ለመጀመር…መጀመር

Published by Abreham D. on

N

በህይወታችን የምንወደውን ነገር ለመስራት ዝግጁ ነን? ሆነንስ እናውቃለን? ዝግጁ መሆንስ አለብን?

ዝግጁ ያልሆንበት አዲስ ነገር ውስጥ እየገባን እንደሆነ አስበን ሁላችንም ፈርተን እናውቃለን። ፈሪ ሆነን አይደለም ፥ ተፈጥሮአዊ ነው። አንጎላችን (አዕምሮአችን) ያለመደውና የማያውቀው ነገር ውስጥ ስንገባ ሊጠብቀን ይሞክራል [ለምሳሌ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋና ስንዋኝ እንደ ማለት ነው]።

ያለንበት የመረጃ እና የቴክኖሎጂ ዘመን መረጃንና እውቀትን [በአንጻንዊ መልኩ ቢሆንም] ለሁላችንም ተደራሽ አድርጎታል። ነገር ግን መረጃንና እውቀትን ወደተግባር በመቀየር ሂደት መካከል ጣልቃ የሚገባው ልምድ የሚባለው ነገር ነው። ለዚህም ነው ለአዲስ ነገሮች ራሳችንን ማስለመድ ያለብን ፥ በዙሪያችን የምናያቸው ‘የተሳካላቸው’ ሰዎችም ከእኛ የተሻለ ያላቸው ነገር ልምድ ነው።

አንድ ሀኪም ብቁ ለመሆን ስንት ጊዜ ማከም አለበት? ብላችሁ አስደንጋጭ ጥያቄ ነው [እሺ ፥ ቢያንስ እኔን ያስደነግጠኛል ፥ ሆ!]። ግን ደግም ህክምና ተግባራዊ ትምህርት ስለሆነ ሀኪሞቻችንም የሚማሩት ብቁ በሆኑ ሀኪምች ህክምና የሚደረግላቸው ሰዎችን በማየት ፥ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ደግም ከጎናቸው ብቁ የሆኑ ሀኪሞች ቆመው ስለሆነ ተንፈስ ያስደርጋል። ግን ኢንጅነሮቻችን ፣ አርክቴክቶች ፣ የማህበረሰብና የስነ-ልቦና ባለሙያዎቻችንስ? አያድርገውና አንድ ሰው መጥቶ “ራሴን ላጠፋ ነው” ቢለኝ? “ቆይ በደንብ ራስህን አላወከውም ፥ ራስህን በደንብ ማወቅና መረዳት አለብህ። እስቲ ራስን ስለማወቅ የሚጠቅሙ መጻህፍትን አንብብ” ነው ምላሼ የሚሆነው?

ከላይ እንደምናየው የ”ሳምሰንግ” ‘የማትችለውን አድርግ’ ወይም Do What You Can’t ማስታወቂያ [የድርጅቱ መፈክርም ነው] ሁላችንም (ሰዎች) የማንችለውን ለመስራት እንደተፈጠርንና ፥ መፍጠር እንደምንችል ይነግረናል። በደንብ ለማብራራት ያህል ፥ እኛ ሰዎች ትልልቅ ነገሮችን ለመስራት በሚያስችል አቅም ታጭቀን ወደ ምድር መጥተናል ፥ ይህንንም ብቃታችንን የመረጃ ፥ የዕውቀትና የልምድ ውሀ ስናጠጣው ማድረግ የሚያቅተን ነገር የለም የሚል ይመስላል።

ምን ያህሎቻችን በህይወታችን ውስጥ አንድን አዲስ ነገር ለማድረግ ዝግጁ ሆነን እናውቃለን? ወደዚህ ምድር ለመምጣት ዝግጁ ነበርን? ምርጫም አልነበረንም። ቤተሰቦቻችንንና አገራችንንም አልመረጥንም። ለመጀመሪያ ጊዜ በእግራችን ስንቆም ፣ ስንራመድ ፣ ስናወራ ፣ ስንጽፍ ፣ ትምህርት ቤት ስንገባ? ትዳር ስንመሰርት ፣ ልጆች ስንወልድ? ለእነዚህ ሁሉ ቀድም ተዘጋጅቶ የነበረ ሰው ካለ ብተዋወቀው ደስ ይለኛል።

የልምድ ትምህርት ቤት ውስጥ ስንገባ ሁላችንም መውሰድ ያለብን ኮርሶች ፤ ፍጥነትና ውድቀት

ትልቁ የስራና ሰራተኞች ፣ ድርጅቶችና ተቋማት ማህበራዊ ድህረ ገጽ ፥ ሊንክድኢን [LinkedIn] ተባባሪ መስራች [Co-Founder] የሆነው ሪድ ሆፍማን [Reid Hoffman] አዲስ ንግድን ለመጀመርም ይሁን ድርጅትን ለመምራት የመጀመሪያው መርሁ ፍጥነት ነው [ይህን የተሰመረበትን ዐረፍተ ነገር በመጫን በጥልቀት ስለዚህ ርእስ ማንበብ ይችላሉ]።

ይህንንም በደንብ የሚያብራሩ ሁለት አባባሎች አሉት፦ 
1. “መጀመሪያ ባመረትከው ምርትህ ካላፈርክ ፥ በጣም ዘግይተህ ጀምረሀል።” “If you aren’t embarrassed by the first version of your product, you shipped too late”.

ዛሬ በጣም ትልቅ የምንላቸውን ፥ የህይወታችን አንድ አካል የሆኑትንና ተሰልፍን የምንገዛቸውን እቃዎች መነሻ ብንመለከት ፥ ከላይ የተገለጸውን የሪድን ሀሳብ በደንብ ያብራራሩታል። ይህንንም እንደ የቤት ስራ ብንወስድና የእነዚህን አምራች ድርጅቶች አጀማማር ብንመለከት ጥሩ ነው።

2. “አዲስ ንግድ መጀመር ማለት ራስህን ከተራራ ጫፍ ላይ ወርውረህ ፥ እዛው ወደታች እየወረድክ አውሮፕላን ሰርተህ ራስህን እንደማዳን ነው።” “In founding a startup, you throw yourself off a cliff and build an airplane on the way down.”

እነዚህ መርሆች ፥ በተለይ የመጨረሻው ትንሽ የሚያሳቅቅ ይመስላል። ነገር ግን ሪድ ያለ ቢዝነስ ዲግሪ ትክክለኛ የሆነ የንግድን እውነታ ከልምዱ በመነሳት በቀላል ቋንቋ ሲነግረን እናያለን። ሪድ ኤም.ቢ.ኤ [MBA] አይኑረው እንጂ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪውን ደግም ከኦክስፎርድ ዩኒቭርስቲ ይዟል። ሊንክዲንን ከመጀመሩም በፊት አንድ የራሱ ቢዝነስ ጀምሮ ነበር [አልተሳካለትም] ፥ ፔይፓልን [PayPal] አብረው ከጀመሩት ሰዎች ውስጥም አንዱ ነው ፥ ከዚያም ለኢቤይ [eBay] ፔይፓልን ሪድ እና ጓደኞቹ ሸጠው ብዙ ገንዘብ አግኝተዋል። ከዚህ ቡድን ውስጥ መካከል አሁን የስፔስ ኤክስ [SpaceX] መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው ኢሎን መስክ [Elon Musk] ፥ ዩቲዩብን [YouTube አሁን ለጉግል ተሸጧል] የመሰረቱት እና ሌሎች በስም የምናውቃቸውን ድርጅቶች የመሰረቱ ሰዎች የዚህ ቡድን አባል ነበሩ። ከስር ያለውን ሰዕል ይመልከቱ።

Taken from Reid Hoffman’s Book entitled “The Startup of You”

ይህን ሁሉ ያልኩት ሪድ ሆፍማን እና ሊንክድኢን ዝም ብለው ከመሬት አንዳልበቀሉ እና ሪድ ያለውን ልምድ በተጨማሪም በዙሪያው በቀላሉ ሊያማክሩት የሚችሉትን ሰዎች እንድናይ ነው። በሪድ ትምህርት ፥ ልምድና ባለው ግንኙነቶች ይበልጡኑ ካስፈራራኋችሁ ይቅርታ። ነገር ግን ‘የሪድ ራስን ከተራራ ጫፍ ላይ ወርውሮ ፥ እዛው ወደታች እየወረድን አውሮፕላን ሰርተን ራሳችንን ማዳን የሚለው ሃሳብ እውነታ አለው [በተለይ ለንግድም ሆነ ፥ ሙያችንን ለመሸጥ ለምናስብ ሰዎች። Risk መውሰድ አለብን ለማለት ነው ፤ ባጭሩ] ፥ አዲስን ሀሳብ ስጋ ለማልበስ ከዚ ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም።

“እምነት የለሽ ነው ፥ መንገዱ ሲጨግግ ፥ ጉዞውን የሚያቋርጥ።” ጄ.አር.አር. ቶክን

“Faithless is he that says farewell when the road darkens.” J.R.R. Tolkien

ብዙዎቻችን ውድቀትን ቁጥጥር በሚደረግለት አካባቢ [controlled environment] ውስጥ ነው የተለማመድነው። ይህ ማለት ውድቀታችን ጥንቃቄ የተሞላበት ስለሆነ ፥ ብዙም ቁስል ላይኖረውና ጠባሳ ትቶ ላያልፍ ይችላል። ግን በአንቀልባ ታዝለን ከኖርንባቸው ጊዜያቶች ይልቅ ፤ ስራ አጥተን የተቸገረንባቸው ፥ ከስራ የተባረርንባቸው ፥ ንግዳችን ያልተሳካበት ጊዜያት ምን ዓይነት ነገር አስቀምጠውብን አልፈው ይሆን? ዛሬ ላይ ላለን ማንነታችንስ ምን ዓይነት ተጽእኖ አሳድረዋል? ለህይወት ያለንንስ አመለካከት ምን ዓይነት ቅርጽ ሰጥተውት ይሆን? እኔ በበኩሌ ፤ የትኛውም ትምህርት ቤት ፥ መጽሀፍ ፥ የሰው ምክር ሊሰጠኝ የማይችለውን ትምህርት በእነዚህ ጊዜያቶች አግኝቻለው።

ሰው ለመማር የግዴታ መውደቅ አለበት እያልኩኝ አይደለም ፥ የውድቀት ትምህርት ቤት ሰው የሚያጨበጭብለት ውጤት ላይሰጠን ይችላል ፥ እኛ ብቻ ነን ገፈት ቀማሹ። ግን ደግም በሳልም ያደርገናል ፥ በውስጣችንም ያለውን ሀሳብ እንደዚያው ያበስለዋል። ሰውዬው ሲበስል ፥ ሀሳቡም አብሮ ይበስላል ፤ ምጣዱ ከሰማ እንጀራውን መጋገር ቀላል ነው። ሰውንና ሀሳቡን ፥ ሀሳቡንና ድርጊቱን መለያየት ይከብዳል ብዬ ነው።

ስለዚህ አዲስን ነገር/መንገድ ለመጀመር ልባችሁ በሀሳብና በፍላጎት የጋለ ሰዎች [Passionate የሆናችሁ ሰዎች] ላበረታታችሁ እፈልጋለው። መጨራሻውን አውቆ ህይወትን የጀመረ የለም ፥ ሁላችንም የእምነት ጉዞ ነው የምናደርገው። የህይወታችን ስዕል ፈጣሪ ጋር እንዳለ አምናለው ፤ ግን አብረነው እንድንስል እድሉን ሰጥቶናል። ስለዚህ ብሩሻችንን ለምን አናነሳም ፥ ሁሉም ሰው የራሱን ስዕል በመሳል ‘ቢዚ’ ነው ፥ ማንም የኛን ለመሳል ጊዜ የለውም ፥ የሰውንም ስዕል በማየትና በማድነቅ ጊዜያችንን አናጥፋ። ይልቁንስ ከላይ እንደጠቀስኩት ስዕላችንን መሳል ለመልመድ እንፍጥን ፥ ለመውደቅ አንፍራ ፥ አብሮን የሚስለው ፈጣሪ ቀድም ስዕሉን ስለጨረሰው ፥ ስንሳሳት ወደ ቀድምው ንድፍ ይመልሰናል ፥ ብቁ ሰዓሊ ከጎናችን አለ።

ስለዚህ፦

ለመልመድ እንፍጠን ፥ ለመውደቅ አንፍራ
ምጣዱ እየሰማ ፥ እንጀራው ይቦካ

ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
ጤና ይስጥልኝ
አዳዲስ የቢዝነስ መረጃዎችና ዶክመንቶች ሲመጡ እንዲደርስዎ ይመዝገቡ
select another Language »