣ አንዴ ሌላ ቦታ ሲሽከረከር የነበረው ሰለሞን ይቼን ሞተሯን፣ ጥላሸቷን ማርመጥመጥ ለምዶ የለ አደስ አበባ መጣና ብር ጋራዥ በረዳት መካኒክነት መስራት ጀመረ፡፡ ያኔ እድሜ ለዘመኑ አንድ ዳቦ በአስር ሳንቲምና አሁን ማማ ወተት እንደምንለው ያለውን ወተት በሰላሳ ሳንቲም ገዝቶ ዳቦውን እየገመጠ፣ በወተቱ እየማገ የሚወደውን ሁሉ፣ የቤተሰቡን እጅ ሳያይ እየሰለቀጠ ራሱን የሚያስችለውን ትግል ይጋፈጠው፣ መኪና ልፈትሽ በሚል ሰበብ እየነዳ ነፍሱን ረሀ ያደረገው ጀመር፡፡ ደግነቱ በወቅቱ ከነበረው የቀይሽብርና የጥይት ወላፈን መዳኑ ራሱ ትልቅ ዕድል ነበር፡፡ አንድ የእህቱ ሃሳብ ህይወቱን እስከለወጠው ድረስ፡፡
“አንተ እኮ ዝም ብለህ ነው ጓደኞችህ ወደ ውጪ እንዲያወጡህ ማድረግ ትችላለህ!” ትለዋለች፡፡ ጓደኞችህ ያለችው ደግሞ እነዚያኑ ሚሲዮኖቹን እንጂ ሌላማ ጓደኞች አሜሪካ የሉት! … እሱ ግን ያን መሰሉ አመኔታ ስላልነበረው “ምን እዳ አለባቸው ብለሽ ነው?” ሲል መለሰላት፡፡ ለጊዜው የሷን ሀሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ የማድረግ ፍላጎቱ አልነበረውም፡፡ እና ነገሩ ጨዋታ መስሎ አለፈ፡፡
ለሌቱን ግን ነገሩ ጨዋታ ከመሆን ዘሎ አዕምሮውን ወጥሮ የያዘ ውጋት ሆነና አረፈው፡፡ ብትሞከረው ምን ይቀርብሀል? በሚል አዕምሮው ላቀረበለት ጥያቄ መልስ አልባ መሆኑ ነበር ውጋት የሆነበት፡፡ አይነጋ የለም ብርሀን ሲፈነጥቅ ደብዳቤውን ግጥም አድርጎ ፅፎ በአድራሻቸው ላከው፡፡ ምን ይቀርብኛል? ምን አልቀረበትም ነበር፡፡ እንዲያውም አትርፎ ቁጭ አለ፡፡ መልስ ሆኖ የመጣላት ደብዳቤ “አንተ ይሁንልህ እንጂ ከጎንህ ነኝ!” የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ ጥሩ ያልሆነ ሁኔታ ቪዛውን ለማግኘት ሁለት አመት ከስምንት ወር ይፍጅበት እንጂ ፍላጐቱ ሰምሮለት ረዥም በረራ ወደ አሜሪካ አደረገ፡፡
“እንኳን ደህና መጣህ!” ሲሉ የተቀበሉትን ሚሲዮናውያን በአግባቡ ከጎበኘ በኋላ የማንንም እርዳታ ስለልፈለገ ላደረጉለት ትብብር አመስግኖ ህይወትን በአግባቡ ሊያጣጥማት ወደ ሚሽጋን አቀና፡፡ ያን ጊዜ የሰመረ ህይወትን ለመምራት ስላቀደ የሚሰራውን ሁሉ እየሰራ መማር እንዳለበት ወሰነ፡፡ ወይ ስራ? እሱ ያልሞከረው፣ ያልሰራው፣ ያልገባ፣ ያልወጣበት አለ ማለት ውሸት ሊያስመስለው ይችላል፡፡
ከትርፍ ጊዜ ሰራተኝነት ጀምሮ እስከ ሙሉ ቀን ሰራተኝነት፣ ከሳህን ማጠብ እስከ አውሮፕላን አብራሪነት ድረስ ሰርቷል፡፡ የሚማርበት ኮሌጅ በሳህን አጣቢነት ተቀጥሮ ሳህን ሲያጥብ ለጉድ ነበር፡፡ ፅድት አድርጎ በጥንቃቄ የማጠብ ተሰጥኦውን ገመገሙና እድገት ሰጡት፡፡ “ብራቮ ሰለሞን! እያለ ለራሱ ተገቢው ሞራል ይሰጠው ጀመር፡፡ መሻሻሉ ግን እዚህ ላይ ብቻ አላቆመም፡፡ ሶል ለራሱ ለውጥ ፈለገና ወደ መኪና አጣቢነት ተሸጋገረ-የኮሌጁን መኪና ማጠብ ጀመረ፡፡ ከዚህ የከፋው ስራ የመጣው ግን ከዚህ በኋላ ነው፡፡
አንድን በአል ምክንያት በማድረግ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ከተማው ይጎርፉ ነበርና እነሱን ለማመላለስ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ አውቶቢሶች ተመደቡ፡፡ አውቶቢስ ሲባል አንደኛ ሀገር አርጎ ማሰብ አይፈቀድም፡፡ ልጄ! አውቶቢሶቹ የራሳቸው መፀዳጃ ቤት ሳይቀር ያላቸው ናቸው፡፡ እንግዲህ ስራው ይሄ ነበር የሚመጡትን አውቶቢሶች ሽንት ቤታቸውን እያራገፉ ለቅለቅ አድርጎ መላክ ነበር- ቀውጢ አደረገዋ፡፡ ድብን አድርጎ ነው የሰራው፡፡ እሱ ግን የአውቶቢስ ሽንት ቤት እንዳጠበ አልቀረም-እድል ቀንቶት አውቶብስ ባይገዛም በአውቶቢስ ሹፌርነት ላለመቀጠር ያገደው አልነበረም፡፡ የኮሌጁን አውቶቢስ ነድቷል፣ የእንጨት ፋብሪካ ውስጥ የቀን ሰራተኛ ሆኖ፣ እዛው ፋብሪካ ውስጥ ሴኩውሪቲ ጋርድ (ያው በግልጥ አማርኛ ዘበኛ ማለት መሆኑ ነው) ሆኖ ሰርቷል፡፡ ሶል በተተከለበት የሚበቅል መሆኑ -ዘይገረም ነው፡፡ እዛው የእንጨት ፋብሪካ ውስጥ በዘበኝነትና በአንጨት ስራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ እያለ ድርጅቱ አዲስ በኮምፒዩተር የሚሰራ መሳሪያ በማስገባቱ በማያውቀው ስራ ላይ “እኔ ኮምፒዩተር አላውቅም፣ የእንጨት ስራ ላይም ቢሆን ከዚህ በቀር ሌላ ጋ ሰርቼ አላውቅም፡፡ እድሉን ከሰጣችሁኝ ግን እሞክራለሁ!” ይላል፡፡ ይሄ መቼም ድፍረት ነው፡፡ ከማሽኑ አዲስነት አንፃር የሌላ ማሽን ሰራተኛን መድቦ ከማደናገሩ ለሱ እድሉን መስጠቱ ስለታያቸው ፈቀዱለት፡፡ ሰውየው ጨርሶ የዋዛ አልነበረም-ማስተር አደረገውና ቁጭ አለ፡፡ ይባስ የሚገርመው ግን ደረጃውን የጠበቀ ማሽን ላይ እየሰራም ዘበኝነቷን አለመተው ነው ሰው ብርቱ አለ ያገሬ ሰው!
በረዶ በሚበዛበት ወቅት በረዶ በመጥረግ፣ ብዙ ሰዎች ሊሰሩት የማይሞክሩትን አደገኛ ኬሚካሎች የመጣል ስራን፣ ሳር የማጨድ ስራን… ብቻ ሁሉንም… እጅግ መጥፎ ተብለው አይከፋም እስከሚባሉ ድረስ ያሉትን ስራዎች ሁሉ ሰርቷል፡፡ ምክንያት ግን ነበረው፡፡
ራሱን መቻሉ ለሱ ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ ዘበኛ ሆኖ የቤት ኪራዩን መክፈሉ፣ ሳህን እያጠበ ትምህርቱን መማሩ፣ እጅግ አደገኛ የተባለለት ኬሚካል የመጥረግ ስራ እየሰራ ቅዳሜና እሁድ ለአንድ ሁለት ሰዓት ያህል አውሮፕላን ማብረሩ እርግጥም እጅግ ልዩ ደስታው ነበር፡፡ ምክንያቱም ዘላለሙን ዘመኛ እንደሆነ፣ ሽንት ቤት እንዳጠበ እንደማይኖር ጠንቅቆ ያውቀዋላ! ሰው የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት በ-ማይፈልገው መንገድ ቢሄድ ነውሩ ምንድነው? እርግጥ ስንቶች ይህን ደፍረው ሊናገሩት የማይፈልጉትን ነገር ይሆናል ያወራው፡፡ ምናለበት- ሲሰራው ያመነበትን አሁን አልፎ ሲያወራው ቢደሰትበት? ሰውየው ነገሮችን እንዳመጣጣቸው የመቀበል ተሰጥኦ የተርከፈከፈለት ነው፡፡ እና ይሰራ የነበረበት ምክንያት ህይወቱን ለመለወጥ ነበር፡፡ እንጂማ እንደ ጓደኞቹ ሁሉ ሳህን ጣበበበት ሳንቲም አስረሽ ምቺው ቢል፣ ቫኪየችን ቢወጣ፣ አለሙን ቢቀጭ ምን ነበረበት? አሁን የዛሬ ሃያ አምስት አመት ያሳለፈውን ቁጭ ብሎ ለቅፅበት ባሰበ ቁጥር ፈገግ ብሎ “እግዚአብሄር ይመስገን ለዛሬ እንድበቃ ነው ያኔ እንዲያ የሆንኩት” እያለ ለእግዚአብሔር ክብር መስጠት ነው፡፡ አሃ! ከሀያ አምስት ዓመትም በኋላ ሽንት ቤት አጣቢ ሆኖ ይቀር ነበራ! ደሞ እድሉ ሲሰምር ሚሺጋን ስቴት መኖሩ ጠቀመው፡፡ ጥሎበት ዋሽንግተን ዲሲን አይወደውም፡፡ ዲሲ ቢሆን ኖሮ የሞተር ድምፅ እንደመውደዱ አሪፍ የታክሲ ሹፌር በወጣውና ሳንቲም አሳዳጅ ሆኖ በቀረ ነበር፡፡ እዛ ደሞ ያለውን አስተሳሰብ፣ ያለውን ውድድር ደህና አድርጎ ያውቀዋል፡፡ አብዛኛው ሰው የሚሰራው ለሰው ነው- ለሾው! ፈቅር እንኳን የሚይዘው ወይም የሚያስይዘው ለሰው ሲል ነው፡፡ ለእሱ ደግሞ ይሄ አይዋጥለትም፡፡ ይጠላዋል፡፡ ስለ መኪና አይነት፣ ትናንት ስለተጠጣ ውስኪ- ባዶ ጉራ ሲቸረችር መስማት ይደብረዋል፡፡ damned-braggart! Damned-Show-Off! ምክንያቱም በዚህ ወሬ አሜሪካኖቹ ይስቁባቸዋላ፣ ምክንያቱም ጓደኞቻቸው ይስቁባቸዋል፣ ምክንያቱም እግዚአብሄር ሳይቀር ይሳለቅባቸዋል፡፡
ለሱ ግን እግዜሩ አዳልቶለታል፡፡ የሰለሞንን አቅም አውቆ ነዋ ሚሸጋን ሲያክለፈልፍ የወሰደው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ “ኧኧኧ… አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” እያለ የፀለየውን ሰምቶታላ! እና ለምክንያቱ ረዳው፡፡
እሱ ስራን ማድነቅ ተሰጥቶታልና ሳርም እያጨደ፣ ሽንት ቤትም እያጠበ ሌት ተቀን በመስራት ኮሌጅ እየተማረ፣ ጎን ለጎን በሚያገኘው ገንዘብ ህይወቱን መስመር ለማስያዝ የሚያስችለውነ የአብራሪነት ትምህርት መውሰድ ጀመረ፡፡
ያ- የአውሮፕላን ድምፅ እየሰማ ውስጡ ለጉድ ሲጓጓ የነበረ ሰው አልፍለት ስለ አውሮፕላን በደንብ ሊያውቅ ነው፡፡ እና ተምሮ ሲጨርስ በሰማይ ላይ ሊበር ነው፡፡ ወቸው ጉድ “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” በእንዳላለ በተራው በሰማይ እየበረረ ሌሎች ልጆች ሊሉለት ነው… ለነገሩ መቼ አሜሪካ ውሰጥ እንዲህ የሚል ዘፈን አለና?! በዕውነት ግን ሰው የሚመኘውን፣ የሚያስበውን መሆን እንደሚችል በትክክል ሊገባው ነው፡፡ ትምህርቱን እየተከታተለ ሳለም በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ረዥም ጊዜ እንደወሰደበት ያወቁትና ከኢትዮጵያ እንዲወጣ የረዱት ሚስዩናዊ ትምህርት ቤት ሄደው “ይህን ያህል ጊዜ የወሰደበት ለምንድነው? ለምን አትረዱትም?” ይላሉ፡፡ አስተማሪውም “ሰለሞን በጣም ጎበዝ ልጅ ነው፡፡ ካሉኝ የውጭ ሀገር ተማሪዎች ከብዙዎች ይሻላል” ይላል፡፡ ይህን የሰማው ሰለሞንም እንባውን ለጉድ እያጎረፈ ሲንሰቀሰቅ ይውላል፡፡ አሀ! አይደለም ከውጭ ሀገር ተማሪዎች ከዚያው የአሜሪካ ተወላጅ ተማሪዎችም በጣም መወዳደር የማያንሰው ተማሪ ነበራ፡፡ እልህ ወለደና ሌት ተቀን ብሎ ከ600 ሰዓት በላይ የፈጀ በረራ ተምሮ ጨርሶ ወጣ፡፡ ከዚሁ ጋር ተከትሎ የኮሌጅ ትምህርቱን ጨርሶ በቢዝነስና ሥነ-ኃይማኖት ዲግሪ ተመረቀ፡፡ አሁን ዓይወት ሊቀየር ነው፡፡ እነሳህን፣ ሽንት ቤት፣ ሳሮች ሁሉ ደህና ሰንብቱ ሊባሉ ነው፡፡ ሰው ግን የህይወቱን አላማ ይዞ እልኸኛ ከሆነ የማይደርስበት አለመኖሩ አይገርምም? መቼም የሰለሞንን ጉዳይ ስናነሳ በነዚህ በሞተር የሚሰሩ መኪኖችና ሞተሮች ያለውን ልክፍት ሳንገረምበት አንቀር፡፡
አሜሪካንም እያለ ጨርሶ ሊታመን የማይችል ገጠመኝ ነበረው፡፡ ወደ ቤቱ እየሄደ እያለ አንድ መኪና ላይ የተፃፈ ማስታወቂያ ያያል፡፡ ውድ ድር ነበር- እጅን መኪና ላይ ለብዙ ሰአት አድርጎ የመቆየት ውድድር፡፡ መቼም ትምህርት እያለበት፣ ስራ መስራት እያለበት፣ እንዲህ ያለውን ቀሽም ነገር እንደማያደርገው ከመገመት የዘለለ ማሰብ ትንሽ ልክ አይመስልም፡፡ እሱም ለጊዜው የተሰማው እንዲሁ ነበር፡፡ ቤቱ ሲገባ ግን ምን እንዳቃዠው እንጃ መወዳደር አንዳለበት ወሰነ፡፡ መቼስ ውድድሩ ጠዋት ተጀምሮ ማታ ማለቁ አይቀርምና አንድ ቀን ቢያጠፋ ምንም አይደል፡፡ ደሞ እኮ የመኪና ፍቅሩ የትዬለሌ ነው፡፡ ታዲያ ምን አለበት?
ውድድሩ ሲጀመር ገሚሱ እጁን መኪና ላይ፣ ገሚሱ አልጋ ላይ፣ ገሚሱ ቱቦ ላይ ታስሮ ነበር፡፡ ውድድሩ ቀጠለ፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ አነጋ፣ አልፎ ተርፎም አሰለሰ፡፡ ይሄ ተአምር ነው! በአንድ ቀን ያልቃል የተባለው ውድድር አራትተኛ ቀኑን አስቆጠረ፡፡ የውድድሩ ቦታ ላይ ፈረፋንጎ ለፈረፋንጎ እየተላተመ፣ መኪና በመኪና ሆኖ ህዝቡ ለጉድ ውድድሩን መመልከቱን ቀጠለ፡ አምስተኛ ቀኑ ሲቆጠርም ሰዎች እከሌ ያሸንፋል፣ እከሌ ያሸንፋል እያሉ መወራረድ ጀመሩ፡፡ ጋዜጠኞችም ስለዚህ ጉድ ለመዘገብ ቀረቡና ሰለሞንን ጠየቁት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማንነቱን ማሳወቅ ስላልፈለገ ከምዕራብ አፍሪካ አገር እንደመጣና ስሙን ለውጦ ነገራቸው፡፡
ብዙ ሰዎች እየቀረቡ “ምናለ ብትተወው!” ቢሉትም እልህ ተጋብቶ “ሁለት አመትመ ቢፈጅ አልተወው!” ብሎ ድርቅ አለ፡፡ ለሽንት ምናምን ከሚፈቀድላቸው በስተቀር ውድድሩ ለዘጠኝ ቀን ያህል ቀጠለ፡፡ ሰለሞን እጅግ እልህ ስለነበረበት ውድድሩን ማቋረጥ አልፈለገም፡፡ ደግነቱ አለቃው መጥቶ “በርታ እኔ ቦታህ እንዲሸፈን ስለማድረግ ሃሳብ አይግባህ፡፡ አንተ ብቻ አሸንፈህ ና!” ሲል ሞራል ሰጠው፡፡ ከዘጠኝ ቀናት እልህ አስጨራሽ ውድድር በኋላ አሸነፈና- ሁለት ሺ አምስት መቶ ዶላር የሸጣትን መኪና… ተሸለመ፡፡
የበረራ ትምህርቱን እንደጨረሰ ሚሽን አቭየሽን ተቀጥሮ ስራውን መስራት ጀመረ፡፡ እዛ ደግሞ በአብራሪነት ብቻ ሳይሆን በቴክኒሻንነትም ነበር የሚሰራው፡፡ ወደ መቶ ሰማንያ አውሮፕላኖች ያሉትና እምብዛም ጥቁሮች የሌሉበት፣ ቢኖሩበትም የበረራውንና የቴክኒኩን ስራ አጣምረው የሚሰሩ በሌሉበት ነው እሱ የነገሰው፡፡
ተቀጥሮ የሚሰራበት ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም አብሮ መጣ፡፡ ድርጅቱ ቆይታውን ጨርሶ ወደመጣበት ሲመለስ ግን አብሮ መመለስ ፈፅሞ ባለመፈለጉ ነው ለአለቃው እንደቀልድ ያንን ደብዳቤ ፅፎ እያሳየው ኢትዮጵያ በመቅረቱ ላይ እርግጠኛ የሆነው፡፡ ይሄን የግል የበረራ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለመክፈት የሚያስችል ገንዘብ ሊኖረው ቀርቶ ተደጋግሞ ሊጠራ አንኳን ለመስማቱ ፈፅሞ አጠራጣሪ ነው፡፡
ፋይናንስ! ፋይናንስ! መነሻ ካፒታል፣ ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ደግሞ ሊያስይዘው የሚችለው ደረጃውን የጠበቀ ቤት የለውም፡፡ ለነገሩ ቢኖረውስ እንዴት ሆኖ ነው አውሮፕላንን ያህል ትልቅ ነገር የሚገዛለት? ድንቄም ሀሳብ አሉ! ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ምንም አይነት ነገር ለመግዛት ባንኮች መኪና ካላዩ ሲያልፍም አይነካካቸው፡፡ ቤትና መኪናስ ቢኖር መች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያሰጥ ሊሆን? እንግዲህ የሆነ ተአምር ካልተፈጠረ በቀር ይሄ እየቀላለደ፣ እንዳንዴም ቃዠት ሲያደርገው ይፅፈው የነበረው ደብዳቤ …እውነትም ተራ ሀሳብ ሆኖ ሊቀር ነው፡፡ ደግነቱ እሱ ራሱ ጨዋታ ስለሚመስለው ነገሩ ተሳካ፣ አልተሳካ ግድ ላይሰጠው ይችላል፡፡ እውነቱ ግን ይህ አይደለም፡፡ የስነ-ልቦና ጠበብቶች አንድ የሚጠቅም ሀሳብ ካለህ ያ- ሀሳብ ሁለንተናህ እየሆነ ያስቸግርሀል እንዳሉት ሀሳቡ ፈፅሞ እረፍት ሊሰጠው አልቻለም፡፡ መቼስ ሰው በሀሳቡ ላይ ጊዜ ወስዶ በጥንቃቄ ካሰበበት መፍትሄ አያጣም አይደል? ከልጅነቱ ጀምሮ በታማኝነት ሲያገለግላቸው የነበሩት ለሀያ አመታት አብሯቸው የሰራባቸው ድርጅቶች አውሮፕላን የሚዋሱባቸው እህት ኩባንያዎች ስላሉ ማመልከቻውን ግጥም አድርጎ ፃፈላቸው፡፡ አውሮፕላን… አንድ አውሮፕላን ያለቴክኒክ ወጪው ብቻ እንኳን አንድ ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከአንድ በቢዝነስ ዓለም ምንም ልምድ ከሌለው ሰው ደሞ የአንድ ሚሊየን ዶላር እቃ ብድር መጠየቅ በእውነቱ ለቃላት አጠቃቀም ካልተጨነቅን በግርድፉ ራሱ እንዳለው ወፈፍ ያደረገው ቢባል ይታመናል፡፡ ጥያቄውም ሆነ ጨዋታው የአንድ ሚሊዮን ዶላር አንድ አውሮፕላን ማግኘት ብቻ አይደለም! ሁለት አውሮፕላን ነው፡፡ ለሁለቱም አውሮፕላኖች ደሞ በነፍስ ወከፍ ኢንሹራንስ መግባት ያስፈልጋለ፡ ከዛ በኋላ ፓይለት መቅጠር አለ፣ ማሰልጠን አል፣ ብዙ እቃ መግዛትአለ፣ መኪና አለ፣ የቢሮ እቃ አለ… እነዚህ ሁሉ አውሮፕላኖቹ መገኘት ጋር መምጣት ያለባቸው ናቸው፡፡
የላከውን ደብዳቤ ያነበቡት እህት ካምፓሊዎች እርግጡን ለመግለጽ ጨርሶ ግራ ሳይገባቸው የቀረ አይመስልም፡፡ እንዲህ ያለ ነገር በታሪካቸው አያውቁማ! … አውሮፕላንን ያህል ነገር በብድር ሰጥተው አያውቁም፡፡ ይህንን ደብዳቤ ግን ገና እንዳነበቡት “ሌላ ሞክር! መልካም ዕድል! ሊሉት አልቻሉም፡፡ ሰለሞንን በደንብ ያውቁታል፡፡ ትግሉ ያማረ፣ ተአማኒነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን ያምናሉ፡፡ ይህንን አሳምረው ቢያውቁም ግን አውሮፕላኖቹን መስጠት ከበዳቸው፡፡ በሁለት አጣብቂኝ ነገር ውስጥ ናቸው፡፡
ካፕቴን ሰለሞን ደግሞ አላማውን ለማሳካት የማይችልበትን ችግር ሁሉ አስወግዶ ስኬታማ ለመሆን ያቺ የመኪና ውድድሯ እልህ መጥታ ልታንቀው ደርሶለች፡፡ ህይወት ወይ ትጥለዋለች፣ ወይ ይጥላታል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ያ- የሞተር ድምፅ ሲሰማ ልቡ ትፈነድቅ የነበረ ልጅ ጨርሶ ሰምቶ የማያውቀው ሀይለኛ የሞተር ድምፅ ሰማና ልቡ ተደበላለቀ፡፡ ይሄንን ነገር የት ላይ ነበር የሚያውቀው? ለማስታወስ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ መፅሄት ላይ በደንብ አድርጎ አይቶታል፡፡ በተወለደበት ሞቻ በተራራ ላይ ሲያልፍ የራቀ ድምፅ እየሰማ “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” እያለ ብዙ ጊዜ ዘፍኗል፡፡ ያ- አውሮፕላንን በስሙና በመልኩ በቀር የማያውቀው ልጅ አሁን ድምፁን እየሰማ ጨርሶ ርብሽብሽ እያለ ነው፡፡ ምክንያቱ አይግባው እንጂ ከደስታው ይልቅ ፍርሀቱ ትንሽ አየል ብሎበታል፡፡
ህልሙን ለሚኖር ልጅ ነገሩ ቅዠት ነበር፡፡ ጥቅጥቅ ያለ ደኑን ጥሩ ተገኑ አድርጎ አውሮፕላኑ ወደ ቆመበት ቦታ እየተሰረቀ ተጠጋ፡፡ ትንሿ አውሮፕላን የሰማይ ስባሪ ያህል ገዝፋ ታየችው- ምን ያርግ ከዚህ የሚበልጥ ለመኖሩ በምን አውቆ? ብቻ በቅዠት ውስጥ… ፈፅሞ ሊያምነው ባልቻለ የለየለት ቅዥት ውስጥ ሆኖ ወደ አውሮፕላኑ ተጠጋ፡፡ እጁን አውሮፕላኑ ገላ ላይ ጭኖ ሲዳስስ ተሰምቶት የማያውቅ ፈፅሞ መንፈስን ወደ ሀሴት የሚከት ልዩ የፍቅር ዓለም ውስጥ ያለ መስሎ ተሰማው፡፡ ፈገግ እያለ ከዳሰሰው በኋላ ጎንበስ ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በከንፈሩ ሳመው፡፡ አውሮፕላኑን ሳመው፡፡ ከመሳሙ ተከትሎ ግን “ምናባክ ትሰራለህ?” የሚለው የዘበኛ ጩኸት ሲሰማውና ዱላው ሲያርፍበት አንድ ሆነና አንበሳ እንዳየች ሚዳቋ ተስፈንጥሮ ጥቅጥቅ ወዳለው የቡና ደን ውሰጥ ገባ፡፡
መወሰን እንዳለባቸው ያምኑ ስለነበር ብልሀት የታከለበት ውሳኔ ነበር ያስተላለፉለት፡፡ ጨርሶ ይሄ ሀሳቡ እንደማይሰምር፣ በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጣጣዎችን አልፎ ተግባራዊ ያደርገዋል ብለው ስላላመኑ “አንተ ፈቃድ አግኝ እንጂ ተግባራዊ ያደርገዋል ብለው ስላላመኑ እንዲያ እጅግ ጉጉት ላከነፈው ቀልደኛ ሰው ምናልባት ከሱ የተሻለ አሪፍ ቀላጆች እንዳሉ የሚያሰገነዝበው ነበር፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? የዛሬ ሰባት አመት ለጓደኛው እንዲያ ያለ የቀልድ ዳብዳቤ ፃፈለት… እሱስ እሺ ይሁን ተጉዳይም ስላልፃፈለት- ነገሩ ጥሩ ፈገግታ ፈጥሮ አለፈ፡፡ ከሰባት አመት በፆላ ደሞ ለአለቃው ሰጠው፡፡ አሁን ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው እንዲሉ፣ ቀልዱ ምር መሆን ጀመረ፡፡ አሁንማ ይሙት ነገሮች ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ይሄዱለት ይሆን?
ድፍረቷ ግን ይገርማል፡፡ ቃሉን አስረግጣ ነበር ፡ከዚያ ጫካ ውስጥ…” አይን፣ አይኑን እያየችው፡፡ በመሰረቱ ጓደኛው ነች፡፡ “ከዚያ ጫካ ውስጠ ሊያወጣ የሚችል እግዚአብሄር ብቻ ነው!” ማለቷ፡፡ ንግግሯ እንደቀልድ ይሁን እንጂ ነገሩስ እውነትነት አለው፡፡ አሀ! ተደጋግሞ እንኳን ለመሰማቱ ከሚያጠራጥረው ቄቶ ተወልዶ ሰው የህልሙን ይሆናል ብሎ እንዴት ይታሰባል? አንወሻሽና እሱ ራሱ “የኔ ታላቅ ነገር ሞቻ ተወልጄ ለዚህ መብቃቴ ነው!፡ አይደል ያለው? ደግነቱ በአምላኩ ያለው እምነት ከጥንካሬው ጋር ተጣምሮ እጅግ ረዳው እንጂ ፅናት በማጣትስ ስንት ትላልቅ ግብ ገደል ይገባ የለ?
የሚያውቀቸውን ጥቂት ፓይለቶችና ባለሙያዎች፣ ያለውን ያልተጨበጠ ሀሳብ ነገራቸውና አብረውት ይሰሩ እንዲሁ ጠየቃቸው፡፡ ምንም ማስተማመኛ በሌለው ሁኔታ ውስጥ እንኳ ሆኑው ሁሉም ፈቃደኛ ነበር የሆኑለት፡፡ በየወሩ ለትራንስፖርት አምስት መቶ ብር ሊሰጣቸውና ባለው ሁኔታ ግቡን ሊያሳካ ለመንቀሳቀስ ራሱን አዘጋጀው፡፡ አሁን ፈተናዎችን ሁሉ ማለፍ አለበት፡፡ አለበለዚያ ያ-የግል አውሮፕላን ትራንስፖርት እከፍታለሁ ያለው ጉረኛ አይደል? ሊባል ሁሉ ይችላልና፡፡ ቁም ነገሩ ግን ይህን መባሉ አይደለም፡፡ እሱ ውጪ በነበረበት ወቅት ያገኘው ልምድ፣ ሀገር ውስጥ ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማይደርስባቸው በርካታ ቦታዎች እንዳሉ ገብቶታል… ሁሉን ተረድቶታል፡፡ ያቃተው ነገር ቢኖር አውሮፕላኖችን ማግኘቱ ነበር- እግዚአብሄር ይመስገን ለሱም ቢሆን ጨርሶ የማይጨበጥ ተስፋ ተሰጥቶታል፡፡ ልጄ ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል ነው ነገሩ… ያለውን ይዞ ኢንቫስትመንት ቢሮ፣ ሲቪል አቭየሽን ቢሄድ ይሻለዋል፡፡
አቤት እድል? ሰው እንዲህ እድሉን ሊያሳካ ከልቡ ሲነሳሳ ለካ በቀላሉ መማረክ ይችላልና? በየገባበት ቢሮ እብደቱ ተጋብቶባቸውም ሊሆን ይችላል ይህን ሰርዝ፣ ይህን ደልዝ፣ እንዲህ ብለህ ፃፍ፣ እንዲያ ብለህ አስተካክል እያሉ እጁን ይዘው ወፌ ቆመች አሉት፡፡ አለቻ! ፈፅሞ ባልገመተውና ባልጠበቀው ሁኔታ ከልዩ ማበረታታት ጋር ጣጣውን ሁሉ ሲቪል አቪየሽንና ኢንቭስትመንት ቢሮ ጨርሱለት፡፡ አሁን ይሄ ነገር በቅርቡ የሚጣፍጥ ዜና ሊወጣው ነው፡፡ ይሄንን የተገኘ ድል አውሮፕላኑን በዱቤ እንዲሰጠው ለጠየቀው ድርጅት አበሰረው፡ ነገሩ ሁሉንም ነበር ያስደነቀው- ይሄ ነገር ይሳካለታል ብሎ የጠበቀ አልነበረማ፡፡ ያም ሆኖ ግን እንዲህ አውሮፕላኖቹ በዋዛ ፈዘዛ የሚገኙ መሆን አልቻሉም፡፡ ተጨማሪ ትግል መጠየቃቸው አልቀረም፡፡
ከብዙ ትግል በኋላ በማያነቃንቅ የማዱታ ስምምነት አውሮፕላኖቹ ሊሰጡት ተወሰነ፡፡ ድል ሙሉ በሙሉ ለዚያ የሞተር ድምፅ አፍቃሪ ለነበረው ካፕቴን ሰለሞን ተንበረከከችለት፡፡ የአውሮፕላኑ እዳ በመንግስት በኩል በየወሩ እንዲከፈል ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ሌላው መያዣ ደሞ እዳው ተከፍሎ እስኪያለቅ ድረስ የአውሮፕላኖቹ ባለቤትነት በሰጪው ድርጅት ባለመብትነት እንዲቆይ ተባለ፡፡ ለሁለቱ አውሮፕላኖችም ሰላሳ አምስት ሚሊዮን ዶላር ኢንሹራንስ ስለተገባ የኢትዮጵያን መንግስት የሚያስጨንቅ ግዙፍ ችግር አልነበረም፡፡ ያ- ቀልድ ባልተጠበቀ ሁኔታ የምር ሆነ፡፡ ሁለት አውሮፕላኖች፡፡ አቤት ጊዜ?! የአውሮፕላን ፍቅር አናውዞት በልጅነቱ አሻሽቶ ሲሰመው እንዳልተገረፈ ሁለት የሱ የሚሆኑ አውሮፕላኖች ባለቤት ሊሆን ነው፡፡ አንድ አቪየሽን ውስጥ ያሉ ትልቅ ሰውም እንዲህ አሉት “ብዙ ሀብታሞች አሉ፡፡ አንተ ከምታስባቸውም ትናንሽ አውሮፕላኖች የተሻሉ ትላልቅ መግዛት የሚችሉ፡፡ ግን አንድ ሰው 10 ሚሊዮን ብር አውጥቶ አውሮፕላን ገዝቶ ተነሳች፣ ተከሰከሰች፣ እያለ ምን አስጨነቀው? እውነቱን ልንገርህ እንደ አንተ አይነት እብዶች እንፈልጋለን፡፡”
ለመጀመሪያ ጊዜ ቴፒ ላይ አውሮፕላኑን እንዳሳረፈ ህፃናት ግር ብለው አውሮፕላኑን እንደብርቅ እያዩ ሲነካኩት የተመለከተው ካፕቴን ሰለሞን ግዛው ዘበኛው ልጆቹን ለመምታት እያደረገ ያለውን ጥረት አንዲያቆም ያደርገውና ልጆቹን ሁሉ ጠርቶ ምን እንደሚፈልጉ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሁሉም መብረር ነበር ፍላጎታቸው፡፡ “አውሮፕላኑ ሁላችሁንም ስለማይችል ሰልፍ ትይዛላችሁ፡፡ ተራ በተራም እየገባችሁ ትበራላችሁ፡፡ አላቸው፡፡ ልጆቹ ልባቸው ቆማ በያዙት ሰልፍ መሠረት ተራ እየጠበቁ ወደ አውሮፕላኑ ውስጥ እንዲገቡ ያደርግፀ በርራችኋል እያለ በሌላኛው በር ያስወጣቸው ጀመር፡፡ ሁለት መቶ ሀምሳ ልጆች በአንድ ቀን፣ በአንድ አውሮፕላን በማሳፈር ሪከርድ ያዘ፡፡ “ለልጆች የምትለግሰው ገንዘብ ወይም ልብስ አይደለም መድህናቸው-ህልማቸውን ብቻ አሟላላቸው፡፡”
እንዲህ አይነት ቀልድ ጨርሶ አይገባውም-አንድ ሰው “ተወለደ፣ አደገ፣ በላ፣ ጠጣ፣ አገባ፣ ምትክ ፈጥሮ ሞተ! “የሚባል ቀልድ ጨርሶ አይመቸውም፡፡ የተፈጠረበት፣ እግዚአብሄር እሱን የፈጠረበት አንድ አይነት ምክንያት እንዳለ ነው የሚያምነው፡፡ ምናልባት እንዲህ መገመት ከተፈቀደልን እሱ የአውሮፕላን ፍቅር ሰውን እንዴት እንደሚያቃዠው፣ አልፎ ተርፎም እንደሚቻል አምኖ ራሱን ለሀሳቡ ተገዢ ካደረገ ፈፅሞ ያልተጠበቀ ትርፈ እንደሚያገኝ ተምሯል፡፡ ምን ላይ ነበር እሱ ትርፍ እብደት ያልታከለበት ህይወት ጣዕምናው የለተተ ነው የሚል ነገር ያለው?ማበድ በጀው እቴ!…
ሃያ ዓመት ሙሉ የፈለገው፣ የትምህርት ተቋም ገብቶ የማይማረውን፣ ልዩ የህይወት ትምህርት በሶስት አመታት ጨጓራ መላጥ ትምህርቱን ተክኖት ቁጭ አለ፡፡ ያን ጊዜም ነበር ዝም ብሎ በአፉ ብቻ፣ በሀይማኖት ብቻ፣ በከንፈሩ ብቻ የሚያውቀውን ክርስቶስ በልቡ የከተበው፡፡
ከልቡ ያመናቸው ሰዎች (ስማቸውም ሆነ ድርጊታቸው ዝርዝሩ ይታለፍልን) በችግሩ ሰአት ከሱ ጎን እንደሚቆሙ ያመነባቸው ሁሉ እንደ ይሁዳ አባልፈው ሰጡት፡፡ እንደሚለው በትክክል እሱን ለመጉዳት ነበር፡፡ ጨርሶ ሰው የማመን ልክፍት የተጠናወተውና ጥቂት የዋህነት ያለው ሰለሞን ክፉኛ ህይወቱ ተመሰቃቀለበት፡፡ ዳዴ እያለ ነበረው አቢሲኒያ ፍላይት ሰርቪስ አደጋ ውስጥ ሆነ፡፡
ካፕቴን ሰለሞን ገንዘብ አጣ፣ ከልቡ የሚያምንባቸውን ሰዎች አጣ፡፡ በሚጣፍጥ ቃል እንደገለፀው ሞቶ ተቀበረ፡፡ እንደ መፅሀፍ ቅዱሱ አላዛር ከሞት ተነሳ፡፡ ይህ ግን ሶስት አመት ያህል መፍጀቱ አልቀረም ነበር፡፡ ያኔ ለእየሱስ ያለው ፍቅር እጅግ ተለወጠ፡፡ የሶስት አመቱ ቆይታ ትንሽ ጨጓራውን በዛ ሲል ፀጉሩን አሳሱበት፡፡
አዙሮ ማየት አልቻለም ነበር፡፡ እምነት ብቻ ነበረው- እንደሱ አባባል፡፡ አዙሮ ባለማየቱ ተጋጨ፡፡ ቀልጠፍ ብሎ አንገቱን እንደማዞር ለምን ተጋጨሁ ብሎ መሪውን እየደበደበ ቢውል ጊዜውን ቢያጠፋ እንጂ ለመሪውም ሆነ ለሱ ጥቅም የለውም፡፡
በጣም ትልቅ ውለታ የዋለለት ሰው የማይጠበቅ ትልቅ ማጭበርበር ያጭበረብረዋል፡፡ ይህንን የሚያውቁ ሁሉ “ሰለሞን መቼ ይሆን የሰውየውን አንገት አንቆ የሚገላግለው?” እያሉ መጠበቅ ጀመሩ፡፡ እጅግ ብዙ ገንዘብ ነበር ያጣው፡፡ ህልውናውን ነበር ያጣው፡፡ ነገሩ አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ሽማግሌዎች ገቡበት፡፡ በዳይና ተበዳይ፣ አጥፊና ጠፊ አንድ ቦታ ላይ አንደተቀመጡ ሰለሞን ከልቡ እንዲህ አለውና ነገሩን ርግፍ አድርጎ ተወው፡፡ “ስማ!…” አለው፡፡ ጥልቅ ከሆነ ስሜት የተነፈሰው ያ ቃል ንዴቱን፣ ብስጭቱን፣ ሞቱን ሁሉ ጠቅሎ እንዲገልፅለት ነበር የፈለገው፡፡ “ስማ! በጣም አዝኜብሀለሁ፡፡ ትሰማኛለህ? በጣም አዝኜብሀለሁ… ቢያንስ ሞኝ ሆኜ እዚህ እንዳልደረስኩ ይገባህ!” ሌላ የተጨመረ ነገር አልነበረም፡፡
ህይወት የእውነት ብቻ ምርኮኛ እንዲሆን አስተማረችው፡፡ ነገርን አለማብሰልሰል፣ ምናልባት የዋህ መሆንን ትንሽ ቀንሶ ነገሮችን አዙሮ ማየት፣ መጠንቀቅ፣ አልፎ ተርፎም ችግሮችን ሲፈጠሩ ጉዳዬ ብሎ ጨጓራና ፀጉሩን ሳይነካ “ስለመሰላቸው ነው!” በሚል ማለፍ ልምዱ አደረገ፡፡ ሰለሞን እንደልጅነቱ “አውሮፕላን መጣ እየገሰገሰ…” እያለ ባይጫወትም ተግባቢ፣ ለሰው ልጅ ግምት፣ አክብሮት ያለው፣ ከሰራተኞቹ ጋር ጥሩ ቅርበት ያለው ሰው ነው፡፡ ለሱ አውሮፕላን የሞተር ያህል ፍቅር የሚያሳድርበት ነው፡፡ አሁንም ሞተር ሳይክል እያሳዩ ፍቅር በፍቅር ማድረግ እሱን ከባድ አይደለም፡፡ ከሰራተኞቹ ጋር ቁርስ ሆነ ምሳ ተሻምቶ ሲበላ ላየው፣ የሁለት አውሮፕላኖች ባለቤት ቀርቶና ጎበዝ የመርካቶ ነጋዴ የማያስመስለውን መኪና ሲይዝና፣ ሁሌም የቢሮው በር እንግዳ እንኳን ሲያናግር ተዘግቶ አለማውቁን ላየ የሰውየውን ከፊል ስብእና በቀላሉ ለማወቅ አያዳግትም፡፡
አሁን እንደበፊቱ ነገር ሁሉ አረንጓዴ ነው ብሎ ባያምንም መኪና ማገጃውን፣ የዳኞች ማስጠንቀቂያውን ቢጫ ቀለም ለይቶ አውቆታል፡፡ ትንሽ ጥንቃቄ ለህይወቱ ፈፅሞ ዋስትና ባይሆንም አለ አይደል ለደህንነት? ይጠቀምበታል፡፡
ስራው እሱን ስለሚመራው የተነደፈና በሰአት የሚከናወን ፕሮግራም ባይኖረውም ያለውን ሰአት ሁሉ ስራውን የተሻለ ለማድረግ ሊጠቀምበት ከማዋል ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ ለጊዜ ደግሞ፣ የሀገራችን ሯጮች ተመክሮ ግዙፍ ትምህርት ሰጥቶታል፡፡ አንድ ሯጭ በ1/100ኛ ሰከንድ ተሸነፈ ሲባል የሰከንድ 1/100 በሰው ህይወት ላይ የዘላለም ውሳኔ ሲያደርግበት ስላየ የግዜን ዋጋ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡
የአቢሲኒያ ፍላይት ሰርቪስ መከፈትም አንዱ ዓላማ በጊዜያቸው ለሚጠቀሙ ሁሉ ፈጥኖ ለመድረስ፣ ህይወት ለማዳን ነው፡፡ እዚህ አገር የምንሞተው አንዱ ጊዜን ባለማወቃችን ነው፡፡ “በኬንያ በጄት መጥተህ 1 ሰአት ተኩል ፈጅቶብህ እዚህ ጉምሩክ ዕቃህን ስትጠብቅ አንድ ሰዐት ተኩል የምታጠፋ ከሆነ ምን ያህል ችግር እንደሁ ይታይህ” የሚለው ሰለሞን አንድ ሁለት ሶስት ቀናት እግሩን ዘርግቶ ጧ ያለ እንቅልፍ የሚተኛበትን ጊዜ ከመናፈቅ ውጪ እያንዳንዷ ሰከንድ ዋጋ እንዳላት ህይወት አስተምራዋለች፡፡ ለዚያስ ሳይሆን ይቀራል የድርጅቱ ማስታወቂያ አውሮፕላን እየበረረ አህየዋ እያየችው ጊዜዎ ምን ያህል ዋጋ አለው? የሚል ጥቅስ የተጠቀመው? ሚስጥሩ አህያ ሀገራችን ውስጥ ያላት ግልጋሎት የላቀ በመሆኑ እንደ አህያ ልናገለግላችሁ ዝግጁ ነን፣ የትም ገብተን እንወጣለን፣ የሚል ትርጓሜ ያለው ነወ፡፡ ለመዝናኛ ጊዜ የሌለው ሰለሞን ስራው ህይወቱ ነው፡፡
“የማይቻል ነገር አለ፡፡ እሱም ልታደርግ የማትፈልገው ነገር ብቻ ነው” የሚለው ሰለሞን ካሰበው ነገር በላይ ተሻግሯል፡፡ ይሄ ግን ማብቂያው፣ መቆሚያው አይደለም፡፡ ስኬት እጁን ኪሱ ውስጥ ከቶ የተወጣጣበት መሰላል አልነበረም፡፡ እንዳይወድቅ መሰላሉን በእጁ ይዞ ደረጃ በደረጃ፣ እየታገለ ነው የወጣው፡፡ ድርጅቱ እጅግ ተስፋፍቶ ሁለት መቶ፣ ሶስት መቶ ሰው ቀጥሮ የተሻለ መስራት እስኪችል ድረስ ትግሉ ይቀጥላል፣ የእሱ ስኬታማነት ሊመጣ የሚችለው በዚያን ጊዜ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አሁን የሁለቱንም አውሮፕላኖች እዳ ከፍሎ ለመጨረስ እጅግ ጥቂት ወራት ክፍያ ብቻ ነው የቀረው፡፡ የተሳካለት ትዳር ባይኖረውም ቅሉ ትዳሩ ሁለት ከእድሜያቸው 10 ዓመት ቀድመው የሚያስጡ ልጆችን አትርፎለታል፡፡ ገብሬላ ሰለሞንና ናታኒኤል ሰለሞንን፡፡ የ14 እና የ13 ዓመት ልጆች ሲሆኑ ቢኒንግህም የሚባል ትምህርት ቤት ይማራሉ፡፡
የአውሮፕላኑን ድምፅ ከሰማበት ቀን ጀምሮ በጥልቁ ስለአውሮፕላኑ ማሰቡ አልቀረም ነበር፡፡ ከልጆቹ ጋር ሆኖ አውሮፕላን መጣል እየገሰገሰ ከሚለው ዘፈን ጋር በአውሮፕላኑ ሲገሰግስ በምናቡ ከመሳል አልቦዘነም ነበር፡፡ መሰረቱ ከሚሲዩናውያን ጋር መስራቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ያን ጊዜ አውሮፕላኑ የተጎዱ ሰዎችን ለህክምና የሚያመላልስ ነበር፡፡ ያኔ ትንሽ አውሮፕላን ይዞ የእርዳታ ድርጅቶችን፣ ወይ ሀኪሞችን፣ ወይ በሽተኞችን ማመላለስ አጥብቆ ተመኘ፡፡ በትናንሽ አውሮፕላን ትላልቅ ስራዎችን ለመስራት፡፡
ከረዥም ጊዜ በኋላ እዚህ ቦታ ላይ አውሮፕላኑን ከመሬት አሳርፎ ሲወርድ ትዝታ ተገጠገጠበት፡፡ ያ- እብድ፣ ቀዥቃዣ፣ የሞተር ድምፅ በሰማበት ቦታ ሁሉ ነፍሱ ተመንጥቃ የምትበርበት ትንሹ ሰለሞን ታወሰው፡፡ ይሄ ቦታ ትልቅ ታሪክ አለው፡፡ ካፕቴን ሰለሞን ጫካውን ተገን በማድረግ አውሮፕላኑን ከፍቅሩ የተነሳ በእጁ ዳስሶ ሲስመውና የዘበኛው ዱላ ሲያርፍበት አንበሳ እንዳየች ሚዳቋ ከገደል የተወረወረበት ትዕይንት የተፈጠረበት ቦታ ነው፡፡
እንባው በጉንጮቹ ላይ እየወረደ አውሮፕላኑን እንጥንት ጠዋቱ በፍቅር ሲስመው እንባው የአውሮፕላኑን ገላ ማጠብ ጀመረ፡፡
ዛሬ ግን ከኋላው የሚያርፍበት ዱላ የለም!