ስለ ቫት፣ደረሠኝ እና ከቀረጥ ነፃ
ስለ ተጨማሪ እሴት ታክስ በጥቂቱ (VAT)
ግብር/ታክስ ማለት በመዝገበ ቃላት ፍቺው በህግና ደንብ ላይ ተመርኩዞ መንግስት ከህዝብና ከድርጅቶች ላይ ገቢ የሚያገኝበት ስልት ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት የህዝቡን ሁለገብ ጥያቄዎች ይፈታ ዘንድ የበጀት ምንጩ ግብር/ታክስ ነው፡፡
ግብር/ታክስ ቀጥተኛ፣ ቀጥተኛ ያልሆኑና ሌሎች ተብሎ በሶስት ምድብ ይከፈላል፡፡ ቀጥተኛው፤ ከመቀጠር ፣ ከቤት ኪራይ እና ከንግድ ስራ የሚገኝ ገቢ ግብርን ሲያጠቃልል፤ ቀጥተኛ ያልሆኑት በሚለው ምድብ ውስጥ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ተርን ኦቨር ታክስ፣ ኤክሳይዝ ታክሰ፣ የጉምሩክ ቀረጥ፣ የቴምብር ቀረጥ እና ሱር ታክስ ተካተዋል፡፡ ከእነዚህ ውጭ ያሉት “ሌሎች” ተብለው ተፈርጀዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለ ተጨማሪ እሴት ታክስ ጥቂት ብለናል፤ መልካም ንባብ፡፡
ተጨማሪ እሴት ማለት በፍጆታ እቃ ወይም በተጠቃሚ ወጪ ላይ የተመሰረተ ታክስ ሲሆን የሚሰበሰበውም ምርት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ወይም ማንኛውም ታክሱ የሚከፈልበት ዕቃና አገልግሎት ግብይት ሲካሄድበት፤በታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ወይም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚሰበሰብ የታክስ አይነት ነው፡፡
ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚሰላው፤ ታክስ ከፋዩ ከደንበኞቹ የሚሰበሰበውን ተጨማሪ እሴት ታክስ /output tax/ በሚከፈልበት ጊዜ ምርቱን ለማምረት ወይም አገልግሎት ለመስጠት በግብዓትነት ለተጠቀመባቸው ጥሬ ዕቃዎች ግዢ ሲፈጽም የከፈለውን ተጨማሪ እሴት ታክስ በመቀነስ ይሆናል፡፡ ይህም ሂደት የመጨረሻው የምርቱ ወይም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ዘንድ እስኪደርስ ድረስ ይቀጥላል፡፡
ታክሱ፤ ለተጨማሪ እሴት ታክስ የተመዘገበን ወይም መመዝገብ ያለበትን ሰው፣ ታክስ የሚከፈልባቸው ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባን ሰው እንዲሁም በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይመዘገብ አገልግሎት የመሥጠት ሥራ ላይ የተሰማራን ማንኛውንም ሰው የሚመለከት አይነት ሲሆን፤ ይህ የሚመለከተው የሚከተሉትን መፈፀም ይኖርበታል፡-
ሀ. ለተጨማሪ እሴት ታክስ መመዝገብ
ለ. መዝገብ የመያዝ ግዴታ
ሐ. ግብይትን ለታክስ ሰብሳቢው መ/ቤት /ባለሥልጣን/ ማሳወቅ
መ. የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ /ካሽ ሬጅስተር/ መጠቀም
ተጨማሪ እሴት ታክስ፤ የመኖሪያ ቤት(በዋናነት ለመኖሪያነት እንዲውል ታቅዶ የተሰራ ህንፃ)፣ ያገለገለ መኖሪያ ቤት ሽያጭ እና ኪራይ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሚቀርብ ወርቅ ማስገባት እንዲሁም በሀይማኖት ድርጅቶች የሚሰጡ የአምልኮ ግልጋሎቶች (የኃይማኖት ተቋማት ለገቢ ማስገኛ የገነቧቸውን ህንጻዎችና የንግድ አገልግሎቶችን አይመለከትም)፣ የህክምና አገልግሎቶች፣ የትምህርት አገልግሎቶች፣ የኤሌክትሪክና የውሃ እና የመሳሰሉት ከታክሱ ነፃ የሆኑ ግብይቶች ሲሆኑ፤ ማንኛውም እቃ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባበት ወቅት የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዳይጣልበት ካልተደነገገ በስተቀር የ15 በመቶ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚጣልበት ይሆናል፡፡
ደረሠኝ
ደረሠኝ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ግብይት ላይ ተመስርቶ ከሻጩ/አቅራቢው/ ለገዥው የሚሠጥና ግብይት ስለመፈፀሙ ፣ ገንዘብ ስለመሰብሰቡ ፣ ዋጋው ስለመከፈሉ ወይም ለወደፊት ለመክፈል ውል መግባቱን የሚያሣይ ሰነድ ነው፡፡በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 መሰረት ከደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች በስተቀር የደረጃ “ሀ” እና “ለ” ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ፣ አስፈላጊ መረጃዎችንና ደረሰኞችን የመያዝ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በርግጥ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ በህግ ባይገደዱም በፍላጎታቸው መያዝ ይችላሉ፡፡ የደረጃ “ሀ” እና የደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች የንግድ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ግብይቱ በደረሰኝ እንዲደገፍ ያደርጋሉ፡፡
ደረሰኞችመያዝ የሚገባቸው ዝርዝር መረጃዎች
የሽያጭ ደረሰኝ ቢያንስ የሚከተሉት መሰረታዊ መረጃዎች ሊይዝ እንደሚገባ መመሪያው በአንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2 ያስቀምጣል፡-
- የአቅራቢውሙሉ ስም፣ አድራሻና የተመዘገበ የንግድ ስም የታተመበት፤
- የአቅራቢው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር እና ለታክስ የተመዘገበበት ቀን የታተመበት፤
- የደረሰኙ ተከታታይ ቁጥር የታተመበት፤
- የገዥው ሙሉ ስም፣ አድራሻና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፤
- የተጓጓዘው፣ የተሸጠው ዕቃ ወይም የተሰጠው አገልግሎት አይነትና መጠን፤
- ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ላይ የሚፈለገውን የተጨማሪ እሴት ታክስ/ የተርን ኦቨር ታክስ መጠን፤
- በፊደልና በአሃዝ የተፃፈ ጠቅላላ የሽያጭ ወይም ግብይት ዋጋ፤
- ደረሰኙ የተሰጠበት ቀን፤
- ደረሰኙን ያዘጋጅው እና/ወይም ገንዘቡን የተቀበለው ሠራተኛ ሥምና ፊርማ፣
- የደረሰኝ አታሚው ድርጅት ስም፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የታተመበት ቀንና የአታሚው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ቁጥር፤
- ደረሰኙ እንዲታተም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተፈቀደበትን ደብዳቤ ቁጥርና ቀን ናቸው፡፡
የደረሰኝ ተጠቃሚ ግብር ከፋይ ምን ምን ሃላፊነነቶች አሉበት?
በመመሪያው አንቀጽ 19 ላይ ማንኛውም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዕውቅና ያለውን ደረሰኝ የሚጠቀም ግብር ከፋይ የሚከተሉት ሃላፊነቶች እንዳሉበት ተቀምጧል፡-
በባለስልጣኑፈቃድ እና ዕውቅና ያልተሰጣቸውን /ህገ – ወጥ/ ደረሰኞችን አለመጠቀም፤
ለአንድ ግብይት ጥቅም ላይ የዋለን ደረሰኝ ለሌላ ግብይት አለመጠቀም፤
በበራሪና ቀሪ ቅጠሎች ላይ የተለያየ መረጃ አለመመዝገብ፤
ግብይቱ ከተከናወነበት ሽያጭ ዋጋ የተለየ የገንዘብ መጠን በደረሰኙ ላይ አለማስፈር፤
የደረሰኝ ህትመት ከተፈቀደለት ግብር ከፋይ ውጪ ለሌላ ግብር ከፋይ ጥቅም ላይ እንዲውል አለማድረግ፤
ያለደረሰኝ ሽያጭ አለማከናወን፤
ደረሰኝ ለሚጠይቁ ግዥ ፈፃሚዎች ሽያጭ አለመከልከል፤ለአንድ አይነት ተግባር የሚውል ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማሳተም ጥቅም ላይ አለማዋል፤
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህትመት ፈቃድ መስጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ የታተሙ ደረሰኞች በባለስልጣኑ ሳይመዘገቡ ወይም እንዲቋረጡ ከተደረገበት ጊዜ በኋላ አለመጠቀም፤
በእያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል /ቅጅ/ ላይ በመመሪያውአንቀጽ 7 የተመለከቱ መረጃዎችን አሟልተው የያዙ ደረሰኞችን መጠቀም፤
በራሪና ቀሪ ቅጠሎች ያለው ደረሰኝ ማሳተም፣ ደረሰኞችን በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈፀመባቸውን ደረሰኞች በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈፀመባቸውን ደረሰኞች በግብር/ታክስ ህጉ እስከተገለፀ ጊዜ ድረስ ይዞ መቆየት፣ ለሒሳብ ምርመራ ወይም ለግብር አወሳሰን እንዲቀርብ በሚጠየቅበት ጊዜ ማቅረብ፤
የደረሰኝ አጠቃቀም መከታተያ ሌጀሩን ለሁሉም በግልጽ በሚታየበት ቦታ መስቀል እና ትክክለኛ መረጃ አንዲይዝ ማድረግ፤
የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው በተለያየምክንያት አገልግሎት መስጠት ሳይችል ሲቀር በባለስልጣኑ ፈቃድ እና እውቅና የታተመ የሽያጭ ደረሰኝ መስጠት፤
ግብይት ተከናውኖ ለግዥ ደረሰኝ አንደተሰጠ 2ኛውን ቅጂ ወዲያውኑ ለሒሳብ ክፍል ማስተላለፍ እና/ ወይም ከማመሳከሪያ ሰነዶች ጋር ማያያዝ እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን፤
ያሳተመውን ደረሰኝ በቅደም ተከተል መጠቀም፣ በስህተት ቅደም ተከተል ሳይጠብቅ ጥቅም ላይ ያዋለ እንደሆነ በግብር ከፋይነት በሚስተናገድበት የባለስልጣኑ ቅ/ጽ/ቤት ማሳወቅ፤
ደረሰኝ ያሳተመ ግብር ከፋይ በተለያየ አካባቢ ወይም በተለያየ የንግድ ዘርፍ ለሚጠቀምባቸው ደረሰኞች የደረሰኝ ቅደም ተከተል ተፈፃሚ የሚሆነውን ለየንግድ ቦታው ወይም ለዘርፉ የተከፋፈሉትን ደረሰኞች መሰረት ማድረግ አለበት፡፡
ከቀረጥ ነፃ
ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግና ባለ ልዩ መብቶችን ለማበረታታት የተለያዩ ማምረቻዎችና መገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል፡፡ በዚህም መሰረት ብዙዎች ተጠቃሚ ሆነው አገራቸውን ወደ ተሸለ ደረጃ ለማድረስ በኢንቨስትመንቱ መስክ ተሰማርተው ልማቱን በማፋጠን ላይ ይገኛሉ፡፡
ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት ተጠቃሚዎች እነማን ናቸው?
ልዩ ልዩ ሽልማት ያገኙ ፡- ሀገራቸውን ወክለው በውጭ አገራት ለውድድር ሄደው የሚመለሱ ተወዳዳሪዎች ከተሸከርካሪ በስተቀር ያሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (መመሪያ ቁጥር 23/1997 እና 28/1998)
በውጪ ሀገራት ለሚያገለግሉ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች፡-
በውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ሚሲዮን ሆነው ያገለገሉ ዲፕሎማቶች አገልግሎቱን ጨርሰው ሲመለሱ አንድ ተሸከርካሪና የግል መገልገያ ዕቃዎች ይፈቀድላቸዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ አካላት፡- (በደንብ ቁጥር አመ147/28/17 ቀን 03/10/2001)
ከቀረጥ ነፃ ማስገባት የሚችሉት በ10 ዓመት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ ነው
ተሸከርካሪና የግል ዕቃዎችን ካስገቡ ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችሉም፡፡
የአካል ጉዳት ያለባቸው፡-
እንደ ጉዳታቸው መጠን እየታየ አንድ ተሽከርካሪ ማስገባት ይችላሉ፡፡ ይህም በገደብ የተያዘ ነው፡፡ (በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር የወጣው መመሪያ ቁጥር 41/2007)
የእነዚህ ደግሞ፡-
ከ1600 ሲሲ መብለጥ የለበትም
ከ10 ዓመት በፊት መሸጥna መለወጥ አይቻልም
የጉዳታቸው መጠን የሚገልፅ በሀኪሞች ቦርድ የተሰጠ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
ልዩ አውቶሞቢል የሚያስመጡ ከሆነ የደመወዝ መጠናቸው የተጣራ አመታዊ ገቢ 40,000 ብር መሆን ይኖርበታል፡፡
አውቶሞቢል የሚያስመጡ ከሆነ የተጣራ አመታዊ ገቢያቸው ቢያንስ 80,000 ብር መሆን አለበት፡፡
ይህም ግብር ሰብሳቢው መ/ቤት በአመት የሚያገኙትን ብር ተጠቅሶ ግብር መክፈላቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ የሚሰጣቸው ከሆነ ብቻ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
ለኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶች ከኢንቨስትመንቱ ጋር የተያያዘ የካፒታል ዕቃዎችን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በደንብ ቁጥር 04/76/32/22 ቀን መጋቢት 02/1996)፣ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በተሰጠው የተሽከርካሪ ከቀረጥና ታክስ ነፃ የማስገባት መብት መሰረት በተፈቀደው መጠን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በመመሪያ ቁጥር 4/2001 መሰረት) እና በተመረጡ የኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ባለሃብቶች ለተሰማሩበት ዘርፍ በተፈቀደላቸው የተሸከርካሪ የቀረጥ ነፃ መብት መሰረት በተፈቀደው መጠን ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በመመሪያ ቁጥር 4/2005 መሰረት)
ማንኛውም ለኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ከ5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያላነሰ ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ኢንቨስት ማድረጋቸው ሲረጋገጥ ተሽከርካሪን የማይጨምር የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች ያስገባሉ፡፡ ይህም ከ10,000 የአሜሪካ ዶላር የማይበልጥ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ጨምሮ አንድ ጊዜ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (በደንብ ቁጥር 1.6/5/1 ቀን ሚያዝያ/2001)
በኢትዮጵያ ለመኖር ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡ ቱሪስቶች እና እውነተኛ ጎብኚዎች በጉምሩክ ታሪፍ (ለ) ቁጥር (2) በተመለከተው መሰረት ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር እንዲያስገቡ ሲፈቀድላቸው፤ ይህም የግልና የቤት ውስጥ ዕቃዎች ጠቅላላ ዋጋ ከ5,000 የአሜሪካ ዶላር ያልበለጠ ከሆነ ነው፡፡ (በደንብ ቁጥር 1.6/19/2 ህዳር 9/2002)
በተለያየ አለም አቀፋዊና አህጉር አቀፍ ስራዎች ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖር የሚመጡ ወይም በአለም አቀፋዊ ተራድኦ ስምምነት መሰረት የሚመጡ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት ይፈቀድላቸዋል፡፡
የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች /ሆቴሎች/፣ ለሆቴሎች የካፒታል ዕቃዎች አገልግሎት የሚውሉ አላቂ ዕቃዎች ጨምሮ ማስገባት ይችላሉ፡፡ (የኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 5/2007)
በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጅቡቲ ቅ/ፅ/ቤት ሰራተኞች፡-
ሶስት እና ከዚያ በላይ አመታት በጅቡቲ ቅ/ፅ/ቤት የቆየ ሰራተኛ ስራውን/ዋን አጠናቆ/ቃ ሲመለስ/ስትመለስ አንድ አውቶሞቢል እና የግል መገልገያ እቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይፈቀድላዋል፡፡ (በደንብ ቁጥር ተ/ከ/ቀ/ዳ/539 ቀን ጥር 12/2007)
እነዚህ ባለመብቶች፡-
በ10 ዓመታት ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ መኪና የሚያስገቡ ይሆናል፡፡
መኪናውንም ሆነ ዕቃውን ከቀረጥ ነፃ ካስገቡ ከ5 ዓመት በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ አይችሉም፡፡
ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት መፈቀዱ ምን አይነት ጥቅም አለው?
ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገቱን እና የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋግጣል፤
በርካታ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ገብተው መዋለንዋያቸውን ለኢንቨስትመንት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፤
ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድልን ይፈጥራል፣ ከሚሰበሰበው ግብር ልማቶች ይገነባሉ ህብረተሰቡን ከዚህ ተጠቃሚ ይሆናል፤
የቴክኖሎጂ እና የዕውቀት ሽግግርን ይፈጥራል፤
ይህም በመሆኑ መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 11 ቢሊዮን ብር ያህል ከቀረጥ ነፃ መብት በመፍቀዱ ለኢንቨስትመንት መስክ ከፍተኛ ማበረታቻና የመደገፍ ስራ ተሰርቷል፤ በሃገሪቱም ላይ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ተሰርተው በርካታ ባለሀብቶችን መፍጠር ተችሏል፤ ለበርካታ ዜጎችም የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡