ለማሸነፍ የተቀባ

ለማሸነፍ የተቀባ

…ውድድሩ የመጨረሻ ዙር ላይ ደርሷል…
ፖልቴርጋት እየመራ ነው….
የሚያስገርም ብቻ ሳይሆን በሚያስደነግጥ ሁኔታ ክንያዊው ፓልቴርጋት እየመራ ነው፡፡
ሀይሌ ገብረስላሴ ከኋላ እየተከተለ ይገኛል፡፡ ይህ በታሪክ ሆኖ የማያውቅ ክስተት በመሆኑ የሀይሌን መሸነፍ አለም ሲሰማ ጉድ ይላል… የዓለም ጋዜጠኞችም የሱ ማሸነፍ ዜና አይሆንም እንዳሉት ጮማ ዜና ሲያገኙ በመሆኑ ተንሰፍስፈዋል፡፡ ምክንያቱም ዝንተ ዓለም የሀይሌን አሸናፊነት መዘገብ ሰልችቷቸዋላ!…
  
ለነገሩ እሱም ተስልችቶ ነው የተወለደው፡፡ ምናልባትመ ቤተሰቦቹም በማያስታውስት ሁኔታ ለቤተሰቡ ዘጠገኛ… ወይ አስረጃ አልያም አስራ አንደኛ ሆኖ ሊሆን ይችላል የተወለደው፡፡ ከሱ መወለድ በፊት የተወለድና ዓመት፣ ሁለት ዓመት ሲሞላቸው የሞቱ ልጆች አሉ፡፡ እና ስንተኛ ልጅ እንደሆነ ባይታወቅም ገጠር ውስጥ እንኳን ደህና መጣችሁ በሚል ሞቅ ያለ የፌሽታ አቀባበል ከሚደረግላቸው የመጀመሪያ ሶስት ልጆች መካከል አንዱ ለመሆን ባለመታደሱ ተሰልችቶ መወለዱን ያውቀዋል፡፡ ምን ማድረግ ይቻላል ይታደሱታል እንጂ አይታገሉትም አይደል ወግ ማጣፈጫው?! ምንም እንኳን እድለ ወርቅ ሆኖ የፌሽታና የዕልልታ አቀባበል አልገጠመውም ቢባልም ከቆውንም ግን እግረ ደረቅ አልነበረም፡፡ እናም ባባቱ ዕልፍኝ በስተጀርባ ከሚገኘው የከብቶች በረት ለምለም ግት ያንዠረገጉ አራት ወተት መጋቢ ላሞች አለንልህ ሲሉ ከተፍ አሉ፡፡ ያለ ሀሳብ የአራት ላሞች ወተት አየተጋተ ማደግ ነው፡፡ የተወለደው አርሲ ከአሰላ ከተማ ትንሽ ወጣ ብላ በምትገኝ ዳራ በተባለች ገጠር ውሰጥ ሚያዚያ 10 ቀን 1966 ዓ.ም ነው፡፡ እድሜው ትንሽ ከፍ ሲል ማንም የገጠር ልጅ ይገጥመዋል ተብሎ ከሚታመነው ከብት መጠበቅ አላመለጠም፡፡ ይሄ እንደ ዕድል እንኳን ከተቆጠረ የከብት ጥበቃው ላይ የተሾመው እሱ ነበር፡፡ ከብት ጥበቃ የቱንም ያህል አሰልቺ ስራ ቢሆንም ልጁ ኃላፊነቱን የሚወጣ፣ ያወጣቸውን ከብቶች በአግባቡ ቆጥሮ የሚያስገባ አንደኛ ደረጃ ከብት ጠባቂ በመሆኑ ከሱ ሌላ ከቶም ያስከፋው ስለነበር እኔ ብቻ ነኝ እንዴ ልጅ? እያለ መነጫነጭና መበሳጨትን የአልፎ አልፎ ጎብኚዎቹ አድርጓቸው ቁጭ አሉ፡፡
  
… ሩጫው ቀጥሏል፡፡ ከመጨረሻው ዙር ላይ ትንሽ እየተቀነሰለት ነው…
በሀይሌ ገብርስላሴ ግንባር ላይ ላብ ቦይ ሰርቶ በመስመር እየወረዳ ነው፡፡ ጨርሶ ሊታመን የማይችል ነገር የሚፈጠር ይመስላል፡፡
እስከዛሬ በተደረጉት ውድድሮች ሁሉ ፖልቴርጋት ከሀይሌ ፊት ቀድሞ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ጊዜ ፊቱን ያዞረ ይመስላል፡፡ እና ታሪክ ከመጀመሪያ ጊዜ የፖልቴርጋትን ስም በአሸናፊነት ሊመዘግብ ነው….
ፖልቴርጋት ይመራል…
  
ልጅነቱን ወግ ያለው ጨዋታ ከብጤዎቹ ጋር ተጫውቶ አለማሳለፉ የሚደንቅ መለያው ነው፡፡ ወሬና ቅርበቱ… ጨዋታው ሁሉ ከአዋቂዎች ጋር ነበር፡፡ የልጅ አዋቂ ለመሆን የሚያደርገውን ጥረት የሚያውቁ ሁሉ “ሂድ ወዲያ ደሞ ከአዋቂ ጋር ወሬ?!” ቢሉትም በተለይ ፖለቲካና ታሪክ ላይ ከቻለ በግልፅ ማውራት ካልሆነለትም ተደብቆ መስማት ነፍሱ ነበር፡፡ ወደ ትምህርት ቤት እንኳን ሲሄድ ከጓደኞቹ ጋር ሳይሆን መንገደኛ የሆኑ ትላልቅ ሰዎችን ቀርቦ ከነሱ ጋር ያገር ወሬ እያወራ መሄድን ነበር የሚመርጠው፡፡ እድሜ ራሱ ትምህርት ቤት ነው ይባል የለ? ለሱ በትክክልም ትምህርት ቤቱ ነበሩ፡፡ ያኔ ታዲያ በእድሜ የገፉ ሴቶች ከብት፣ እንጨት፣ እህል ተሸክመው ሲያይ ልርዳ ብሎ መሸከምና ከነሱ የሚያገኘውን ምርቃት አጣጥሞ እየሰማ በደስታ ሲፈነድቅ መዋል አንዱ ልምዱ ነበር፡፡ ሽማግሌ ተሳድቦ የሚሮጥ ልጅም ካየ አባሮ ይዞ ለሽማግሌው በማስረከብ የታወቀ በመሆኑ ምርቃት እየተዥጎደጎደለት ነው ያደገው፡፡ ለእሱ በእድሜ የገፉ ሰዎች ልዩ ፍቅሩ ናቸው፡፡
ስራ ወዳድነቱ ይሄን ከዚህ የሚባል አይደለም፡፡ ልጅ ሆኖም እጅግ ታታሪና ተስፋ የማይቆርጥ ሰራተኛ ነበር፡፡ ከስራ ወዳድነቱ በበለጠ በፈጠራ ያለው ስሜትና ይሰራቸው የነበሩ ነገሮች የቤተሰቡን አባላት በሙሉ በማስደነቅ የት ይሆን መድረሻው?” ያስብሉ ነበር፡፡ ያለማጋነን ያልሞከረው ነገር የለም ቢባል መዋሸት አይሆንም፡፡ ስዕል ይሳላል፣ ቅርፃ ቅርፆችን ይሰራል፣ ሌላው ቀርቶ እንኳ የሀገራችን የአስተራረስ ዘዴ ኋላ ቀር መሆን በጣም ያሳስበው ስለነበር ለመጀመሪያ ጊዜ በአራት በሬ የሚታረሰውን መሬት ከእንጨት በሰራው ለየት ያለ የማረሻ መሳሪያ በአንድ በሬ ላይ ብቻ በመጥመድ በአንድ ጊዜ አርሶ፣ አለስልሶ፣ ማልበስ የሚቻልበትን ድንቅ የፈጠራ ስራ ሰርቷል፡፡
መሳሪያው ልክ የትራክተር ላይ የሚገጠመውን ማረሻ የሚመስል ሲሆን በፈጠራ ጥበቡ ከእንጨት ነበር የስራው፡፡ ያን ጊዜ ለቤተሰቡ አባላት ለእያንዳንዳቸው አንድ ወይም ሁለት ጥማድ የሚውል መሬት ይሰጣቸውና ያንን አልምተው ከሚያገኙት ገንዘብ ለደብተርና ለሌሎች ወጪዎቻቸው እንዲያውሉት ይደረጋል፡፡ እሱ ታዲያ በራሱ የፈጠራ አስተራረስ የተሻለ የጤፍ ምርት በማግኘት ቀዳሚ መሆኑ ያስደስተው ነበር፡፡
ከዚህ ሌላ ወንበርና ጠረጴዛዎች በተሻለ ሁኔታ በመስራትም ላይ ጎበዝ አናፂ ነበር፡፡ በብረታ ብረት የሚሰሩ ስራዎችንም ልቅም አድርጎ ነው የሚሰራው፡፡ በአጭሩ ሁለገብ ባለሙያ ነው ቢባል ቃሉን አጣጥሞ ለመዋጥ የሚጎረብጥ አይመስልም፡፡
  
… አሁን ውድድሩን የሚመለከት ሁሉ ትንፋሹን መቆጣጠር ያልቻለበት ቅፅበት ላይ ይገኛል…
ሁሉም በሚያሰቅቅ ጭንቀት ውስጥ ነው፡፡ ከ27 ደቂቃ በፊት የውድድሩን መጀመር ያበሰረው ጥይት ሲተኮስ የነበሩት ሀያ ሯጮች የሉም፡፡
ሁለቱ ብቻ እልህ አስጨራሽ፣ የሞት ሽረት ትግል ውስጥ ናቸው፡፡
ይህ ስፖልቴርጋት የመጨረሳ እድል ነው፡፡
ማሸነፍ አለበት፡፡
ይሄው ደሞም ውድድን በጥቂት ርቀትም ቢሆን እየመራ ይገኛል፡፡ ታሪኩን ይቀይራል… ታሪክ ይሰራል…
የሱ ብቻ ሳይሆን የሀይሌም ታሪክ ይቀየራል በተሸናፊነት፡፡
አሁን ኬንያዊው አትሌት ፖልቴርጋት እየመራ ቢሆንም በመካከላቸው ያለው ርቀት ተጋኖ ሲወራ የሚችል አይደለም፡፡
በመስመሩ ላይ በሚያርፈው የመጨረሻ አንድ እርምጃ የታሪክ ገፅታ ይቀየራል… ይህን ታሪክ ደሞ ፖልቴርጋት እንደሚሰራው እርገጠኛ ሆኗል…
  
ልጁ በነገሮች ላይ ሁሉ ጥንቁቅ ነበር፡፡ በገንዘብ አጠቃቀሙ ሳይቀር ጎበዝ ነበር፡፡ ትንሽ የሚጎለው ዕድል ብቻ ነው፡፡ ወንድሙ ግን በሚገርም ሁኔታ እድለኛ ነው፡፡ ዕድለኛነቱ ገንዘብ ማግኘት ላይ እንጂ ገንዘብን እንዲወልድ እና እንዲዋለድ ማድረጉ ላይ አልነበረም፡፡ ልጁ ደግሞ ገንዘብን በዘዴ የመጠቀም ችሎታ የተሰጠው ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ታዲያ ልጁ በፈጠራ ችሎታው እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ የንብ ቀፎ ይሰራና ይሰቅለዋል፡፡ እድል ደጋግማ ፊቷን አዙራበት ነበርና ንቦች ሊገቡለት አልቻለም፡፡ እድል ያፈቀረችው ወንድሙ ግን ጠዋት ሰቅሎ ማታ ንብ ይዞ ይገባል፡፡ ያኔ የወንድሙን እድለኛነት ያወቀው ያ-ልጅ የእኩል እንስራ ብሎ ተጠጋ፡፡ እሱ ቀፎውን ማሰማመርና መስራቱን ይችልበታል፣ ወንድም ደሞ እድል አለችው-ልጁ ታዲያ ጠጋ ብሎ ትንሽ እየሰራ የተሻለ ማለቡን ተካነበት፡፡
የሱ ችግር ፀብ ፈሪ መሆኑ ነው፡፡ ፀብ ባለበት ቦታ ሁሉ ፊቱን አዙሮ ነው የሚሄደው፡፡ ልጅ ሆኖም አንድ ግዜ ከመጣላቱ በዘለለ ጎልቶ የሚታወስ ትዝታ የለውም፡፡
ለታሪኩ ማድመቂያ እንኳን እንዲሆን ሪከርድ ያስመዘገበበትን ፀብ ያደረገው አሰላ ሀይስኩል ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ ነው፡፡ አንድ ተማሪ በእጁ እያመለከተው “ኳሷን ምታልኝ … ምታው!” ይለዋል፡፡ ጫማ የሚባል ነገር እግሩ አይቶ የማያውቀው ያ-ልጅ ደሞ “እሺ!” ብሎ ተንደርድሮ ኳሷን ያጎናል፡፡ በኳሷ ፈንታ የጎነው እሱ ሆነና አረፈው፡፡ እግሩ የእሱ አልመስለውም፡፡ በካልሲ የተጠቀለለው ድንጋይ እግሩን ገሽልጦ አንገበገበው፡፡ ያኔ እልሁ ገነፈለበትና ለፀብ ተጋበዘ፡፡ ከዛ ተንኮለኛ ልጅ ጋር ግብ ግብ ተያያዘ፡፡ ሆኖም ልጁን አልተቋቋመውም፡፡ ተመታ፡፡ ዳግም ዱላ ቀመሰ… እና እሱ እቴ ፀብ አይደለም አታካሮ እነኳ በሩቁ አለ፡፡ ከዚህ ፈሪነቱ የተነሳ ቤቶች ሳይቀር ይደበድቡት ነበር፡፡ የሱ ፀብ መፍራት ሳያንስ፤ ወንድሙ ተጣልቶ በመጣ ቁጥር ብው ብሎ ይናደድበታል፡፡
  
… አሁን ውድድሩ ሲጠናቀቅ 50 ሜትር ብቻ ይቀራል…
እየመራ ያለው ፖልቴርጋትና ሀይሌ ገብርስላሴ ትንቅንቃቸው ቀጥሏል…
…በሩጫው ዓለም ከቆውንም ቢሆን ሀይሌን አሸንፎ የማያውቀው ፖልቴርጋት ዛሬ ያለ የሌለ ሀይሉንና የመጨረሻ ጉልበቱን ሲጠቀም ነው… ቀኑ የእሱ ይሆን?
ፖልቴርጋት ከፊት እየመራ በመሆኑ በውስጡ እየደጋገመ የሚለው ይህን ነበር…
“ማሸነፍ እችላለሁ! ይህን ማሸነፍ እችላለሁ…”
  
ከልጅነቱ ጀምሮ ታላቅ ሯጭ የመሆን ህልም አልነረውም፡፡ ፊትም ሆነ አሁን ከልቡ የሚመኘው የተሳካለት የፖለቲካ ሰው መሆን ነው፡፡ የየሀገራቱን ታሪክ፣ ፖለቲካዊ መረጃዎችን አንድ ሳይቀረው ልቅም አድርጎ ነው የሚያውቀው፡፡ የገጠር ልጅ መሆኑ፣ ከቤቱ እስከ ትምህርት ቤቱ ያለው ርቀት የትየለሌ መሆኑና ሌሎች ሁኔታዎች ባንድ ላይ ተዳምረው ሳያስበውና ሳያልመው ወደ ታላቅ አትሌትነት አስገቡት እንጂ! ታላቅ ወንድሙ ሯጭ ስለነበር ልምምድ ሲያደርግ “ና!” እያለ ይወስደውና ከሱ ጋር እንዲሮጥ ያደርገው ስለነበር መንገድ ከፈተለት፡፡ ወንድሙ አበበ ቢቂላ መታሰቢያ ይካሄድ በነበረ የማራቶን ውድድር አንድ ጊዜ ሁለተኛ፣ ሌላ ጊዜ ሶስተኛ የወጣና የጥሩ ውጤት ባለቤት መሆኑ ረድቶታል፡፡ “ና ይህን ስራ… እንዲህ አድርግ…” እያለ አለማምዶታል፡፡
ልጁ በ1980 ዓ.ም ለስፖርታኪያድ ውድድር (ወጣቶችን መልምሎ የሚያሰለጥን) ማዕከል ውስጥ ታቅፎ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የትምህርት ቤቶች የሩጫ ውድድር ነበርና ይሳተፋል፡፡ ከሯጮቹ ሁሉ ግን ትንሹ እሱ ብቻ ነበር፡፡ ውድድሩ አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ነበር፡፡ ሩጫው ተጀምሮ፣ ሲለቀቁ ለጉድ ተፈትልኮ ሲወጣ ሁሉም ተመልካቾች “አይ ይቺ ተንሽ ልጅ ምኑንም ሳታውቀው … አሁን ትንሽ ሄዳ ትቆም የለ?!” ይሉ ጀመር፡፡ እሱ ግን በዛው ፍጥነት ሄደ፡፡
ያለምንም ተፎካካሪ አንደኛ ወጣ፡፡
ያኔ ሁሉም ተገረሙ፡፡ አንድ ነገሩ ያስደነቀውም ፖሊስ አምስት ብር ሸለመው፡፡ የክፍለ ሀገሩ የስፖርት መምሪያ ሀላፊም ሶስት ብር የሚያወጣ ካኪ ቁምጣ ሸለሙት፡፡ ከዚያ በኋላ ሩጫ ነፍሱ ሆነ፡፡
በዚያው ወቅት ስለሞዴሉ ምሩፅ ይፍጠር ሲዘፈን ይሰማ ነበር፡፡ እንዲያ ስሙ የገነነው ምሩፅ ላይ መድረስ አጓጓው፡፡ የምሩፅ ውዳሴ ለሱ የሚሆንበት ቀን ናፈቀው፡፡ እንዲያ ሲልም የመካከለኛ ርቀት ሯጭ የሆነው ሰኢድ አዊታ ሌላው ሞዴሉ ሆነ፡፡ ሰኢድ አዊታ ከ5ሺ ሜትር የያዘውን ሪከርድ ማንም አይሰብረውም አንዳልተባለለትና እራሱ ሰኢድ አዊታ “የኔን ሪከርድ የሰበረ ከእኔ እንጂ ከላላ አይሸለምም!” እንዳላለ ከሰባት አመት በኋላ ሰብሮለት ቁጭ አለ፡፡ ያሌ ዓለም ሁሉ ለጉድ ነበር የተደነቀው፡፡ እሱ ሞዴሎቹ ላይ መድረስ ብቻ ሳይሆን ጨርሶ ሊገናኙ በማይችሉበት ሁኔታ ጥሏቸው ሄዷል፡፡ ዛሬ ግን በፖልቴርጋት ሊሸነፍ ይሆን?
  
…ሩጫው በታላቅ ጉጉት እየተከታተለ የሚገኘው መላው የስቴዲየሙ ተመልካች ሁሉ ከመቀመጫው ተነስቶ ቆሟል…
በመላው ዓለም ውድድሩን በቴሌቪዥን የሚከታተው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመቀመጫቸው ጫፍ ላይ ደርሰው አፍጥው ቴሌቪዥኑን እያዩ ነው…
የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ከባድ ምጥ ውስጥ ነው….
ሁለቱ ሯጮች ትከሻ ለትከሻ እየገጠሙ… የማሸነፊያው መስመር እጅግ እየቀረባቸው ነው፡፡
በሀይሌ ገብረስላሴ በእምሮ አንድ ሀይለኛ ቃል እያቃጨለ ነው፡፡
“ይቻላል! ይቻላል! ይቻላል!..”
  
ፈፃሞ በስራ ላይ መቀለድ እንደማይወድ፣ በህመም ውስጥ እንኳን ሆኖ ተገቢ ልምምዱን ከማድረግ ወደኋላ የማይል፣ ጠንካራና እልኸኛ፣ በአንድ ነገር ታዋቂ መሆን አለብኝ የሚል ፅኑ አላማ ያለው መሆኑን የቅርቡ የሆኑ ሁሉ ይመሰክሩለታል፡፡ አሰልጣኙ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ በሀሳቦቹ ላይ ከመስማማትም በላይ ስለሱ ሲናገሩ ቀልደኛነቱን፣ ጠንካራ የገንዘብ አጠቃቀም ችሎታ ያለው መሆኑን፣ እንደ ስፖርተኛ ታላቅና በተለይ ለሙያው ግምት ከመስጠቱ የተነሳ ሁለት መርሴዲስ መኪና ተሸልሞ እነዛን ቁጭ አድርጎ ኦሎምፒክ እስኪያልፍ ሳይጠቀምበት መቆየቱን፣ ሀገር ወዳድነቱንና ለሀገሩ ሰንደቅ አላማ ከፍተኛ ቅናት ያለው መሆኑን በአድናቆት ይመሰክሩለታል፡፡
  
…ሯጮች በትክክል ትከሻ ለትከሻ ገጥመዋል…
አሁን ሁለቱም የሚያስቡት ቀዳሚ በመሆን መስመሯን መርገጥ… ማለፍን ነው፡፡
ፖልቴርጋት ድሉን እያሰበ ነው፡፡
በሀይሌ ገብርስላሴ አእምሮ ውስጥ ያ ግዙፍ ሀይል ቃል እያስተጋባ ነው፡፡
መን እንድሚያሸንፍ ለመለየት በሚከብድ ትንቅንቅ ውስጥ አሰራ አምሰት ሜተር … ከሰባት ያልበለጡ ርምጃዎች ብቻ ቀሩ …የሚያስጨንቅ፣ የሚሰቀጥጥ፣ ትንፋሽ የሚያሳጣ…
  
የቅርብ ጓደኛውና የቀድሞው የዓለም ማራቶን ሯጭ ሪቻርድ ሄሩርካር ሃይሌን ከራሱ ይልቅ ለሌላው የሚያስብ በማለት ይገለፀዋል፡፡ “ብዙ ሰዎች ሀይሌን እንደሯጭ እንጂ ሀይሌን እንደ ግለሰብ አያውቁትም፡፡ በሪጭነቱ ከሁሉ የላቀ እንደመሆኑ ሁሉ በስብእናውም እንዲሁ ነው፡፡ ፍፁም ልባዊነቱና ችሮታው ለማንም የማይታመን ነው፡፡ ከፍተኛ የማንቀሳቀስ ችሎታ፣ ሀይልና በራስ መተማመን ያለው የህዝብ መሪ ነው፡፡ የዓለም ደረጃ አትሌት መሆን በሁሉም ሁኔታዎች የራስህን ፍላጎት መጀመሪያ ማስቀደም ነው፡፡ እኔ በምወዳደርበት ጊዜ የማደርገው ይህንኑ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሀይሌ ግን ከቶውንም ይህንን አያደርግም፡፡ ከራሱ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች የሚያስብ ነው፡፡ ህዝቤን ለመርዳት ምን ማድረግ እችላለሁ? ኢትዮጵያ የተሻለ ቦታ እንድትሆን ምን ማድረግ እችላለሁ? ይላል፡፡ ለተለያዩ በጎ አድራጎቶች በሚሊዮን ገንዘብ ያሰባስባል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ህዝቦችን ቀጥሮ ያስተዳድራል፡፡ ከፖለቲካ ሰዎችና ዲፕሎማቶች ጋር የስራ ግንኙነት ያደርጋል፡፡ ይህንን አይነት ኑሮ የሚመራ አትሌት፣ በስፖርቱም የበላይነትን የሚያዝ እንደ ሀይሌ ያለ ባሁኑ ጊዜ የለም፡፡ እሱ በጣም፣ በጣም ልዩ ሰው ነው”
  
…እንዲህ ያለ ሰግጣጭ ሩጫ ገጥሞት አያውቅም…
ብቻ ፖልቴርጋት ጋ ሲደርስበትና ትከሻ ለትከሻ ሲገጥሙ…ቅልጥ ያለ ጩኸት …ቀውጢ የሆነ ጫጫታና ፉጨት ይሰማው ነበር …
በዚያች ቅፅበት በግራ ጎን፣ በግራ አይኑ፣ በጨረፍታ ሲመለከት ከፖልቴርጋት ጋር እኩል ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡
ያኔ እጆቹን እንደክንፍ ዘረጋ፡፡
ትንሽ ቴክኒክ መጠቀም ካልቻለ ማሸነፉ ነው…
እጆቹን እንደክንፍ ዘርግቶ የመጨረሻዋን ርምጃ ሰነዘረ…ፖልቴርጋትም ማሸነፉን ርግጠኛ ሆኖ የመጨረሻውን ርምጃ አወናጨፈ…
የማይረሳ ድል ነበር!
የሰኮንድ ዘጠኝ መቶኛ ሽርፍራፊ ላይ አሸነፈ!
ኃይሌ ገብረስላሴ!
የማይረሳ ቀን!…ከሰቅጣጭ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣ የማይረሳ ድል!…
የዓለማችን ታላቁ የረጅም ርቀት ሻምፒዮንነቱን ያሳወጀበት ጣፋጭ የድል ቀን …
  
አንተም የተወለድከው ሻምፒዮን ለመሆን ነው!
ምንም አይነት እንቅፋቶችና ችግሮች መንገድ ላይ ቢኖሩም ስትፀነስ አሸንፈህ ከመጣሀቸው ችግሮች አንድ አስረኛውን እንኳን አይሆኑም፡፡ ድል በማንኛውም የሰው ልጅ ውስጥ በማይነጠል ሁኔታ ከአካሉ ጋር የተሰራ ልዩ ነገር ነውና!
ከሌላ ፕላኔት የመጣ፣ የማሸነፍ ስልጣና የተሰጠው፣ ከቶውንም በውስጡ ያለው ተቀጣጣይ ነዳጅ የማያልቅበት ወዘተ…እየተባለ በአድናቆት ከሚሞካሸው እና በቅርቡ እየርላንድ ውስጥ ከዮኒቨርስቲ ኮሌጅ ኦፍ ደብሊን፣ በስፖርትና በተለያዩ ሰብአዊ ስራዊች የህግ የክብር ዶክትሬት ካገኘው ከአትሌት ሻለቃ ሀይሌ ገብረስላሴ የስኬት ምስጢር ጋር ራስህን አገናዝብበት… እነሆ!
ስኬት ምን ሚስጥር የለውም!
ታላቁና ዋናው የስኬታማነት ምስጢር ምንም ምስጢር አለመኖሩ ነው፡፡
ሁል ጊዜ መስራት እንደምትችል ከምታውቀው በላይ አልምና ተኩስ፡፡ በጊዜው ካሉ ወይም ከቀድሙህ የተሻልክ ለመሆን አትጨነቅ፡፡ ግን ከራስህ የተሻልክ ለመሆን ሞክር!
በሩጫው ዓለም እንዲህ ነው ብለህ የምታስቀምጠው ምንም የተለየ ሚስጢር የለም፡፡ ምስጢር እንኳን ቢኖር በምታደርገው ዝግጅት ላይ ነው የሚወሰነው፡፡ በፍጥነቱም፣ በትንፋሹም ትዘጋጃለህ፡፡ በደንብ አቅደህ ተለማምደህ፣ ዝግጅትህን ጨርሰህ ትገባለህ፡፡ ሩጫው ውስጥ ከገባህ ግን ማንም ነው አሯሯጥህን የሚያየው…እዛ ላይ የምትደብቀው፣ የምትመሰጥረው የስኬት ምስጢር የለም፡፡
ሩጫው ውስጥ እያለህ ሁኔታውን እያጠናህ ከራስህ ጋር ማጣጣም ነው፡፡ ከኋላ እያስከተልከው ያለውን፣ ትንፋሹን ቀስ ብለህ ታደምጠዋለህ መድከም አለመድከሙን በትንፋሹ ታውቃለህ፡፡ ስክሪን እያየህ ፊቱ ምን እንደሚመስል ታያለህ፡፡ ደሞ ትንሽ ታስቀድመውና አሯሯጡን እግሩ ላይ ታያለህ፡፡ ወይ እግሩ እርስ በርሱ ሲማታ፣ ወይ የሆነ ነገር ታይና ምን ያህል የመሄድ አቅም እንዳለው ትገምታለህ፡፡ ምንም እንኳን ሁሉም የመሮጥ ችሎታና ፍላጎት ስላለው ቢሆንም የሚገባው ልዩነቱ ግን ያለው አንድ ነገር ላይ ነው ሲስተሙን የማወቅ፡፡ እኔ የማደርገው ይህን ብቻ ነው፡፡ በሩጫና በኳስ ጨዋታ የምትመሰጥረው፣ ለብቻህ ደብቀህ የምትይዘው የስኬት ምስጢር የለም፡፡ ማንም ሜዳው ላይ ያይሀልና፡፡
አንዳንድ ጊዜ የውጪ ዜጎች የኛን በሩጫው ስኬታማ የመሆን ምስጢር ለማወቅ እዚህ ይመጣሉ፡፡ ለብዙ ጊዜያት ልምምድ አድርገው ይሄዳሉ፡፡ ግን ብዙም ለውጥ አያመጡም፡፡ እንደኛ ለመሆን እኛው ጋ መወለድ፣ ያለፍንባቸውን መቋደስ፣ የአየር ጠባያችንን፣ የህይወት ውጣ ውረዳችንን፣ አመጋገባችንን፣ የእለት ተእለት ኤክስፖዠሮችን መቅመስ አለባቸው፡፡ እንጂማ ተፈጥሮአችን፣ ከልላችን ላይ የሮጡ ፈረንጆች ሁሉ ለምን አሸናፊ አይሆኑም?
ለምሳሌ የእኔ ልጅ ሴታ እንዳባቴ ሯጭ እሆናለሁ ትላለች፡፡ እኔ ግን ‘አርፈሽ ተቀመጭ አትሆኚም’ ነው የምላት፡፡ ብትሆን ደስ ይለኛል፡፡ ግን እውነታው እሚፈቅድላት አይመስለኝም፡፡ ተፈጥሮአዊ ስጦታ፣ ከኋላ ልምድ ጋር የተገናዘበ መሆን አለበት፡፡ እኔ እንደውም የሚገርምህ ልጆቼ ከሳሎን ወደ አልጋ ሲኖዱም መኪና አለመጠየቃቸው ይገርመኛል፡፡ የትም ሲኖዱ በመኪና ነው… በዚህ አይነት ሯጭ ይሆናሉ? ቢሆኑስ ይሳካላቸዋል ብሎ ማሰብ እችላለሁ?
በማንኛውም ስራ ላይ ስኬት አንዱን ቴክኒክ ከማወቅ፣ ሲስተሙን ከማወቅ ባሻገር ቅንነትን የሚጠይቅ ይመስለኛል፡፡ ቅን መሆን ከስኬታማነት መንገዶች አንዱን ተራመድክ ማለት እኮ ነው ያውም ታላቁን፡፡ ከዚያ ታማኝ መሆን አለብህ፡፡
ብዙ ጊዜ ታማኝ መሆን ያለብህ ለራስህና ለራስህ ብቻ ነው፡፡ የስኬት መስመርህ በንፅህና መደገፍ አለበት፡፡ ታማኝነት ግዙፍ ዋጋ አለው፡፡ አለበለዚያ አእምሮህም፣ ሰውነትህም ታማኝ ባለመሆንህ ይከዱሀል፡፡ እኔ ከጠቃቀስኳቸው ነገሮች በተጨማሪ በህይወቴ እለት በእለት የማደርገው ጠንካራ ፅናት እንዲኖረኝና ጥሩ ስነ ምግባር እንድገነባ ነው፡፡ ለጥሩ ስነ ምግባር ግድ ሀይማኖተኛ መሆን አይጠበቅብህም፡፡ የአእምሮ ህጎችም፣ አስርቱ ትእዛዛትም በቂ ናቸው የጠቃቀስኳቸው ነጥቦች ደሞ ፈረኝጆች Win Yourse if First እንደሚሉት ስኬታማ ለመሆን ራስን ማሸነፍን ነው የለመድኩት፡፡ ከዛ ሌላውን ታሸንፋለህ፡፡ በአዝጋሚነት ይሁን በፍጥነት ስኬት ያንተ ይሆናል፡፡

ባላመንክበት ስራ አትሰማራ!
በስራህ ላይ ደስተኛ ካልሆንክ የመከፋት መርዝ በህይወት ዘመንህ ሙሉ አንተ ውስጥ ለሰራጭ ይችላል!
አንተ አሁን እንዳልከው ሳይኮሎጂስቶች ስላሉት ሳይሆን እኔ ለማላምንበት ስራ ላይ መሰማራት ደስ አይለኝም፡፡ ከምትሰራው ስራ እኮ ደስታና ገንዘብ ነው የምታተርፈው፡፡ መጀመሪያ ደሞ ደስተኛ መሆንህ ይቀድማል፡፡ አሁን እኔ ቤት ውስጥም ሆነ ከብዙ ሰዎች ጋር የማልገባባው.. ’ለምን በኢምፖርተርነት ቢዝነስ አትሰራም?’ እያሉኝ ነው፡፡ አውቀዋለሁ እኮ ምንም ገንዘብ ሳላወጣ የተለያዩ የውጭ ምርቶችን በወኪል አከፋፋይነት እያመጣሁ በነሱ ገንዘብ ብዙ ማትረፍ እንደምችል፡፡ እኔ ግን ፍቅሩም፣ ደስታውም፣ ስሜቱም የለኝም፡፡ ከዛ ይልቅ አንድ ህንፃ ገንብቼ እሱን እያየሁ መቀመጡ ነው እርካታን የሚሰጠኝ፡፡
አንዳንድ ጊዜ እኮ እየከሰርክም ስራውን ስለምትወደው የምትስራው ስራ አለ፡፡ ባህር ዳር አሁን ትምህርት ቤት ከፍቻለሁ፡፡ ከኪንደርጋርተን ጀምረው ልጆቹ 5ተኛ ክፍል ደርሰዋል፡፡ ልጆቹ ያላቸውን ችሎታ ብታይ ጉድ ነው የምትለው፡፡ ትምህርት ቤቱ ግን በትርፍ ዝቅ ያለ፣ በኪሳራ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ግን እየወደድከው የምትሰራው ስራ ይቆይ እንጂ ጥሩ ስኬት ነው የሚያመጣልህ፡፡ አስበው ነገ እኮ የአገር መሪ፣ ተመራማሪ ዶክተሮች ከዛ ይወጣሉ፡፡ የት ነው የተማርከው ሲባል ሀይሌ ት/ቤት ሲል ማሰቡ ራሱ ያስደስትሀል፡፡
ስራን እንደማክበር የሚያረካኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ምን ትጠላለህ ብትለኝ የማይሰራ ሰው ነው፡፡ ስራ የሚወድ ሰው በእኔ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡
ከትንሽ ተነስተው የሚያድጉ ሰዎች እጅግ ያስፈነድቁኛል፡፡ እኔ ትልቅ ግምት የምሰጠውን አንድ ገጠመኝ ልንገርህ፡፡ በልጅነቴ ካለኝ ጥልቅ የስራ ፍቅር ቀጥሎ የገነባኝ ገጠመኝ ነው፡፡ ለአዲዲስ ማስታወቂያ ስራ ወደ ስፔን ሄጄ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት የሆነ ሰው አገኘሁ፡፡ ገምት እስኪ ሰውየውን የት የምታገኘው ይመስልሀል? እንደ እኔ ከሚጠቀሙ፣ ከሚገለገሉ ሰዎች ጋር የምታገኘው አይመስልህም? ወይ ደሞ ’አንተ ይህን አምጣ… ይህን አርግ እያለ ሲያዝ?’ ባለቤቱ …የሆቴሉ ባለቤት ግን የወጥ ቤቱ ሀላፊ ሆኖ የማብሰያ ልብሱን ለብሶ ምግብ ሲያበስል ነው የምታገኘው፡፡ የሱ ሴት ልጅ ደግሞ ሪሴፕሽኒስት (እንግዳ ተቀባይ) ናት፡፡ ሁለት ወንድ ልጆቹ ደግሞ የሆቴል ተጠቃሚዎችን ሻንጣና ካፖርት እየተቀበሉ ወደ ክፍሉ የሚመሩ ሆነው ነው የሚሰሩት፡፡ ነገሩ አስገርሞኝ ለምንድነው ብዬ ብል ’እኛ ያላከበርነውን እንግዳ ማን ሊያከብርልን ነው?’ ነው ያሉኝ፡፡ የሰውየውን አነሳስ ስታይ ደሞ ልትወድቅ ካለች ትንሽ ሬስቶራንት ተነስቶ ነው ከስድስት ያላነሰ ሬስቶራንት፣ ከ150 በላይ የመኝታ ክፍሎች ያሉት እጅግ ዘመናዊ ሆቴል ባለቤት የሆነው፡፡ አንዱን ልጁን ’ትፕ ቢሰጥህ ትቀበላለህ?’ ብሎ ብጠይቀው ’ተገኝቶ ነው?’ ነው ያለኝ፡፡ በቃ ስራን ማክበር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ነው ያስረዳኝ፡፡
ሌላ የሚገርም ነገር ልንገርህ፡፡ የእኔን ማናጀር ውሰድ.. ይህ ሰው ከኛ ሀገር የኔም፣ የነቀነኒሳም ማናጀር ነው፡፡ ከውጭ ሀገር ደግሞ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ሯጮች (አትሌቶች) ማናጀር ነው፡፡ ይህ ሰው ምግቡን ራሱ አብስሎ የሚመገብ መሆኑ ይገርመኛል፡፡ ለስራ ባለኝ ጠንካራ እምነትና ክብር ላይ ይህም ሁኔታ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ነው የሆነልኝ፡፡
እኛጋ ለስራ ያለው ግምትና ክብር ትንሽ ችግር አለበት፡፡ እኔ የሚገርምህ ቤተክርስቲያን ሳይቀር ነው ከቄሶቹ ጋር የምጋጨው፡፡ ’እናንተ ሰው የስራ ባህል እንዳያዳብር የተራዘመ ፀሎት፣ ቅዳሴ… ይህን ትምህርት ሳትሰሙ አትሄዱም… እያላችሁ’ እያልኩ፡፡ ምንም ይሁን ምን ለስሜትህ ቅርብ የሆነ ስራ ላይ ተሰማርተህ መስራት አለብህ፡፡ የምትሰራው ደሞ ለነገ የሚጠቅምህ፣ ሕይወትህን የሚያቀናልህ ሁሉ ሊሆን ይገባል፡፡ እኔ የማደርገው ይህን ነው፡፡ ምክንያቱም ልጅ ሆኜ ያለኝ ልምድ ጠቅሞኛል፡፡
እህል ይታጨዳል… ይወቃል አይደል? ሲወቃ ጉድጓድ ይቆፈራል፡፡ ወደታች ጥልቀቱ ለአንድ ዓመት ወይም ወቅት መውጪያ የሚሆን እህል እንዲይዝ ተደርጎ ነው፡፡ ከተቆፈረ በኋላ እንዳያነቅዝ ተደርጎ በደንብ ከውስጥ ይለቀለቃል፡፡ እህሉ እዛ ውስጥ ይደረግና በደንብ ተመርጎ በላዩ ላይ ድንጋይ ይደረግና አፈር ይለብሳል፡፡ ያ እህል ለችግር የሚቀመጥ ነው፡፡ ቀጣዩ አመት ላይ ሰላም ተደርሶ ምርት ከተገኘ ያ ይወጣና አዲሱ ይቀመጣል፡፡ ልመናም ሆነ ችግር ውስጥ የሚያስገባ ነገር አይኖርም፡፡ እኛ ግን ’እርዳታ እያለ?’ ብለን እሱን በመልመዳችን የካናዳ፣ የአውሮፓና አሜሪካን ስንዴ ነው እየጠበቅን ያለነው፡፡ እርዳታ የሚቆምበትን መንገድ መፈለግ አለብን፡፡ ይሔ ’ጥገኝነት’፣ መረዳት’ የሚሉ አስተሳሰቦች በፍፁም መበረታታት የለባቸውም፡፡ እንዲያውም ሊነቀፉ ነው የሚገባቸው፡፡
የምትወደውና የምትፈልገውን ስትሰራ እኮ ደስታ…ነው የምታተርፈው፡፡ ሩጫ ደስ ስለሚለኝ ወድጄው ነው የምሮጠው፡፡ በመሰረቱ ስፓርት አንዱ ’ፈን’ ስለሆነም ይሆናል፡፡ አሁን ጋዜጠኞች ከሰጡኝ ስም ሁሉ ’ሳቂታው ሯጭ’ የሚለውን ነው የምወደው፡፡ በሩጫ እኮ ቀልድ የለም፡፡ ተሟሙተህ…ራስህን ስተህ ነው ለድል የምትበቃው ግን ደስ እያለህ ትሮጣለህ፡፡
እቅድ ይኑርህ!
እቅድ እንዳለህ ለዓለም ከመንገርህ በፊት አድርገህ አሳይ!
ማንም ሀብትን መመኘት ይችላል፡፡ ብዙዎችም ይመኙታል፡፡ የተጠና እቅድና ፅኑ ፍላጎት ብቸኛና አስተማማኝ መንገዶች መሆናቸውን የሚያውቁ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡
አቅድ፡፡ አንዴ አቅደህ ከጨረስክ በኋላ ቶሎ ወደተግባሩ መግባት ይኖርብሀል፡፡ ይህ ፅኑ እምነቴ ስለሆነ የማደርገው ይህንኑ ነው፡፡ አቅደህ ቶሎ ወደ ተግባር ካልሄድክ ዕቅድህ ሳንካ ይገጥመዋል፡፡
አሁን የሆነ ህንፃ መሰራት አለበት ብዬ አቀድኩ አይደል? አርክቴክስ ክፍል ሄደህ ብጠይቅ ይነግሩሀል- ጉዳችሁ ፈልቷል.. እንዲህ አይነት ህንፃ በዚህ ቦታ ይሰራል ብሎ አቅዷል፣ እንግዲህ 24 ሰዓት መስራት ሊኖርባችሁ ነው የሚላቸው ማናጀሩ፡፡ ለምን ብትል ውጋት ነኝ፡፡ እንደውም እኔ ያቀድኳት ነገር በ24 ሰዓት ብታልቅልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ውጤቱን ለማየት ነው የምጓጓው፡፡ እርግጥ እቅዱን መጀመሪያ በጣም ደጋግሜ አብሰለስለዋለሁ አወጣ፣ አወርደዋለሁ፡፡ ታዲያ ወደ ሰው ወስጄ እንዲህ አይነት ቢዝነስ እያቀድኩ ነው አይደለም የምለው፡፡ ይህ ስላቀድኩ ስራ ነው!
ስራውን ነው ለሰው የማወርደው፡፡ እምነቴ መጀመሪያ ከእቅድህ ጋር ተጫወት፣ አብሰልስለው የሚል ነው፡፡ እቅድህን ለሰው ስትነግር ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በተፈጥሯችን ሳንካ፣ እንቅፋቶች መሆኑን እንችልበታለንና ይህን ነው የምታተርፈው፡፡
አሁን በሩጫውም ዓለም የተመለከትክ እንደሁ በጥንቃቄ ነው የማቅደው በዚህ ረገድ ደሞ ከማናጀሬ ጋር በደንብ ተናበናል፡፡ እኔ ሳቅድ እንደማደርግው ስለሚያውቅ ጥሩ አድርጎ ነው በገንዘብ የሚደራደርልኝ፡፡
በተለይ ዙሪክ በፈረንጅ 95 ዓ.ም ላይ በ5ሺ የተያዘ ሪከርድ ነበር፡፡ ያንን ሪከርድ መስበር ታፍ ተደርጎ ነበር የሚታሰበው፡፡ ውድድሩ እሁድ ሊካሄድ አርብ ማታ ከማናጀሬ ጋር ተነጋገርኩና ሪከርድ ለመስበር ስለምሮጥ ክፍያው እንዲሻሻልልኝ ሂድና የውድድር ማናጀሩን አነጋግረው አልኩት፡፡ መልሱን ይዞ ሲመጣም ችግር የለም ብሏል አለኝ፡፡ መልካም እንግዲያው ተፈራረሙ አልኩት፡፡ እርግጠኛ ነህ? አለኝ፡፡ አዎ! አልኩት፡፡ ያኔ ለዛ ሪከርድ የሚከፍለው 50ሺ ዶላር ነበር፡፡ እና ድርድሩ እንዲካሄድ የፈለግኩት ተጨማሪ በሚሰበረው ሪከርድ ሰከንድ ብዛት ልክ ተጨማሪ ብር እንዲኖረው ነው፡፡ እና ከ1 ሰከንድ በላይ በየሰከንዱ ሶስት ሺ ዶላር እንዲጨመር ነበር ስምምነቱ፡፡ የውድድሩ ማናጀር አይ ሀይሌ ይሄ እኮ ከባድ ውድድር ነው፣ ቢሰብር እንኳን ከአንድ ሰከንድ በላይ ለማይሄደው ነገር! ብሎ ተፈራረመ፡፡ በኋላ ሪከርዱን በ11 ሰከንድ አሻሽዬ ስሰብረው እንዴት ሊሆን ቻለ? ነበር ያለው፡፡ በል ደምርና አምጣ ነው ያልኩት፡፡ እኔ ቀድሜ አቅጄው ነው ወደ ተግባሩ የሄድኩት፡፡ እዚህ ላይ እቅድህን ይዘህ ጥሩ ቁማር ነው የምትጫወተው፡፡ እርግጥ ስፓርቱን ቅድሚያ ሳትሰጠው ገንዘቡ ላይ የምታተኩር ከሆነ አደጋ ነው ትወድቃለህም፡፡ እና በዚህ አይነት ወደ 18 ጊዜ ነው የተለያዩ ሪከርዶችን የሰበርኩት፡፡
ሰበብ አታብዛ!
ዕቅድህን ልታሳካ የማትችልበትን አንድ መቶ ምክንያት ከማሰብ ይልቅ ልታሳካው የምትችልበትን አንድ መንገድ ፈልግ!
ሁልጊዜ ታዲያ በምንም ነገር ላይ ሳቅድ የማየው አዎንታዊ ገጽታውን ነው፡፡ ይሄ ነገር ላይሳካ ይችላል፣ ላልሰራው እችላለሁ ብዬ አልጀምረውም፡፡ የሚያስኬድ መሆኑን ማመን አለብኝ፡፡ እኔ የሰዎች ሁሉ ውድቀት ብዬ የምለው ልሞክረው! የሚለውን ነው፡፡ ሳቅድ ለምሳሌ አስር ኪሎ ሜትር መሮጥ እንዳለብኝ ከሆነ የማቅደው እዛው አስሯ ላይ ደርሼ ካቆምኩ ፈጽሞ ደስ አይለኝም፡፡ የግድ ወይ 11 ወይም ከዛ በላይ ሄጄ መቆም አለብኝ፡፡ አንተ እንዳልከው ካቀድኩት በላይ አንድ እርምጃ ጨምሮ ነው የማቆመው፡፡ ያኔ በእቅዴ ትክክለኛነት እምነቱም ይኖረኛል፡፡
የእኔ መመሪያ እቅድህን ጀምረው በራሱ ጊዜ አይሳካ (ፌል ያደርግ) ብዬ ነው፡፡ ግን ይሄ የሪሰርች፣ የቅመማ ነገር ካልሆነ በቀር ልሞከረው! ብሎ ነገር የለም፡፡ ምንም እቅድ አልጋ በአልጋ ሆኖ አይሳካም፡፡ የሆነ ቦታ ላይ ሊጥልህ፣ ችግር ሊኖረው ይችላል፡፡ ያንን ለይተህ አውቀህ ማስተካከል ነው፡፡ ወይም አቅጣጣና እቅድን መቀየር ነው፡፡ ዝም ብሎ ሙከራ የሚባል ነገር ትልቅ ውድቀት ነው ለኔ፡፡ ብዙ ሰዎች ሲሉ ከሰማህ ይህን …ይህን ሞክሬ አልሳካ አለኝ ነው… ሙከራ ብለው እንዴት ይሳካል? ልትሞክረው ሳይሆን እቅድህን ልትተገብረው መነሳትን ነው እኔ በህይወቴ ያካበትኩት፡፡
ስኬት በስጦታ መልክ ሳህን ላይ ተደርጎ የተሰጣቸው የሉም!
ማዕበል እያፏጨ ሲመጣ አትሸሸው፣ በጠንካራ እምነትህ እየተጋፈጥከው ሰንጥቀኸው እለፍ፡፡ አሁን ሀይለኛ ማእበል ቢያጋጥምህም ተመልሶ ፀጥ ማለቱ አይቀርምና ተረጋጋ፡፡ የተናጋው አንደተናጋ አይቀጥልም፡፡ እንደ ብረት ጠንክረህ ከተቋቋምከው መጨረሻ የተረጋጋ የአየር ፀባይ ያጋጥምሀል፡፡
የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት ብዙ ስቃዮችን ማለፍ አለብህ፡፡ እንደው በቀላሉ እንኳን ወደ ጂፓን ስሄድ የገጠመኝን ያየህ እንደሁ ያለመሰናክል የሚገኝ ስኬት እንደሌለ ትረዳለህ፡፡
ጃፓን ለመድረስ ረዥም ጉዞ ነበር የምንጓዘው፡፡ ከዚህ ዱባይ ሄደን ከዱባይ ደሞ ኩዋላላምፑር ማሌዥያ መሄድ ነበረብን፡፡ ዱባይ ላይ ብዙ ሰአት ቆየን፡፡ ከዛ ከኩዋላላምፑር ወደ ቶክዩ በማሌዥያ ኤርላየንስ ከ16 ሰአታት ቆይታ በኋላ ነበር የምንሄደው፡፡ ያን ጊዜ እኔ አዲስ ተጓዥ ነበርኩ፡፡ ችግሩ ይፈጠራል ብዬ ስላልገመትኩ ገንዘብ አልያዝኩም ነበር፡፡ እግዜር ያሳይህ አብረውኝ የነበሩት ልጆች ሲወጡ እኔ ምን ብዬ እወጣለሁ ብዬ እዛው ኤርፓርት ቀረሁ፡፡ በቃ-ራበኛ! እንዳልበላ ገንዘብ በኪሴ የለም፡፡ ስቅይት አልኩኝ፡፡ እዛው ኤርፓርት ውስጥ በመሸጫ ሱቆች በመስታዎት ሆኖ የሚታይ ኬክ ምናምን አለ፣ እሱን እያየሁ አስሬ በስሩ አልፋለሁ፡፡ ልለምናቸው? ራበኝ ልበላቸው? እያልኩ አወጣለሁ…አወርዳለሁ፡፡ አስበው አስራ ስድስት ሰአት እኮ ስንቆይ ከዛ በፊት ደሞ ሌላ ምግብ አልበላንም፡፡ በቃ በመስታወቱ በኩል ላይ ታችስል ደከመኝ፡፡ አትታዘበኝና አንደው ምናልባት ፈረንጅ ተርፎት የሄደውን አንስቼ ለመብላት ሁሉ አስቤ ነበር፡፡
ርሀቡ በጣም ጠናብኝ፡፡
ዝም ብዬ ይሄን ውሀ በየ5 እና 10 ደቂቃው እየጠጣሁ መንጎራደድ ሆነ፡፡ ብዙ ሰአት ከቆየን በኋላ ወደ ከተማ የሄዱት ልጆች መጡ፡፡
እናንተ እኔ ርቦኛል ስላቸው በቃ አሁን ፕሌን ላይ ትበላለህ አሉኝ፡፡ እነሱ ከከተማ ውስጥ ትንሽ ቀማምሰው ነው የመጡት፡፡ በቃ ምን አለፋህ 16ቱ ሰአት አስራ ስድስት ቀን ሆነብኝ፡፡ እንደምንም ፕሌን ላይ እንደገባን አንድ ንጉሱ የምንለው ልጅ አለ ሂድና አስተናጋጇን ሀንግሪ በላት አለኝ፡፡
ገና ፕሌን ላይ እንደገባን በሩ ላይ የሰው መተላለፊያውን ዘግቼ ፊት ለፊቷ በመገተር ሀንግሪ አልኳት፡፡ ‘Take a seat’ አለችኝ፡፡ ሰው እያስተናገደች ዞር ስትል አሁንም እዛው እንደተገተርኩ ነው፡፡ አየት ስታደርገኝ ሀንግሪ አልኳት፡፡ በኋላ ከባልደረባዋ ጋር ተነጋገሩና ሄዳ ውሀና የተጠቀለለ ትንሽ ዳቦ አመጣችልኝ፡፡ ገና ሰጥታኝም እጇንም ሳትመልሰው ዋጥ አደረግኩትና ወደ መቀመጫዬ ሄድኩ፡፡ እንደው ምግቧ ኪኒን ነበረች የሆነችኝ፡፡
ሌላው ጉድ ደሞ አውሮፕላኑ መንቀሳቀስ ሲጀምር ምግብ ይቀርብልናል ብዬ ነበር የምጠብቀው ለካ ከምሳ በኋላ ስለነበር አውሮፕላኑ የተነሳው ሁሉም ምሳ በልቶ ስለሚመጣ ገና ብዙ ሰአት መቆየት ሊኖርብኝ ነው፡፡…በቃአ እንደገና ሀንግሪ! አልኳ፡፡ መጨረሻ ላይ ኡኡታዬ ተሰምቶ ለእኔ ለብቻዬ መጣልኝ፡፡ ይህችን ገጠመኜን በምሳሌነት የጠቀስኩልህ ገጠመኟ በራሷ ተምሳሌታዊ አንድምታ ስላላት ነው፡፡ አየህ በህይወት ውስጥ ሁልጊዜ ሁሉም ነገር በቀላሉ ተመቻችቶ (like a piece of cake) አይቀርብልህም፡፡ ይብዛም ይነስ እያንዳንዷ ትንሽ ነገር በራሷ፣ ጥረት ትጠይቃለች፡፡ ስኬትም እንዲሁ ነው በሩ እንዲከፈት ሳትሰለች ደጋግመህ ማንኳኳት፣ በትእግስትና ፅናት መትጋት ይኖርብሀል፡፡
ፈፅሞ አታቁም!
እውነተኛ አላሚዎች ፍፁም አያቆሙም፡፡
የምታገኘው ስኬት ሲነፃፀር የሚችለው ከእቅድህ ትክክለኛ መሆን፣ አለመሆን ጋር ብቻ ነው፡፡ ማንም ሰው በራሱ ጊዜ ካላቆመ በቀር ሲረታ አይችልም ምክንያቱም ውድቀት የእምነትን ሀይል ተግባራዊ ለማድረግ ካለመፍቀድ የሚመነጭ ተግባር ነውና፡፡
የቀረውን ህይወትህን ቢጠይቅ እንኳን ለአላማህ ቁም!
እኔ በማቆም አላምንም፡፡ ይህንን ባህርዬን ብዙ ሰዎች ያውቁታል፡፡ ያቀድኩትን ነገር ባሰብኩት ሁኔታ ካላሳካሁት በሌላ መንገድ እሄዳለሁ፡፡ ይሄ ባህርዬ ነው፡፡ ለምሳሌ በሩጫው ዘርፍ አንድ ወቅት ላይ አትሌቶችን ማሰልጠን ጀምሮ ነበር፡፡ ስልጠናውን ለማናጀሬና ከአዲዳስ ካምፓኒ ጋር በመተባበር ነበር ያዘጋጀሁት፡፡ ምን ዋጋ አለው እኔ ጋ የሚሰለጥኑትን ልጆች የተለያዩ ክለቦች አያባበሉ እሱ ቋሚ ሰራ የለውም… እያሉ ወስደው ጨረሷቸው፡፡ እኔ ደሞ ከዚሁ ከእስፖርቱ ጋር በተያያዘ አንድ ለየት ያለ ነገር መስሪት እቅዴ ስለነበር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ጀመርኩ፡፡ ምንድነው ቁም ነገሩ በሁለቱም መንገድ አትሌቶች መውጣት ይችላሉ፡፡ አንዱ ሲከሽፍ አላቆምኩም፡፡ በሌላ እቅድ ተካሁት እንጂ፡፡
ብዙ ሰዎች ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋለህ? ሩጫው ይብቃህ! ይሉኛል፡፡ ሰዎችን ላለማስቀየም እሺ በቃ ምን ችግር አለ… አቆማለሁ! እላቸዋለሁ፡፡ የእኔ ህልም ግን ማቆም አይደለም፡፡ ስፖርት አንተ ላቁመው ብለህ የምታቆመው አይደለም፡፡ ራሱ ስፖርቱ ያቆምሀል፡፡ እኔ በራሴ ላይ በቃኝ ብዬ ገደብ መጣል የለብኝም፡፡ ደሞ እኮ የሰው ልጅ ፍላጎት ማቆሚያ የለውም፡፡ አስተያየት የሚሰጡኝ ሰዎች ፍላጎት እንጂ የኔ ማቆሚያ የለውም፡፡ አሁን አንተ ስኬታማ ነህ ብለህ ነው ልታነጋግረኝ የቻልከው፡፡ እኔ እስካሁን የሚሰማኝ ሌላ ነው፡፡ ገና ነኝ ነው የምለው፡፡ ደሞ ጥረቴን እንቅስቃሴዬ ስሞት ይቁሙና ከመቃብር በላይ የሚጠራ ነገር ይኑረኝ እንጂ ተሳክቶልኛል ብዬ ማቆም አልፈልግም፡፡
በተቻለ መጠን የጋለ ስሜት አንደላጣ ነው የምጥረው፡፡ ወደ ውድድርም ውስጥ ስገባ እንደማሸንፍ ተሰምቶኝ፣ ነገሮችን ሳከናውን የጋለ ስሜት ኖሮኝ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡ ይሄን ስሜት ካጣሁት ግን ምንም ነገር ውስጥ መሳተፍን፣ ለውድድር መግባቱን እተወዋለሁ፡፡ በተለይ ደሞ ሩጫ ፊዚካል ብቻ የሚወሰነው አይደለም፡፡ አስር ጊዜ ረጅም እግር፣ አሰር ጊዜ ፈርጣማ ጡንቻ ይኑርህ ብቻቸውን ፋይዳ የላቸውም፡፡ ውስጥህ…ሀሞትህ ከፈሰሰ ሁሉ ነገርህ አብሮ… እንደውም ቀድሞ ነው የሚፈሰው፡፡ የውስጥህ ባሎን በደንብ ከተወጠረ ነው የውጪውን አቅሎ የሚያበርረው፡፡ ይህንን እስካጣ ድረስ ለማቆም ፈፅሞ ፍላጎት የለኝም፡፡
ይቻላል!
ትልቁ የሰው ልጅ ድክመት አይቻልም ከሚለው ቃል ጋር መተዋወቁ ነው!!
አንተ የሆንከው አንተ የምታስበውን ነው፡፡ ድህነትን ካሰብክ ድሀ ትሆናለህ…ስኬትን ካሰብክ ስኬታማ ትሆናለህ…ሀብታምነትን ካሰብክ ሀብታም ትሆናለህ፡፡ እንደምታስበው ነህ! ታላቁ መፅሀፍም ሰው በልቡ እንደሚያስበው እንዲሁ ነው ይላል!
ብዙውን ጊዜ ሊከሰትብኝ እንደሚችል የሚሰማኝ ነገር በትክክል ይሆናል ወይም ይከሰታል፡፡ ለምሳሌ ቤት ውስጥ የምሰራው ነገር ከሌለኝ ልውጣ እላለሁ፡፡ ባለቤቴ ታዲያ አርፈህ ተቀመጥ ትለኛለች፡፡ ባክሽ ተይኝ ቤት ቁጭ ብዬ ልውል ነው? ብዬ እወጣለሁ፡፡ የሆነ ነገር እንደሚደርስብኝ ስለሚታወቀኝ ወይ ተናድጄ፣ ወይ ተጋጭቼ ነው የምመጣው፡፡ ገና ስወጣም ተው ካለችኝና እንቢ ብዬ ከወጣሁ የማስበው እንደሚሆን ስለማውቀው ነው የሚከሰትብኝ፡፡
ደፋር ነኝ ብለህ ካሰብክ ደፋር ነው የምትሆነው፡፡ ድፍረት ግን በራስ ከመተማመን ነው የሚመጣው፡፡ ያ ከሌለህ ግን ፈሪነት ነው የሚሰማህና የምትሆነው፡፡ በአውሮፕላን ላይ የሚበር ሰው በዛ ቴክኖሎጂ ላይ መተማመን ከሌለው ፍርሀት ያድርበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በሩጫው ውስጥ የምፈራበት ጊዜ አለ፡፡ ያ ደግሞ በራስ መተማመን እጦትና በቂ ልምምድ ካለማድረግ ነው፡፡ ያኔ ደሞ እሸነፋለሁ፡፡ እዚህ ላይ አይቻልም! ካልክ ነው የማትችለው፡፡ መላ አንተነህም እኮ እንደማይቻል ተነግሮታል፡፡ እንዴት ይችላል? ስለዚህ አነሳስህ ይቻላል! ብለህ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ይቻላል የሚለው ጥቅስ የክቡር ገና ጥቅስ ነው፡፡ እኔ ለቃሉ እንደምመጥን ስለተሰማው ነው ፎቶዬን የተጠቀመው፡፡ አሁን የአዲዳስ ማስታወቂያም Nothing Impossible (የማይቻል ነገር የለም) ብሎ ተነስቷል፡፡
እንዳልኩህ በጥቅስ ደረጃ ክቡር ገና ይቻላል ይበል እንጂ ውስጤ፣ እኔም በአእምሮዬ የማምንበት ነገር ነበር፡፡ ሁልጊዜ አይቻልም ብዬ አላውቅም፡፡ ይሄ ነገር ከባድ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ባለፈው ካንተ ጋር ስንነገገርበት የነበረውን ኮንሽስና ሰብኮንሽስ የአእምሮ ክፍል ያልከኝ ላይ ነው ጨዋታው ያለው፡፡ ሰብኮንሽስ የአዕምሮ ክፍልህን በመጠቀም እንደምትችል እምነት ሊኖርህ ይገባል፡፡
እኔ እግዚአብሔር የፈጠረኝ ማድረግ ያለብኝን እንዳደርግ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ሌላው የማስበው እንዲሳካ እጸልያለሁ፡፡ ጸሎቴ ብዙ ግዜ አጭር ነው፡፡ ላደረክልኝም ለምታደርግልኝም አመሰግናለሁ፡፡ አንተው ጠብቀኝ ው !! በተረፈ አስርቱን ትእዛዛት በአግባቡ ነወ የምጠብቀው፡፡ አትዋሽ ከምትለው በቀር ሁሉንም አከብራለሁ፡፡ ይቺ አትዋሽ ግን ብዙ ጊዜ ሰው ለማስታረቅ ስለምጠቀምባት እዋሻለሁ መቼስ የሌሎቹን ህይወት ከለወጠ ምን ታደርገዋለህ?
እኔ የማስበው መጥፎ የሆነ ነገር እንዲኖርና ያ በእኔ ውስጥ አድጎ መጥፎ እንዲያደርገኝ አልፈልግም፡፡ በእምነቱም፣ በሳይኮሎጂውም ሆነ በሞራል ህጉ የማስበውን ጥሩ ነገር እንደሆን ነው ራሴን የማስለጥነው፡፡
ለስህተቶችህ እውቅና ስጥ!
አስታውስ የትም ቦታ ለመድረስ በትክክለኛው አቅጣጫ መሄድ አለብህ!
ብዙ ደካማ ጎኖች ቢኖሩኝም ለስህተቶቼ እውቅና ያለመስጠት ችግር አለብኝ፡፡ ባብዛኛው ማወቅ የምፈልገው ጠንካራ ጎኖቼን ነው፡፡ ግን አለ አይደል አንዳንድ ጊዜ ሲወራም፣ አንተም አመዛዝነህ የምታውቃቸው ስህተቶች አሉ፡፡ ጥሩ ነው እነሱን አወቅካቸው ማለት ልታርማቸው ትችላለህ፡፡
አሁን እኔ በጣም ማውራት እወዳለሁ ፓለቲከኛ እስከመባል ድረስ፡፡ እና ደሞ በአንድ ነገር ላይ አይሆንም ማለት አልችልም፡፡ የሆነ ይሉኝታ ያጠቃኛል፡፡ ይሄን አይሆንም ማለት ብለምድ ደስ ይለኛል፡፡ ለምን መሰለህ፣ ሰዎች ካንተ ይልቅ በራሳቸው ብቻ ተስፋ እንዲያደርጉ ማድረግ ትችላለህ፡፡ ህብረተሰቡ የማይቀበላቸውን ነገሮች በማድረግ ከህብረተሰቡ ጋር አለመጣጣም በራሱ ደካማ ጎን ነው፡፡
ሌላው ድክመቴ አኩራፊነት ነው፡፡ የማኮርፈው ግን ለባለቤቴ ነው፡፡ በፊት እሷ የማስማማባቸው ነገሮች ካሉ ታኮርፍ ነበር፡፡ አሁን ለምን? ስትለኝ አንቺ አስተምረሽኝ! እላለሁ፡፡ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ መመገብ አይሆንልኝም፡፡ ቤታችን እንግዳ ተጋብዞ ብፌ ተዘጋጅቶ እንኳን እኔ ነኝ ሮጩ በመጀመሪያ የማነሳው፡፡ ያው ባለቤቴ ባህርዬን በእንግዶች እያስረዳች ይቅርታ ትጠይቃለች፡፡ ታዲያ እኔ በልቼከጨረስኩ መቀመጥ፣ እንግዳ ብሉ ጠጡ ማለት አልችልበትም፡፡ በቃ ወይ ጥዬ እወጣለሁ ወይ ደግሞ ተነስቼ ቴሌቪዥን ምናምን አያለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ሽማግሌዎች ይመጡና ይቆጡኛል እሺ በቃ እተዋለሁ! እልና በበነጋታው ያው ነኝ፡፡
አንዳንዴ የሆነ ነገር ውስጤ ካለ ተረጋግቼ ረፍት አላገኝም፡፡ ብዙ ጊዜ ምንም የተለየ ፕሮግራም በሌለኝ ሰዓት መኪና ስነዳ ቀስ ብዬ ነው፡፡ ኃይሌ ተጋጨ ከተባለ ግን በቃ የተቻኮልኩበት ነገር ነበር ማለት ነው፡፡ ከቸኮልኩ እጋጫለሁ፡1 ትናንት እንኳን ሁለት ስብሰባ እንዳለብኝ ነግሬህ አልነበር? እዛ … እዚህ ስቸኩል ተጋጨሁ፡፡
እኛ አገር ያሉት በርካታ ችግሮችና መሰናክሎች ፈጣሪ ፈጥሮ የሰጠን ሳይሆን እኛው የፈጠርናቸው ናቸው፡፡ ስህተቶቻችንን ለይተን አውቀን የምንፈታቸው ደሞ እኛው ነን፡፡ ምንም ነገር ላይ ችግር፣ መሰናክል፣ ስህተት አታጣም፡፡ አሁን ብዙ ከውጪ የሚመጡ ሰዎች ጋር ስንጨዋወት ወር ባልሞላ ጊዜ ሲበሰጫጩ ነው የምሰማው፡፡ እና አትቀልዱ እንጂ! ለመሆኑ አሜሪካ በአንድ ጊዜ እኮ አይደለም የተገነባችው፡፡ ሁለት፣ ሶስት መቶ አመት አልፋ ነው… እያልኩ እጋጫለሁ፡፡
መቼም የኛን ችግር እነ ጆርጅ ቡሽ፣ ቶኒ ብሌየር መጥተው አይፈቱልንም፡፡ መፍታት የምንችለው እኛ ነን፡፡
የአዕምሮ ጤናህን ጠብቅ!
አስተሳሰብህ ላይ መጥፎ ጥላ ያጠሉትን የሸረሪት ድሮች አስወገድ፡፡
ዘወትር አዕምሮህን የምትፈልጋቸው ሀሳቦች ላይ ብቻ አድርግ፡፡
ከማትፈልጋቸው ሀሳቦች ላይ አዕምሮህን አርቅ!
ሯጭ ስለሆንኩ እኔ ለጤናዬ ብዙም አላስብም፡፡ ሲያመኝ ሄጄ እታከማለሁ እንጂ፣ ይሄ ይቆረጥመኛል፣ ይሄን ይወጋኛል ብዬ አላውቅም፡፡ ማናጀሬ እንኳን ሙሉ ምርመራ እንዳደርግ ሲነግረኝ እየተናደድኩ ነው የምሄደው ምናለ ቢተወኝ? እያልኩ፡፡ እርግጥ እንዳልከው የአእምሮ ጤናን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ እኔ ግን የአእምሮ ጤናዬን የምጠብቀው በስፓርቱ ነው፡፡ የሆነ የሚያስጨንቀኝ፣ ሲያናድደኝ ያደረ፣ ያበሳጨኝ ነገር አለ አይደል? በቃ ሁሉም ጣጣ በላብ ታጥቦ ይጠፋል፡፡ ድካምህን ታስታውሳለህ ወይስ ጭንቀቱን? ጭራሽ የት እንደገባ ይጠፋሀል፡፡
ሌላው ደሞ የፈለገ ልናደድ፣ ልብሸቅ እንጂ ለነገሩ ስናደድ በጣም ነው የምቃጠለው ግን ቶሎ የመርሳት እድሉም አለኝ፡፡ ያም ሆኖ ግን የማልረሳቸው እና ሁልጊዜ ባስታወስኳቸው ቁጥር ምን ነካኝ የምላቾው ነገሮች አሉኝ፡፡ ለምሳሌ ስቱትጋርት በተካሄደው ውድድር የአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር ሩጫ ላይ ሪከርዱን ለመስበር ከሰኮንድ ያነሰ 48 ማይክሮ ሰከንድ ቀርቶኝ ካለፈ በኋላ ፊልሙን እያጠነጠንኩ እያየሁት የምቆጭበት ጊዜ አለ፡፡ ሌላው ደሞ ሆላንድ ከ8 ደቂቃ በታች መግባት ነበር አንድ ሚሊዬን ዶላር የሚያስገኘው፡፡ ገንዘቡ ብቻ ሳይሆን ታሪኩ ራሱ ትልቅ ነበር፡፡ ለነገሩ ገንዘቡም ብዙ ነው፡፡ ታዲያ እዚያም ላይ አንድ ሰከንድ ከምናምን ነበር የቀረኝ፡፡ ይሄን ሳስብ እናደዳለሁ፡፡ ምነው እንዲህ ከሚሆን 10 ወይንም 20 ሰከንድ በቀረኝ ነበር ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም አስቀድሜ ሶስት አራት ዙር ሲቀረኝ ብሄድ ኖሮ ሪከርዱን እሰብር ነበር አለማድረጌ ነው የሚቆጨኝ፡፡
ለሁለተኛ ግዜ ስቱትጋርት ለ5ሺ ሜትር እኔ፣ ፊጣ፣ ወርቁ ቢቂላ ነበርን የምንሮጠው፡፡ ያሸነፈን ልጅ እኔ የማሸንፈው ነው፡፡ ያን ጊዜ ፊጣ ባይሳ አንደኛ ደረጃ ላይ ስለነበር እሱን ነበር የምጠብቀው፡፡ ቀስ ብሎ ይደክማል ብዬ ነበር፡፡ ምን አለፋህ ልጁ በዛው እየተገላመጠ አሸነፈ፡፡ ያን ጊዜ ምን ልሁን ይሄን ልጅ ለምን አልተከተልኩትም? እስካሁን ይገርመኛል፡፡
ግሪክ ስሮጥ ካስታወስክ 5ኛ ነው የወጣሁት፡፡ በዛ አልቆጭም፡፡ ምክንያቱም የምችለውን ሁሉ ስላደረግኩ ነው፡፡ ቀነኒሳና ስለሺ ትንሽ ብትጨክን ኖሮ ነው ያሉኝ፡፡ እኔ ግን ከመጨከንም አልፌ መስዋእት ሆኚበታለሁ፡፡ እና አልቆጭም፡፡ ሌላው ለንደን ላይ ሶስተኛ የወጣሁ ጊዜ ካሊጅ ካኦች ሪከርድ የሰበረ ጊዜ አይኔ እንባ እስኪያግት ነው የሮጥኩትና አልተቆጨሁበትም፡፡ ሰው ግን በጣም ነው የተናደደው፡፡ ቶሎሳ ቆቱ ያኔ አንተ ነህ መስበር የምትችለውን ያሰበርከው አለኝ፡፡ ኧረ ባክህ እኔ ደስ ብሎኛል አልኩት፡፡ ምን ስለሆነ? አለኝ፡፡ እስክጠግብ ሮጫለሁ አልኩት፡፡ የማይቆጨኝ፣ እንደስህተት የማላየው፣ የምችለውን ያህል ስላደረግኩ ነው፡፡
ግብህን በቀመር ከፋፍለው
ግብህን ለይተህ የምታውቅ ከሆነና የጉዞህን የመጀመሪያ እርምጃ ከተራመድክ አንተ በስኬታማነት ጎዳና ላይ ነህ!
አንድ ነገር ለማሸነፍ ስትፈልግ የግድ በካልኩሌሽን፣ በስኬት ነው የምትሄደው፡፡ አሁን ሩጫው ውሰጥ የማደርገው በየዙሩ ምን ያህል ሰከንድ መሄድ እንዳለብኝ ነው የማሰላው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ሰአት አንድ ዙር 1ደቂቃ ከ3 ሰከንድ ነው ሩጫው ላይ መጫወት ያለብህ፡፡ በዚህ ፍጥነት ከሄድክ ነው ሪከርድ የምትሰብረው፡፡ ሪከርድ ሳትሰብር ለማሸነፍ ከሆነ የምትሮጠው ዝም ብለው መከተልና የመጨረሻው ላይ ነው መፈትለክ የሚያስፈልግህ፡፡ ካልኩሌሽን የሚያስፈልግህ ሪከርድ ላይ ነው፡፡ በየኪሎሜትሩ ካልኩሌሽን ትሰራለህ፡፡ በአንድ ኪሎ ሜትር ስንት፣ በሁለተኛው፣ በሶስተኛው … እያልኩ ካልኩሌሽን ትሰራለህ፡፡ ጨዋታው ሁሉ ያለው ካልኩሌሽኑ፣ ስሌቱ ላይ ነው፡፡ የምትፈልገው ግብ ላይ ለመድረስ ታሰላዋለህ እንጂ ዝም ብለህ አቅሙ ስላለህ አትሮጠውም፡፡ ይህ ህግ ካላወቅከው ደሞ ሯጭ መሆን አትችልም፡፡ በነገራችን ላይ 63 መሄድ ከባድ ነው አንድ ደቂቃ ከ3 ሰከንድ፡፡ በዚህ ፍጥነት እንሂድ የሚሉ በተለይ ጀማሪዎች ይቆማሉ፡፡ ምክንያቱም ኦቨር ኢላክቲክ አሲድ ራሳቸው ላይ ይወጣል፡፡ አሁን በዚህ ሰአት እኔ ራሴ 63 ልሂድ ብል አልችልም፡፡ ይህንን የመሄጃዬ ጊዜ ከዛሬ 6 እና 5 አመት በፊት አልፏል፡፡ እድሜውም ነው፡፡
እኔ ከሩጫ 10ሺ ሜትርን በጣም እወደዋለሁ፡፡ ይቀለኛል፡፡ 5ሺን የወሰድክ እንደሆነ ፈጣን ነች፡፡ በፊት በፊት አምስት ሺን እወዳት ነበር፡፡ ሰባት ጊዜ ያህል ሪከርድ የሰበርኩት በአምስት ሺ ነው፡፡ ግን አስር ሺ አራት ጊዜም ቢሆን የዓለም ሻምፒዮና የሆንኩበትና በኦሎምፒክ ያሸነፍኩበት ስለሆነ ይበልጥ ፍቅሩ አለኝ፡፡
ሩጫው ውስጥ የምትደርስበትን ማወቅ ለዝግጅት ይረዳሀል፡፡ እኔ የማደርገው ይህንን ነው፡፡ ወይ በሪከርድ፣ ወይ ከሰው፣ ከማን እንደምወዳደር እለየዋለሁ፡፡ ከዚያ ለማንና ለምን ልምምዱን እንደምሰራው አውቀዋለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ ውድድሬ ከፖልቴርጋት ጋር ከሆነ ለሱ ነው የምዘጋጅው፡፡ ፖልቴርጋት የመጨረሻዎቹ 5ዙሮች ላይ በጣም ይፈጥናል፡፡ ለሱ እንግዲህ ከመጀመሪያው ጀምሬ የማዳከምን አሯሯጥ እከተላለሁ፡፡ ሌላው ደሞ ዲተርቦባ የጀርመን ሯጭ አለ፡፡ ጀርመን በሚደረግ ውድድር ላይ እሱ አለ ማለት በቃ መፋለጥ ነው፡፡ ምክንያቱም እሱ ህዝቡ ፊት መሸነፍ አይፈልግም፡፡ በተለይ እሱ የመጨረሻዎቹ 200 ሜትር በጣም ሸምጣጭ ነው፡፡ ሳላህ የሱፍም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ አስከመጨረሻው ማስኬድ ስለሌብኝ ከመጀመሪያው እፈጥናለሁ፣ እብስ እላለሁ፡፡ ወደኋላ ሲቀር ሞራሉን ስለሚነኩት እና ለመከተል ሲል ስለሚዳከም በዚህ ረገድ እዘጋጅበታለሁ፡፡ እንግዲህ ይሄ ማለት ቀድመህ መሰናክሎችን፣ እንዳታሸንፍ የሚያደርጉህን ነገሮች ለይተህ አውቀህ ትዘጋጅባቸዋለህ ማለት ነው፡፡
እስከመጨረሻው ሂድ! ተስፋ አትቁረጥ!
በጣም የተለመደው የውድቀት ምክንያት አንድ ሰው ሊሸነፍ እዚያ ጋ የማቆም ልምድ ነው፡፡
አሸናፊ ተስፋ አይቆርጥም… ተስፋ ቆራጭ አያሸንፍም!
እኔ ለተስፋ መቁረጥ ፊት ስለማልሰጠው ነው እንጂ እንዳልከኝ ስድኒ ላይ ከፖልቴርጋት ጋር ስናደርግ የነበረው የእልህ ትንቅንቅ እንድሸነፍ ሊያደርገኝ የሚችል ሁሉ ነበር፡፡ አሁን እዚህ ላይ አለማቆም፣ ቶሎ መሸነፍን አለመቀበል፣ እንቢኝ ብለህ መሄድ ጥቅሙን ነው የምታይበት፡፡ ለነገሩ የእግዜርም ታአምር ታክሎበታል ብዬ ነው የማምነው፡፡
ያኔ የሚሰማኝ እጅግ የቀለጠ ጫጫታ፣ጩኸት ነበር፡፡ ከፊት ቀድሞኛልና ማሸነፍን የምታስበው ለሱ ነው፡፡ እና እኔ እየደረስኩበት ሄድኩና… ያው ብዙ ጊዜ አልፈህ የምትሄደው በቀኝ በኩል እየሄድን በጎን በግራ አይንህ ፊት እያየህ በጎን ጨረፍ ስታደርግ በጎንህ ትክክል ከሌለ ቀድመኸዋል ማለት ነው፡፡ እና አየት ሳደርገው ጠፋብኝ፡፡ ያንን ቅፅበት ነበርና የምጠብቀው የመጨረሻዎቹ 15ሜትሮች ከአምስት፣ ሰባት እርምጃ በፊት በሱ በኩል ገባ አልኩና ያኔ ለኔ እራሱ አስደንቆኝ ስለነበር ብቻ እጄን ማውጣት እንዳለብኝ ተስምቶኝ አደረግኩት፡፡ አሁን እኔ ራሴ ፊልሙን ደጋግሜ ሳየው ህልም ነገር ነው የሚመስለኝ፡፡ያኔ ደግሞ ትልቅ ችግር የሆነብኝ እግሬን መታመሜ ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ተስፋ ሳልቆርጥ እስከመጨረሻው ያደረግኩት ጥረት ለዛ ድል አብቅቶኛል እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ካደረግኳቸው ውድድሮች ሁሉ ትልቅ ወቅት፣ የማይረሳና ለተመልካች ሳይቀር ይሰቀጥጥ የነበረ ውድድር ነበር፡፡
በውድድሩ አለም እኔ ተስፋ መቁረጥን ቦታ አልሰጠውም፡፡ በተለይ በኋላህ የሚከተሉህን ጥቂት ጊዜ የሚፈጥኑትን እያየህና እያሰብክ ተስፋ መቁረጥ የለብህም፡፡ ይቆማል፡፡ ተከታዩም ሆነ ፈጣኑ ይቆማል፡፡ አንዴ ልምዱ ካለህ እኮ ታውቀዋለህ፡፡ ፈተና የሚሆንብህን በልምድም፣ በቴክኒክም ትቆጣጠረዋለህ፡፡
ተስፋ የሚያስቆርጡ ብዙ ነገሮች ይገጥማሉ፡፡ በተለይ እኔ እግሬን ሲያመኝ እጅግ ነው የምበሳጨው፡፡ ብዙ ጊዜም ኦፕራሲዮን ሆኛለሁ፡፡ የሰው ልጅ ተክለሰውነት፣ እግር የተሰጠው እንዲራመድበት እንጂ እንዲሮጥበት አይደለም፡፡ ሩጫ ደግሞ ድፍረት ነው፡፡ እና ለምን አመመኝ ብለህ አትቃወምም እንጂ ህመም ብዙ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የሆነ ነገር አቅደህ እንኳን ሳይሳካ ሲቀር ያበሳጫል፡፡
አንዴ ባርሴሎና ኦሎምፒክ ለመሳተፍ ሚኒማ (ያለህን የሰአት ብቃት የሚገልፅ) አምጡ ተብለን በዚያ ጊዜ ስታንዳርዱ 13ደቂቃ ከ29 ሰከንድ መግባት ነበርና ኦስሎና ፊንላንድ እንድሮጥ ተደረገና ተመደብኩ፡፡ ከሌሎች ልጆች ጋር ማታ ልንሄድ ትኬታችንን ስንጠብቅ፣ መጨረሻ ላይ ተደወለልንና ትኬት የለም ተባልን፡፡ በቃ ተናደድኩ፡፡ ሩጫ ገና የጀመርኩበት ሰሞን ስለነበርና በዛ ውድድር ላይ ለመሳተፍ በጣም ጉጉት ስለነበረኝ ተበሳጨሁ፡፡ ወንድሜ ያኔ ሯጭ ነበር፡፡ እሱ ብር ከየትም፣ ከየትም ብሎ አመጣና እነሱ ትኬት የማይቆርጡልህ ከሆነ ተከፍሎ መሄድ አለብህ አለኝ፡፡ ተከፍሎማ አልሄድም እነሱ ናቸው መክፈል ያለባቸው ብዬ ተነስቼ አርሲ ገባሁ፡፡ ያኔ ሩጫ ሁሉ አስጠላኝና በቃ ወደ ማቆም ገደማ ደረስኩ፡፡ በዚህ ስሜት ውስጥ እያለሁ አዲስ አበባ ተጠራሁና በዓለም ወጣቶች ሻምፒዮና እንድዘጋጅ ታዘዝኩ፡፡ ዝግጅቱም ለአስር ሺ ሜትር ነበር፡፡ ተዘጋጀሁና ሄድኩ፡፡ እዛ ከደረስኩ በኋላ ለ5ሺ ሜትር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው እዛ ሲደርስ ታመመና ሁለቱንም እሩጥ ተባልኩ፡፡ ልሮጥ የተዘጋጀሁት ለአንዱ ብቻ ነበር፡፡ በቃ ሀሙስ ማታ 5ሺ ማጣሪያ አርብ እለት 10ሺ ፋይናልና ቅዳሜ እለት 5ሺ ፋይናል ሮጥኩ፡፡ በሁለቱም አሸንፌ ወርቅ አገኘሁ፡፡ ያ ሁኔታ የነበረኝን ተስፋ የመቁረጥ ስሜትና ቅሬታ ሁሉ ክሶ አስረሳኝ፡፡
አንዲት ሰከንድ በህይወት ላይ ዋጋ አላት!
ህይወት እንደ ዳማ ጨዋታ ናት፡፡ የምትጫወተው ደግሞ ከጊዜ ጋር ነው፡፡ ለመሄድ ካወላወልክና ትክክለኛውን መንገድ መሄድ ከተሳነህ ቀስ በቀስ ወታደሮችህ በሙሉ ከሰሌዳው ሙልጭ ብለው ይጠፋሉ፡፡ የምትጫወተው ጥርጣሬንና መወላወልን ሲታገስ ከማይችል ባለጋራ ጋር ነው!
በነገሮች ላይ ፕሮግራምድ እንድትሆን የሚያስገድዱህ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የእኔ ችግር ይሄ ይመስለኛል፡፡ አንዳንድ ግዜ ኘሮግራም እይዛለሁ፡፡ በአብዛኛው ግን አይደለም፡፡ ያም ሆኖ እንዳልከኝ ሰከንድ በሩጫው ውስጥ ትልቅ ዋጋ አላት፡፡ በሩጫው ውስጥም በቻ ሳይሆን በህይወትም ውስጥ ዋጋ አላት፡፡ እኔ ብዙ የተለመዱ ቋሚ ፕሮግራሞች ባይኖሩኝም በቀን ሁለት ጊዜ ጠዋትና ወደማታ የሩጫ ልምምድ ማድረግ የማይሰረዝ ፕሮግራሜ ነው፡፡ ሁሌ ሌሊት 11 ሰዓት እነሳና ለልምምድ እሄዳለሁ፡፡ ልምምዴን እስከ ጠዋቱ ሶስት ሰአት እጨርስና ወደ ቢሮዬ እመጣለሁ፡፡ በቢሮ ውስጥ የሚሰሩ ስራዎችና በተለይ ከግንባታ ጋር በተያያዘ እየተዟዟርኩ የማይባቸው ቦታዎች ካሉ እነሱን ተዟዙሬ አያለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ግን ወንድሜ ብዙውን ስራ ስለሚሰራ አልቸገርም፡፡ ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዬችና ስብሰባዎች ከሰአት በኋላ አከናውኜ ወደማታ የሚኖረኝን ትሬኒንግ እንደጨረስኩ እቤት እሄዳለሁ፡፡ ሁልጊዜ ልጆቼ የተማሩትን ደብተራቸውን እመለከታለሁ፡፡ ከነሱ ጋር ስጫወት አመሻለሁ፡፡ ያው ማታ ዜናና የተለያዩ ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን እከታተላለሁ፡፡ ከተጠቀሱት ውጪ መደበኛ ፕሮግራሞች ባይኖሩኝም በተለያዩ ጊዜያት የማደርጋቸው ታሪካዊ ቦታዎችን የመጎብኘት ሆቢ አለኝ፡፡ ይሄ ሆቢ ከመደበኛው የሩጫ ሆቢዬ ቀጥሎ የሚታይ ነው፡፡ በተረፈ ግን ጊዜን በአግባቡ ላለመጠቀም ከሚያስገድዱ ይሉኝታዎች በቀር ቅድም ስናወራ እንደነበረው ሰከንድ ዋጋ አላት፡፡ ይህንን ሁሌ በውድድር ውስጥ ስትሆን የምትረዳው ነው፡፡ በሩጫው አለም በዋዛ ፈዛዛ የምታሳልፈው ነገር የለም፡፡ የተያዘን ሪከርድ ለመስበ ኮ ሰከንድ ሳይሆን ማይክሮ ሰከንድ ዋጋ አለው፡፡ በዚህ ስልጣኔ በበዛበትና ውድድር በሆነበት ዘመን ደሞ የጊዜ ዋጋው ውድ ነው፡፡
ገንዘብ አጠራቅም
ከምታገኘው ላይ አስር ፐርሰንት ቆጥበህ ባማስቀመጥህ ራስህን ይቅር ልትለው አይገባም
የመጀመሪያው ነገር እኔ በሰው አልመራም፡፡ ስለማልመራ እኔ መከተል ያለብኝ የማምንበትን ብቻ ነው፡፡ ልውደቅም፣ አልውደቅም፣ ይጥቀመኝም፣ አይጥቅመኝም ለኔ ነው፡፡ ምናልባትም ጥሩ አካሄድ ላይሆን ይችላል የምሄደው፡፡ ግን ሰው ስላለኝ ያንን ተከትዬ ሄጄ በሚፈጠርብኝ ውድቀት ሰው እኮ እንዲህ ብሎኝ ብዬ ማማረር አልፈልግም፡፡ ለእኔ በገንዘብ ላይ ያለኝ አቋም ጥሩ ነው ብዬ ነው የያዝኩት፡፡ ለእኔ ጥሩ የሆነው ለሌላው ላይሆን ይችላል፡፡ ገሚሱ አንተ ምንድን ነው ገንዘብህን ዝም ብለህ ትበትናለህ? ይልሀል፡፡ ሌላው ደሞ አንተ እንዳልከው ከገንዘብ ላይ ጥብቅ ነው ይልሀል፡፡
እኔ የምከተለው መርህ አንድ ገንዘብ ከመውጣቱ በፊት መግባት ያለበት ቦታ መጀመሪያ መግባት አለበት ብዬ ነኁወ፡፡ ከዚህ ተቀብዬ እዚያ ጋር እሰጣለሁ፣ ከዚያ ወስጄ እንዲህ አደርጋለሁ የለም፡፡ ከዚህ ተቀብለህ መግባት ያለበት መሳቢያው ውስጥ ከሆነ ትከትና ጠርተህ አውጥተህ ብትሰጠው ነው ጥሩ፡፡ ሰዎች ቆንቋና ነው፣ ቆጥቋጣ ነው ይሉኛል፡፡ አዎ ነኝ፡፡ ብበትነው ኖሮ ገንዘቡን እዚህ አገርም ይዤ አልመጣም ነበር፡፡ እዛው በትኜ እጨርሰዋለሁ፡፡ ልብ በል ገንዘቡ እኮ የሚመጣው ከወዲያ፣ ከሌላ አገር ነው፡፡ እኔ ግን እንዲህ ያለ የገንዘብ አጠቃቀሜ እኔንም፣ አገርንም፣ ሁሉንም ይጠቅማል ባይ ነኝ፡፡ ደሞ ገንዘብ ላይ ጠንቃቃ ሆነው የሚጠቀሙ ሰዎች ናቸው በንግዱ አለም ስኬታማ የሚሆኑት፡፡ ይህ ለገንዘብ ያለህ ጠንካራ አመለካከት ከየት መጣ ላልከኝ ግን ምንጩ የልጅነቴ ገጠመኝ ነው፡፡
አባቴ በገንዘብ ላይ ያለው አመለካከት ጠንከር ያለ ነው፡፡ ሁሌም የሰው አይፈልግም፡፡ የራሱንም አያስነካም፡፡ እና አባቴ የአቦ ማህበር ይጠጣ ነበር፡፡ እና ለእዛ የሚከፈለው አንድ ብር ከ5 ሣንቲም ነበር፡፡ አባቴ አንድ ብር ይዞ አምስት ሳንቲም ዝርዝር ያጣል፡፡ ከአንድ ወዳጁ አቶ ታፈሰ ይባላሉ፣ ከሳቸው አምስት ሳንቲም ይበደርና በል ጋሼ ያበደርኩኝን ሳንቲም ማታ ለልጅ እልክልሀለሁ ይላል፡፡ ኧ ግድ የለም ብሎ ያበድረዋል፡፡ ያው ማህበሩ ሲያልቅ አባቴ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ገደማ ይሆናል ይመጣል፡፡ በኋላ አባቴ ዝርዝር አምስት ሳንቲም ከቤት ሲያገኝ በል አሁኑኑ ውሰድና ስጥ ይለኛል፡፡ የአቶ ታፈስ ቤት ከእኛ 5 ኪሎ ሜትር ያላነሰ ርቀት ያለውና ሁለት ወንዝ ተሻግረህ የምትሄድበትና እጅግ ጅብ የሚበዛበት ነው፡፡ እንዴ አባዬ መሽቷል እኮ? ስለው ወንድ አይደለህ? ያንጠለጠልከው ምናምን ነው? ሂድ ብያለሁ ከበላህም ይብላህ! አለኝ፡፡ እያለቀስኩ ነው የሄድኩት፡፡ በተለይ ወንዙን ስሻገር እግርና እጄ እየተንቀጠቀጠ በስቃይ ነበር ሞቼ የደረስኩት፡፡ በኋላ ሰውዬው ቤት ደርሼ ስጣራ ተደናግጠው ሁሉም ወጡ፡፡ ምን አደጋ ደረሰ ብለው ደነገጡ፡፡ አባዬ ይህን ስጥ ብሎኝ ነው አልኳቸው፡፡ ተገርመው አይ የሱ ነገር መች ይሆን ይህን አቋሙን የሚለውጠው? አሉኝ፡፡ አሁን ሳድግ ነው ምስጢሩ የገባኝ እንጂ ያኔ እጅግ በድርጊቱ ተበሳጭቼ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ባህላችን መረዳዳቱ ጥሩ ነው፡፡ ግን ጥገኝነትንና ራስን ያለመቻልን ስለሚያበረታታ ጉዳትም አለው፡፡ አውሮፓዎቹ ያደጉት ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ ነው፡፡ አንዱ አንዱን የሚረዳው ሲጠፋ በቃ መፍጨርጨር ጀመረ፡፡ በፊት የኛ ገበሬ የሚረዳው ስላልነበረ ራሱን በራሱ ነበር ጠብቆ የሚቆየው፡፡ አሁን ግን እርዳታ ለመልመዱ ችግር ነው የሆነበት፡፡ እኛ መልመድ ያለብን ለነገ ማለትም ነው፡፡ አገርን እኮ ማሳደግ ለእኔ የሚገባኝ እራስን መርዳት ስትችል ነው፡፡
ስለነገም መኖር ስትችል ነው፡፡ ስለነገ መኖር ከጀመርክ ገንዘብን ያለምክንያት አታወጣም፣ አትጠጣም፡፡ ስለዛሬ ስትኖር ግን የዛሬውን ደስታ ብቻ ታስብና ጠጪ ትሆናለህ፣ ትራጫለህ፡፡
የኔ መመሪያ ሰለ ነገ መኖርና ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም ነው፡፡ አንተ እንዳልከኝ የማገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ካልተጠቀምኩበት ለራሴ ይቅርታ አላደርግለትም፡፡ የኛ ችግራችን ገንዘብ አለማግኘት ብቻ አይደለም በስርአቱ አለመጠቀም ነው፡፡ የኔ መርህ ማውጣት የማይገባኝ ከሆነ ለአንድ እቃ አንድ ብርም አላወጣ፡፡ ከተገባኝ ግን የፈለገውን ይሁን አደርገዋለሁ፡፡

የሰዎችን ትችት አትፍራ!
የሰዎች ትችት በአለማችን ላይ በቀላሉ የሚገኝ ርካሽ እቃ ነው፡፡
የምትመኘው ነገር ትክክል ከሆነና ካመንክበት በቃ አድርገው፡፡
ህልምህን ለመተርጎም ሞክር፡፡ ድንገት ለጊዜው ውድቀት ቢገጥምህ እንኳን ሌሎች ለሚሉት ግድ አይኑርህ!
በገንዘብ ላይም ሆነ በግል ኑሮዬ፣ ወይም በሩጫው… ብቻ በማንኛውም የሰዎች ትችት ላይ ያለኝ አቋም ጠንካራ ነው፡፡ ሰዎች መቼም መተቸታቸውን አይተውምና ራሴን መሆንን ነው የማምነው፡፡ ይህንን የፈጠረው ደግሞ የማውቀው የኔ መመሪያ የሆነ አፈ ታሪክ ነው፡፡
አባትና ልጅ አህያ እየነዱ ይሄዳሉ፡፡ በአጠገባቸው የሚያልፉ መንገደኞች ያዩዋቸውና እንደው ምን ያሉ ሞኞች ናቸው፣ እንዴት ባዶ አህያ እየነዱ ይሄዳሉ? አንደኛቸው እንኳን አህያው ላይ አይሆኑም? ይላሉ፡፡ ይህን የሰሙት አባት ልጄ እውነታቸውን ነውና አህያው ላይ ተቀመጥ አሉና አህያው ላይ አስቀምጠውት ትንሽ እንደሄዱ ሌሎች መንገደኞች ጉድ እኮ ነው የዞሬ ልጅ አባቱ በእግራቸው እየሄዱ እሱ አህያ ላይ ይሄዳል? ይላሉ፡፡ ልጄ እውነታቸውን ነው ውረድና እኔ አህያው ላይ ልሁን ብለው አህያ ላይ ወጥተው ትንሽ እንደሄዱ አሁንም መንገደኞች አባት አህያ ላይ ልጅ በእግሩ እንደሚሄዱ ያዩና አይይ አሁን ባይወልደው ነው እንጂ ይህን አንድ ፍሬ ልጅ እንዴት በእግሩ እያስኬደ እሱ ባህያ ይሄዳል? ይላሉ አባትም አይ ልጄ እውነታቸውን ነው ና ተፈናጠጥ ይሉና አፈናጠውት ትንሽ እንደሄዱ አሁንም መንገደኞች አያችሁ አፍ የለውም፣ አይናገርም ብለው ለሁለት እንስሳውን ሲገሉት? ይላሉ፡፡ ያን ጊዜ ልጁ እንዴ አባዬ!? አህያው ባዶውን ሲኖድ አንድ አስተያየት… እኔ ስቀመጥ ሌላ … አንተ ስትቀመጥ ሌላ ምንድነው የሚሻለን? ወይ ደሞ አህያውን እንሸከመው ይሆን? ብሎ አባቱን ጠየቀው፡፡ አባትየውም የለም ልጄ ለሱም ቢሆን ሌላ ስለሚሉን ሰው ያለውን ይበል እኔና አንተ እንደ መጀመሪያችን አህያውን እየነዳን እንሂድ ብለው ጉዞአቸውን ቀጠሉ፡፡
ምንም አድርግ ምን ትችት አይቀርም፡፡ አንተ ቅድም እንዳልከው የሚጠቅመውን ብቻ በመውሰድ እንደርካሽ እቃ ቆጥሮ የራስን እምነት ማራመድ ብቻ ነወ፡፡ አሁን ለምሳሌ በስፖርቱ አለም ብዙ ችግሮች፣ እንቅፋቶች ሳይኖሩ ቀርቶ አይደለም እዚህ የተደረሰው፡፡ ብዙ የታለፈ ነገር አለ፡፡ አንድ ጊዜ በ85 ዓ.ም ወደ እንግሊዝ አገር ስሄድ ያኔ የመጀመሪያዎቹ ስለነበርን በራሳችን ፈቃድ እኔን ወርቁ ቢቂላ ሄደን ነበር የተወዳደርነው፡፡ ለአትሌቱም በእንቢተኝነት በር የከፈትንለት እኛ ነን፡፡ እና እዛ እንደሄድን በቃ ጠፉ … ተብሎ እንደትልቅ የሀገር ክህደት ተወራ፡፡ አይመጡም ተብሎ ተደመደመ፡፡ እኛ ግን ዙሪክ በተካሄደው ውድድር አሸንፈን እኔ ቶፕ ፋይፍ ውስጥ፣ ወርቁ ቢቂላም ቶር ቴን ውስጥ ነበር የገባነው፡፡ በወቅቱ ከፌዴሬሽኑ ፈቃድ ውጪ ከሄድክ እንደማትመለስና በዛው እንደምትቀር የሚታወቅ ነበር፡፡ ከዚህ የተነሳ ሚኒስትሩ ሳይቀር በከሀዲነት ፈርጀውን ነበር፡፡
ቀጥሎ ስቱትጋርት የሚደረግ ውድድር ስለነበር ቆይ መቼም ከዚህ በኋላ አይጠፉምና ከዛ ሲመለሱ ነው የምንቀጣቸው ብለው ወሰኑ፡፡ ስቱትጋርት በተካሄደው ውድድር በ5ሺ፣ በ10ሺ ወርቅ ይዘን ስንመጣ አይ ይሄ ነገር እነሱ ናቸው ትክክል ተባለና ተውን፡፡ በዛው አመት ጃፖን ስሄድ ቴክኒካል ዳይሬክተር ተመደበልኝ፡፡ እንግሊዝ ድረስ መጣንና ሌላ ውድድር ስላለኝ ሌላ ቤታ እሄዳለሁ ስለው እንዴ አሁንም ልትሸፍት? አለኝ ከጠፋሁም አልተገናኘንም አልኩት፡፡ ያው እንደለመደው ነው ተብዬ ዝም ተባልኩ፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ ነው እንዲህ ከሆነ ለምን ሌሎች ሯጮችስ በነፃ እንዲንቀሳቀሱ አይደረግም? ተብሎ የተለቀቁት፡፡
ምኞት አያልቅም!
የምትፈልገው ነገር ላይ ተጠንቀቅ ልታገኘው ትችላለህና፡፡
የሰው ልጅ የአዕምሮ ችሎታ እኛ ከምንፈጥርለት ገደብ በቀር ገደብ የለውም!
ከዚህ በኋላ ምኞትህ ምንድነው አልከኝ? ምኞት ኮ ማቆሚያ፣ ማለቂያ የለውም፡፡ ሩቅ ሳንሄድ እንኳን አሁን በቢዝነሱ አለም ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ የማልመው እንደ አላሙዲ መሆን ነው፡፡ አማልመው ግን ላይሆን ይችላል ብዬ አይደለም፡፡
ያኔ ምሩፅ ይፍጠር ሲያሸንፍ እየሰማሁ ያንን ደረጃ ስመኝ ምንም ያልነበረኝ ነበርኩ፡፡ አሁን ግን ስለ አላሙዲን ሳስብ ቢያንስ ወደዛ መሄድ የሚያስችለውን መንገድ ጀምሬዋለሁ፡፡ እዛ አላሙዲን ጋ ስደርስ ወይም እንደሱ ስሆን ደሞ ሌላ ህልም እይዛለሁ፡፡ ከዛ በኋላስ? ያው የሰው ፍላጎት ማብቂያ የለውምና አንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡ ልብ አርግ በሩጫው አብቅቶለታል ብለህ እንዳታስብ፡፡ በሱም በኩል ቢሆን እኮ ገና ነኝ፡፡ አሁን ቅድም የምትፈልገውን ነገር ካወቅክና ወዴት እንደምትሄድ ካወቅክ አለም ራሷ ቤት አዘጋጅታ ትጠብቅሀለች አይደል ያልከው? ጨርሰኸዋልካ፡፡

ከያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች!
አዲስ አበባ እንደመጣሁ በሁለተኛ አመት ይመስለኛል… ያኔ ትሬይኒንግ የምንሰራው ጃንሜዳ ነበር፡፡ ታደያ ከእኔ ቤት ወደ ጃንሜዳ ለመሄድ ባስ ይዤ 5ኪሎ መውረድና አንድ አስፓልት አለች በነሱ ደጅ የምታወጣ፣ እና በበራቸው አልፌ ነው የምሄደው፡፡ ያው እንግዲህ አቋራጭ መሆኗ ነው፡፡ ሲያገጣጥም ደግሞ የአሰልጣኛችን ወንድሙ ቤት እሷ ቤት አጠገብ ነበር፡፡ በዛ ስናልፍ አሰልጣኛችን ወንድሙ ቤት ሲገባ እኔ ውጭ ቆሜ እሱን መጠበቄ የተለመደ ነበር፡፡ እሷን የማያት ሱቃቸው ውስጥ ተቀምጣ ነው፡፡ ዝም ነው የምትለው፡፡
በቃ የገጠር ልጅ ነበር የምትመስለኝ፡፡ እኛ የምናውቀው የከተማ ልጆች ብልጣ ብልጥ እንደሆኑ ነዋ? በኋላ አሰልጣኛችንን ትእዛዙን ይቺን ልጅ እንዲት ነው? ስለው ምናምንህን ሳትጠርግ ደግሞ? አለኝ፡፡ እንደምንም ከሶስት ወር በኋላ ስልኳን ሰጠኝና ደወልኩላት፡፡
ተናደደች፡፡
ብዙ ከቆየሁ በኋላ ትእዛዙ ያለኝን እውነተኛ ስሜት ተረድቶ አገናኘኝና አስተዋወቀን፡፡ ሲያስተዋውቀን ደግሞ እኔን ዘመድ ነው ምናምን ብሎ ነው፡፡ ምናለፋህ ወይ እሷ አትናገር ወይ እኔ አልጋገር እንደው በቃ ዝም፣ ዝም ተባባልን ተለያየን፡፡ እንዴት ነሽ፣ እንዴት ነህ፣ ምንድን ነው የምትሰራው፣ ምንድነው የምትሰሪው? ብቻ ነበር ልውውጣችን፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ልብ አድርግ ከእሷ ጋር በስልክም ሆነ በአካል የምንነጋገረውና ሀሳብ የምንለዋወጠው ከወራት በኋላ ባለ ክፍትት ነው እንጂ እንዲህ ቶሎ፣ ቶሎ አይደለም፡፡ በኋላ ምን ይሻላል? ብዬ ትእዛዙን ስጠይቀው የራስህ ጉዳይ ስልኳ አለህ አይደል አትደውልላትም? አለኝ፡፡
በስንት ፍራቻ ደወልኩላትና አይ የባለፈው ልጅ ነኝ … ከጓደኛሽ ጋር ቴአትር ልጋብዝሽ ነበር አልኳት፡፡ እኔ ኮ ከዛን ቀን በፊት ቴአትር የሚባል አይቼ አላውቅም እንደው ሲባል የሰማሁትን ነው፡፡ አሰልጣኜ ትእዛዙንም አደረግኩና (እንዳልፈራ ነው) ጋበዝኳቸው፡፡ ከዛ በኋላ በቃ ለጓደኝነት ነው ምናምን ሳልል፣ ለመጫወት ነው እያልኩ እንድንገናኝ ዘዴ መፍጠር ጀመርኩ፡፡ ቀስ በቀስም እየተግባባን መጣን፡፡ እሷም ስለእኔ ማወቅ ጀመረች፡፡ አሰልጣኜ ትእዛዙ ዋ ኋላ ከዘመዶቼ ታጣላኝና? ሲለኝ ምን አጣላሀለሁ? ዘመድ እሆንሀለሁ እንጂ! አልኩት፡፡ ከሱ ጋር በጣም ነው የምግባባው፡፡ ቀስ በቀስ ተገናኝታችሁ ነበር? ሲል ሸምጥጥ አድርጌ ኧረ እንደውም ካየኋት ወር ሊሆነኝ ነው እለው ጀመር፡፡ በዚህ ሁኔታ እኔ እና እሷ እየተገናኘን ብሄረ-ፅጌ ነበር የምንዝናናው፡፡
ያኔ ታዲያ ስቱትጋርትም አሸነፍኩና ትንሽ እየታወኩ ስመጣ እየተደበቅን ሆነ የምንገናኘው፡፡ ፌዴሬሽንም አካባቢ ይሄ ነገር ከተሰማ እንደባለጌ ነበር የሚያስቆጥረኝ፡፡ ፍቅራችን ሁሉ እጅግ መደበቅ የበዛበት የሠቀቀን ነበር፡፡ እኔመ ሪከርዶችን እየሰበርኩ እየታወቅኩ መጣሁ፡፡ በመጨረሻ ላይ የአትላንታው ውድድር እንደደረሠ የአትላንታውን ካሸነፍኩ እንጋባለን አልኳት፡፡
ካልሆነስ፣ካላሸነፍክስ? አለችኝ፡፡ አይ.. ያው ባለሸንፍም እንጋባለን… ግን የኤርፖርት ሴሪሞኒ ደስ ስለሚል ነው አልኳት፡፡ ያው እሷም እድለኛ ነበረች አሸነፍኩና ተጋባን፡፡
እኔ የሚገርመኝ ትዳር መመስረት ለምን አስፈለገ? ብለው ሰዎሽ ሲጠይቁ ነው፡፡ ዝም ብለህ ያየህ እንደሆነ ትዳር የሌላቸው ሰዎች ሁሉ ሙሉ አይደሉም፡፡ አንድ ነገር ይቀራቸዋል፡፡ ልክ ጨው የሌለው ወጥ፡፡ ቅድም አንዳልከው ከያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ በስተጀርባ አንዲት ሴት አለች ልክ ነህ፡፡ ይሄ ነገር ለእኔ የሰራው መቶ ሀምሳ ከመቶ ነው፡፡ እሷ ባትኖር እኔ እንዱህ በቢዝነሱ ዓለም ባልገባሁ ነበር፡፡ ሁሉንም የቢሮ ስራ የያዘችው እሷ ነች፡፡ ሌላውን ተወው እግሬን ሲያመኝ እንኳን እኛ እሯጮች እግራችንን ሲያመን ነጭናጮች ነን እሉኛ ነኝ … እጅግ ላመሰግናት እወዳለሁ ከጎሌ ሆና ነው ሁሉንም የረዳችኝ፡፡
ይኸው የሶስት ልጆች አባትና እናት ሆነናል፡፡ የመጀመሪያዋ ሰባት ዓመቷ ሲሆን ስሟ ኤደን ነው፣ የቤቱ ኃላፊና የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡ ሁለተኛዋ ሜላት አምስት አመቷ ነው፡፡ የመጨረሻዋ ቤቲ ሶስት ዓመቷ ሲሆን ገና መዋለ ህፃናት መግባቷ ነው፡፡ የሚገርምህ ሜላት በተወለደች ሁለት ዓአት ከሁለት ሰዓት በኋላ ቤቲ ተወልዳ የልደት ቀናቸው አንድ ቀን ላይ ሆኗል፡፡ እንግዲህ ከባለቤቴና ልጆቼ ጋር ይኸው ህይወትን በደስታ እያጣጣምኳት ነው፡፡

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »