መነሻ ገንዘብ

 መነሻ ገንዘብ  

 የንግድ ድርጅቶች መነሻ ገንዘብ

አንድን የንግድ ድርጅት ሥራ ለማስጀመር የሥራ እቅድ ሰነድ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚያስፈልገው አንዱ አብይ ጉዳይ መነሻ ካፒታል ነው፡፡ የሥራ እቅድ ሰነዳችን ላይ ምን ያህል ገንዘብ ወይም መነሻ ካፒታል እንደሚያስፈልገን በፋይናንስ እቅዳችን አማካኝነት ከተሰላና ከታወቀ በኋላ ይህ ገንዘብ ከየት ማግኘት እንደምንችል የተለያዩ አማራጮችን በማየት የተሻለውን እንወስናለን፡፡ ይህንን መነሻ ካፒታል ማግኘት ካልተቻለ ድርጅቱን መመስረት ስለማይቻል የገንዘቡ ምንጭ መታወቅ ወሳኝ ይሆናል፡፡

በእኛ ሀገር ድርጅት ለመመስረት መነሻ ካፒታል የምናገኝባቸው ምንጮች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  • የግል ሀብት
  • ጓደኛና ቤተሰብ
  • ንግድ ባንኮች
  • አነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች
  • ስጦታ ወይም ድጋፍ ናቸው፡፡
  1. የግል ሀብት

አንዳንድ ሥራ ፈጣሪዎች የሚመሰርቱትን አዲስ የንግድ ሥራ በራሳቸው ካጠራቀሙት የግል ገንዘብ ፋይናንስ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡ ይህ አማራጭ ከሌሎች ምንጮች ያገኘነውን ገንዘብ መመለስና አለመመለስ ላይ ሊኖር የሚችል ስጋትን ከማስወገዱም ሌላ በሥራ ፈጣሪው ላይ በራስ መተማመንን ያሳድጋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በራስ ሀብት የሚመሰረት ድርጅት በራሳችን ሙሉ ነፃነት የምንመራው እና ከማንኛውም አይነት ጣልቃ ገብነትና ቁጥጥር ነፃ ነው፡፡

ብዙ ሰዎች አዲስ የንግድ ሥራን ለመፍጠር በጣም ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን በርካታ ሥራ ፈጣሪዎች በራሳቸው አነስተኛ ገንዘብ በመነሳት አቅማቸውን የፈቀደውን ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ በመስራት ለትልቅ ደረጃ ሲደርሱ ይታያሉ፡፡ ይህ የበርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ባህሪ ነው፡፡ ይህም ሲባል ሥራ ፈጣሪዎች ሌሎች አማራጮችን አይጠቀሙም ማለት አይደለም፡፡

በተለያዩ ሚዲያዎች ቀርበው ተሞክሯቸውን ያካፈሉን ሥራ ፈጣሪዎች የንግድ ሥራ ለመጀመር በማይታሰብ እጅግ አነስተኛ ካፒታል በመነሳት ዛሬ ለትልቅ ደረጃ ደርሰው አይተናል፤ ሰምተናል፡፡ ይህ የሚያሳየን የገንዘቡ አቅም ብቻውን ጥቅም ሊያመጣ አንደማይችልና አነስተኛ ገንዘብም ቢሆን የራስ ተነሳሽነትና ለሥራው ያለን ቁርጠኝነት ለውጤት እንደሚያበቃን ነው፡፡

በግል ገንዘብ የሚመሰረት ድርጅት ኪሳራ እንኳ ቢያጋጥም የሚከስረው የራሱን ገንዘብ እንጂ በብድር የተገኘ ባለመሆኑ ለሌላ እዳ ተጠያቂ ከመሆን ይድናል፡፡ በሌላ በኩል አንዳንድ የገንዘብ ምንጮች ገንዘብ ለማበደር ወይም ለመስጠት ሲፈልጉ በግሉ ያደረገውን የገንዘብ መዋጮ ይመለከታሉ፡፡ ለድርጅቱ ከራሱ ገንዘብ ያላወጣ ሥራ ፈጣሪ ለንግድ ሥራው ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ እንደሆነ ይገምታሉ፡፡ ስለዚህ ከእንደዚህ አይነት የገንዘብ ምንጮች ተጨማሪ ካፒታል ለማግኘትም የግል ገንዘብን ለንግድ ሥራው ማዋል ተገቢ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የግል ገንዘብ በቀላሉ ለማግኘት የማይችሉ ሥራ ፈጣሪዎች የራሳቸውን የንግድ ሥራ አስኪመሰርቱ ድረስ ለንግድ ሥራቸው መመስረቻ የሚሆን ካፒታል በተለያዩ ተቋማት ለማግኘት ተቀጥሮ ወይም በማይፈልጓቸው ሥራዎች በመሰማራት ሰርተው ገንዘቡን ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለንግድ ሥራው መመስረቻ የሚሆን ገንዘብ እንዳገኙ ወዲያው የራሳቸውን ሥራ ይጀምራሉ፡፡

  1. ጓደኛና ቤተሰብ

ሥራ ፈጣሪው በራሱ ድርጅቱን ለመመስረት የሚያስፈልገውን ሃብት ማግኘት ካልቻለ በሁለተኛ ደረጃ የምንመለከተው ከጓደኛና ቤተሰብ የሚገኝ የገንዘብ ምንጭ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለድርጅቱ የሚያስፈልገውን ካፒታል ወጪ የሚያደርጉ ከሥራ ፈጣሪው ጋር ካላቸው ቀርቤታ አንፃር ነው፡፡

ከጓደኛና ቤተሰብ የሚገኝ የገንዘብ ምንጭ በሁለት መንገድ የሚታይ ነው፡፡ አንደኛው ጓደኛና ቤተሰብ ገንዘቡን ለሥራ ፈጣሪው የሚሰጡት በሚመሰረተው የንግድ ድርጅት ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ እንዲኖራቸው በመፈለግ ነው፡፡ ይህኛው አማራጭ ሥራ ፈጣሪው የንግድ ሥራውን በነፃነት ብቻውን እንዳያከናውን እና በእነዚህ ሰዎች አማካኝነት የንግድ ሥራውን የማስተዳደር፣ ውሳኔዎችን የመወሰንና የቁጥጥር ሥራዎችን የሚጋሩት በመሆኑ የንግድ እንቅስቃሴው ሥራ ፈጣሪው በሚፈልገው መንገድ እንዳይሄድ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ስንመለከተው ደግሞ ይህ አይነቱ የገንዘብ ምንጭ ዋስትናን የማይጠይቅ እና የተወሰነ የድርጅት ባለቤትነት ድርሻን በመስጠት የሚገኝ ነው፡፡

ሁለተኛው መንገድ ጓደኛና ቤተሰብ ገንዘቡን ለሥራ ፈጣሪው የሚሰጡት በብድር መልክ ነው፡፡ ጓደኛና ቤተሰብ ገንዘቡን በብድር መልክ ለሥራ ፈጣሪው የሚሰጡት ከሆነ የንግድ ስራው ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚያከናውን ሲሆን እነዚህ ግለሰቦች ገንዘቡን ሲያበድሩ ብድሩን የሚሰጡት ካላቸው ቀረቤታ በመነሳት በመሆኑ እንደሌሎቹ አበዳሪ ተቋማት ዋስትና ላይጠይቁት ይችላሉ፡፡

ከጓደኛና ቤተሰብ የሚገኝ የገንዘብ ምንጭ አንዱ እና ዋነኛው ችግር የንግድ ድርጅቱ አትራፊ መሆን ባይችል ሥራ ፈጣሪው ከእነዚህ አካላት ጋር ያለው ግንኙነት የሚሻክር መሆኑ ነው፡፡

  1. ንግድ ባንኮች

በንግድ ባንኮች ለምንበደረው ብድር በቂ ዋስትና ማቅረብ እስከቻልን ድረስ ለድርጅት መመስረቻ የሚሆን ካፒታል የምናገኝባቸው አማራጮች ናቸው፡፡ ባንኮች ብዙ ጊዜ ለመካክለኛና ለትላልቅ የግድ ድርጅቶች ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ያገለግላሉ፡፡

ከባንክ የሚገኘው ገንዘብ መጀመሪያ ለመበደር በቂ ዋስትና ማቅረብ እና በተገቢው መንገድ የተጠና የአዋጭነት ጥናት ሰነድ የሚጠይቅ ሲሆን የሚገኘው ገንዘብም ወለድ የሚከፈልበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ብድሩ የሚከፈልበት የጊዜ ገደብም ያለው በመሆኑ በሥራ ፈጣሪው የንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተጨማሪ ጫናን ይፈጥራል፡፡

በብድር አመላለስ ወቅትም የንግድ ስራው በአጋጣሚ አዋጪ ላይሆን ከቻለ የንግድ ድርጅቱ መክሰሩ ብቻ ሳይሆን ያስያዘውን ዋስትና ለምሳሌ ቤት ወይም መኪና ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከባንክ ብድር ከማግኘታችን በፊት የአዋጭነት ጥናቱን አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማጥናትና በንግድ ሥራ እንቅስቃሴ ወቅትም ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  1. አነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች

አነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ድርጅቶች በንግድ ባንክ የሚጠየቀውን ዋስትና በማቅረብ ብድር ማግኘት ለማይችሉና በአነስተኛ አቅም የሚመሰረቱ የንግድ ሥራ ተቋማት አይነተኛ የገንዘብ ምንጭ ናቸው፡፡

እነዚህ ተቋማት አሰራራቸውና የብድር አሰጣጥ ስርዓታቸው ከንግድ ባንኮች ጋር ተመሳሳይነት ያለው ቢሆንም የሚጠይቁት ወስትና በተነፃፃሪ ቀላል የሚባል ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት ለሥራ ፈጣሪዎች ብድር ከማቅረባቸው በተጨማሪም የምክርና ሌሎች አገልግሎቶችንም ይሰጣሉ፡፡

  1. ስጦታ ወይም ድጋፍ

አንዳንድ  መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተቋቋሙለትን ዓላማ መሰረት ያደረጉ መስፈርቶችን በማውጣት ለአንዳንድ ግለሰቦች የንግድ ሥራ ለመጀመር የሚያስችላቸውን ካፒታል በስጦታ ወይም በእርዳታ መልክ ይሰጣሉ፡፡

እነዚህ ድርጅቶች አብዛኛውን ጊዜ ትኩረት የሚያደርጉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ፣ ወይም ወላጅ የሌላቸው ህፃናትና አሳዳጊ ሞግዚቶቻቸው እና የመሳሰሉ ዜጎች ላይ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አንደንድ ተቋማት የተለየ የፈጠራ ሥራ ላላቸው ሥራ ፈጣሪዎች የፈጠራ ሥራቸውን ለማምረት ወይም ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል በጀት ይመድባሉ፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነው በቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ይህንን ተግባር ለመደገፍ በጀት መያዙን ማስታወቁ በዋናነት የሚታይ ነው፡፡

ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ግለሰቦች እና የንግድ ድርጅቶች እንደዚህ አይነት ሥራዎችን በግላቸው የሚደግፉ ይኖራሉ፡፡ ስለሆነም ሥራ ፈጣሪዎች እነዚህን የቀረቡ የካፒታል ምንጮች በሚገባ በመገምገም የተሻለውን አማራጭ ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ አማራጮችን በሚገመግሙበት ወቅት የተለያዩ መስፈርቶችን ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ እነዚህ መስፈርቶችም የሚከተሉትን ሊያካትቱ ይችላሉ፡፡

  • ገንዘቡ በሥራ ላይ ሊቆይ የሚችልበት ጊዜ
  • ገንዘቡን ለማግኘት የምናወጣው ወጭ
  • በድርጅቱ ላይ ሊኖር የሚችለው ቁጥጥር እና የመሳሰሉት፡፡

 

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »